Print this page
Saturday, 12 February 2022 11:34

የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ያቀረቡትን “ክሴ ተሰርዞ እንደ ሌሎቹ ልሰናበት" ጥያቄን ፍ/ቤቱ ውድቅ አደረገው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      - ክሳችን ተሰርዞ ካልተሰናበትን፣ ፍ/ቤት አንቀርብም ብለዋል
          - ፍ/ቤቱ ለቀጣይ ቀጠሮ በችሎት እንዲቀርቡ አዟል
          - እስካሁን ከ45 በላይ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰምተዋል
          - ተከሳሾቹ ባልተገኙበት ችሎት የፍርድ ሂደቱ ሊቀጥል ይችላል
              ከሐምሌ 26 ቀን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ባሉ ቀናት በሱማሌ ክልል በተፈጸሙ የሃምሳ ዘጠን ንፁሃን ገድያዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት መቃጠልና በበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ወንጀሎች ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ኡመር (አብዲኢሌ) “ከእኛ ጋር ተከሰው የነበሩ እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ እየተደረገ፣ እኛ ብቻ በእስር ላይ የምንቆይበት ምክንያት ስለሌለ ክሱ ተቋርጦ ከእስር እንድንፈታ ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የህገ-መንግስትና የጸረ-ሽብር ጉዳዮች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ውድቅ አደረገው።
አቶ አብዲ ፍ/ቤቱ በህገ-መንግስቱ የተሰጠንን በእል የመታየት መብታችንን የነፈገን በመሆኑ በችሎት አንቀርብም በማለት ሳይቀርቡ ቀርተዋል። ከትናት በስቲያ የአቃቤ ህግን ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ፍ/ቤቱ በያዘው ቀጠሮ አቶ አብዲኢሌን ጨምሮ 14 ተከሳሾች በችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል። በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ይገኙ የነበሩ 3 ተከሳሾች ግን በችሎት ቀርበው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ችሎት ይዞን መጥቷል ሲሉ አቤቱታ አሰምተዋል።
ፍ/ቤቱ በአቶ አብዲኢሌና በሌሎች ተከሳሾች የቀረበውንና “ሌሎች እስረኞች ተፈተው እኛ ፍርድ ቤት የምንመላለስበት ምክንያት ባለመኖሩ ክሳችን ተቋርጦ ከእስር እንፈታ” የሚል ጥያቄ መርምሮ፣ ተከሳሾቹ አቤቱታቸውን ማቅረብ የሚኖርባቸው ክስ ላቋረጠው መንግስታዊ አካል እንጂ ለፍ/ቤቱ አይደለም ሲል አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል። የዐቤቃ ህግ ምስክሮችን የመስማት ሂደቱ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ያስተላለፈው ፍ/ቤቱ፤ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ያቀረቡት 14 ተከሳሾችም ቀርበው የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን የመስማት ሂደቱ እዲቀጥል አዞ ጉዳዩን ለየካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጥሮታል፡፤
ተከሳሾቸ የቀረበባቸውን ወንጀል ክስ በችሎት ቀርበው በመከታተል መከራከር እንደሚኖርባቸው የተናገሩት የህግ ባለሙያው አቶ ኢሳይያስ ታምራት፤ ይህ ህገ-መንግስታዊ መብታቸው ነው። ነገር ግን ያለ በቂ ምክንያት ጉዳያቸው ሊሰማ ቀጠሮ በተያዘበት ቀን በችሎት ሳይቀርቡ የቀሩ ተከሳሾች ካሉ ፍ/ቤቱ ተከሳሾቹ አለመቅረባቸውን በመዝገብ ላይ እንዲሰፍር ካደረገ በኋላ ጉዳዩ በሌሉበት እንዲሰማ ሊያዝ ይችላል ብለዋል። በመርህ ደረጃ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ክስ ሊሰማ የሚችለው በወ/መ/ሕ/ቁጥር 354 እስከ 365 ድረስ ያሉትን ወንጀሎች ፈጽሞ ጽኑ እስራት አሊያም ከአምስት ሺ ብር በላይ መቀጮ በማያስቀጣ ወንጀል ክስ የቀረበ እንደሆነ ነው። ነገር ግን ተከሳሹ የፍርድ ሂደቱ እንዲስተጓጎል በማሰብ ሆነ ብሎ በችሎት ሳይገኝ ከቀረ፣ ፍ/ቤቱ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ሊወስን ይችልላል ሲሉም ተናግረዋል።
የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 160 እና ተከታዮቹ መሰረት፣ ፍ/ቤቱ ተከሳሹ በሌለበት ሁኔታ ጉዳዩን ማየት የሚችለው፣ ተከሳሹ የፈፀመው ወንጀል  ከ12 ዓመት በሚያንስ ፅኑ እስራ ወይም ከብር 5 ሺ የማይልጥ የገንዘብ ቅጣት ሊደርስ በሚችል ቅጣት የሚቀጣ ከሆነ ነው ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ምንም እንኳን ጉዳዩን ተከሳሾቹ በሌሉበት ማየቱ ከህግ አግባብ የሚያጎድለው ነገር ቢኖርም፣ በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ተከሳሾቹ በሌሉበት አይቶ ውሳኔ መስጠት ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

Read 833 times
Administrator

Latest from Administrator