Saturday, 12 February 2022 11:37

መንግስት በሳኡዲ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ህይወት እንዲታደግ ኦፌኮ ጥሪ አቀረበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      በስደተኞቹ እስር ጉዳይ ለመምከር ወደ ሳኡዲ ያቀናው ልኡክ ተመልሷል
                 
             መንግስት በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ በኢ-ሰብአዊ አያያዝ በስቃይ ላይ የሚገኙ ኢትጵያውያን ስደተኞችን ህይወት እንዲታደግ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ጥሪ አቀረበ።
ፓርቲው ለአዲስ አድማስ ባደረሰው መግለጫ፤ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በሳውዲ አረቢያ በግለሰቦች ቤት በተለያዩ የስራ አማራጮች ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች  “ህገ-ወጥ ናችሁ” በሚል በጅምላ ታፍሰው በአሰቃቂ ሁኔታ በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውሶ፤ መንግስት የእነዚህን ስደተኛ ዜጎች ህይወት ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲታደግ በአጽንኦት ጠይቋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ በዚሁ አሰቃቂ እስር የተነሳ በርካታ ወገኖች ህይወት ማለፉን የጠቀሰው ኦፌኮ፤ መግለጫ መንግስት የቀሪ ወገኖችን ህይወት በአስቸኳይ እንዲታደግ ጠይቋል።
ለዜጎች ህገ-ወጥ ስደትና መከራ መንስኤ ናቸው ያላቸው የፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያለመኖር፤ ለወጣቶች የስራ እድል አለመመቻቸት አንዲሁም የፖለቲካ አመራርና አስተዳደር የተዛባ መሆኑን በመጥቀስም በዘላቂነት ዜጎች በሃገራቸው ሰርተው የመለወጥ ተስፋን የሚሰንቁበት ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችም እንደሚያስፈልጉ ፓርቲው ጠቁሟል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹን ጨምሮ በስደተኛ ታሳሪዎቹ ዙሪያ ከሳኡዲ መንግስት ባለስልጣናት ጋር የሚመክር ልኡክ ወደ ሪያድ አቅንቶ የነበረ ቢሆንም ልዑኩ ውጤታማ መሆን ሳይችል መቅረቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።

Read 1010 times