Print this page
Saturday, 12 February 2022 11:37

ከትግራይ አብያተ ክርስቲያናት የተዘረፉ ቅርሶች በኢንተርኔት በርካሽ ዋጋ እየተሸጡ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ለአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከትግራይ አብያተ ክርስቲያናት የተዘረፉ ጥንታዊ  ቅርሶች በኢንተርኔት እየተሸጡ መሆኑን ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በኢንተርኔት ግብይት በጥቂት ፓውንድ ዋጋ ለጨረታ እየቀረቡ ናቸው ከተባሉ ቅርሶች መካከል አብዛኞቹ ከአብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት የተዘረፉ መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ጥንታዊ ጥቅል የብራና ጽሁፎች፣ ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱስና የተለያዩ መስቀሎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ጀምሮ የነበሩ የክርስትና ሃይማኖት ታሪካዊ ቅርሶችን ጨምሮ በጥንታዊው የነጃሺ መስጊድና የእምነት ስፍራ ላይ ዘረፋና ጉዳት መድረሱን የሚጠቁመው ዘገባው፤ ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ  ግን አይገልጽም።
በትግራይ ሽሬ አካባቢ በሚገኘው ጥንታዊው የአማኑኤል ቤተ ክርስቲያን  ላይ  በተፈጸመው ጥቃት  ቤተ ክርስቲያኑ መጎዳቱን፣ እንዲሁም 8 መቶ ያህል ጥንታዊ የግዕዝ የብራና ላይ ጽሁፎችን የያዙ መፃህፍት መዘረፋቸውን የቤልጅየም ቅርስ ተቆርቋሪዎችን  ጠቅሶ ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል።
እነዚህ ከየአብያተ ክርስቲያናቱና ገዳማቱ የተዘረፉ ቅርሶች ላለፉት 6 ወራት በኢንተርኔት የግብይት መረቦች ላይ ለጨረታ ቀርበው እጅግ እርካሽ በሆነ ዋጋ እየተሸጡ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለልጣን ቅርሶቹ በጦርነቱ ወቅት ከአገር ያልወጡና ቀደም ሲል በተለያዩ መንገዶች ወጥተው አሁን ሌላ አላማ ባላቸው ሰዎች  በስፋት ለገበያ የቀረቡ እንዲመስሉ የተደረጉ ናቸው ብሏል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር  አበባው አያሌው እንደተናገሩት በጦርነቱ ወቅት በሁሉም መውጫ ኬላዎች ጥብቅ ቁጥጥር ስለሚደረግ ቅርሶቹ ከአገር ሊወጡ የሚችሉበት መንገድ የለም ብለዋል።

Read 1021 times
Administrator

Latest from Administrator