Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 September 2012 13:21

“አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አዲስ መንግስት

Written by 
Rate this item
(10 votes)

“እድለኛ መንግስት” ወይስ “ሸክም የበዛበት መንግስት”?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአንድ በኩል እድለኛ ናቸው ማለት ይቻላል። የአገር ሰላም በግጭት ሳይቀወጥ፣ የአገር ኢኮኖሚ በቀውስ ሳይናጋ፣ የአገር ምሁርና አንጋፋ እርስ በርስ ሳይጫረስ... የመንግስትን ስልጣን መረከብ በኛ አገር ብርቅ ነው። አብዛኞቹ የአገራችን መሪዎችኮ፤ በፍርስራሽ ክምር ላይ ቆመው ነው፣ ስልጣን የሚረከቡት። አልያም ደግሞ፤ ከነሱ በፊት የተገነባውን በማፍረስ ነው፣ የስልጣን ዘመናቸውን የሚጀምሩት። ድሮ የነበረውን አፍርሶ፣ ከባዶ የመጀመር መጥፎ ባህል፣ በአገራችን ለበርካታ መቶ አመታት የዘለቀ ከመሆኑ የተነሳ፤ “እርግማን” እስከመምሰል ደርሶ ነበር። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከዚህ “እርግማን” የተረፉ የመንግስት መሪ በመሆናቸው እድለኛ ናቸው ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም።ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአንድ በኩል እድለኛ ናቸው ማለት ይቻላል። የአገር ሰላም በግጭት ሳይቀወጥ፣ የአገር ኢኮኖሚ በቀውስ ሳይናጋ፣ የአገር ምሁርና አንጋፋ እርስ በርስ ሳይጫረስ... የመንግስትን ስልጣን መረከብ በኛ አገር ብርቅ ነው። አብዛኞቹ የአገራችን መሪዎችኮ፤ በፍርስራሽ ክምር ላይ ቆመው ነው፣ ስልጣን የሚረከቡት።

አልያም ደግሞ፤ ከነሱ በፊት የተገነባውን በማፍረስ ነው፣ የስልጣን ዘመናቸውን የሚጀምሩት። ድሮ የነበረውን አፍርሶ፣ ከባዶ የመጀመር መጥፎ ባህል፣ በአገራችን ለበርካታ መቶ አመታት የዘለቀ ከመሆኑ የተነሳ፤ “እርግማን” እስከመምሰል ደርሶ ነበር። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከዚህ “እርግማን” የተረፉ የመንግስት መሪ በመሆናቸው እድለኛ ናቸው ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም።በሌላ በኩል ደግሞ፤ ከከባድ ሸክም ጋር ስልጣን የተረከቡ መሪ ናቸው ማለት ይቻላል። ድሮ የነበረውን በማፍረስ ከባዶ የማይጀምር እድለኛ መሪ፤ ከቀድሞው የበለጠ ነገር በመገንባት የማሳየት ሸክም ይጠብቀዋል። ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር፣ “ካለፈው ስርዓት የወረስነው ችግር ነው” ብሎ መከራከር ወይም ማምለጥ አይችልም። ከዚህም በተጨማሪ፣ በየቦታው የምናያቸው የእድገት ጅምሮችና የግንባታ ውጥኖች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም፤ “የተስፋ እንጀራ” ለብዙ ጊዜ አያዛልቅም። ጅምሮቹንና ውጥኖቹን የተረከበ መሪ፤ የዜጎችን ኑሮ ወደሚያሻሽል ውጤት ሊያደርሳቸው ይገባል። በተስፋ ሲጠብቁ የቆዩ ዜጎች፣ “የምጣድ እንጀራ” ማግኘት ይፈልጋሉና። ይህ ለአቶ ኃይለማርያም ትልቅ ፈተና ነው። ምን ይሄ ብቻ! በተያዘላቸው ጊዜ ሊጠናቀቁና ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ እቅዶችንም ጭምር ተረክበዋል - ለምሳሌ በሚቀጥሉት ሦስት አመታት ከ2 ሺ ኪሎሜትር በላይ  የባቡር መስመር ዘርግቶ ማጠናቀቅ አይቻልም። ይህን የመሳሰሉ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳልተጠናቀቁ ሲታይ፤ የአቶ ኃይለማርያም መንግስት ለወቀሳ መጋለጡ አይቀርም። ይሄ፤ “እድለኛ” አያስብልም፤ የእዳ ሸክም ነው። በዚያ ላይ፣ የዛሬው ዘመን ሰው፣ እንደድሮ ችጋርን አሜን ብሎ የመቀበል፣ ድህነትን ችሎ የማደር ትእግስት የለውም (ማለቴ... ትእግስቱና ችሎ አዳሪነቱ ቀንሷል)። “ህይወቴ መሻሻል አለበት፤ ኑሮዬ መሻሻል ይገባዋል” የሚል ሰው ተበራክቷል። “I deserve a better Life” የሚለው ይሄው የ”middle class” አስተሳሰብ እየተስፋፋ እንደሚሄድ አያጠራጥርም። በእርግጥ እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ትልቅ ፀጋ ነው። ለመንግስት ግን እንደ ትልቅ ሸክም ሊታይ ይችላል። በአጠቃላይ፤ ጅምር የኢኮኖሚ እድገትን የተረከበው አዲሱ መንግስት፣ የዜጎችን ህይወት የሚያሻሽል ውጤት የማስመዝገብ ሸክም ይጠብቀዋል - (“የተስፋ እንጀራን” ወደ “ምጣድ እንጀራ” የመቀየር)። በጊዜ ሊጠናቀቁ የማይችሉ እቅዶችን በመረከብ ለተወቃሽነት የመጋለጥ ሸክምም ያጋጥመዋል። ሶስተኛ፤ ድህነትን ችሎ የማደር ትእግስቱ የተሟጠጠ ዜጋ በመንግስት ላይ የሚያሳድረው ሸክም አለ። ችግሮችን ሁሉ በቀድሞው ስርዓት ላይ ማሳበብ ዛሬ ዛሬ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱም ሌላ ሸክም ነውአለ። እነዚህን የመሳሰሉ ሸክሞች ምን ያህል ፈታኝ እንደሆኑ ስናስባቸው፤ “አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እድለኛ ናቸው” ለማለት ይከብደን ይሆናል። ነገር ግን፤ የድሮውን በማፍረስ ከባዶ ከመጀመር ይልቅ፤ እነዚህን ሸክሞች ተቋቁሞ የመስራት እድል ማግኘት የትና የት ይሻላል።“የነበረውን አፍርሶ ከባዶ መነሳት” ሲባል ቀላል ይመስላል እንዴ? “በፍርስራሽ ላይ ቆሞ ከባዶ መጀመር” ሲባል የእውነት እንዳይመስላችሁ። ብዙዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች፤ የስልጣንዘመናቸውን የሚጀምሩት ከ”ባዶ” ሳይሆን ከ”ኔጌቲቭ” ነው። ከመሬት ተነስተው አይደለም ግንባታ የሚጀምሩት። ከጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ነው የሚነሱት - አንዳንዴም አልም ካለ እንጦሮጦስ። አፄ ቴዎድሮስ፣ በድህነት የሾቀች፣ በጦር አበጋዞች የተተራመሰች፣ በጦርነት ታምሳ የተበታተነች አገር ላይ ነው ስልጣን የያዙት። አፄ ዮሐንስም እንደዚያው፣ በረሃብ የደከመችና በጦርነት የደቀቀች፣ በእንግሊዝ ጦር ተወርራ መሪዋ የሞተባት አገር ላይ ነው የነገሱት። የአፄ ምኒልክም እጣም ያን ያህል የተሻለ አይደለም። በውጭ ወረራ የተደፈረችና በመተማው ጦርነት መሪዋ ተገድሎ ጦሯ የተበታተነባት አገር ላይ የነገሱት ምኒልክ፣ ከረሀብና ከበሽታ እልቂትም አላመለጡም። ንግስት ዘውዲቱና ተፈሪ መኮንን (ንጉስ ኃይለሥላሴ) ተራቸው ደርሶ ወደ ስልጣን ሲወጡ፣ የተረጋጋ አገር አልተረከቡም። በአመፅ፣ በመፈንቅለ መንግስትና በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነው ስልጣን የያዙት። የደርግ አመጣጥናአጀማመርማይዘገንናል።  በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች በረሀብ እየረገፉ የነበረበት ዘመን ነው። የቀድሞውን ስርዓት በሚያፈርስ ዘመቻ አገር እየታመሰ፣ እስርና ግድያ እየታወጀ፣ ምሁራንና አንጋፎች እርስ በርስ ለመጠፋፋት እልቂት እየደገሱ ነው ደርግ ስልጣን የያዘው። ኢህአዴግና ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ደርግን በመጣል ስልጣን የያዙበትንም ታሪክ እናውቀዋለን። በጦርነት የደቀቀችና በረሃብ በምትታወቅ የአለማችን የመጨረሻ ድሃ አገር ውስጥ፣ የቀድሞውን ስርዓት በማፍረስ ነው፣ ጠ/ሚ መለስ ስልጣን የያዙት። በቀድሞው ስርዓት ውስጥ የነበሩ ምሁራንና የልምድ አንጋፎችን ጠራርጎ በሌሎች መተካት... ምን ያህል ብክነት እንደሆነ አስቡት። የነበረውን አፍርሶ ግንባታውን ከፍርስራሽ እንደመጀመር ነው። ከፍርስራሽ ሀ ብሎ የመጀመር አባዜ፣ ከዘመን ዘመን ሳይቋረጥ፣ እንዲያ እየተደጋገመ መከሰቱን ስንመለከት፣ በእርግጥም “እርግማን” ቢመስለን አይገርምም። ምናልባትም፤ የኢህአዴግና የጠ/ሚ መለስ አንዱ ስኬት፤ ያንን የዘመናት መጥፎ ታሪክ የሚለውጥና ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እድል የሚከፍት አዲስ ታሪክ ለመፍጠር መቻላቸው ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ተደጋግሞ ለታየው አስከፊ “እጣ” ሳይዳረጉ ስልጣን መያዛቸው፤ እውነትም “በጣም እድለኛ” ሊያሰኛቸው ይገባል። እንዲያውም፤ ያ የዘመናት “እርግማን” ተመልሶ እንዳይመጣና የጥንት ታሪክ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ መበርታት ነው! አቶ ኃይለማርያም የሚገጥማቸው ሸክምና እዳስ? ከባድ ቢሆንም፣ ሸክሙን አሽቀንጥሮ መጣል አይቻልም። አለበለዚያማ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ትርጉም ያጣል። ነገር ግን እንደተሸከሙ መቀጠል አለባቸው ማለት አይደለም። ያማ ለውጥ አያመጣም። ይልቅስ መፍትሄ እያበጁ ሸክሙን ቀስ በቀስ ማራገፍ ነው የሚጠበቅባቸው። ለምሳሌ በኢኮኖሚው መስክ ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች አንዱን እንመልከት። ከሁለት አመት በፊት በታወጀው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት፣ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በየቦታው እንደተጀመሩና እየተገነቡ እንደሆነ ይታወቃል። የህዳሴ ግድብ፣ የመንገድ፣ የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ግንባታ፣ የስኳር እርሻዎች ዝግጅት፣ የጤና ጣቢያዎች ግንባታ፣ የተለያዩ ፋብሪካዎች ዲዛይን ... ወዘተ። እነዚህን ስራዎች በሙሉ፣ በእቅድ ሰነዱ በተቀመጠው መጠንና የጊዜ ሰሌዳ ሰርቶ ማጠናቀቅ ከባድ ነው። ግን ደግሞ ጨርሶ ሊጠናቀቁ የማይችሉ እቅዶችም አሉ ... ለምሳሌ 10 የስኳር ፋብሪካዎችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የወጣውን እቅድ ማሳካት ፈፅሞ አይቻልም። እስካሁን አንዳቸውም አልተገነቡም። ጭራሽ ከ8 አመት በፊት የተጀመረው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም እስካሁን አልተጠናቀቀም። የባቡር ሃዲድ ግንባታውም በእቅዱ መሰረት ይጠናቀቃል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በእቅዱ መሰረት እስካሁን 1000 ኪሎ ሜትር ያህል ሃዲድ ተዘርግቶ ማለቅ ነበረበት። ታዲያ በቀሪዎቹ አመታትጠቅላላውን እቅድ (ማለትም 2400 ኪ.ሜ ገደማ ሃዲድ) ሰርቶ ማጠናቀቅ እንዴት ይቻላል? እስከ 2007 ዓ.ም ሳይሳኩ እንደሚቀሩ የሚገመቱት እነዚህና ተመሳሳይ እቅዶች፤ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ለወቀሳና ለትችት ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። እቅዶቹ የማይሳኩት በእሳቸው ድክመት ምክንያት ባይሆንም፤ የወቀሳ ሸክም ይጠብቃቸዋል። ግን መፍትሄ ሊያበጁለት ይችላሉ። ከወዲሁ በግልፅ ለዜጎች መረጃ መስጠት፣ እቅዶቹን በመከለስ ማስተካከልና ለግል ኢንቨስተሮች ማስተላለፍ፤ አንድ መፍትሄ ነው።ነገር ግን፤ እንዲህ በቀላሉና በአጭር ጊዜ መፍትሄ የማይገኝላቸው ሌሎች ሸክሞች አሉ። ባለፉት አመታት ብዙ የኑሮ ችግር የተደራረበባቸው ዜጎች፤ እስካሁን ችግራቸውን የተቋቋሙት የነገን ተስፋ በመሰነቅ ነው። የኢኮኖሚ እድገት ጅምሮችን እዚህና እዚያ እያዩ፤ ከዛሬ ነገ ህይወታችን ይሻሻላል በሚል ተስፋ፣ በጎ ዘመን እንዲመጣ ሲጠብቁ ቆይተዋል። “የተስፋ እንጀራ”፣ ስንቅና ቀለብ ሆኖላቸው ዘልቋል። ግን እስከ መቼ? የኢኮኖሚው እድገት፤ የዜጎችን ህይወት የሚያሻሽል መሆን አለበት። “የተስፋ እንጀራ”፣ በእውን በሚጎረስና በሚበላ የእውነት እንጀራ እንዲለወጥ መስራት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትልቁ ፈተና ነው - ለዚያውም ጊዜ የማይሰጥ ፈተና። ለምን ቢባል፤ የዛሬና የነገ ዜጎች፤ ከቀድሞዎቹ የትናንት ዜጎች በእጅጉ ይለያሉ። የቀድሞቹ ዜጎች በአብዛኛው ድህነትን ችለው የመኖር ብዙ ትእግስት ነበራቸው። የዛሬና የነገ ዜጎች ግን፤ ከድህነት ጋር “ተቻችለው” የመኖር ትእግስታቸው ያን ያህልም ብዙ አይደለም። እንዲያውም፣ “የተሻለ ኑሮ ይገባኛል” (“I deserve a better Life”) የሚል መንፈስ የተላበሱ ዜጎች እየተበራከቱ መጥተዋል። የድሮውንና የዘመናችንን የስደት አይነቶች በማነፃፀር ልዩነቱን መገንዘብ የምንችል ይመስለኛል። የድሮው ስደት፣ በአብዛኛው ህይወትን ለማዳን ነው። የዘመናችን ስደት ግን፣ በአብዛኛው “ህይወቴ መሻሻል አለበት” በሚል የሚካሄድ ነው። ለምሳሌ በደርግ የቀይ ሽብር ጊዜ ብዙ ሰው ለህይወቱ በመስጋት ተሰዷል - ከእስርና ከግድያ ለማምለጥ። ለ”ብሄራዊ ውትድርና” በግዳጅ እየታፈሰ በጦርነት ላለመማገድም ብዙ ወጣት አገሩን ጥሎ ሄዷል። በእርግጥ፣ የተሻለ ኑሮ አገኛለሁ ብሎ የተሰደደም ይኖራል፤ ግን ቁጥሩ አነስተኛ ነው። የአብዛኛው ሰው ከአገር የኮበለለው፤ ህይወቱን ለማዳን ነው። እንዲያውም፣ አብዛኛው ሰው፣ እስርና ግድያ አፍጥጦ ካልመጣበት፤ አልያም የሚቀመስ የሚበላ ካላጣ በስተቀር፣ ከሰፈር ከመንደሩ የመነቃነቅ ፍላጎት አልነበረውም። ድህነቱንና ችግሩን ቻል አድርጎ፣ “የባሰ አታምጣ” እያለ በትእግስት መከረኛ ኑሮውን ይቀጥላል። እፍኝ እህል ሲጠፋ ነው፣ ከረሃብና ከሞት ለማምለጥ አገሬው የሚሰደደው። ዛሬ ግን፣ የአገራችን ሰው ረሃብንና ሞትን ለማምለጥ ሳይሆን ከድህነትና ከችግር ለመገላገል ይሰደዳል - የተሻለ ህይወት ፍለጋ። የተማሩ ዜጎችና ተመራቂ ወጣቶች በየአመቱ እየጨመሩ ሲሄዱም፣ “ህይወቴ መሻሻል አለበት” የሚለው መንፈስ እየተስፋፋ እንደሚመጣ አያጠራጥርም። “ባለመማሬ ድህነት ተጫወተብኝ” በማለት ራሱን ተወቃሽ የሚያደርግ ዜጋ እያነሰ ይሄዳል - ተምሯላ። ታዲያ ተምሮከተመረቀ በኋላ፣ ከስራ አጥነትና ከድህነት ያላመለጠው ለምንድነው? ተጠያቂው ማን ነው? ያኔ ጣቱን መንግስት ላይ የሚቀስር ሰው ይበራከታል። “ተምሬያለሁ! የተሻለ ህይወት ይገባኛል!” ብሎ ይጮሃል ...”I deserve a better Life”። አቶ ኃይለማርያም ይህንን ዘመን አመጣሽ የዜጎችን ዝንባሌ ለማስተናገድ የሚችል የኢንቨስትመንትና የነፃ ገበያ ስርዓት ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል። በፖለቲካው መስክም እንዲሁ፣ የተረጋጋ ሰላም ቢኖርም፣ ከሰላም በተጨማሪ ነፃነትን የሚጠይቁ ዜጎች ቁጥራቸው መጨመሩ አይቀርም። ወጥቶ ለመግባት እድል የሚሰጥ ሰላም በአገራችን መገኘቱ ጥሩ ነው። ነገር ግን፣ የራስን ህይወት በራስ ምርጫ ለመምራት የሚያስችል ነፃነትም ይስፈልገናል። የወላጆች ወይም የአስተማሪዎች ግርፊያ እየቀነሰ በሄደ ቁጥር፣ የመንግስትን ቁንጥጫና እርግጫ ለመታገስ የማይፈልጉ ዜጎችም ይበራከታሉ። በዚያ ላይ፣ በዛሬው የ”ኢንፎርሜሽን ዘመን”፣ ኢትዮጵያ ከአለም ተነጥላ ወደ ኋላ መቅረት አትችልም። በሌሎቹ አገሮች ስላለው ነፃነት በቲቪ ቻናሎችና በኢንተርኔት ባየንና በሰማን ቁጥር፤ እኛም ነፃነት ያምረናል። ዲሞክራሲና የነፃነት ስርዓት የሚገነባው በሂደት ነው እየተባልን ዘላለም ስንጠብቅ መኖር አንችልም። በአፍሪካ አገራት ሳይቀር፣ የሚዲያ ነፃነት እየተስፋፋ ጋዜጣና ሬድዮ፣ ቲቪና ዌብሳይት ሲበራከቱ በሚታይበት ዘመን፤ ኢትዮጵያ ለብቻ ተነጥላ ወደኋላ ብትቀር ምን ይባላል? በአፍሪካ አገራት ሳይቀር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት እየተንቀሳቀሱና እየተከራከሩ፣ በምርጫ እየተፎካከሩና ስልጣን ላይ በሰላም እየተፈራረቁ ስናይ፣ ኢትዮጵያ ብቻዋን እንደ ቻይና ወይም እንደ ኩባ በአንድ ፓርቲ ስር መቀጠል አለባት? በእርግጥ፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማየት መብቃታችን አንድ መልካም እርምጃ ነው። የተጀመረው የመተካካት አሰራር ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ለማድረግ፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ያሳለፈው ውሳኔም በጎ ነው። ከቻይናና ከኩባ የተገኘ ልምድ ሳይሆን አይቀርም። ለምሳሌ፣ የቻይና መንግስት መሪ ከ10 አመት በላይ ስልጣን ላይ እንዳይቆይ የሚከለክል ህግ ወጥቷል - አገሪቱን በብቸኝነት እየገዛ በሚገኘው ፓርቲ። በ1985 ዓ.ም የቻይና ፕሬዚዳንት የሆኑት ጂያንግ ዘሚን ለአስር አመታት ስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ ወርደዋል። በምትካቸው በ1995 ዓ.ም ወደ ስልጣን የወጡት ሁ ጁንታው፣ ዘንድሮ በሌላ ተተክተው ስልጣን ይለቃሉ። በኩባም ተመሳሳይ አሰራር ተጀምሯል። ከሃምሳ አመት በላይ ኩባን ሲገዙ የቆዩት ፊደል ካስትሮ በእርጅናና በህመም ከስልጣን ሲወርዱ፣ ወንድማቸውን የተኩ ቢሆንም፣ ፓርቲው ወዲያውኑ አዲስ ህግ አውጥቷል። የአገሪቱ መሪ በስልጣን ላይ መቆየት የሚችለው ለአስር አመታት ብቻ ነው ይላል ህጉ። ኢህአዴግም ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ የፓርቲ ህግ አውጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎች ሚኒስትሮችን ጨምሮ፣ በከፍተኛ ስልጣን ላይ የሚቀመጡ የፓርቲው ሪዎች፣ ከሁለት የምርጫ ዘመን (ከ10 አመት) ለበለጠ ጊዜ ስልጣን ላይ እንዳይቆዩ ይደረጋል ብሏል - ኢህአዴግ። መልካም ውሳኔ ነው። የስልጣን እድሜን ለማራዘም በማሰብ በባለስልጣናት የሚፈፀሙ ጥፋቶችን ለመቀነስ ያግዛል ብዬ አምናለሁ። ምንም ላይፈይድለት ለምን ጥፋት ይሰራል? ከአስር አመት በላይ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችል ቁርጡን ካወቀ፣ የስልጣን ጊዜዬን አራዝማለሁ ብሎ ወደ ህገወጥ ድርጊት የሚገባበት ምክንያትአይኖረውም።ባለስልጣናት የህግ ተገዢ እንዲሆኑ ሊገፋፋቸው ይችላል ማለት ነው። እንዳሻው ህግን እየጣሰ ጥፋትና ግፍ ቢፈፅም፣ የስልጣን ዘመኑ ሲጠናቀቅና ከስልጣን ሲወርድ የተጠያቂነት ጣጣ አፍጥጦ ሊመጣበት እንደሚችል ያውቃላ። እውነትም፣ የስልጣን ዘመን የጊዜ ገደብ እንዲኖረው መደረጉ ደግ ነው። ነገር ግን፣ በሰለጠኑት አገራት እንደሚታየው፤ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበትና ስልጣን ላይ የሚፈራረቁበት ሰላማዊ የነፃነት ስርዓት በአገራችን እውን ሆኖ ማየት አለብን - እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገራት። ይህም የኢዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸክም ነው።

 

 

Read 26570 times Last modified on Friday, 05 October 2012 13:34