Saturday, 12 February 2022 11:42

ያለ ህጋዊ ፍቃድ የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ ተከለከለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ህጋዊ ፈቃድ ሣያወጡ በተለያዩ መንገዶች የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በማቋቋም፣ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ መከልከሉን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግለሰቦችና የተደራጁ ቡድኖች በተለያዩ ሁኔታዎች “ለተቸገሩ ለተፈናቀሉና ለታመሙ ሰዎች” በሚል የእርዳታ ገንዘብ በማሰባሰብ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት እንደሚገኙ ተደርሶበታል። ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠርና ለማስቀረት የእርዳታ ማሰባሰብ ተግባር ህጋዊ አሠራርን እንዲከተል ማድረግ የግድ መሆኑን ያመለከተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤  ያለ ህጋዊ ፈቃድ የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብን የሚከለክል መመሪያ ማውጣቱን ጠቁመዋል።
መመሪያው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮም ማንኛውም ሰው ከሚመለከተው አካል ህጋዊ ፈቃድ ሳይወስድ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በማቋቋምም ሆነ በግሉ  ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ መስራት የማይችል መሆኑ ተመልክቷል። በዚህ መሠረትም፤  ከባለስልጣኑ ፈቃድ ሳያወጡ  በህዝብ  ስም በማንኛውም መንገድ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራዎችን መስራት የተከለከለ በመሆኑ ህብረተሰቡ በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ ከመሳተፍ እንዲቆጠብ ያሳሰበው  ባለስልጣኑ፤  በህዝብ ስም የሚሰበሰብ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ እንዳይባክን የመከላከልና የመጠበቅ ስልጣንና ኃላፊነት  እንዳለበትም   አስታውቋል።
 ከዚህ ቀደም ፈቃድ ሳይኖራቸው በተለያየ ሁኔታ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ አቋቁመው ገንዘብ በማሰባሰብ ተግባር  ላይ የሚገኙ በርካታ  ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸውን የጠቆመው ባለስልጣን መ/ቤቱ፤ እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ከባለስልጣኑ ፈቃድ በመውሰድ ወደ ህጋዊ አሰራር መግባት እንዳለባቸውም  አሳስቧል።
በመመሪያው መሰረት ወደ ህጋዊ አሠራር በማይገቡ አካላት ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም ነው ያስጠነቀቀው።



Read 965 times