Print this page
Saturday, 12 February 2022 11:43

ቢጂአይ ኢትዮጵያ፤“ቢጂ አይ ኤክስ ፒ የተባለ” ፕሮግራሙን ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያስተዋውቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ተማሪዎች በየዓመቱ ለ2 ወራት ወጪያቸው ተሸፍኖ የስራ ልምምድ ያደርጋሉ

             ቢጂአይ ኢትዮጵያ የፊታችን ማክሰኞ ከጠዋቱ 3፡30፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኤፍቢኢ አዳራሽ የ”ቢጂ አይ ኤክስ ፒ” ፕሮግራሙን አዲስ ለገቡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚያስተዋውቅ ገለጸ።
ፕሮግራሙ ተማሪዎች ገና ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ በሚፈልጉት ሙያ ከአካዳሚ ዕውቀት በተጨማሪ የሥራ ልምምድ እንዲያገኙና ሲመረቁ በሙያቸው የተሻለ አቅምና ችሎታ እንዲኖራቸው ለማገዝ ታልሞ የተቀረፀ ነው ተብሏል።
በዚህ ፕሮግራም የሚታቀፉ ተማሪዎች፣ በየዓመቱ ለ2 ወራት ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ወጭያቸው ተሸፍኖ በቢጂአይ 5ቱም ፋብሪካዎች ውስጥ ሙያቸውን ለማዳበር የሥራ ልምምድ ያደርጋሉ።
በፕሮግራሙ ውስጥ የሚያልፉ ወጣቶች ሙያቸውን ጠንቅቆ ከማወቅ በተጨማሪ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር፣ በመረጡት የሥራ መስክም በልበ ሙሉነት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅምን እንደሚፈጥርላቸው፣ በቢጂአይ ኢትዮጵያም የመቀጠር ከፍተኛ ዕድል እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል። የፊታችን ማክሰኞ በሚካሄደው የፕሮግራሙ ትውውቅ ስነ-ስርዓት ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ግቢዎች (አራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ኤፍቢኢ እና ንግድ ሥራ ካምፓስ) በፈቃደኝነት የተመዘገቡ የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች የሚታደሙ ሲሆን የቢጂአይ ባለሙያዎችም “ቢጂአይ ኤክስፒ”ን በተመለከተ ማብራሪያ በመስጠት ለተማሪዎቹ ግንዛቤ እንደሚያስጨብጡ ታውቋል።
ተቋሙ ከተመረጡ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር የ2ኛ ዓመት የተለያዩ ዲፓርትመንት ተማሪዎችን የሚያሳትፈውን “ቢጂ አይ ኤክስ ፒ” የተባለ ፕሮግራም የጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን ዓምና መመዘኛውን ያሟሉ ተማሪዎችን ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተቀብሎ እጅግ አመርቂና አስደሳች ውጤት ማግኘቱን ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

Read 4465 times
Administrator

Latest from Administrator