Saturday, 12 February 2022 11:46

በማንነት ተኮር ጥቃቶች ጉዳይ መንግስት የራሱን አስተዳደር እንዲፈትሽ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   መንግስት በየጊዜው የሚፈጸሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም ያሳሰቡት የተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ለዚህም መንግስት የራሱን አስተዳደር እንዲፈትሽ አበክረው ጠይቀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተለይ በምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞኖች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ ማፈናቀልና ንብረት ማውደም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የጠቆመው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ "ይህ ወንጀል የሚፈፀመው በኦነግ ሸኔ ብቻ ሳይሆን በከፊሉ የመንግስት አመራር ደንታ ቢስነትና በከፊሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ መሆኑ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል" ብሏል።
"እነዚህ የተቀናጀ ጥቃት ፈጻሚዎች የአገር አንድነት ጠንቅ ናቸው፡፡" ያለው ፓርቲው፤ በጥቃቱ ፈጻሚዎች ላይ አስተማማኝ ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም በህዝብ ላይ ወንጀል የፈጸሙ ለህግ እንዲቀርቡና ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) በበኩሉ፣ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው በፌደራል መንግስቱ ቸልተኝነት ነው የሚል እምነት እንዳለው በመግለፅ፣ መንግስት ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፣ ህዝብም በመንግስት ላይ ግፊትና ጫና እንዲያደርግ አበክሮ ጠይቋል።
ዜጎች እጅግ በተበራከተ ጥቃት ሳቢያ "መንግስት ደህንነቴን አያስጠብቅልኝም” ብለው ከደመደሙ ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ እንደምንገባ ሊታወቅ ይገባል ያለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ መንግስት ዜጎችን ከማንኛውም ጥቃት የመታደግ ቀዳሚ ሃላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ፣ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስቧል።
የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ያልቻሉ መንግስታዊ ሃላፊዎች ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ያስገነዘበው ፓርቲው፤ የሟች ቤተሰቦችና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎችም ተገቢ ካሳ እንዲያገኙ ጠይቋል፤ በወለጋ የተፈጸመውን የንፁሃን ጭፍጨፋና ማፈናቀል ባወገዘበት መግለጫው፡፡
መንግስት ባወጣው መግለጫ፤ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ፣ 168 ንፁሃን ዜጎች በኦነግ ሸኔ ግድያ እንደተፈጸመባቸውና ከእነዚህም ውስጥ 87ቱ በጅምላ ተገድለው አስከሬናቸው መገኘቱን አስታውቋል፡፡ በተለያዩ ወረዳዎችም 81 ተጨማሪ ዜጎች በተመሳሳይ ጥቃት መገደላቸውን መንግስት አስታውቋል፡፡


Read 10147 times