Saturday, 12 February 2022 11:51

በሰኔ 15ቱ ግድያ ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾች ከዕድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት ሊደርስ የሚችል ቅጣት ይጠብቃቸዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - ከ32ቱ ተከሳሾች መካከል አራቱ በነጻ ተሰናብተዋል
    - ተከሳሾቹ በተሰጠው የጥፋተኛነት ውሳኔ በእጅጉ ማዘናቸውን ተናግረዋል
                 
            ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ፕሬዚዳንትና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በእስር ላይ ከነበሩትና ጉዳያቸው ሲታይ ከቆዩ 32 ተከሳሾች መካከል 28ቱ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሲባሉ፣ አራቱ ደግሞ ከክሱ በነጻ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጥቷል  
28ቱ ተከሳሾች ጥፋተኛ ናችሁ በተባሉበት የወንጀል ህግ መሰረት፤ ከዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እስከ ሞት ሊደርስ የሚችል ቅጣት  እንደ ሚጠብቃቸው አንድ የህግ ባለሙያ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ላይ እንደተገለጸው፤ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት በህብረትና በማደም ህገ-መንግስትንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን በመናድ አደጋ ላይ ለመጣልና የክልሉን  ስልጣን ባልተገባ መንገድ ለመቆጣጠር በማሰብ፣ በወንጀል ድርጊት ላይ ተሳትፈዋል ተብሏል።
በክሱ ጥፋተኛ የተባሉት 28ቱ ተከሳሾች፣ የአማራ ክልል አመራሮች የነበሩትን ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ እዘዝ ዋሴ፣ አቶ ምግባሩ ከበደንና ሌሎች የልዩ ጥበቃ አባላት በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉና እንዲቆስሉ  በማድረጋቸው ጥፋተኛ ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል ዐቃቢ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበውን ክስ ያስረዱልኛ ያላቸውን የሰውና የሰነድ ምስክሮች ተቀብሎ መመርመሩን ያመለከተው የፍ/ቤቱ ውሳኔ፤ የዐቃቤ ህግ የሰው ምስክሮችና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት የተገኙ የሰነድ ማስረጃዎች ተከሳሾች በወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጦኛል ብሏል እነዚህን ተከሳሾችም በነጻ ከክሱ እንዲሰናበቱ  ማድረጉን አመልክቷል።  ከክሱ በነጻ እዲሰናበቱ የተወሰነላቸው ተከሳሾች ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባው፣ ኮሎኔል  ሞገስ ዘገየ፣ አቶ የማነ ታደሰና አቶ ስለሺ ከበደ እንደሆኑም ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ አመልክቷል። ፍ/ቤቱ ቀሪዎቹ 28ቱ ተከሳሾች የዐቃቤ ህግን ማስረጃ ማስተባበል አለመቻላቸውን ጠቁሞ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ናችሁ ብሏል።
ከ70 በላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ የቀረበባቸውን ክስ በአግባቡ መከላከላቸውን የገለፁት ተከሳሾች፤ ፍ/ቤቱ በቀረበባችሁ የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ናችሁ የሚል ውሳኔ መስጠቱ በእጅጉ ያሳዘናቸው መሆኑን መናገራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
ተከሳሾቹ ጥፋተኞች ናችሁ የተባሉበት የአማራጭ የወንጀል ህግ ቁጥር 238/2፣ ከዕድሜ ልክ ፅኑ ክሊከት እስከ ሞት ሊያደርስ በሚችል ቅጣት ሊያስቀጣ እንደሚችል ያብራሩት የህግ ባለሙያና ጠበቃው አቶ ኢሳያስ ታምራት፤ ፍ/ቤቱ ተከሳሾቹ የሚያቀርቡትን የቅጣት ማቅለያ ተመልክቶና እስካሁን በእስር የቆዩበትን ጊዜ ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ የቅጣት ማሻሻያ ሊያደርግላቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸው የወንጀል ክስ የአማራ ክልል አመራሮችን ከመግደል በተጨማሪ በህዝብ አሮና ደህንነት ላይ ሁከትና አደጋ በመፍጠር፣ በህገ መንግስት የተቋቋመ ስርዓትን በሃይል ለማፍረስ መሞከርና ሌሎች ወንጀሎች እንደሆኑ ያመለከቱት የህግ ባለሙያው፤ እነዚህ ወንጀሎች ደግሞ በወንጀል ህጉ ከባድ ወንጀሎች ተብለው የተገለፁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ፍ/ቤቱ ከክሱ ነጻ ያደረጋቸው አራት ተከሳሾች ከእስር እንዲፈቱ ለባህርዳር ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ጥተኛ የተባሉትን የ28ቱን ተከሳሾች የፍርድ ማቅለያ ለመቀበል ለየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

Read 10361 times