Saturday, 12 February 2022 11:53

ያለጊዜው የመጣው አገራዊ ምክክር

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)


               ማስፈንጠሪያ
አገረ መንግሥቱን በማይናወጥ መሰረት ላይ ለማቆም፤ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት የሚያስችል የውይይት መድረክ ማመቻቸት አስፈላጊ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በላይ  አምባገነናዊ አገዛዝ ጭኖብን የከረመው ሕወሓት፣ ጊዜውን ጠብቆ፣ ወደ ዳር መገፋቱ ደግሞ አገራዊ መቃቃርን በሰላማዊ መድረክ ለመፍታት ትልቅ ዕድል ከፍቷል፡፡
ይህን መሰሉ ውይይት ከጥቃቅን ልዩነቶቻችን ይልቅ፤ በጋራ እንደ ሕዝብ ለተሻገርናቸው የታሪክ ጉድባዎች፣ እውቅና የሚሰጥና የትስስር ገመዳችንን የሚያጠናክር መሆን ይኖርበታል፡፡ ትልቁ ሥጋት፣ አገራዊ ምክክሩ ከዚህ ቀደም በተሞከሩ መንገዶች እንዳይሄድና ፍጻሜው ፍሬ አልባ  እንዳይሆን ነው፡፡
በዘመናት የተፈራረቁ ገዢዎች፣ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሄዱበት አግባብ፣ ሕዝብን ማእከል ያደረገ እንዳልነበረ ታሪካችን ይመሰክራል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ፣ ሥልጣን ላይ ባለው ኃይል አነሳሽነት፣ አጀንዳው ይቀረጽና ከላይ ወደ ታች ይጫናል፡፡ በማሳረጊያው ሕዝብ እንደመከረበት ተደርጎ ይጸድቃል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ በአሁኑ የምክክር መድረክም እንዳይንጸባረቅ ስጋት ያላቸው  ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
ኮሚሽኑን የማቋቋሚያ አዋጁ ውስንነት
የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁ፣ በውስጡ የያዛቸው አንዳንድ አንቀጾች ብዥታን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ገና በመንደርደሪያው ላይ ያስቀመጠውን አሻሚ ጽንሰ ሐሳብ  ለአብነት ያህል መጥቀስ  ይቻላል፡፡
“መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ፣ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመገንባትና በሂደቱም የመተማመንንና በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት፤ ታሳቢ ያደረገ ነው፤” በማለት ያትታል፤ በመንደርደሪያው፡፡
“መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች” የሚለው ነጥብ ለትችት በር የሚከፍት ነው፡፡ በአዋጁ ላይ ለጽንሰ ሐሳቡ ተገቢው ትርጓሜ አልተቀመጠም፡፡ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚባሉት ምንድን ናቸው? ሕገ መንግሥቱ? የፌዴራል ሥርዓቱ? ወይስ ዘውግ ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀት? ምንም የተብራራ ነገር የለም፡
አዋጁ ለኮሚሽኑ መቋቋም እንደ መግፍኤ የወሰደው፣ በሀገረ መንግሥቱ ላይ ሲንከባለል የመጣውን ዘርፈ ብዙ ችግር  ነው፡፡
እዚህ ጋ ለሂስ ተጋላጭ የሚያደርገው፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ተገዳዳሪ ፈተና፣ በጊዜ ማእቀፍ አለመቀመጡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ታሪክ፣ ከ3000 ዓመታት በላይ እንደሚሻገር ይታወቃል፡፡ ስለዚህ፤ አሁን የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑት መጠነ ሰፊ ችግሮች፣ መነሻቸው ከየትኛው ዘመነ መንግሥት እንደሚጀምር በግልጽ መጠቆም ነበረበት፡፡
የምክክር ኮሚሽኑ እና የትግራይ ሕዝብ
የሀገሪቱን ቀውስ በማባባስ ረገድ አፍራሽ ሚና የነበረው አሸባሪው ሕወሓት፣ አሁንም የትግራይ ህዝብን እንደ ምርኮ ይዟል፡፡ ሕወሓት እንኳን ጠባብ የቆዳ ስፋት ያላትን ትግራይ ክልል ይቅርና መላው ኢትዮጵያን ለሃያ ሰባት ዓመታት፣ በማያፈናፍን የአገዛዝ ሰንሰለት ጠርንፎ ይዞ ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ወንድም የሆነው የትግራይ ሕዝብ፣ ከዚህ አውዳሚ ድርጅት ነጻ ሳይወጣ የሚደረግ ሀገራዊ ምክክር ምን ያህል ምሉዕ ይሆናል? የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ  ነው፡፡
አንዳንዶች ይህ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ፣ ለምክክሩ እንቅፋት እንደማይሆን ይሞግታሉ፡፡ ከክልሉ ውጪ ያሉ በርካታ የትግራይ ማኅበረሰብና የሲቪክ ድርጅቶች፣ ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን አውድ በመፍጠር የሚፈለገውን ግብ ማሳካት እንደሚቻልም ያምናሉ፡፡
እነዚህ የፖለቲካ አካላት ግን፤ የትግራይ ሕዝብን ፍላጎት በአግባቡ ያንጻባርቃሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡እንኳን በትግራይ ክልል፣ በመላው ኢትዮጵያ ያሉት የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁመና የሚያስመካ አይደለም፡፡ ሕወሓት ባልጠፋበት ኹኔታ፣ በቀሪው ሕዝብ ዘንድ የሚደረግ ፖለቲካዊ ምክክር፣ ለዘመናት የኖረውን ሀገራዊ ቁስላችንን በቅጡ ያክማል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው፡፡ ለመሆኑ፣  ከምክክሩ በፊት መጤን የሚገባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
የዜጎች ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ
አንድ መንግሥት ሉአላዊ ሥልጣን አለው የሚባለው፣ ሕግ የማውጣት የማስፈጸምና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱ ከጥያቄ ውስጥ የማይወድቅ ከሆነ ብቻ እንደሆነ  ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ በዚህ ረገድ ብዙ እንደሚቀረው በገሀድ እየታዘብን  ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በየቀኑ እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው። መንግሥት ማንኛውንም የዳር ኃይል፣ አደብ ለማስገዛት የሚያስችለውን አቅም (monopoly of violence) በተገቢው ረገድ አልተላበሰም፡፡ ሰላምና ደህንነትን በአግባቡ ማስጠበቅ የሚያስችል አደረጃጀት እስከ ታችኛው አስተዳደራዊ መዋቅር ድረስ አልወረደም፡፡ የታችኛውን መዋቅር፣ ጽንፈኞች እንዳሻቸው እየፈነጩበት ነው፡፡ ኦነግ ሸኔ በሚል የዳቦ ስም፣ ሕጋዊ መዋቅር ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየተድበሰበሱ ነው፤ በሚል የሚከሱ በርካቶች ናቸው፡፡
የኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር አሰፋ ተገኝ፣ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ምልከታቸውን ከኢሳት ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡
 “የሀገራዊ ምክክር አጀንዳው ጊዜው አሁን አይደለም፡፡ ከምክክሩ በፊት መከወን የሚገባው ወሳኝ ተግባር ይኖራል፡፡ ከእዚህ ውስጥም፤ በዜጎችና በሀገር ደህንነት ላይ ጋሬጣ የሆኑትን እንደ ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔን የመሳሰሉ አውዳሚ ድርጅቶችን የማጥፋቱ ዘመቻ በተገቢው ረገድ መከናወን  ይኖርበታል፡፡”  ብለዋል፡፡
የሁሉም ዜጋ ድምጽ የተካተተበት ሀገራዊ ምክክር እውን እንዲሆን ከተፈለገ፤ በቅድሚያ የመንግሥት የውስጥ ሉአላዊ ሥልጣን በማያሻማ መልኩ መረጋገጥ ይገባዋል፡፡
የሕገመንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋም
አሁን ለምንገኝበት ሁሉን አቀፍ ቅርቃር፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ያወጣው ሕገ መንግስታዊ ሰነድ፣ የአንበሳው ድርሻ እንደሚወስድ  እሙን ነው፡፡
ሰነዱ ለዘር ማንነት የሚሰጠውን ትኩረት ያህል፣ ለዜግነት ወይም ሁለት እና ከዛ በላይ የዘር ማንነት ላላቸው /meta-ethnic identities/ ወገኖች እውቅና አይሰጥም። ሰነዱ ኢትዮጵያዊ አሰባሳቢ ማንነትን ወዳ ዳር ገፍቶታል፡፡  በሕገመንግሥቱ ፊት ግርማን ለመላበስ፤ በአንድ የዘር ከረጢት ውስጥ ራስን መቀንበብ  የግድ ይላል፡፡ ይህን ዓይነት ሥነልቦናዊ ቅኝትን የታጠቀ ከፋፋይ ፖለቲካዊ ስሌት ደግሞ፤ እንደ ሕወሓት ላሉ ሕዳጣን የፖለቲካ ኃይሎች ከፍተኛ ትርፍን ሲያስገኝ ኖሯል፡፡
በመሆኑም፤ ስለሌሎች ጉዳዮች ለመወያየት መድረክ ከመመቻቸቱ በፊት፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዜጎች ፈቃድ የሚቀረጽ ሕገ መንግሥትን ለዐይነ ሥጋ ለማብቃት፣ የአርቃቂ ኮሚሽን መቋቋም አለበት፡፡
ማሰሪያ
በአጠቃላይ፣ ሀገራዊ ቀውሱን የሚያባብሱ ጉዳዮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የውይይት መድረክ የማመቻቸት እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚበረታታ ነው፡፡  
ነገር ግን፤ ከዚህ ቀደም በታሪክ አጋጣሚ ይህንን በመሰሉ የውይይት ማእቀፎች ላይ የተስተዋሉ ሕጸጾች ዳግም እንዳይከሰቱ፣ ቅድመ ኹኔታዎችን በአግባቡ ማጤን ማሳረጊያውን የሰመረ  ያደርገዋል፡፡

Read 1674 times