Sunday, 13 February 2022 00:00

የተሻለ እንጂ የባሰ ለውጥ እንዳይመጣ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

     • የትኞቹን ነባር ነገር ለማስወገድና ለማጥፋት፣ ለማስተካከልና ለማሻሻል?
      • የትኞቹን ህጎች ለማወጅና ተግባራዊ ለማድረግ?
                
                በምክክር አዋጅ ውስጥ፣ “አዲስ የመንግስት ስርዓት ለመፍጠር” የሚለው አባባል፣ ከሌሎቹ “አብዮተኛ አባባሎች” ይልቅ፣ ለቁጥብ አተረጓጎም ያስቸግራል። “ሕገ-መንግስትን መቀየር” ከሚል ትርጉም  ጋር የተቆራኘ ይመስላል። ቢሆንም ግን፣ ከዚህ ውጭም ሊታይ ይችላል።
ያለፉት ጥቂት አመታትን በምሳሌነት ተመልከቱ። እጅግ አወዛጋቢ የነበሩ ህጎችን (የምርጫ፣ የፓርቲዎች ምዝገባ፣ የጸረ-ሽብር፣ የማህበራት ምዝገባ ህጎችን) በማሻሻል፣ የቅራኔ መንፈሶችን ለመቀነስ ተሞክሮ የለ? ሕገመንግስት ሳይቀየር ነው፤ በርካታ አወዛጋቢ ሕጎች የተሻሻሉት ወይም የተለወጡት። አሁንስ አይቻልም?
ህገ-መንግስትን የመቀየር ሽኩቻ ሳይባበስ፣ ፖለቲከኞችም ወደ ትንቅንቅ ዘመቻ መሽቀዳደም ሳይስፈልጋቸው፣ ቅራኔን የሚያረግቡ ዘዴዎችን መፍጠርና ወደ መግባባት የሚያመሩ መንገዶችን መክፈት አይቻልም ወይ? ከተቻለ፣ እና ከተሳካ፣ ውጤቱ ቀላል አይሆንም። “አዲስ የፖለቲካ ስርዓት” እንደመፍጠር ይቆጠራል።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ህገ-መንግስትን በመቀየር ብቻ አይደለም፤ መልካም አገራዊ ለውጥ የሚመጣው ማለቴ ነው።
አዎ፣ “ህገ-መንግስትን መለወጥ”፤ “አዲስ ለውጥ”፣ … “ለውጥ”፣ “ለውጥ”.. “ለውጥ” የሚል ንግግር፣ የብዙዎቻችንን ቀልብ ለመማረክና ትኩረት ለማግኘት ያመቻል። ድጋፍ ያስገኛል። ብዙዎቻችንን ያግባባል፤ ያስማማል። ይሄ፣ ጥሩ ገፅታው ነው - “የስር-ነቃይ ምክክር” ማራኪ ገፅታ።
ደግሞም፣ ጠንካራ ድጋፍ ማግኘትና የሰዎችን ትኩረት መሳብ፣ በጣም ጠቃሚ ነው። ቢሆንም ግን፤ ብቻውን በቂ አይደለም።
ህገ-መንግስትን በመለወጥ፣ አዲስ ስርዓት በመፍጠር፣ ብዙ የአገራችን የፖለቲካ ችግሮችን በአንዴ ማስወገድና መገላገል ቢቻል፣ መልካም ነበር። ያጓጓል። መታደል ነበር።
ችግሩ ግን፤ “ለውጥ” የሚለው ቃል፤ ምን አይነት ለውጥ እንደሆነ አይገልጽም። “አዲስ ስርዓት መፍጠር” ብለን ስናስብም፣ ምን ዓይነት አዲስ ስርዓት እንዳሰብን፣ አንዱ የሌላውን ሃሳብ አያውቅም።
አንተና አንቺ፣ እሱ እና እኔ፤ ይሄኛው ፓርቲና ያኛው ፓርቲ፣… በምናብ የሚታየን የለውጥ አይነት ምን ምን እንደሆነ አስቡት።
አንዷ ፖለቲከኛ፣ በምናብ የቀረፀችው ሃሳብና ምኞት፣ ከነባሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል።
የሌላኛዋ ፖለቲከኛ ሃሳብና ምኞት ደግሞ፤ ከነባሩ እጅግ የባሰ፣ አስፈሪና አደገኛ እንደሚሆን አትጠራጠሩ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ እንዲህ አይነት ብዙ ልዩነቶችን፣ ከበቂ በላይ አይተናል። ስንቱን ነውጥና ስንቱን ጥፋት እንዳሳለፍን አስቡ።
“ለውጥ” የሚለው ሃሳብ፣ ብዙዎቻችንን ቢያስማማም፤ “የአንዳንድ ሰው የለውጥ ሃሳብ”፣ የቱን ያህል ፍሬን እንደሚበጥስ አላያችሁም?
“የአንዳንዱ ፓርቲ የለውጥ ምኞት”፣ ምንኛ አስፈሪና አጥፊ እንደሚሆን በተደጋጋሚ አልታዘባችሁም?
“የስር-ነቀል ለውጥ” ትልቅ ተስፋና ትልቅ አደጋ፣ የዚህን ያህል ከባድ ነው።
“ለውጥ” ማለት፣ “አንቺ የተመኘሽው ለውጥ” ማለት ብቻ አይደለም።
አንተ የተመኘኸው “አዲስ ስርዓት” ማለት ብቻ አይደለም - “አዲስ ስርዓት” ማለት።
አንቺ ብቻ ወይም አንተ ብቻ የምትቆጣጠሩት ነገር አይደለም - ጉዳዩ።
ታዲያ፣ ልትቆጣጠሩት የማትችሉትን ጉዞ፤ በጥድፊያና በስሜት ሳይሆን፣ በጥንቃቄና በስክነት ብትጓዙት አይሻልም?
አዎ፣ በፍጥነት መጓዝ ያጓጓል። ግን፣ ከቁጥጥራችሁ ውጭ እንደሆነና ወዴት እንደሚያመራ እንደማታውቁ ስታስቡትስ?
ቁጥብነት (prudencre)፣ … አንድ የፖለቲካ መርህ መሆን የሚገባውም በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
በሌላ አነጋገር ልንገልፀው እንችላለን።
የተሻለ ለውጥ እንጂ፣ የባሰ ለውጥ እንዳይመጣ መጠንቀቅ፤ ሁሌም በጎ ነው።
“አዲስ የመንግስት ስርዓት” የሚለው አገላለጽም፣ በዚህ መነጽር ብናየው ይሻላል።
“አዲስ” የሚል ቃል፣ እንዲሁ በጥሬው፣ ከነባሩ የተሻለ ይሁን፣ ወይም የባሰ ይሁን ይነግረናል? አይነግረንም። ግን፣ ምንነቱን በግልጽ ባናውቅም፤ በየፊናችን የየራሳችንን ምኞት እያሰብን፣ “አዲስ” በሚለው ቃል ልንግባባ እንችላለን።
ችግር የሚመጣው፤ “ከተግባባን” በኋላ ነው።
“የትኞቹን ነባር ነገሮች” ለማስወገድና ለማጥፋት እንደፈለጉ፣ ብዙ ሰዎች በየአቅጣጫው እልፍ ተቃራኒ ሃሳቦችን መናገር ሲጀምሩ፤… ያኔ፣ አንዱ ተናጋሪ በሌላው ተናጋሪ ላይ መቆጣት ይጀምራል።
“ምን ምን አይነት አዲስ ነገሮችን” ለማወጅና እንደ አዲስ ለማዋቀር እንደሚፈልጉ ለመግለፅስ፣ እልፍ ፖለቲከኞች፣ እልፍ ተቃራኒ ሃሳቦችን መናገራቸው ይቀራል? አይቀርም። ያኔ፣ ተጻራሪነታቸው ይቀጣጠላል።
“አዲስ የመንግስት ሥርዓት” የሚለው አባባል፣ ብዙዎቻችንን የሚያግባባ መፍትሄ መስሎ ይታየናል። ይሄ አይካድም። ውሎ አድሮ ቅራኔን የሚያባብስ እንዳይሆን ካልተጠነቀቅን ግን፣ ለከፋ ትርምስ ሊያጋልጠን ይችላል። “ለውጥ” የሚለው ቃል ምን ያህል ብዙዎቻችንን አግባብቶ እንደነበርና፤ ከጊዜ በኋላ ስንት መምታታትና አለመግባባት እንደተመለከትን እናስታውስ። ለምን?
የመግባቢያ ቃላት - “ለውጥ”፤ “አዲስ”።
“ለውጥ” ለክፉም ለደጉም ነው። ወደ ከፍታም ወደ ዝቅታም ሊሆን ይችላል።
መልካም ለውጥ እና መጥፎ ለውጥ፤… አቅጣጫቸውና መጠናቸው ቢለያይም፤ “ለውጥ” ናቸው።
ወደ ግራና ወደ ቀኝ መጓዝ፤ መራቆትና መጎናጸፍ፤ መሻሻልና መበላሸት ሁሉ፣ … የለውጥ አይቶች እንደሆኑ ግልጽ ጉዳይ ነው።
ጥያቄው ምንድነው?
ምን አይነት “ለውጥ” እንደፈለግን ሳንገልፅ፤ የ”ለውጥ ፍላጎት” ላይ ብቻ የተግባባን ሰዎች፣ … አንተና እሱ፣ እንቺ እና እሷ፣ እኔም ሌላም፣… “ለውጥ” በሚል ቃል ተማምነን የተስማማን ሰዎች ብዙ ነን። ነገር ግን፣ ከምር፣ ምኑ ላይ ነው ስምምነታችንና መግባባታቸውን?
ምን ያህልስ ነው የተግባባነው? መቶ ከመቶ የተግባባን ይመስላል። “ለውጥ” በሚል መፈክር፣ ከዳር ዳር ተባብረናል።
ነገር ግን፣ “ለውጥ” የሚለው ሃሳብ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ ሶስት ፍሬ ነገሮችን እንደሚያካትት ተንትነን ተግባብተናል?
ከነባር ነገሮች ውስጥ፣ “ይሄ፣ ይሄ፣ ይሄ”፣… ሊወገዱ፣ ሊለወጡ ይገባል።
ከአዲስ ተፈላጊ የለውጥ ውጤቶች መካከል፤ “ይሄ፣ ይሄ፣ ይሄ”፣… በፋይዳቸውና በተገቢነታቸው ተመራጭ ናቸው።
ከነባሩ ወደ አዲሱ ከሚያሸጋግሩ መንገዶችና የጉዞ ሂደቶች መካከል፣ “ይሄ፣ ይሄ፣ ይሄ”፣ … አስተማማኝና ተገቢ መርሆች ናቸው፤ ያዋጣሉ፤ ያዛልቃሉ።…
እንደዚህና እንደዚህ ተነጋግረን ነው የተግባባነው?
“ለውጥ”፣ የእስከ ዛሬ ነባር ነገሮችን፣ የወደፊት አዲስ ነገሮችን፣ እንዲሁም ከመነሻ ወደ መድረሻ የጉዞ መንገዶችን ያካትታል። ይሄ የምኞት ጉዳይ አይደለም። የተፈጥሮ እውነታ ነው።
የለውጥ ተፈጥሯዊ እውነታን ያገናዘበ መሆን አለበት - የለውጥ ሃሳብ። መሆን ነበረበት። አሳዛኙ ነገር፤ እንደዚያ አሟልተን አላሰብንበትም። ለምን?
ለምን አላሰብንበትም? ሦስት ምክንያቶች አሉ።
አንደኛ ነገር፣ አሟልቶና አዋህዶ ማሰብ፣ ከባድ ስራ ነው። ብዙ እውቀትንና የዳበረ ጥበበኛ አስተሳስብን ይጠይቃል። በቅጡ፣ ሰብሰብ ሰብሰብ እያደረጉ፣ በልኩ ዘርዘር ተንተን እያደረጉ ማሰብ፣ ብዙ ሰዎችን አይማርክም።
ሁለተኛ ነገር፣ አሟልቶ ማሰብ፤ በቀላሉና በፍጥነት፣ የሰዎችን ስሜት ለማነሳሳት ወይም ብዙ ሰዎችን ለማግባባት አያመችም።
ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ዋና ዋና ነባር ነገሮች፣ …
በለውጥ የሚመጡ ዋና ዋና ተፈላጊ አዲስ ነገሮች፣ …
ለለውጡ የሚያስፈልጉና የሚመጥኑ፣ አስተማማኝና ውጤታማ፣ ተገቢና የሚያዛልቁ መንገዶች፣ … እኚህ እኚህ ናቸው ብሎ፤ ቅጥ አስይዞና በልካቸው ተንትኖ መግለፅ፤ … ከብዙ ጥረትና ከረዥም ጊዜ በኋላ፣ ብዙዎች የሚያግባቡበት ሃሳብ ሊሆን ይችላል።
ለጊዜው ግን፣ ከመግባባት ይልቅ አለመግባባትን፣ ከስምምነት ይልቅ ክርክርን የሚያቀጣጥል ይሆናል።
እና ምን ይሻላል?
በደፈናው፣ “ለውጥ” በሚል ቃል ብቻ፣ ብዙ ሰዎች ማግባባትና ማስማማት ይቻላል። በቅጡ ካላሰቡና ዝርዝር ውስጥ ካልገቡ፤ ይግባባሉ።
ይህ፤ “ውጤታማ ዘዴ” ይመስላል። የብልጥ ዘዴ። አሟልቶ አለማሰብ፣ እንደብልጠት ሊቆጠር የሚችለው በዚህ መንገድ ነው።
ሦስተኛ ነገር፤ “የዘመኑ ወረት”፣ ለሃሳብ ምልዓት ቦታም ደንታም የለውም። የእልፍ ሃሳቦች መምታታት ግን፣ “የሃሳብ ብዝሃነት” ተብሎ ይወደሳል።
ብጥስጣሽ ሽርፍራፊ ሃሳቦች ከመብዛታቸው የተነሳ፣ ከሌላ ሰው ጋር ይቅርና፣ ከራስ ጋር መግባባትም ከባድ ሆኗል። አሟልቶ የማሰብ ጥረት፣ ሙከራና ፍላጎት ጨርሶ ጠፍቷል ማለት ይቻላል።
ይሄ፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚታይ ችግር አይደለም። ዓለማቀፍ ወረርሽኝ ነው- “መምታታት፣ መሻማትና መጋጨት” እንደ መደበኛ የሰው እጣ ፈንታ የተቆጠረበት የትርምስ ወረርሽኝ።
የግጭት ኑሮ የሰው እጣ ፈንታ ከሆነ፤ “የግጭት አስተዳዳሪዎች” ያስፈልጉናል?
“መግባባት፣ መገበያየት፣ መከባበር”፣… መደበኛ የሰው አኗኗር መሆን አለባቸው የሚል አስተሳሰብ፣ ዛሬ፣ ዛሬ  ተበጣጥሶ ሊጠፋ ደርሷል።
“የሃሳብ ብዝሃት፣ የሃብት ክፍፍል፣ የቡድን ማንነት”… የሚሉ መፈክሮች በርክተዋል።
የእልፍ ሃሳቦች ማለቂያ አልባ ፍጭት፣ የእልፍ ቡድኖች ማብቂያ የለሽ ግጭት… እንደ ኖርማል አኗኗር” እየተቆረጠ ነው። ከዚህም ከመቆጠሩ የተነሳ፣ በየአገሩ ከነባሩ የፍትህ ስርዓት ውጭ፣ ከመደበኛ ህግና የዳኝነት ተቋም ውጭ “የግጭት መከላከለያ” የሚል ነገር አምጥተዋል። ይህ በቂ አልሆነም።
ፍጭትና ግጭት፣ መደበኛ የሰው እጣፈንታዎች እንደሆኑ የሚሰብክ ዘመን፣ “ግጭትንና ፍጭትን መከላከል” የሚችል ዘመን አይሆንም።  ግጭትን መከላከል ካልተቻለ፣ “ግጭትን መፍታት” የሚል አባባል መምጣቱ አይገርምም (Conflict Resolution)::
ግጭት የሰው እጣ ፈንታ ከሆነ፣ ግጭትን መፍታት እንደ መደበኛ የሁልጊዜ ስራ መታየት አለበት ማለት ነው። ግን፤ የዘወትሩ “እጣ ፈንታ”፣ እንደ ድንገተኛ አደጋ፣ በአንዳች ዘዴ “መፍትሄ” እንዲገኝ ማድረግ ይቻላል? አይቻልም።
“የግጭት አያያዝ” የሚል አባባል እየገነነ የመጣው በዚህ ምክንያት ነው። “መፍትሔ ይኖራል” ብለን እንዳንጠብቅ፣ ቁርጡን እየነገሩን እንደሆነ አስተውሉ። ግጭትን መከላከል ወይም ግጭትን መፍታት እንደማይቻል የሚጠቁም ነው- “የግጭት አያያዝ” የሚለው አገላለጽ። “የግጭት አስተዳደር” ብለውም ይስይሙታል (Conflict Management)::
በዚህ የሃሳብ ቅኝት ከተስማማንና ከተግባባን፤ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት።
“ለግጭት አስተዳዳሪዎች” አዲስ ሲሳይ ሊሆንላቸው ይችላል- ከቶ የማይነጥፍ፣ ዘወትር የሚበረከት፣ የተትረፈረፈ ግጭት ያገኛሉ።
ለሌላው ሰው ግን፣ የዘወትር ሲኦል ይሆንበታል።


Read 1272 times