Saturday, 12 February 2022 12:00

የመረጃ መንታፊዎች ጉዳይ!

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

ዘመናዊ ኑሮ ያለ ኮምፒውተር ሥርዓት፤ ያለ እጅ ስልክ አገልግሎት ሊታሰብ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። እንደ ሰፋፊ ጎዳናዎች፥ የባቡር ሃዲዶች ወይም አውሮፕላን ጣቢያዎች በግልፅ የማይታየውን የመረጃ መረብ ፍሰት እንዳይስተጓጎል የሚያደርጉ ባለሙያዎች በየደረጃው እንዳሉ መገመት ይቻላል። በሀገር ደረጃ የመረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዝውውሩን እንዲከታተል ሃላፊነት የተጣለበት መሥሪያ ቤት ነው፡፡
ኢመደኤ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለተወካዮች ምክር ቤት የዕቅድ አፈፃፀሙን ሲያቀርብ፣ በመቶ አንዳንዴም በሺህ የሚቆጠሩ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን ሳይታክት ያስታውቃል። ጥቃቱ ምን እንደሆነ የሚጠይቅም የሚያስረዳም የለም። ምክር ቤቱም “የሰማነውን በልቦናችን…” አይነት ሆኖ ይበተናል።
“በተቀየረ ቁጥር ሁሌም ተመሣሣይ ይሆናል” የሚል የፈረንሣዮች አነጋገር አለ። ባለፉት ሶስት አመታትም የኢመደኤ የሥራ ሃላፊዎች ስለመሥሪያ ቤቱ እንቅስቃሴ በሚያስረዱበት ጊዜ አሃዝ እየጠቀሱ አክሽፈናል የሚሏቸውን ጥቃቶች መጠን ይናገራሉ። አንዳንዴ የበፊቱን ቅፅ ተውሰው ቁጥሩን ብቻ እየቀየሩ የሚመጡ ይመስላል። ጥቃቱ ስለሚፈፀምባቸው፤ ወይም ስለፈፃሚዎቹ አልፎም ለምን እንደሚፈፀም የመሣሠሉት ሾላ በድፍን በመሆኑ የተዓማኒነት ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ደግነቱ ጉዳዩ ግድ የሚለው ሰው ብዙም አይደለም።
ይልቁንም የዕለት ተዕለት ኑሮን ባያውኩም ድረገፆች በሚጠለፉበት ጊዜ ሰዎች ያስተውላሉ። ድረገፆችን እየጠለፉ መዘባበቻ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል። ሰሞኑን መንግሥት በሚቆጣጠረው የዋልታ ፌስቡክ ገፅ ላይ ያየነው ይህንን ያረጋግጣል። በሁኔታው ከመማረር ይልቅ በአንደኛው ቀን ጠላፊዎቹ ገፁ ላይ ለጥፈውት በነበረው የጡት መያዣ ብዙዎች ሲዝናኑበት ነው የተስተዋለው። የት እንደሚሸጥ ከሚጠይቁት ጀምሮ በነካ እጃቸው ሌሎችንም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንዲጠልፉላቸው የሚማፀኑም ነበሩ። (ወንጀልን ማበረታታት ይሏል ይሄ ነው!)
ጉዳዩን በባለቤትነት መግለጫ የሰጠበት ኢመደኤ ነው። እሱም ጣቱን ቅርብ የተንጠለጠለው ፍሬ ላይ ቀስሯል  -  “ከሕወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች።”  ጉዳዩንም እያጣራሁ፤ ከፌስቡክ ሃላፊዎችም ጋር እየተነጋገርኩ ነው፤  በቅርቡ ይፈታል የሚል መግለጫም ሰጥቷል።
ነገሩ እገታ ይመስላል። “ይህን ያህል ገንዘብ ካልሰጣችሁኝ አለ’ቅም” ነው። እገታ ወንጀል እንደመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚያገባው ፖሊስ ነበር። ለእንደዚህ አይነት ወንጀሎች አዲስ ከመሆናችን ጋር ተያይዞ የሚና መደበላለቅ ይታያል።
የአንዳንድ ድረገፆች መጠለፍ ለጊዜው ጉዳቱ ከፍተኛ ላይሆን ይችላል። ግን የአደጋውን ግልፅነት ያሳያል። ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ፈተና የተሰረቀበትን ጊዜ ማስታወስም ይቻላል። በርካታ መሥሪያ ቤቶችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።
የሰሞኑ እገታ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ለባለሙያዎች እንተወውና፣ የመረጃ መረብ ደህንነት መሥሪያ ቤት ጠለፋ ከመፈጸሙ በፊት በቅድሚያ መከላከል የሚቻልበትን መላ ማበጀት እንደሚገባው ሳልጠቁም አላልፍም፡፡

Read 1255 times