Saturday, 12 February 2022 12:00

“ታዲያስ” በሉልኝ ዲያስፖራን

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ (ቤተሳይዳ ሜሪላንድ- አሜሪካ)
Rate this item
(2 votes)

  "--ንጉሠ ነገሥቱ በዚህ የታሪክ መስቀለኛ መንገድ ላይ የገጠማቸው ወይም ለውሳኔ ከፊታቸው የቀረበው ጥያቄ ስለትላንቱ የማውሳትና የመተረክ ሳይሆን የዛሬና ይልቁንም የነገን የሚመለከት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ከወደቀችበት ትነሳ? ኢትዮጵያ እንዴት ራሷን ትቻል? ኢትዮጵያ እንዴት ወደፊቷን ታስቀጥል? ነው ይልቁንም፡፡--"
            
              ከሀገር ቤት ለዲያስፖራ መስተንግዶ ደፋ ቀና የመባሉን ዜና ዕለት በዕለት እንሰማለን።  የኢትዮጵያ የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች በየዕለቱ የዜና እወጃቸው ‘ዲያስፖራ’ ወይም ‘ትውልደ ኢትዮጵያውያን’ ሳይሉ የቀሩበትን ዕለት ፈልጎ ማግኘት ያስቸግራል። ደግሞ የእኛ ሀገር መገናኛ አውታሮች እንደ ፋሽን አንድ ነገር  ከጀመሩ ያንን ይይዙና ‘ችክ - ግፍግፍ’ እስኪላችሁ ያሰሟችኋልና ከዲያስፖራ ጋር በተያያዘ የሚጠቀስ ምሳሌ እንዳላጣ ረድተውኛል፡፡ በዜናዎቻቸው ውስጥ ‘በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ያለው የልማት እርምጃ አበረታች እንደሆነ ተናገሩ’ “ዲያስጶራ ኢትዮጵያውያን ሁሉም ሀገሩን ተባብሮ መጠበቅ እንዳለበት አሳሰቡ...’ የመሳሰሉ ዜናዎች እንደ መዝሙር አዝማች ብዙ ጊዜ ብትሰሙ አትገረሙ፡፡  ግን እዚህ መሀል የቸገረ ነገረ ይገጥማል፡፡ ቴሌቪዥኑ መስኮት ላይ የሚቀርቡ ‘በውጭ ከሚኖሩ’ ወይም ‘ዲያስጶራ’ዎች ጠፍተው አያውቁም። ታዲያ ዘወትር ‘የምናምን’ ‘የምንትስ’ ተወካይ እየተባሉ ‘ቃለ ምልልስ’ ሲደረግላቸው ስመለከት ችግር ታየኝ፡፡ እዚህ አሜሪካ በቅርብ እርቀት የማውቀው ወንድሜ - ’ተወካይ’ ተብሎ ሲተዋወቅ የተመለከትኩ ቀን ራሴን ወቅሻለሁ፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ‘የተወካይነት ሹመት’ ማግኘቱን ባውቅ ኖሮ ከመሄዱ በፊት እንደ ወግ ይትበሀሉ ፋሽኮ ‘ወይን ጠጅ’ ይዤ ቤቱ ድረስ ተጉዤ ‘እንኳን ደስ ያለህ’ እለው ነበረና ነው፡፡ በነገሬ ላይ እንደምንም ብዬ ጊዜዬን አብቃቅቼ የቴሌቪዥን መስኮት ከከፈትኩ ብዙ ራሴን የሚያሲዝ (አፍ ላይ እጅ የሚያስጭን ነው የሚባል) እያጋጠመኝ ተቸግሬያለሁ፡፡
ባለፈው ሰሞን ደግሞ ሁለት ወዳጆችና እዚህ የጉድ መንደር ዋሽንግተን ዲሲ በአካለ ስጋ የማውቃቸው (ስም አልጠራም) እንዲሁ ‘ዲያስጶራን’ ጥሪ ተከትለው መግባታቸውን ያየሁት በቴሌቪዥኑ መስኮት ነበር፡፡ ያየሁዋቸው ጊዜ ሁለቱ ጓደኛሞች አንዱ የ’ምናምን’ ንቅናቄ ሌላው መጨረሻው እንቅስቃሴ የሆነ ድርጅት መሪዎች እንደሆኑ ተገልጾ፣ ረዘም ያለ ቃለ ምልልስ ሲሰጡ በጥሞና ሰማሁዋቸው። እንዴት ያለ ጅምናስቲክ ቢሠሩ እንደሆነ አላውቅም ወይም እንዴት ብለው የ’ፖለቲካ ድርጅቱን በቀናት እንደጠፈጠፉት ሲገርመኝ ቆየ፡፡ ከዚያም ብሶ ‘መሪ’ የመሆናቸው ነገር እስካሁን ያስፈግገኛል፡፡ ትንሽ እንኳን ለማሰቢያ ጊዜ ቢሰጡን ብዬ ተመኘሁ፡፡
መለያና ማጣሪያ ሳይኖር እንዲህ ሲሆን ስመለከት- ‘ስደት ለወሬ ያመቻል’ የሚባለውን የአዛውንት ብሂል አስበዋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ጥሪ ስታደርግ - ሀገሬን ያሉ ሲረባረቡ ለማንም ብለው ሳይሆን ለሀገራቸው ለወገናቸው ሲሉ ነው፡፡ ዲያስፖራ ስለሆኑ ‹ልዩ መብት› ያላቸው አይደሉም - እንዲሆኑም አያሻም፡፡ ጥቂቶች ኮራ ጀነን ይሉ እንደሆነ - በአራዳው አገላለጥ ‹ኸረ ኳስ በመሬት› ማለት ያስፈልጋል፡፡ ተቀባዩም በተለይ መንግሥት የትና እንዴት ሀይላቸውንና ምንጭነታቸውን ለመጠቀም እንደሚችል ማሰብ - መወጠንና መተግባር ይገባዋል፡፡ በአንፃራዊ የኑሮ ደህንነት ዕድል የተነሳ የቁስ ሀብት በለጥ ያለለት ሰው ሁሉ - ምድርን የተሸከመ ሲመስለው መቀበል አደጋ አለው። አንዳንድ ጉምጉምታ ሰሞኑን እሰማለሁ። ወደ ሀገር እንድትመጡ የሚል ጥሪውን ሰምተው ለመጓዝ ከወሰኑት መካከል አንዳንዶች በየኤምባሲው ‹የቤት መገንቢያ መሬት መንግሥት እንዲቸራቸው› የትብብር ደብዳቤ ማጻፍ ይዘዋል አሉ። ለኢትዮጵያ ታግለናልና ‹ክፍያ› ያሻናል የሚል አተያይ የተሸከሙ መታየታቸውን በሀዘን ነው የማነሳው።  
እንዲህ ነው ጉዳዩ። ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ነው ከሀገራችን ተነቅለን የምንገኘው፡፡ ለመሰደዳችን ፖለቲካዊ - ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ሊዘረዘሩ ይችላሉ፡፡ አሁን ለአብነት የዚህ የአሜሪካ ስደተኞችን ነገር ብንፈትሽ አመጣጣችን፣ ምክንያታችንና አሁን ደግሞ አኗኗራችን ብዙ ሊፈተት የሚችል ርዕሰ ጉዳይ ነው። የስደተኛውን ምጣትና ግብዓት በየትውልዱ ሰንጥሮ ማየትና መፈተሽም ይቻላል። ታዲያ ሁላችንንም አንድ ወጥ ባህርይ - ወይም ከአንድ ጣቃ የተቀደድን አድርጎ መመልከት ከስህተት ይጥላል፡፡ ስደት ደግሞ በአስተሳሰባችን - በእኛነታችን ላይ የፈጠረው ማህበራዊ ስነ ልቡናዊ ተጽዕኖም አብሮ መታየት አለበት። ወደፊት የስደትን ክፉንና ደጉን ፀጋና መርገሙን፣  በስነ ማህበራዊ አተያይ - በስነ ልቡናዊ ውቅር ተንትኖና ናሙና እያቀረቡ መወያየትና ማሳየት ይቻል ይሆናል። እንደ አንድ የስደተኛ ማህበረሰብ ግን የምንመዘንበትና ምጣታችንና ኑሯችንን እንደዘበት የምናወሳበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ዛሬ በተፈጠረው ‹ወደ ሀገር ጉዞ› ሰበብ ጥቂት ማለት የሚሞከረውም ለዚህ ነው።
ስደት በተፈለገው መስፈርት ባሻዎት መልክ ይተርጉሙት ‹ምርቃት› አይደለም። ‹ልጄ አሜሪካ ተሰደደልኝ› ብሎ ሰዎች የሚደሰቱበት ዘመን በመምጣቱ ያዘንን፤ ምን ያህል ቁልቁል እንደወደቅን ያየን እንበዛለን። በስብስቴው ዘመን ‹ፈረንጅ እጄን ነካኝ› ብለው ጠበል ከሚረጩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች የወጣን ልጆቻቸው፣ የውጭ ናፋቂ የሆንንበት አደጋ እንዴት ብሎ እላያችን ላይ እንደወደቀ መመርመር አለብን፡፡ እርግጥ ነው መሰደድን በደስታ የሚቀበሉበት ጊዜ ሲገጥመን፣ በሀገራችን በተወለድንበትና ባደግንበት ቀዬ አንዳች ክፉ ጭጋግ እንደወረደ የሚያሳይ ነው፡፡
የስዊድን ዜጋ እስራኤላዊው ድሮር ፌለር “ለእኔ ስደት በተዋበ የሙዚቃ ቅንብር ውስጥ ያለ ጩኸት አይነት ነው” ይለዋል። የተዘበራረቀ እንደማለት፡፡ ሰው በህይወት ዘመኑ ተለምዷዊና የሰከነ ትርጉም ፈጥሮና ተሸክሞ ሊኖር ሲገባው በሀይል ተገፍቶ በግፍ ተወርውሮ ከቁጥጥሩና ከፍላጎቱ ውጪ ሲወጣ፤ በአግባቡ ከተቀናባበረ ውብ ሙዚቃ ውስጥ ያልታሰበ ጩኸት ሲገባና ሲዘበራረቅ ከሚሰማው የድምጽ መረበሽ ጋር አመሳሰለው ምሁሩ። ከሚያውቁት ወደማያውቁት፤ ከለመዱት ወዳልለመዱት ሲሸጋገሩ ያለ ባይተዋርነትም ክቡድ ነው። ስደት ደግሞ እንደዘመኑ ይለያይ እንጂ በሰው ዘንድ የተሰጠው ትርጓሜው ወይም ድባቡ እየቅል ሲሆን አስተውለናል።
ስደትን እንደርግማን የተመለከቱት - እንደቅጣትም የወሰዱት ነበሩ፤ አሉም። መነሻው ክፉ ቢሆንም ጉዞውና የበስተመጨረሻው ከልፋቱ የሚገኝ ውጤቱ ደግሞ መልካም ሲሆን የገጠማቸውና ይልቁንም እነርሱ ተግተው ፍሬ ያፈሩበት - ስደት ትርጉም አለው ብለው ያውጃሉ። ተልዕኮውን ፈጸምን - ለመጪው ርባና ያለው ተግባር ተገበርን ብለው ይመካሉ። በ8ኛው ምዕተ ዓመት ከሮም በኦገስተስ እንዲሰደድ የተገደደው ገጣሚው ኦቪድ ‘Exilium mors est’ (መሰደድ ሞት ነው) ያለበትን ለናሙናነት ይጠቅሷል። ቪክቶር ሂውጎ ደግሞ ‘ስደት እንደገና መታደስ ነው’ ይለዋል። ያም አለ ይህ ግን - ሞትም ተባለ ህይወት ትርጉም ሰጪ ተሰዳጅ ሊኖረው ይገባል። ከቶውንም ወደ ሁዋላ እየተመለከቱ ትላንቱን ለማብራራትና ለመተርጎም ወይም በዚያ የትውስታ ጓዳ ውስጥ ለመኖር ማሰቡ ነው ክፉው።
ስደት በባሕርይውና በይዘቱ የተሰዳጁን የቀድሞ ሕይወቱን ባዶ ያደርጋል። እና ‘አለኝ’ የሚሉት ‘በየለም’፤ ‘ነኝ’ የሚባለውም ‘አይደለሁም’፣ ‘ነውም’ ወደ ‘ነበር’ ይቀየራል። እና እንደብሂሉ ሁሉንም ‘በአግዳሚ ወንበር ላይ ያስቀምጣል’። በስደት ጉዟችን እኛነታችን የተመሰረተባቸው ፋይዳዎች አብረውን ከሌሉ፤ ወይም ከኮሰመኑ፤ ከቀደሙት መማር የሚገባው ስደተኛ በአውቃለሁ እንዲደነድን በባዶ እንዲኮፈስ ያደርገዋል። በዚህም የተነሳ የሁሉንአወቅ በሽታ ይዛመታል። አንድ አዋቂ እንዳሉት እያንዳንዱ በኪሱ ‘ዘውድ’ ይዞ መሄድም ይጀመራል። ‘ሁሉም ከሆነ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ’ ተብሏል በተረት። እና እንኳንስ ተሰደድንበት ላልነው ምክንያታችን የተሟላ ትርጉም ልንሰጥ ቀርቶ - የነበረንን ጸጋ የማጣት ዕጣችን እየሰፋ ይሄዳል።
የስደታችን ምንጭ ቀደም ሲል እንዳልኩት ምክንያቱ የትየለሌ ነው፡፡ ከዚያ የስደት ጓዳ ወደተወለዱበት ሀገር ጥሪ ተቀብሎ ሲጓዙ ዕድሉ ደስ ይላል፡፡ እና ዲያስጶራ ላለፉት አስርታቱ ዓመታት ከተነጠለበት ሀገሩ ሲመለስ - የተለወጡትን የመስኩን እውነታዎችን ያላገናዘብ አካሄድ እንዳይጀምር መስጋት ይገባል፡፡ ደግሞም አንዳንዱ ዲያስፖራ ራሱንም የሁሉም ነገር ቁልፍ አድርጎ የመመልከት ካባ ለብሶ ብቅ ሊል ይችላል፡፡ መንግሥትም በአስተዳደር ውሳኔ - ሲያሳልፍ ሲሰማ ‘ምነው ሳያማክሩኝ’ የሚል ቢያጋጥምም አትፍረዱ፡፡ ስሜታዊነት ያጠቃው አመለካከትንም የሚያስነብቡ የእኛ ሀገር ነዋሪዎች (ዲያስጶራዎችም ማለቴ ነው) መኖራቸውን እረዳለሁ፡፡ ምግብ ለመርዳት የተሰባሰቡ ጥቂት ዲያስጶራዎች - ሳምንት ባልሞላ ጊዜ መንግሥት ስለሾማቸው ወይም ስለወሰደው አቋም አንስተው ‘የውግዘት ቃል‘ በዩቱብ መድረክ ሲያሰራጩ ብታደምጡም ግር አትሰኙ፡፡ እንደኔ ተቀባዩ ሀገርና ወገን ለዲያስጶራው የሚገባውንና የሚችለውን ቢለዩለት ተመራጭ ይመስለኛል፡፡
በነገሬ ላይ አንዳንድ በታሪክ ጉዟችን ውስጥ የገጠሙንን ወደ ሁዋላ መለስ ብለን ማየት ብንችል ሸጋ ይመስለኛል፡፡  ከፋሺስት ጣልያን ወረራ በሁዋላ በሀገራችን ወደነበረበት ሁኔታ ለመመልከት ሻትኩ። የፋሺስት ጣልያን ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንደተጠናቀቀ በስደት ይኖሩ የነበሩት ንጉሱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ፤ የፈረሰውን ለመጠገን - የተዛባውን ለማቃናት - የወደመውን ለመተካት እንደገና ‘ሀ’ ተብሎ የተጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡ በእርጋታና በሰላም ሲጓዝ የነበረው የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ በፋሺስት ጣልያን እጅግ የከፋ ጥቃትና ፋሺስታዊ ግፍ የተነሳ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል፡፡ ብዙ ነገር ማጣፊያው እያጠረ ተግዳሮቱ እንደከፋ የታሪክ ድርሳናቱ ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ህዝቡ ወደፊት የምትወጣውን ጀንበር እያየ ወደፊት መጓዝና መራመድ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ወቅቱ ተስፋን ሰንቆ - ወገብን አጥብቆ መነሳትንም ጠይቋል፤ - ከቶም። ንጉሡ ደግሞ ይህን ከጦርነት የወጣውን ህዝብ በወደመው ሳይሆን በመጪው ተስፋ ላይ አነጣጥሮ እንዲጓዝ የሚያስችል አመራር እንዲሰጡ ግድ ብሏቸዋል፡፡
ንጉሡ ከስደት እንደመመለሳቸው እንግሊዝ ኢትዮጵያን ረድቻለሁ በሚል ሞግዚት ካልሆንኩና ካልገዛሁም የሚል የተቀነባበረ ሴራ የምታካሂድበትም ክፉ ጊዜ ነበር፡፡ ታዲያ የተረከቡትን ሀገር ከፈተናዎቹ ሁሉ አድኖ ሚዛኑን ጠብቆ ተስፋውን ሰንቆ እንዲጓዝ፤ በሁሉም መስክ ‹አመራራቸውን› የፈተነም አሰላለፍ ገጥሟቸውም ነበር - እንደታሪክ በሰሎች አሰኛኘት። የፖለቲካ ስርዓቱንም ይሁን የኢኮኖሚውን ሂደት ከተረጋጋ ማማ ላይ ለማዋል፣ በእርስ በእርስ ቅራኔ ውስጥ ሀገር እንዳትገባ ፈተና እንዳይገጥማትም ያሻ ነበር። በዚያን ወቅት ንጉሡና አብሯቸው የገባው ስደተኛ አንድ ማህበረሰብ ክፍል ነበር። እግራቸውን ተከትሎ በስደት ሲጮህና ሲታገል የቆየው ኢትዮጵያዊ፣ የነፃነት ሰንደቅ ዓላማዋን ለማውለብለብ ወደ ሀገር በምልዓት ነው የገባው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሀገር ውስጥ ሆኖ በአምስቱ ዓመታት የአርበኞች ትግል ደሙን ሲያፈስ አጥንቱን ሲከሰክስ የነበረውም አርበኛም አለ። በፋሺስት ጣልያን ይዞታ ስር ሀገሪቱ ወድቃ በነበረችበት ጊዜ ውስጥ አብረው በተለያየ ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩና ‘ባንዳ’ የሚል ስም ያላጡ የሀገር ልጆችም ነበሩ፡፡
እነዚህ ሦስቱ መደቦች ወይም የማህበረሰብ ክፍሎችን አቻችሎና አግባብቶ ሚዛናቸውን ጠብቆ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዞ ውስጥ ማስጓዝና ለሀገራቸው የሚጠቅሙበትን ፋና መቅደድ እጅግ የከበደ ሂደት እንደነበር የታሪክ በሰሎቹ ይገልጻሉ፡፡ አርበኞች በይገባናል ስሜት - ለዋልነው ውለታ ወሮታ ይገባናል በሚል ቆመዋል፡፡ በሀገሪቱ ቀዳማይ ተጠቃሚ ልንሆን ይገባናል የሚልም ስሜት ተጠናውቷል፡፡ ስደተኞችም በበኩላቸው ወደው ሳይሆን ተገደው - በአጋርነትም ለመቆም ችለው ለዚያች ሀገር የአርበኝነት ትግል አስተዋጽኦ አለን - ባይ ናቸው፡፡ ከንጉሡም ጋር በየዓለም አቀፉና በየሀገራቱ ደጃፍ አብረን ቆርቁረናል - ብሶት አሰምተናል ይላሉም። ንጉሡ በዚህ ስብስብ ውስጥ ቢሆኑም በታሪክ ከእጃቸው ላይ የወደቀው ኃላፊነት ግን ሁሉን የማቻቻልና የማስተዳደር ጥበብ የሚሻ ነበር፡፡ ሦስኛው የማህበረሰብ አካል የነበረው ከጣልያን ቢሮክራሲ ጋር የሠሩና ያገለገሉ - ‹ባንዳ› የተባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ በዘመናዊ አስኳላና አሠራር ስልጡን የሆኑ በሥራ አገልግሎት በቢሮ አስተዳደር የ›ተማሩ› የሚባሉም ናቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ በዚህ የታሪክ መስቀለኛ መንገድ ላይ የገጠማቸው ወይም ለውሳኔ ከፊታቸው የቀረበው ጥያቄ ስለትላንቱ የማውሳትና የመተረክ ሳይሆን የዛሬና ይልቁንም የነገን የሚመለከት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ከወደቀችበት ትነሳ? ኢትዮጵያ እንዴት ራሷን ትቻል? ኢትዮጵያ እንዴት ወደፊቷን ታስቀጥል? ነው ይልቁንም፡፡ ንጉሡ ምርጫቸውን ስለትላንቱ አድርገው ስላለፈው እያወሱ ስለጀግንነቱ እየተረኩ ሊቆዩ ይችሉ ነበር። ቁም ነገሩ ግን ሀገር መነሳት ነበረባት። አቧራዋን አራግፋ መሮጥ ይገባትም ነበር። የትላንቱን ጥንካሬዋን በመፃኢው ዕድሏ በሥራ ሊተረጎምና ሊታይም ግድ ሆነ። እና ያ ወቅት ሦስቱንም አቻችሎ ሀገርን በጋራ የማራመድ ጥበብ - የአመራር ክሂሎት ንጉሡን ጠየቃቸው። በእርግጥም ከታሪክ መዛግብት እንደምንማረው እዛና እዚህ አነስተኛ መንገራገጭ ቢገጥምም የኢትዮጵያን መርከብ በተረጋጋ ሁኔታ ለመቅዘፍ የሚያስችል ጉዞና ብልሃት ለማግኘት ተቻለ፡፡ ሀገርን ለማስቀጠል - የእርስ በእርስ ግጭትን ለማለዘብ የሚያስችሉ መሰረቶችም በብልሃትና በጥበብ ተገንብቶና ታንጾ ያ ፈታኝ ዘመን ታለፈ፡፡ በሀገሪቱ ግንባታ ውስጥ የሦስቱም ብቃትና ችሎታ - እንዲቀናጅም ሆነ፡፡
ዛሬ ያለንበት መስቀለኛ መንገድ ቀደም ሲል ከመግቢያዬ እንዳልኩት ‹ቁርጥ አንድ› ባይባልም፣ ተመሳሳይነት ያላቸው ክስተቶችና ኹነቶች ይስተዋሉበታል። ከአስከፊ ጦርነትና ግጭት ውስጥ ነው የወጣነው፡፡ በታሪካችን በዚህ ደረጃ እንዲህ አይነት የውስጥ ግጭት የታየና የተከሰተ አይመስለኝም፡፡ ሀገርን ከስሯ ያናጋ ግጭት ነበረ። ያ ግጭትና ጦርነት ጋብ ብሏል እንበል እንጂ አለማለቁን ነው እየተነገረ ያለው፡፡ ፀጥ ያላለ ፀጥታ ይመስላል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ዛሬ ኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ምክንያት ከሚወዷት ውድ ሀገራቸው የተነጠሉ ዲያስጶራዎች ጥሪ ተደርጎላቸው በአስደሳች መልኩ ምላሽ እየሰጡ ናቸው፡፡ የዋሽንግቶንና የለንደን የስቶክሆልምና የብራስልስ አውራ መንገዶች ጸጥ እረጭ እስኪሉ ድረስ ‘ንቅል’ ብሎ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተጉዟል። ይህ ሀይል በአግባቡና በዘዴ ከተመራና ከተቃኘ ለሀገሪቱ የማይደርቅ ምንጭ ነው። መለስ ብዬ የቀደመ ታሪኩን መዘርዝር ስመለከት - ንጉሡ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ የፖለቲካና ማህበራዊ ኑሮ ዘርፍ ውስጥ ከጦርነቱ በሁዋላ የነበሩትን የማህበረሰብ ክፍሎች የተጠቀሙበትንና ያሰለፉበትን አግባብ እንዲጤን እሻለሁ፡፡ ‘ዲያስጶራውን’ የምንመለከትበት አተያይ ‘እምቅ ሀይሉን’ ማወቅና በዚያው ትይዩ እንዴት መጠቀም ይቻላል በሚል መንገዶችን መቀየስ ይገባል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና፣ ዲያስፖራ በአንጻራዊነት የገንዘብ አቅሙ የበረታ ስለሆነ ‘ሁሉን የሚችል’ አድርጎ የመገመት ወይም የመቀበል ዝንባሌ አደጋ አለው፡፡
ዲያስፖራ ሀገሩን በመውደድ ማንም አይጠረጥረውም፡፡ በልቡ ጽላት ከትቦ - ከአንደበቱ ሳይለያት ጠብቆ ያቆያት ሀገሩንና ወገኑን ከልቡ ይወዳል፡፡ ውዴታውን በተግባር እንዲገልጽ ማስቻልና ማቀናጀት ያለበት ደግሞ ተቀባዩ ሕዝብና መንግሥት ናቸው፡፡ ብዙዎቻችን በልባችን ይዘናት የወጣናት ኢትዮጵያ በቅርጽም በይዘትም የለችም፡፡ የራሴን ብናገር ከሦስት አስርታት ዓመታት በፊት ይዣት የወጣሁዋት ኢትዮጵያ አይደለችም ያለችው። ብዙ የተቀየረ - የተለወጠ ነገር አለ፡፡ ያንን ማወቅና መረዳት ይጠይቃል፡፡ የመቆየት ነገር ሲነሳ የቆዩ ዲያስጶራዎችን ለማወቅ የየአዲስ አበባ አራዶች መለያ ቋንቋቸውን በቧልት መልክ ሲያነሱት እሰማለሁ፡፡ ከዲያስጶራ የመጡ ኢትዮጵያውያን ሰላምታ ሲሰጡ “ታዲያስ’ ካዘወተሩ ውጭ ሀገር ብዙ የከረሙ ናቸው አሉ፡፡ ደግሞ ሲነጋገሩና ጭውውታቸውን ሲጨርሱ “አይዞህ’ ‘አይዞህ’ ማለት ያዘወትራሉ ይሉናል፡፡ የእኔ ነገር ሀገር ቤት በስልክ ባገኘሁት ቁጥር ‘ታዲያስ’ የምለውን ወዳጄን አስቤ ፈገግ አልኩ፡፡ በሉ አይዟችሁ ልበል፡፡ በእርግጥ ለውጥ አለ፡፡
“ታዲያስ” በሉልኝ ዲያስፖራን!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1742 times