Print this page
Monday, 14 February 2022 00:00

“በዓለም ላይ የተካሄዱ ጦርነቶች የተቋጩት በድርድር ነው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “እስራኤል በአሸማጋይነት እንድትገባ ያደረግነው ሙከራ በትግራይ ተወላጆች ምክንያት ከሽፎብናል”
          “ጦርነት እንዴት እንደሚጀመር ሊታወቅ ይችላል እንዴት እንደሚጠናቀቅ መገመት አይችልም”


           ጎንደር ውስጥ ጭልጋ መንገድ ላይ በሚገኝ ሰቀልት አካባቢ አይምባ በምትባል የገጠር ከተማ አቅራቢያ ነው የተወለዱት፡፡
ቤተሰቡ ካፈሯቸው 11 ልጆች መካከል ላይ የተወለዱትና በልጅነታቸው የጎረቤት ልጅ በመደብደብና ጠብ በመግጠም ቤተሰባቸውን ከጎረቤት ጋር እያጋጩ ያስቸግሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በዚህ ባህሪያቸው የተቸገሩት ወላጆቻቸው፣ እዚህ እየረበሸ ከሚያስቸግር ቀልጣፋም ስለሆነና ትምህርት የመያዝ አቅም ስለሚኖረው፣ በማለት ራቅ ወዳለና ቤተ እስራኤሎች ወደሚኖሩበት የእናታቸው አጎቶች  ዘንድ ተልከው ትምህርት እንዲጀምሩ ተደረገ፡፡
በ3 ዓመት ውስጥ  5ኛ ክፍል በመድረስ በትምህርታቸው ጎብዝናቸውን አሳዩ፡፡ -
ቤተ እስራኤላዊው የዛሬ እንግዳችን ረሀሚም አላዕዛር፡፡
በንጉሱ ጊዜ ወደ እስራኤል ሄደው በርካታ ቁም ነገሮችን የሰሩ፣ ለ29 ዓመታት በጋዜጠኝት ያገለገሉ፣ኢትዮጵያዊ አይሁዶች አይሁድነታቸው እውቅና እንዲያገኝና “በዘመቻ ሙሴና” “በዘመቻ  ሰለሞን” ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ወደ እስራኤል እንዲሄዱ ካደረጉት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ አሁንም የተለየ ፍቅር ያላቸው አንጋፋው ጋዜጠኛ ረሀሚም፤ አለዕዛር ሰሞኑን ለስራ ጉዳይ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን ከአዲሰ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ፣ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል እስራኤል በአሸማጋይነት እንድትባ ያደረጉት ሙከራ የከሸፈበትን ሁኔታ፣የአለም የጦርነት ታሪኮች እንዴት እንደተቋጩ ኢትዮጵያ ጦርነቱን ለመቋጨት ማድረግ ስላለባት ጉዳይ፣እርሳቸው እስራኤል ሆነው በሚዲያ ይሰሙት የነበረውና አሁን መጥተው ያዩት ነገር ምን  እንደሚመስልና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ  ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

            የሀገር ቤት ወይም የልጅነት ሰምዎ ምህረቱ ሙጬ ነበር፡፡ እንደት ወደ ረሃሚም አልአዛ ተቀየረ?
የስሜ መቀየር እኔ ወደ እስራኤል ከመሄዴ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ረሃሚም በእብራይስጥ ቋንቋ ምህረቱ ማለት ነው፡፡ ሙጬ የአባቴ ሰም ነው፡፡ አልአዛር ደግሞ የአያቴ ስም ነው፡፡ እዛ እንግዲህ በቤተሰብሽ ስም ነው የምትጠሪው፡፡ ረሂም አልአዛር ተባልኩ፡፡
እንዴት ወደ እስራኤል በልጅነት የመሄድ እድል ገጠመዎት?
ምን መሰለሽ… እየረበሸኩ ሳስቸግር ቤተሰቤ ተማክሮ፣ ወደ እናቴ አጎቶች ዘንድ ተልኬ፣ ትምህርቴን ስጀምር ቤተሰቤ “ቢረብሸም፤ ቀልጣፋ ነው ትምህርት የመቀበል ሁኔታው  ጥሩ ይሆናል” ብለው ገምተው ነበር፡፡ እውነትም በትምህርቴ ጎበዝ ሆንኩና በ3 ዓመት ውስጥ  5ኛ ክፍል ደረስኩኝ፡፡  ትምህርቱንም ወደድኩት። ነገር ግን እናቴ አጎቶች አካባቢ ያለው ት/ቤት እስከ አምስተኛ ክፍል ብቻ ስለነበር  ትምህርቴን ለመቀጠል ወደ ከተማ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ከተማ ልሂድ ብዬ ለቤተሰቦቼ ጥያቄ አቀረብኩ፤ ነገር ግን ደስተኛ አልነበሩም፡፡
በምን ምክንያት ቅር ተሰኙ?
ያው ስለ ከተማ ያላቸው ግንዛቤም ይመስለኛል፡፡ ከተማ ከገባህ ትበላሻለህ፣ ሀይማኖት ትረሳለህ፤ በቃ ጥሩ አይደለም አሉ፡፡ ያው ለኔ ጥሩ መሆን በማሰብ ነው። ሁለተኛ ከተማ ስገባ መራራቃችንን አስበው ደስ አላላቸውም ነበር፡፡ እኔ ግን በአካባቢው ያሉትን መሰሎቼን አሳምኜና አደራጅቼ ጎንደር ከተማ ገብተን ቤት ተከራይተን ትምህርታችንን ቀጠልን፡፡ ጎንደር ትምህርቴን በጥሩ ሁኔታ በመከታታል ላይ አያለሁ፣ ፈረንጆች ለጉብኝት ከተማ ውስጥ ይመጡ ነበር፡፡ እነሱን ማየትና ጠጋ ጠጋ ማለት ጀመርኩኘ፡፡ ገበያ ሲሄዱ ባለችኝ  አቅም በማውቃት እንግሊዘኛ አስተረጉምላቸው ነበር፡፡ ወደዱኝ፡፡ ልብሰ፣ጫማ፣ ሸሚዝ… ብቻ የሚያስፈልገኝን  ሁሉ ይገዙልኝ ጀመር፡፡ በኋላ እንደውም ለሁላችንም ብርቅ የሆነ አድርገነው የማናውቀውን ሰዓት ገዙልኝ። በጣም ብርቅ ነበር። አይተነው አናውቅማ!
ሌላ ጊዜ ሶስት ፈረንጆች አየሁና ጠጋ አልኳቸው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ነው ያየኋቸው። እናም በእብራይስጥ ቋንቋ ያወራሉ፡፡ በልጅነቴ እብራይስጥ ቅዱስ ቋንቋ ነው፤ የመፅሀፍ ቅዱስ ቋንቋ ነው እያሉ ሲያወሩ ሰምቻለሁ። ቋንቋውን የሚናገሩትም እስራኤሎች ብቻ ናቸው ስለሚባል፤ እነዚህማ አይሁዶቸ ናቸው ብዬ እየፈራሁም ቢሆን “ሻሎም” አልኳቸው፡፡
“ሰላም” ማለት ነው አይደል?
አዎ! በእብራይስጥ ቋንቋ ሰላም ማለት ነው፡፡ ደንገጥ ብለው ዞሩና አዩኝ፡፡ ትንሽ ነኝ፡፡ በግርምት እኔንም ያያሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይተያዩ ጀመር፡፡ ከዚያ “እኔ እኮ አይሁድ ነኝ፣ ቤተ እስራኤላዊ ነኝ” አልኳቸው፡፡ ታዲያ አዚህ ምን ታደርጋለህ? አሉኝ፡፡ ገጠር መወለዴንና ጎንደር ለትምህርት መምጣቴን ነገርኳቸው “ነገ ሆቴል ና” አሉኝና በተባልኩት ሰዓት ሄድኩ፡፡ አወራን፡፡ በቃ እስራኤል ውሰዱኝ” አልኳቸው፤ “አሁን አንችልም ምክንያቱም ፓስፖርት፣ ቪዛ የሚባል ነገር አለ” አሉኝ፡፡ እኔ ብድግ ብሎ ተሳፍሮ መሄድ ነበር የመሰለኝ፡፡ እሺ ብዬ ተሰናበትኳቸው፡፡ ሄዱ፡፡ በአጭሩ ወደ እስራኤል ከተመለሱ በኋላ ሰንጻጻፍ ቆይተን ከሁለት ዓመት በኋላ ተሳክቶልኝ እስራኤል ገባሁ፡፡ በቀላሉ አይደለም የሄድኩት ረጅም ነው ታሪኩ፡፡ ብቻ ውጣ ውረድ አይቼ ነው የሄድኩት
እስራኤል ሲገቡ ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበሩ የሄዱትም በንጉሱ ጊዜ ከ50  ዓመት በፊት እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ እዛ እንደደረሱ ምን ገጠመዎት? ምን  ዓይነት ፈተናዎችስ ተጋፈጡ?
እነዚህ ሶስቱ እስራኤላዊያን ሰዎች አየር መንገድ ድረስ መጥተው ተቀበሉኝ። ወላጆቼም “እየሩሳሌም ልሄድ ነው” ስላቸው፤ ሀዘንም ደስታም ተቀላቀለባቸው፡፡ መራቄ አስጨነቃቸው ነገር ግን እየሩሳሌምን ልረግጥ ነው ስላቸው፡፡ ደግሞ ተደሰቱ፡፡ ብቻ እነዛ ሰዎች ተቀብለው እንደኛው ሰው ቤት ለአንድ ሳምንት ካረፍኩ በኋላ አዳሪ ት/ቤት አስገቡኝ፡፡ ት/ቤቱ “አሎኔ ይስሃቅ” ይባላል፡፡ በእብራይስጥ “አሎኔ” ማለት የጥድ ዛፍ ማለት ነው፡፡ ት/ቤት ስገባ ተማሪዎቹ፣ ት/ቤቱ፣ ባህሉ ቋንቋው፣ አካባቢው ሁሉም ለእኔ አዲስ ነበር፡፡ በተለይ የትምህርት ደረጃው ከፍተኛና ከባድ ነበር። መጀመሪያ የግብረ ገብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ያንን በእብራስይጥ መማር ለኔ ከባድ ስለነበር፣ አንድ ቀደም ብሎ እስራኤል የሄደ ዘመዴ ሊጠይቀኝ ሲመጣ ይህንን ችግሬን ተመልክቶ ከኢየሩሳሌም የአማርኛ መፅሐፍ  ቅዱስ ገዝቶ አመጣልኝ፡፡ ክፍል ውስጥ በእብራይስጥ የሚሰጡትን ትምህርት፣ የአማርኛ መፅሐፍ ቅዱስ እገልጥና ተመሳሳይ ገፅና ምዕራፍ ላይ እያየሁ ነበር የማጠናው፡፡ ሌላው ቅዳሜ ትምህርት ዝግ ነው። ሌላው ተማሪ ሲዝናና ሲጫወቱ እኔ ቁጭ ብዬ ነበር የማጠናው፡፡ በዚህ መልኩ ነው ተቋቁሜ ትምህረቴን የጨረስኩት፡፡ አንድ ጊዜ እንደውም ዶርም የሚጋራኝ ከሮማንያ የመጣ ተማሪ እሱከተኛ በኋላ መብራት እያበራሁ ሳጠና መብራቱ ይረብሸዋል፡፡ ሁልጊዜ አቤቱታ ያቀርባል አንድ ቀን ተናድዶ መብራን አጠፋብኝ፡፡ መቼም ሀበሻ ሀበሻ ነው፤ ተነስቼ በቦክስ አፉን ስለው ጥርሱ ሁሉ ደም በደም ሆነ። ከዚያ ሀላፊዎች መጡ፤ ጉድ አሉ፤ ነውር ነው አሉ፤ ተወቀስኩ፡፡ ደንግጬ ይቅርታ ጠየኩ። በዚህ ሁኔታ ነው 12ኛ ክፍል ያጠናከኩት፡፡
ከዚያ በኋላ  የግድ ውትድርና ትገቢያለሽ፤ 18 ዓመት የሞላው እስራኤላዊ ወንድ 3 ዓመት፣ ሴት 2 ዓመት ውትድርና ገብቶ ያገለግላል። እኔ ውትድርና ስገባ በጣም ከሲታ ኪሎዬ የማይመጥን ስለነበር ሁለት ዓመት ሳይሞላኝ “መቀጠል አትችልም” ብለው አሰናበቱኝ፡፡ ከዚያ ተመልሼ ዩኒቨርስቲ ልመዘብ ስል፣ ውትድርና ግዴታህን አላጠናቀቅክምናአንቀበልም” አሉ፡፡
ታሪኩን ነገረኳቸው “ኪሎዬ ስላልፈቀደ ነው” አልኩኝ፡ በመጨረሸ ተቀበሉኝ፡፡ አንድ ዓመት የመሰናዶ ትምህርት ጀመርኩኝ። የዩኒቨርስቲ ትምህርቱ ከባድ ነው፡፡ ቶሎ ቶሎ መፃፍ አለብሽ፡፡ እኔ ቋንቋው ቢገባኝም እንደ አገሬው ሰው ቶሎ ቀልጠፍ ብዬ መፃፍ ከበደኝ። ከሌሎች ደብተር እየለመንኩ እያጠናሁ ነበር ለፈተና የምቀርበው፡፡ ብቻ በዚህ መልኩ መሰናዶ 1 ዓመት የዩኒቨርስቲውን መደበኛ ትምህርት 3 ዓመት፣ በድምሩ 4 ዓመት ተምሬ ዲግሪዬን ያዝኩ፡፡
ምን አጠኑ?
“ሚድል ኢስት ስተዲስ ኤንድ ኮንቴምፖራሪ አፍሪካ ሂስትሪ” የሚል ትምህርት ነው ያጠናሁት፡፡
እርሶ ግን የሚታወቁት በጋዜጠኝነት ነው። ምናልባትም ለ29 ዓመት ያህል በጋዜጠኝነት አገልግለዋል፡፡ የተማሩት ትህርት ከጋዜጠኝነት ጋር ግንኙነት አለው ወይስ ጋዜጠኝነት ተማሩ?
እኔ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የኢትዮጵያ አይሁዶች አይሁድነታቸው እውቅና ያግኝ በሚል ትግል ከጀመሩት፣ ያንንም ትግል ከመሩት አንዱና ግንባር ቀደሙ ነበርኩኝና፣ በሚዲያም በምንም በተደጋጋሚ ስሜ ይጠራ ነበር፡፡ በዚህ ላይ እያለሁ ምን ሰማሁ መሰለሽ… በቴልአቪቭ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት አዲስ ሊጀመር ነው ተባለ፡፡ ጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ አይቼ በተቀመጠው ስልክ ደወልኩና፤ አነጋገርኳቸው፡፡ እነሱ ደግሞ “ይህን ትምህርት ለመማር የሚፈቀድላቸው በጋዜጠንንት ሥራ 5 ዓመትና ከዚያ በላይ ልምድ ያላቸው ናቸው፤ አንተ ገና ጀማሪ ነህ” አለችኝ፡፡ “እና ልሁና መማር እፈልጋለሁ” ሰላት ጸሀፊዋ “ቆይ ከአለቃዬ ጋር ልነጋገር” ብላ ገባች፡፡ ተነጋግራ መጣችና መዘገበችኝ፡፡ ከዚያም የጋዜጠኝነት ትምህርቴን ጀመርኩኝ፡፡ ያም ከባድ ነበር፡፡ ነገር ግን ታግዬ ሁለት ዓመት ተምሬ ተመረቅኩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በጣም የሚደንቅ ነገር ልንገርሽ፡፡ ሶስቱ እስራኤላዊያን ማለትም ጎንደር አግኝቻቸው ወደ እስራኤል  የወሰዱኝ ሰዎች ሁሉም ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ አንደኛው “መዓሪብ” የተሰኘ ጋዜጣ (evening news ማለት ነው) መስራችና ዋና አዘጋጅ ነው። ሁለተኛው ሰው ደግሞ የእስራኤል አርሚ ሬዲዮ አዛዥ ነው፡፡ ሶስተኛው የአስራኤል አየር መንገድ ኩባንያ ቃል አቀባይ ነበር፡፡ ጋዜጠኛና  አሜሪካዊ ነው፡፡ እኔ የጋዜጠኝነት ትምህርት ልመዘገብ የጠየኩት  የማዕሪቭ ጋዜጣ ባለቤት ዋና ጸሀፊ ናት፡፡ የግል ጋዜጣ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እስራኤል የመንግስ የሚባል ጋዜጣ የለም፡፡ ሁሉም የግል ነው፡፡ እንደገና፣ ጋዜጠኝነት ስማር ይሄው የጋዜጣ ባለቤት መምህር ሆኖ መጣ፡፡ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ሀላፊውም እርሱ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ጎንደር እያለሁ አሁን ጋዜጣውን አላስታውስም፡፡ የጠቅላላ እውቀት ጥያቄ ይወጣል። ለምሳሌ ስልክን የፈለሰፈው ማን ነው?” “ኤሌክትሪክን ማን ፈጠረ?” “ፕሪንተርን ማን ሰራ?” አይነት ጥያቄዎች  ይወጣሉ፡፡ ሶስት ጊዜ  መልስ ልኬ በትክክል አልመለስኩም በአራተኛው በትክክል መልሼ ምህረቱ ሙጬ መልሱን በትክክል መልሷል” ተብሎ ስሜ በጋዜጣ ወጣ፡፡ ከዚያን ጀምሮ ነው እንግዲህ ለጋዜጠኝት ፍቅር ያደረብኝ፡፡
እስኪ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በሱዳን  በኩል ወደ አስራኤል ስለወጡበት “ዘመቻ ሙሴ”፣ ከጎንደር አዲስ አበባ መጥተው ወደ እስራኤል ስለሄዱበት “ዘመቻ ሰለሞን” ትንሽ ያጫውቱኝ… ምክንያቱም እርሶ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወደ እስራኤል ይሂዱ ከሚለው በፊት እውቅና እንዲያገኙም ከታገሉትና ትግሉን ከመሩት ግንባር ቀደሙ እንደሆኑም ስለሚነገር ማለቴ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት የመሩት ያቋቋሙት “የእስራኤል ድምጽ” (voice of Israel)  ሬዲዮ ጣቢያም ለኢትዮጵያ አይሁዶች ተብሎ የተቋቋመ መሆኑን ሰምቻለሁ …
ልክ ነው፤ በዘመቻ ሙሴ  ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች እስራኤል ሲገቡ ነው ለእነሱ የሚያገለግል ሬዲዮ ጣቢያ መክፈት ያስፈለገው። በዚያን ወቅት ይህን የሚያደራጅና የሚመራ ሰው ሲፈለግ እኔ የጋዜጠኝነት ትምህርቴን ተምሬ ተመርቄ ስለነበረ፤ ይሄ ሰው አለ ተብዬ ተጠቁሜ ወደ አስተዳዳሪው ተጠርቼ ሄድኩኝ። ይሄ ሀሳብ ስላለ ሀላፊነት ወስደህ አቋቁመው ተባልኩኝ፡፡ ቀላል አልነበረም፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ አልፌ ነው ያቋቋምኩት፡፡ እ.ኤ.አ በ1985 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡ ልምድ ስላልለነበረኝ ብዙ ችግር ነበረው፡፡ ፈተናውን እዚህ ለመዘረዘር ጊዜውም አይበቃም፡፡ ይህን ሬዲዮ ጣቢያ ለ23 ዓመት መርቼ ለተተኪ አስረክቤያለሁ፡፡ ወደ ዘመቻ ሙሴ ስንመጣ እንዳልሽው፤ ሬዲዮ ጣቢያው ያስፈለገው የኢትዮጵያ አይሁዶች ወደ እስራኤል መግባትን ተከትሎ ነው፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ፤ በአብዛኛው አይሁዶች በምዕራቡ አለም እንዳሉ ብቻ ነበር  የሚታሰበው እዚህ ይኖራሉ ብሎ ማን አሰበ፡፡ ግንኙነቱ ከ2 ሺህ ዓመት በፊት የተቋረጠ ነበራ፡፡
ታዲያ በምን መልኩ ነበር ኢትዮጵያ ውስጥ የአይሁዶች ዝርያ እንዳሉ የታወቀው?
በ1867 ዓ.ም አንድ ፈረንሳዊ የሴሜቴክ ቋንቋ አጥኚና ተመራማሪ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ፣ ወልቃይት አካባቢ ሲያገኛቸው እና “እኔ አይሁድ ነኝ” ሲላቸው አላመኑትም፡፡ ተመራማሪው ጆሴፍ ሀሌቪ ይባላል፡፡ “እንዳንተ ቆዳው የተበላሸና በለምጥ የተጠቃ አይሁድ አናውቅም” አሉት፡፡ አልተቀበሉትም፡፡ በመጨረሻ በብዙ ድካም  በሀይማኖት ቋንቋ ማውራት ሲጀምሩ ነው የተግባቡት፡፡ ይህ ተመራማሪ ወደ ፈረንሳይ ሲመለስ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ አይሁዶች እንዳሉ ገለፀ፡፡ ከዚያ በምዕራቡ ዓለም ያሉ አይሁዶች ስለ ኢትዮጵያ አይሁዶች ማጥናትና መመራመር ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ እስራኤል ይግቡ የሚለው ሀሳብ አልተነሳም ነበር፡፡ ከዚያ እኔም ሄድኩኝ፡፡ ከእኔም በፊት ከመርከብ እያመለጡ እስራኤል የገቡ የኢትዮጵያ አይሁዶች ስለነበሩ “እውቅና ስጡ” የሚለውን ዘመቻ ጀመርን፡፡
ያኔ ብዙ አከራካሪ ጉዳይ ነበር፡፡ ታሪኩ ረጅም ነው፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ የእስራኤል መንግስት እውቅና ሰጠ፡፡ እውቅና ከሰጣችኋቸው ደግሞ ወደ እስራኤል ይምጡ የሚለውን ዘመቻ ጀመርን፡፡ ይሄም ብዙ ጊዜ ወሰደ፡፡ በስኮላርሽፕ በስራ እያልን ጥቂቶችን ለመውሰድ ሞከርን፤ ግን በዚህ መልኩ ወስደን እንደማንጨርስ ስንረዳ፣ ከሱዳን መንግስት ጋር በመነጋገር በሱዳን በኩል ብዙ ወጣቶች ወደ እስራኤል ገቡ፡፡ እነዚህ ወጣቶች እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም ነው እስራኤል የገቡት፡፡
እነሱ እስራኤል ከደረሱ በኋላ ለቤተሰቦቸቸው ደብዳቤ ይፅፋሉ፡፡ “እኛ እስራኤል ገብተና”ል ብለው ማለት ነው፡፡ ያን ጊዜ ለእየሩሳሌም በሱዳን በኩል መንገድ ተከፈተ ማለት ነው በማለት  ሃብት ንብረታቸውን እየተዉ ወደ ሱዳን መትመም ጀመሩ፡፡ 50፣100 እና 200 እየሆኑ ገቡ፡፡ ከዚያ በኋላ የእስራኤል መንግስት የሞሳድ ሰዎችን ልኮ ሁኔታውን እንዲያጠኑ አደረገ፡፡ ሰዎቹን ማስገባት ስለሚቻልበት መንገድ ከሱዳን መንግስት ጋር እንዲነጋገሩ ነው የተላኩት፣ ከዚህ ሂደት በኋላ “ዘመቻ ሙሴ” ከኖቬሞበር 1984 አስከ ጃንዋሪ 5 ቀን 1985 ዓ.ም  ተካሄዶ፡፡ በሱዳን በኩል ብዙ ሰዎች ወደ አስራኤል ገቡ፡፡
በዘመቻ  ሙሴ ምን ያህል ሰው ወሰዳችሁ?
ከ8 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ እስራኤል ማስገባት ችለናል፡፡ እነዚህ አይሁዶች በብዛት ሲገቡ ነው፣ ለቋንቋው ለባህሉ አዲስ ስለሆኑ፣ በአማርኛ ቋንቋ ሬዲዮ ጣቢያ የተከፈተው፡፡
ወደ ዘመቻ ሰለሞን እንምጣ እስኪ?
ዘመቻ ሰለሞንን በተመለከተ ያን ጊዜ ሱዳን ሳይደርሱ  የቀሩ ሰዎችን ያመጣንበት ኦፕሬሽን ነው፡፡ ዘመቻ ሙሴ ከአሜሪካና ከሱዳን መንግስት ጋር በሚስጥር የተካሄደ ነው፡፡ ያንን እንግዲህ የሚዲያ ሰዎችና አንዳንድ የእኛን ወደ አስራኤል መግባት ያልወደዱ ሰዎች ሆን በለው ይፋ አደረጉትና ለሚዲያ በተለይም ለ”ቦስተን ግሎብ” እና ለ“ኢንዲፔንደንት” ጋዜጦች ወሬው ደረሰ፡፡ “ይሄ ነገር አደገኛ ስለሆነ ይቅር” ተብሎ ተቋረጠ፡፡ ከዚያም በኋላ ከቋራና ከጎንደር መጥተው እዚህ አዲስ አበባ ተሰበሰቡ። እነዚህን ሰዎች ለማውጣት ሌላ ዘመቻ ያስፈልጋል ተባለና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ብዙ ውስጣዊ ስምምነቶች ተካሂደው፣ እ.ኤአ በ1991 ዘመቻ ሰለሞን ተካሄደ፡፡       
በዚህኛውስ ዘመቻ ምን ያህል የኢትዮጵያ አይሁዶችን ወስዳችሁ?
14 ሺህ 200 ሰዎችን ወስደናል፡፡ በ32 ሰዓታት ውስጥ በ36 በረራ ነው የወሰድናቸው። የሚገርምሽ ያን ጊዜ አንድ አውሮፕላን 700 ወይም 800 ሰው ነበር በአንድ ጊዜ የሚያጓጉዘው፡፡ እኛ ኦፕሬሽኑን ስንሰራ በአንድ በረራ እስከ 1 ሺህ 9 ሰዎች ሄደዋል፡፡ ይሄ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ላይ ተመዝግቧል። በዚህ ኦፕሬሸን ባልሳሳት ሰባት ሴቶች በረራ ላይ  እንዳሉ ወልደዋል፡፡ በዚህ መልኩ ነው ኦፕሬሽኑ የተጠናቀቀው፡፡ በሌላ በኩል ቀሪዎቹ ይምጡ አይምጡ፣ናቸው አይደሉም፣ ክርስትና ተነስተዋል፤ ለምን ተነሱ፣ የአይሁድ ዝርያ አላቸው ወይስ የላቸውም፣ የሚለው በክርክር ላይ ነበር፡፡
እርስዎ ኢትዮጵያን አብዝተው እንደሚወዱ ይነገራል፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ሰዎች የሚያነሱት እዚህ ተወልደው በህጻንነታቸው የሄዱ፣ እዛ የተወለዱ ቤተ እስራኤሎች የተፈጠሩበትን ያደጉበትን ባህል እንዲያውቁ ስለ ኢትዮጵያ እንዲገነዘቡ ብዙዎችን ወደ ኢትዮጵያ እያመጡ አሉ የሚባሉ የኢትዮጵያ መዳረሸዎችን አያስጎበኙ እንደሚገኙ ነው የሰማሁት እስኪ በዚያ ላይ ጥቂት እናውጋ
ታሪኩን የሚረሳ እውነታውን የሚረሳ ማንነቱ እንደረሳ ነው የምቆጥረው፡፡ እኔ ደግሞ ማንነቴን የምረሳ ሰው አይደለሁም፡፡ ታሪኬ፣ የተወለድኩበት፣ አያት ቅድመ አያቶቼ ያሉት እዚሁ ነው፡፡ ይሄ ታሪክ መረሳት ሳይሆን መወረስ ነው ያለበት፡፡ እኔ ራሴን የማየው ካለፈው ትውልድ አዳሪነት እንዳለብኝ ይሄ የሽግግር ትውልድ እንደ ድልድይ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ተሻገሮ ወደ እስራኤል ሲሻገር የነበረውን ሳይረሳ፣ በዚያ ድልድይ የሚመለስበት፣ተመልሶ የነበረበትን የሚያይ አድርጌ ነው የማየው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት ነበርን፣ ቀርታለች የነበረው ድልድይ ይሰበርና አሻግረን እንተያይ የሚባል ነገር የለም፡፡ አብዛኛዎቹ ከአገር ቤት ወደ እስራኤል የሄዱት  እዛ ሄደው ትዳር ይዘው፣ ጥሩ ገቢ ኖሯቸው፣ ልጅ ወልደው እያሳደጉ ነው፡፡ ከተማ የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው። ለገበያ ከተማ ሄደው የሚመለሱ፡፡ እነዚህ አብዛኛው የኢትዮጵያን ክፍል አያውቁትም፡፡ እነዚህ ሰዎች ባህሉ ይናፍቃቸዋል ይመጣሉ፡፡ ጠላው፣ ጠጁ፣ ዕጣኑ፣ ቡናው፣ አየሩ፣ ልብሱ፣ ቋንቋው ቀለሙ ይናፍቃቸዋል፡፡ እነዚህን ሰዎች ይዣቸው ስመጣ፣ የናፈቃቸውን ባድማ አይተው፣ቀምሰው አየሩን ምገው በደስታ ሲያለቅሱና ናፍቆታቸውን ሲወጡ ሳይ እረካለሀ። ከዚህ በፊት አገሩን የማያውቁትም የአያት የቅድመ አያቶቻቸውን መፈጠሪያ አይተው ሲደመሙና ሲያደንቁ ሳያቸው ደስ ይለኛል፡፡ በኮቪድና በፀጥታው ሁኔታ ትንሽ ተስተጓጉሏል እንጂ ይህንን እሰራ ነበር፡፡ አሁንም የመጣሁት በውጭ የሚነገረውና እውነታው ምን ይመስላል የሚለውን አይቼ ስራውን ለመጀመር ነው፡፡
በአንድ ወቅት የእስራኤል አምባሳደር በኢትዮጵያ ሆነው ለመስራት መስፈርቱን አሟልተው ተመርጠው ካለፉ በኋላ አምባሳደር ሆነው ሳይመጡ መቅረትዎ ይነገራል፡፡ ምን ቸግር ተፈጥሮ ነው? ምን አጋጠመዎት?
በህይወቴ የሚያሳዝነኝ ነገር ካለ ይሄ ነው። ሹመቱ አይደለም፤ ሹመቱን ንቄውም አይደለም፣ እኔም ሹመት ፈላጊ ሰው አይደለሁም፡፡ እኔ ምኞቴ የነበረው ባለኝ ችሎታና እውቀት አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ውጤታማ ስራ መስራትና ሁለቱንም ሀገራት መጥቀም ነበር፡፡ ያ ነበረ  ዋና ዓላማዬ፡፡ በእርጥ መስፈርቱን አሟልቼ ለስልጠና ስቃረብ ነው አሻጥር (ሴራ) የተሰራው። ምክንያቱም “አንተ ተመርጠሀል ስልጠናውን ሰሞኑን እንጀምራለን” ተብሎ የሴኩሪቲ ሂደቱን ሁሉ አልፌ ነው ይሄ ነገር የተበላሸው፡፡
ዋናው ምክንያት ግን ምን ነበረ…. የተበላሸበት?
እኔም ጉዳዩን በትክክል ላውቀው አልቻኩም። እስካሁን ድረስ “የተወሰኑ ሰዎች ናቸው ስላንተ የተዛባ መረጃ አቅርበውና እንዲህ አይነት ችግር አለበት” ብለው ያበላሹት የሚል ነገር ነው የሰማሁት፡፡ ያኔ የመረጠኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ሊበር ማን የሚባለው፣ ጉዳዩን ይዤ ፍርድ ቤት እቀርባለሁ ብሎ ነበር። እንዲያውም የፓርቲው አባላት “ለራስህ ችግር ውስጥ ነህ” ሌላ ጭቅጭቅ ውስጥ አትግባ፡፡ አሉት፡፡ ያኔ በራሱ ጉዳይ ተከሰሶ ፍርድ ቤት ይመላለስ ነበር፡፡ እሺ ብሎ ጉዳዩን አቆመው፡፡ እኔ ስሜ አንድ ቀን በክፉ ተነስቶ አያውቅም፡፡ በጋዜጠኝነት ስራዬ ተጠንቅቄ ህዝብ አክብሬና ተከብሬ የኖርኩ ነኝ፤ እውቅናውም አለኝ፡፡ ወይ “ይሄን አጥፍተሃል” ተብዬ ተከስሼ ፍርድ ቤት ቀርቤ፣ ጥፋተኛ ነህም አይደለህምም አልተባልኩም፡፡ አንድ አስነዋሪ ነገር ሰርቼ አላውቅም ብቻ ነገሩ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ በዚያው ቀረ፡፡ እስካሁን ውስጤ ያዝናል፡፡
ከዚያ በኋላስ ለመወዳደር አልሞከሩም?
ከዚያ በኃላ አስጠላኝ፡፡ ያኔም መከራከርና መሟገት እችል ነበር፡፡ የሰዎች አመለካከትና ሁኔታ እንደዚህ የታመመ ከሆነ ለምን አልተውም ብዬ እርግፍ አድርጌ ተውኩት፤ እንኳን ድጋሚ ልወዳደር፡፡ ያኔ ለአምባሳደርነት ተመርጠሃል ስባል ሶስት ዶክሜንት አዘጋጅቼ ነበር፡፡ እዚያ በአምባሳደርነት “ስሰራ ምን ምን ጠቃሚ ተግባራትን እከውናለሁ” የሚል በቅድሞ ተከተል ሶስት ሰነድ አዘጋጅቼ ነበር። ስትራቴጂክ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መካከል “ምን እርባና ያለው ነገር ልሰራ እችላለሁ” ብዬ ነው ሰነዱን ያዘጋጀሁት፡፡ አየሽ አምባሳደርነት ማለት ሱፍና ከረባት አድርጎ በምቾት መጋለብ አይደለም፡፡ ብዙ ትርጉም ያለው ስራ የሚሰራበት ትልቅ ቦታ ነው፡፡ እኔም ሸሚዜን ወደ ላይ ሰብስቤ ስራ የመስራት፣ ጭንቅላቴን የማሰራት ዕቅድ ነው የነበረኝ፡፡ በነገርኩሽ መልኩ ግን ተበላሸ፡፡
ኢትዮጵያና እስራኤል እንደሌሎቹ አገራት የዲፕሎማሲና የሁለትዮሽ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን እትብታቸው የተሳሰሩ አገራት ናቸው። በአማርኛችን  እንደሚባለው “በአምቻ ጋብቻ” የተሳሰርን እንደመሆኑ የተለየ ግንኙነት ነው ያለን፡፡ እናንተም እዚህ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ በመሆኑ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስባችኋልና፣ የፌደራል መንግስት  ህወኃት ከሚባለው ቡድን ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባና ነገሩ እየከፋ ሲመጣ፣ እስራኤል በአሸማጋይነት እንድትገባ ጥረት አድርጋችሁ፣ ያ ጥረት መክሸፉን ሰማሁ፡፡ ምን እክል ገጠመው?
 እንዳልሽው ነው፡፡ እትብታችን የተሳሰረ የተዋለድን አገራት ነን፡፡ ጉዳዩ በእጅጉ ያሳስበናል፡፡ አኛ ይህንን ጉዳይ ያሰብነው ጦርነቱ ተጀምሮ ወደ አደገኛ አዝማሚያ እየሄደ መሆኑን ስንገነዘብ ነው፡፡ ይሄ ነገር የእርስ በእርስ መተላለቅ፣ የወንድማማች መቋሰልና መዳማት፣ እየተባባሰ ነው፡፡ እኛ እንዳልሽው ኢትዮጵያ ተወልደን ያደግንባት በመሆኗ፣ ችግሩን አሻገረን ማየት ሳይሆን የመፍትሄ አካል መሆን የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡ እርግጥ ነው መለዮ ለብሰን ጦርነት አንሰለፍም፤ ነገር ግን ማድረግ የምንችለው እንዲሸማገሉ ሀሳብ ማቅረብ ነው ብለን አሰብን፡፡ መሸማገል መታረቅ ሲባል በታሪክ የጦርነቶች መጨረሻ ሁሉ መደራደርና ሰላም ማውረድ ነው፡፡ እንደምታውቂው በዓለም ላይ ብዙ የከፉ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ ለምሳሌ ጀርመኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት 6 ሚሊዮን አስራኤላዊያንን ጨርሰዋ፤ ጨፍጭፈዋል፡፡ ያ ሁሉ ሆኖ መጨረሻው ምንድነው ያልሽ እንደሆነ ታርቀው ዛሬ ጀርመንና አስራኤል ወዳጅ አገሮች ናቸው፡፡ ጀርመን እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ባህር ሰርጓጅ የጦር መርከቦችን ለእስራኤል በቅናሽ እየሸጠች ነው ያለችው፡፡ በአሁኑ ወቅት እስከዚህ ደርሰዋል፡፡
ሌላው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ በጃፓን ሂሮሺማና ነጋሳኪ መርዛማ ቦንብ በመጣል ከፍተኛ ጥፋት አድርሳለች፡፡ የእዚያ ርዝራዥ አሁንም በሚወለዱት ህፃናት ላይ የጤና እክል ማስከተሉን አልተወም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካና ጃፓን የቃል ኪዳን ወዳጅ  አገሮች ናቸው፡፡ ይህ የሆነው እርቀ ሰላም ላይ ስለደረሱ ነው፡፡ ሌላም ሌላም ምሳሌዎቸን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ግን የእኛ አገሩ አሁን ከጠቀስሷቸው አገራት ይለያል…
የእባቡን እሬሳ እባብ በላውና
መድሃኒቱ ጠፋ እርስ በእርስ ሆነና
እንደሚባለው አይነት ሆኖብን ነው የተቸገርነው…
ቢሆንም ቢሆንም እንደውም አስቸኳይ እርቀ ሰላም የሚያስፈልገው አንድ ቤት እየኖሩ አስቸጋሪ ጉዳይ ውስጥ ለገቡ የአንድ እናት ልጆች ነው፡፡ አየሽ ጦርነት አስቸገሪ ነው፤ እንዴት እንደምትጀምሪው ታውቂያለሽ፡፡ እንዴት እንደምትጨርሺው ግን አታውቂም። ወይ ተሸንፈሽ አሊያም አሸንፈሽ ነው፡፡ በዚህ መሃል ብዙ ጥፋት ብዙ ውድመት፣ ሞትና መፈናቀል ይደርሳል፡፡ በዚህ መንገድ መሃል ላይ ያለው መሸማገል ብቻ ነው፡፡ እኛም ይህንን በተመለከተ ከጓደኞቼ ጋር ተሰብስበን እኛ  የኢትዮጵያ ተወላጆች ነን፤ ፖለቲካ ውስጥ ገብተን ውሳኔ ወይም አስተያየት መስጠት አንችለም፤ ነገር ግን እንዲሸማገሉ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ አንቺም ቅድም እንዳልሽው ሁለቱ አገራት እትብታቸው የተሳሰረ ወዳጅ አገራት ናቸው፡፡ ስለዚህ የእስራኤል መንግስት ለምን አሸማጋይ አይሆንም ተባባልን፡፡ እናም እዚህ እስራኤል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከሌላም ክልል የወጡ ኢትዮጵያውያንና  እኛ ሆነን አንድ ደብዳቤ ለእስራኤል መንግስት እንፃፍ ተባለ፡፡ ደብዳቤውን አረቀቅን፡፡ የህግ ባለሙያዎቸ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የህግ ቋንቋ እንዲያረቁጽ ተደረገና አንድ ገፀ ተኩል ደብዳቤ ተፃፈ፡፡ የዚህ ኮሚቴ ሰብሳቢ እኔ ነበርኩኝ፡፡ “በሉ ይህንን ደብዳቤ  እንፈርምበትና ወደ ሚመለከተው አካል ይግባ ስንል አንዱ ከመካከላች “የትግራይ ተወላጆች አንፈርምም  ብለዋል” አሉን አለ ለምን ስንል “እዛ ትግራይ ወገኖቻችን እየተገደሉ እያለቁና እየተጨፈጨፉ አንፈርምም እንዳሉ ነገሩን፡፡
“እንዴት!! ከዚህ ችግር በሁለቱም ወገን ያሉት እንዲድኑ ነው እኮ ይሄንን ጥረት እያደረግን ያለነው እንጂ ጨምራችሁ ደበድቧቸው፤ ጨፍጨፏቸው ብለን አይደለም” ብንል  “አይ አንፈርምም ብለዋል” ተባለ፡፡  በዚህ ምክንያት ፈረሰ፡፡ ደብዳቤውን እስካሁን መሳቢያዬ ውስጥ አስቀምጨዋለሁ፡፡
የኮቪድ ወረርሽ ከተከሰተና ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም ነበር፡፡ አሁን ለአንድ ሳምንት በኢትዮጵያ ቆዩ ጎንደርም ባህርዳርም ደርሰው ተመልሰዋል፡፡ በውጭ የሚወራውንና እዚህ ያለውን የኢትዮጵያን ሁኔታ እንዴት አዩት?
መጥቼ ከሄድኩት ሁለት ዓመት ሊሆን ነው መሰለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ጦርነቱ ሲከፈት እዚህ ነበርኩ፡፡ በአጋጣሚ ወደ ባህር ዳር ኤርፖርት ከባድ መሳሪያ ሲተኮስም ባህርዳር ነበርኩኝ፡፡
ስለዚህ 14 ወይም 15 ወር ሆኖዎታል ከመጡ ማለት ነው…
አዎ፤ አንድ ዓመት ከምናምን ሆነኝ፡፡ ያኔ ከጎንደር ወደ ባህርዳር ስመጣ የነበረውን ፍተሻ ክብደት አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ባለፈው ሳምንት ከጎንደር ወደ ባህርዳር ስመለስ ፍተሻው ቀላል ነበር፡፡ አንደባለፈው የጠበቀ አልነበረም የመረጋጋት ሁኔታ አይቻለሁ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ መረጋጋት ቀጣይነት አለው ወይ? አስተማማኝ ነው ወይ? የሚለው መመለስ አለበት፡፡ ውጪ ሆነን የምንሰማው ሌላ ነው። ደህንነትን በተመለከተ ብዙ ችግር እንዳለ፣ ዘራፊውና ቀማኛው እንደበዛ፣ የዜጎች ደህንነት አደጋ ውስጥ እንዳለ፣ የኮሮናው ጉዳይ ጥንቃቄ የጎደለውና የሚሞተውን ሰው ብዛት መንግስት ግልጽ እንደማያደርግ ነው የሚናፈሰው፡፡ እኔ ባየሁት በታዘብኩት ግን ቱሪስቱ  ከትግራይ ውጪ ያለውን ቦታ መጎብኘት እንደሚችል ነው፡፡ እኔ ጦርነቱን በተመለከተ ለማንም አልወግንም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የዘር የጎሳ ጉዳይ እኔ ጋር ቦታ የለውም፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነተ ጥላቻና ደም መቃባት የትም አያደርስም፡፡ ማን ማንን ነው የሚያሸንፈው?  ወንድሙ ወንድሙን ማሸነፉ ውጤቱና ትርጉሙ ምንድን ነው? ውጤቱ ሞት፣ መቁሰል፣መፈናቀል፣ እንግልትና ቅስም ሰባሪ ሀዘን ነው፡፡ ውጤቱ የኢኮኖሚ መውደምና የሀገር እድገት የኋልዩሽ ጉዞ ነው፡፡ ይሄ ማንን ነው የሚጠቅመው? በእኔ አመለካከት የእልህ ሩጫውንና ጦርነቱን ትቶ ሰከን ባለ ሁኔታ ወዴት እያመራን ነው፣ የደረሰው ወድመትና ጥፋት ምን ያህል ነው? የምናገኘውስ ውጤት ምንድን ነው? ብሎ አመዛዝኖ መሸማገል፣ ያጠፋው በጥፋቱ መቀጣትና ሀገርን ከመጪው ጥፋት መታደግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ይመስለኛል፡፡
ሌላው ሀገር ይህንን እያደረገ ነው ከባሰ ጥፋትና ውድመት ሀገሩንና ህዝቡን የሚታደገው፡፡ እንታረቅ እንሸማገል፣ቁስላችንን እናክመው ጥላቻና ቂሙን እናፅዳው ማለት ነው ያለባቸው ሌላ ነገር አይታየኝም፡፡ ሌላው ማለት የምፈልገው እስራኤልና ኢትዮጵያ ቁርኝታቸው የተለየና የጠበቀ እንደመሆኑ ከመንግስታቱ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲያደርጉ ፍላጎቴ ነው፡፡ ለዚህም የምችለውን አደርጋለሁ፡፡ ተመሳሳይ ዝርያ፣ባህል ዝምድና ያላቸው ህዝቦች እንደመሆናቸው በባህል ልውውጥ፣በስፖርትና በመሰል ጉዳዮች ሁለቱ ህዝቦች መገናኘት እንዲችሉ ፅኑ ፍላጎት አለኝ፡፡ በመጨረሻም ይህን ሀሳቤን እንዳካፍል አንቺንም የጋዜጣሽን ዝግጅት ክፍልም ለሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ፡፡


Read 965 times
Administrator

Latest from Administrator