Print this page
Monday, 14 February 2022 00:00

እውን አፍሪካውያን ፍልስፍና አላቸው?

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(4 votes)


          "--ለዋናው የጎጠኝነትና ኔግሪቲውድ ፍልስፍና ደቀ መዝሙር ሴንጎር፣ የአፍሪካ ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ ከአውሮፓውያን ፍልስፍና የተለየ ባሕርይ ያለው ፍልስፍና ነው፡፡ ይህ ማለት፣ እንደ ሴንጎር እሳቤ፣ አመክንዮ (logic) የአውሮፓ ፍልስፍና መገለጫ ባሕርይ እንጂ የአፍሪካ ፍልስፍና መገለጫ ባሕርይ አይደለም፡፡ የእዚህ እሳቤ አንድምታ፣ አፍሪካውያን በስሜት (emotion) የሚመሩ በመሆኑ ነጮቹ ያላቸው አመክንዮአዊ ንቃተ ኅሊና ይጎድላቸዋል የሚል ነው፡፡--"            
       
               የጥቁር ህዝቦችን ፍልስፍና ህልውና በተመለከተ፣ በአፍሪካውያን እና በምዕራባውያን ፈላስፎች መካከል መግባባት የለም፡፡ የእዚህ ብርቱ ሙግት ዋናው መነሻ ምክንያት፣ ምዕራባውያን ፈላስፎቹ ኢማኑኤ ካንት፣ ጆርጅ ዊልሄልም ፍሬድሪክ ሄግል እና ዴቪድ ሂዩም የጻፉት እጅግ የተዛባ ትርክት ነው፡፡ የምዕራባውያን ፈላስፎች የተዛባ ትርክት፣ ጥቁር ህዝቦች እንደ ነጮች መፈላሰፍ የሚያስችል ንቃተ ኅሊና ስለሚጎድላቸው ፍልስፍና የላቸውም የሚል ነው (ኢዜ፣ 1997፡9)፡፡ በተቃራኒው፣ አፍሪካውያን ፈላስፎች፣ በጽሑፍ የሚገኙ ጥንታዊ የአፍሪካ ፍልስፍናዎችን በዋቢነት በማቅረብ የነጭ ፈላስፎቹ ትርክት ነጭ ውሸት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ እንደውም፣ አፍሮሴንትሪስቶች እንደሚነገሩን፣ የግሪኮች ፍልስፍና ምንጩ ጥንታዊያን ግብፆች ናቸው፡፡ ይኸን አስተምህሮ የሚያራግበው ንቅናቄ አፍሮሴንትሪዝም (Afrocentrism) ይሰኛል፡፡ የእዚህ ንቅናቄ ተቀናቃኙ ንቅናቄ ኢሮሴንትሪዝም (Erocentrism) ተብሎ ይጠራል፡፡ የእዚህ ንቅናቄ ደቀመዛሙርት እንደሚሞግቱት፣ የግሪኮች እና የጥንታዊያን ግብፆች ንፅረተ ዓለም (world outlook) ፍፁም የተለየ በመሆኑ የግሪኮች ፍልስፍናና ሳይንስ ከግብፆች የተቀዳ ነው የሚለው አስተያየት የተሳሳተ ነው (ቤል፣ 2002፡ ገጽ 4)፡፡ እንደ ግሪካዊው የታሪክ አባት ሄሮዶተስ ገለፃ ግን፣ የግሪኮች ባህል ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳንና ከግብፅ የተቀዳ መሆኑን መስክሯል (ኦንይዊኒ፣ 1991፡ ገጽ 32)፡፡ ኢኖሰንት ኦንይዊኒ እንደሚነግረን፣ አፍሪካውያን፣ እንደ ነጮቹ፣ ሁሉ ቱባ የዲበአካል (metaphysics)፣ የሥነ ዕውቀት (episetemology) እና የሥነ ምግባር (ethics) ፍልስፍና ባለቤት ናቸው (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 39-44)፡፡
የአፍሪካ ፍልስፍና ህልውናን አስመልክቶ የቀጠለው ሙግት በጥቁር እና በነጭ ፈላስፎች ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ርእሰ ጉዳዩ፣ አፍሪካውያን ፈላስፎች ሳይቀር የማይግባቡበት፣ ሙግቱ ያልተቋጨ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሙግት የገጠሙት አፍሪካውያን ፈላስፎች ሁለት ተቃራኒ ጎራዎችን ሙጥኝ ያሉ ፈላስፎቸ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ፈላስፎች የጎጥ ፍልስፍና አቀንቃኞች (ethnophilosophers) ይባላሉ፡፡ ለእነዚህ ፈላስፎች፣ የአፍሪካ ፍልስፍና የአፍሪካውያንን የጋርዮሽ ርዕዮተ ዓለም (impersonal views) በሚያንፀባርቁት አፋዊ ሥነ-ጽሑፍ (oral literature) ውስጥ የሚገኝ፣ ከምዕራቡ ዓለም የተለየ አቀራረብ (method) ያለው ፍልስፍና ነው፡፡
ሁለተኞቹ ፈላስፎች ሉላዊያን ፈላስፎች (universalists) ይባላሉ፡፡ ለእነዚህ ፈላስፎች፣ የአፍሪካ ፍልስፍና ህልውና አለው ብለው የማይቀበሉ ፈላስፎች ናቸው። ምክንያቱም፣ ለሉላዊያን ፈላስፎች፣ የአፍሪካ ፍልስፍና ህልውናው አለ ተብሎ መታወጅ የሚችለው ለመፈከር በሚመች መልኩ በአግባቡ ተጽፎ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም፣ እነዚህ ፈላስፎች፣ የአፍሪካ ፍልስፍና በጽሑፍ በማይገኙት በአፍሪካውያን አፋዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ፍልስፍና ነው የሚለውን የጎጥ ፍልስፍና አቀንቃኝ ፈላስፎችን አቋም አበክረው ይቃወማሉ (ኢምቦ፣ 1998፡ ገጽ 4)፡፡ ለእነዚህ ፈላስፎች፣ ፍልስፍና ሉላዊ የሆነ ዲሲፒሊን (universal enterprise) ነው፡፡ በመሆኑም፣ ለዋናው የእዚህ ንቅናቄ አጋፋሪ ጋናዊው ፈላስፋ ክዋሲ ዊሬዱ፣ የአፍሪካ ፍልስፍና ከቀሪው ዓለም ልዩ የሆነ ባሕርይ ያለው ፍልስፍና ነው የሚለው የጎጠኛና ኔግሪቲውድ ፈላስፎች እሳቤ ኢ-አመክንዮአዊ ነው (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 18)፡፡ ለዋናው የጎጠኝነትና ኔግሪቲውድ ፍልስፍና ደቀመዝሙር ሴንጎር፣ የአፍሪካ ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ ከአውሮፓውያን ፍልስፍና የተለየ ባሕርይ ያለው ፍልስፍና ነው፡፡ ይህ ማለት፣ እንደ ሴንጎር እሳቤ፣ አመክንዮ (logic) የአውሮፓ ፍልስፍና መገለጫ ባሕርይ እንጂ የአፍሪካ ፍልስፍና መገለጫ ባሕርይ አይደለም፡፡ የእዚህ እሳቤ አንድምታ፣ አፍሪካውያን በስሜት (emotion) የሚመሩ በመሆኑ ነጮቹ ያላቸው አመክንዮአዊ ንቃተ ኅሊና ይጎላቸዋል የሚል ነው። ዊሬዱ የእዚህ የሴንጎር እሳቤ ዋናው ተሟጋች ነው። እንደ እሱ እሳቤ፣ የሴንጎር የተዛባ ብያኔ የአፍሪካውያንን የንቃተ ኅሊና ተፈጥሮ ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡ እንደ ዊሬዱ እሳቤ፣ ፍልስፍና በባሕርይው ሉላዊ ነው፣ በመሆኑም አፈሪካውያን እንደ ነጮቹ ሁሉ የመፈላሰፍ ክህሎት ያላቸው ሰብአዊ ፍጡራን ናቸው፡፡ ኢ-አመክዮአዊ ንፅረተ ዓለምም ቢሆን በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ያለ እክል ነው፡፡ ይኸን ጉዳይ አስመልከቶ ዊሬዱ እንዲህ ጽፏል፡
It should be noted, conversely, that the principle of rational evidence is not entirely absent from the thinking of the traditional African. Indeed, no society could survive for any length of time without basing a large part of its daily activities on beliefs derived from the evidence. You cannot farm without some rationally based knowledge of the soils, seeds, and climate; and no society can achieve any reasonable degree of harmony in human relations without the basic ability to assess claims and allegations by the method of objective investigating. The truth, then, is that rational knowledge is not the preserve of the modern West, nor is superstition a peculiarity of the African (Wiredu, 1980፡39)                               
ሌላኛው የሉላዊ ፍልስፍና አቀንቃኝ ቤኒናዊው ፈላስፋ ፓውሊን ሆንቶንጅ ነው፡፡ ለሆንቶንጅ፣ የአፍሪካ ባህላዊ እሳቤ አመክንዮአዊነት የሚጎለው በመሆኑ ፍልስፍና ሊባል አይችልም፡፡ ሆንቶንጂ እንዲህ ጽፏል፣ “Ethnophilosophy is a pre-philosophy mistaking itself for a metaphilosophy, a philosophy which, instead of presenting its own rational justification, shelters lazily behind the authority of a tradition and projects its own theses and beliefs on that tradition” (Hountondji, 1991: 120). እንደ ሆንቶንጅ እሳቤ፣ ከቀሪው ዓለም የተለየ የአፍሪካ ፍልስፍና የለም፡፡ ለሆንቶንጅ፣ የማንኛውንም ፍልስፍና ህልውና ማረጋገጥ የሚቻለው በጽሑፍ ተሰንዶ ሲቀርብ ብቻ ነው፡፡ ይህ የማያወለዳ ቅድመ ሁኔታ ነው (ኢምቦ፣ 1998፡ ገጽ 22)፡፡ ሳሙኤል ኢምቦ እንዲህ ጽፏል፡
Paulin Hountondji defined African philosophy as the set of texts produced by Africans and called by their authors “philosophical.” Such a definition obviously has many implications, one of which is that there does not exist a traditional African philosophy in the collective, unconscious myths of the people. Writing is the crucial determinant of whether philosophy exists (Imbo, 1998:37).
ሆነቶንጅ፣ የአፍሪካን ፍልስፍና በተመለከተ ጎጠኛ ፈላስፎች የሰጡት ብያኔ አሉታዊ የሆነና ዘረኛ ነጮች የሰጡትን ብያኔ የሚያስተጋባ በመሆኑ ከአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ መወገድ አለበት ባይ ነው። በሌላ አነጋገር ለሆንቱንጅ፣ የጎጥ ፍልሰፍና አቀንቃኝ ፈላስፎች የዘረኛ ምዕራባውያን ፈላስፎች አፈ ቀላጤዎች ናቸው፡፡
ሌላኛው ሉላዊ ፈላስፋ ናይጄሪያዊው ፒተር ቦዱንሪን ነው፡፡ የቦዱንሪን አቋም ከሆንቶንጅ ጋር ተመሳሳይን ነው፡፡ እንደ ቦዱንሪን አሳቤ፣ ፍልስፍና ካልተጻፈና አለማቀፋዊ ካልሆነ በቀር ፍልስፍና በሚለው ስያሜ መጠራት አይችልም፡፡ ኢምቦ ቀጥሎ ያለውን ጽፏል፣ “Bodunrin doubts that a philosophical tradition can arise in the absence of literacy, more so since it is literacy that makes possible sustained rigor and systematization. If philosophy is not universal, it is not philosophy” (Ibid: 31).
በግሌ፣ ፍልስፍና የተጻፈ ድርሳን መሆን አለበት የሚለውን የሉላዊያ እሳቤ ተጋሪ ነኝ፡፡ ፍልስፍነና፣ ፅኑ የሆነ የአመክንዮ ሕግን በመመርኮዝ የሰው ልጅ ህልውና የቆመባቸውን መሠረታዊ እምነቶች የመፈተሽ፣ የመንቀስ፣ በአዲስ መልክ የማበጀት…ወዘተ ተግባር ነው፡፡ ይኸ ተግበር የተሳለጠ እንዲሆን ደግሞ የግድ የግልም ሆነ የቡድን ፍልስፍናዎች በጽሑፍ ተሰንደው መቅረብ አለባቸው፡፡ ቃላዊ ፍልስፍናን ከላይ በዘረዘርኳቸውን የፍልስፍና ተግባራት መሠረት በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ ያዳግታል፡፡
ኬንያዊው ፈላስፋ ሄነሪ ኦዴራ ኦሩካ ግን ፍልስፍና የግድ በጽሑፍ ተመዝግቦ የሚገኝ እሳቤ ብቻ ነው የሚለውን የሆንቱንጅ እሳቤ ተቃዋሚ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ እንደ ኦሩካ እሳቤ፣ በአፍሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ ፊደል ያልቆጠሩ፣ ሉላዊ እና አመክኖአዊ የሆነ ፍልስፍና ያላቸው ብዙ ታላላቅ ፈላስፎች አሉ፡፡ ኦሩካ ይኸን ያረጋገጠው ኬንያ ውስጥ የነበሩ ያልተማሩ ልሂቃን ያሰተምሩት በነበረው ቃላዊ ርዕዮተ ዓለም (oral traditions) ውስጥ ያለውን ፍልስፍና ከሃያ ዓመት በላይ በጥልቀት አጥንቶ ነው፡፡ ይኸ የኦሩካ አዲስ ንቅናቄ የልሂቃን ፍልስፍና (philosophic sagacity) ይሰኛል፡፡ የልሂቃን ፍልስፍናውን በሚመለከት ኦሩካ የሚከተለውን ጽፏል።
Philosophic sagacity, however, is often a product and a reflective reevaluation of the culture philosophy. The few sages who possess the philosophic inclination make a critical assessment of their culture and its underlying beliefs. Using the power of reason rather than the celebrated beliefs of the communal consensus and explanation, the sage philosopher produces a system within a system, and order within an order (Odera Oruka፣ 1991፡ 52)
ኦሩካ፣ ልክ እንደ ሆንቶንጅ እና ዊሬዱ ፍልስፍና ሉላዊና አመክንዮን መሠረት ያደረገ ዲሲፒሊን (critical enterprise) ነው የሚለውን ብያኔ ተጋሪ በመሆኑ መደቡ ከሉላዊያን ጎራ ነው፡፡ ይኸን ጉዳይ በተመለከተ ኢምቦ የሚከተለውን ጽፏል፣ “Odera Oruka’s universalist perspective challenges the ethnophilosophers and their claim that philosophy can be geographically unique or culture specific. Philosophy must be a personal, second-order activity that is universal in its methodology” (Imbo, 1998: 25).
እንደ ማጠቃለያ፣ ፍልስፍና በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኝ፣ በመልካም ምድር ያልተገደበ፣ ግላዊ አልያም የወል ንፅረተ ዓለም ነው፡፡ በእዚህም ምክንያት፣ የአፍሪካ ህዝቦች ከቀሪው ዓለም የተነጠሉ ስላልሆኑ የፍልስፍና ባሕላቸውን ጥያቄ ውስጥ መጣል ለትዝብት የሚዳርግ ተግባር ነው፡፡


Read 11246 times