Saturday, 12 February 2022 12:14

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለመከራ የጣፈን ሕዝብ ስለሆንን”
                          ሙሼ ሰሙ

             ከመረጋጋት ወደ ግጭት፣ ከግጭት ወደ ጦርነትና መተላለቅ ቀጥሎም ወደ ሀገር መፍረስ ለመሸጋገር የሚቆረጥልን ቀጠሮና የሚተነበይልን ትንቢት የለም፤ የሚወስነን ሰላም፣ ልማትንና እድገትን ለማስፈን የሚያስፈልገው እውቀት፣ ችሎታና አስተዋይነትም አይደለም። የሚያስፈልጉን ተራ ጨለምተኝነት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ጨካኝነት፣ ግራና ቀኙን አላይም፣ አልሰማምና አላስተውልም የሚል ግትርነት ብቻ ናቸው። እነሱ ደግሞ በገፍ እንዳሉን በተግባር እያየን ነው።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሰበብ አስባቡ፣ በየፈርጁና በየረድፉ እየተደራጁ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ዜጎችን መግደል፣ በገፍ ማጋዝና ማፈናቀል፣ እርስ በርስ ማጋጨት፣ የሃይማኖት ተቋማትን ማቃጠል፣ ሴቶችን መድፈር፣ ሕጻናትንና አረጋውያንን ማረድ፣ ሕዝብን በጅምላ ማዋረድና ማንኳሰስን ያካተተ የእርስ በርስ ግጭትና አስከፊ ጦርነት አስተናግደናል።
ከተሞክሮ እንደምንረዳው፣ ለመጨረሻው መጀመርያ እንዲሆነን የቀረን አንዱና አስፈሪ አጀንዳ ቢኖር የሀይማኖት ጦርነት ይመስለኛል። ለዚህም “የለውጡ ሐዋርያትን” “ተመስገን” እንበል መሰለኝ፣ እስከዛሬ በተዓምር የዘለለን “የሀይማኖት ጦርነት” ከወዲሁ ልብ እስካልገዛን ድረስ ወደፊት የማይቀርልን አስፈሪ እዳ እንደሆነ ፍንጮች እያየን ነው።
በጣት በሚቆጠሩ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከዓለም ሁሉ እጅግ አስከፊ የሆነውን ጦርነት፣ ማፈናቀል፣ ስደትና ማጋዝን አከናውነን፣ “እጃችንን አጨብጭበን በመቅረት ወጤታችን ስለ ሰመረ”፣ በረሃብተኛ መጠሪያችን ላይ “ጭካኔና ግፈኝነት” ታክሎበት ተጨማሪ እውቅና አግኝተን፣ በዓለም አቀፍ የቋንቋ ስርዓት ውስጥ እንደ አዲስ ተመዝግበናል።
ይህ ማለት ትርጉሙ ሌላ አይደለም፤ “ለመከራ የጣፈን ሕዝብ ስለሆንን”፣ ማፍራት የቻልነው የልማት፣ የሰላምና የእድገት ሃይል ሳይሆን በጭፍን ሴራ ታግዘው ግጭት፣ ጦርነት፣ ሁከት፣ ስደትና ማፈናቀልን ጠንስሰው መጋት የተካኑ ሰዎችን  ብቻ ነው።
በዚህ ሰሜንኛ ተረት እንለያይ፡-
አንዱ አርሶ አደር ለሌላው፤
“እንወራረድ ሞኝ ይረታል” ሲለው
“ምን ብሎ?” ቢለው
“እምቢ አልሰማም አላይም ብሎ” አለው ይባላል።


_________________________________________


               ይሄ ሁሉ ጣኦት
                    በእውቀቱ ስዩም

እናት ያበጀችው ከስጋዋ ከፍላ
ያንን ሁሉ ወጣት ፤ ያንን ጅምር አፍላ
በውነት በፍትህ ስም ፥ እየማሉ ከዱት
እንደ ፋሲካ በግ ፥ወደ ካራው ነዱት::
የቀኑ ቀውስነት፤ የሌለው አምሳያ
ዝናብ እንደፈታው ፥ የገጠር ገበያ
ዘመን ተዘባርቆ፥
አገር በግራጁ ፥ ከቀኝ ኪሱ ሰርቆ
ጉዳችን መች አልቆ!
ትናንት አለም አቀፍ ወዛደራዊነት
ዛሬ በየፈርጁ ፥ዘርማንዘራዊነት
ደሞ ያርማው ብዛት፥ የባንዲራው አይነት
ቢያመልኩት አይራራም፥ እጣን እያጨሱ
ሻማ እየለኮሱ
ይሄ ሁሉ ጣኦት፥ የሰው ደም ነው ምሱ፡፡


_____________________________________


                       መንግሥት ሆይ፣ ኢንዱስትሪውን ሳይወድቅ ታደገው!
                            Pace Negaa


            ዓለም በኢንዱስትሪ እየገፋ ነው። እኛስ? የእኛ ጉዞ እንኳ ወደ ኋላ ነው።
በቀደም ጥቃቅን የብሎኬት ፋብሪካና አነስተኛ የዶሮ እርባታ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሲመረቅ በቴሌቪዥን ዓይቼ ገረመኝ። ‘እንዴት እንደዚህ ውርድ አልን?’ ብዬ ደንግጫለሁ። ምክንያቱም የብሎኬት ማምረቻና አነስተኛ የዶሮ እርባታ መመረቅ ለክልል ፕሬዚዳንት ደረጃ አይመጥኑምና ነው።
እስኪ የሀገራችንን የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሁኔታ እንመልከት።
የተለያዩ ውብ አልባሳትን ለዓለም ገበያ ያቀርብ የነበረውና በርካታ ሠራተኞችን የያዘው ዓለምገና የሚገኘው Ayka Addis ለምን ተዘጋ? ሰበታ ዲማ የሚገኘው Saygin Dima ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለምን ተዘጋ? አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ለምን ተዘጋ? አቃቂ መለዋወጫ ለምን ተዘጋ? አቃቂ ቆርቆሮ ፋብሪካ ለምን ተዘጋ? ኦሪጅን ውሃ ለምን ተዘጋ? የአዲስ ሞጆ ዘይት የት አለ? የቸሬአሊያ ፓስታ የት አለ?
ሌሎችም ብዙ ኢንዱስትሪዎች ለምን ተዘጉ? ይህንን ችግር ፈትሾ የሚያስተካክለውስ ማን ነው?
አንድ ፋብሪካ ለመትከል ብዙ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል። መሳሪያዎቹን ተክሎ በአግባቡ አለማምረት ለባለቤቶቹ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ኪሳራ ነው። ፋብሪካ ሲዘጋ ብዙ ቀውስ ይፈጠራል። ሠራተኛው ከሥራ ይቀነሳል፣ ቤተሰቡ ይናጋል፣ የልጆች ደህንነት አደጋ ላይ ይወድቃል።
የፋብሪካዎች መዘጋት ሲደማመር ከባድ የሥራ አጥነት ቀውስ ይፈጥራል። ፋብሪካ ሲዘጋ የሙያ ችሎታ ይቀንሳል፣ ብቃት ያለው ሙያተኛ ወደሌላ ዘርፍ ሥራ ይቀይርና የሙያ ክህሎት ይዳከማል።
ፋብሪካ ሲዘጋ የአቅራቢዎች ሥራ ይቀንሳል ወይም ይዘጋል። ፋብሪካ ሲዘጋ የገበያ መቃወስ ይፈጠራል። ዘይት ፋብሪካ ሲዘጋ ዘይት ይወደዳል። ፓስታ ፋብሪካ ሲዘጋ ፓስታ ይወደዳል። ብረት ፋብሪካ ሲዘጋ ብረት ይወደዳል። በዚህ አገር እጥረት የሌለበት ምርት የለም። እንዲህ እጥረት ባለበት ሀገር አንድም ፋብሪካ ሊዘጋ ባልተገባ ነበር።
ነገር ግን በኤሌክትሪክ እጥረት፣ በጥሬ-ዕቃ ችግር፣ በመስሪያ ካፒታል እጥረት፣ በመለዋወጫ ችግር፣ በሙስና፣ በፀጥታ ችግርና በሙያተኛ ችግር ብዙ ፋብሪካዎች ተዘግተዋል፣ እየተዘጉም ነው። በዚህ ሁኔታ ገና ሌሎችም ይዘጋሉ።
የፋብሪካ መዘጋት ጦሱ ለብዙ ችግሮች መነሻ ነው። አሜሪካ ላይ ካሉት የመኪና አምራች ኩባንያዎች አንዱ የሆነውን Chrysler ኩባንያን የአሜሪካ መንግስት እንዴት ከመዘጋት እንደታደገው YouTube ላይ ተመልከቱ። ከቻላችሁም የLee Iacocaaን ኦቶባዮግራፊ አንብቡ። በነገራችን ላይ መጽሐፉን ማንበብ ማኔጅመንት መማር ማለት ነው።
በገንዘብ ችግር ሊዘጋ የደረሰውን የክራይስለር ሞተር ኩባንያን መንግስት በBailout እንዲያድነው በማግባባት፣ ሊ ያኮካ ኩባንያውን ታድጎታል። እንዲያ ነው መንግስት፣ እንዲያ ነው ማኔጀር።
ኢንቨስትመንት እየተዘጋ ኢንቨስተር መጥራትን የመሰለ እብደት የለም። መንግስት ሆይ፤ መጀመሪያ ያሉትን ችግሮች ፍታ፣ ፋብሪካዎቹ እንዲሠሩ አድርግ፣ ኢንዱስትሪዎቹን በአቅማቸው አሠራ።
አሁን እየሠሩ ካሉት ፋብሪካዎች ውስጥ ብዙዎቹ ከአቅማቸው ከግማሽ በታች እየሠሩ ነው። ሲሚንቶ ለምን ተወደደ? ብሎ የሚጠይቅ ካለ፣ ፋብሪካዎቹ የሚሠሩት ከአቅማቸው ግማሽ በታች በመሆኑ ነው። የምክንያቶቹ ዝርዝር ያው ከላይ የተጠቀሰው ነው። ታድያ ይህንን ችግር ማን ይፍታ?
የኢንቨስትመንት መ/ቤት? የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር? የገንዘብ ሚኒስቴር? ብሔራዊ ባንክ? የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር? የገቢዎች ሚኒስቴር? የኤሌክትሪክ አገልግሎት? ሀገር በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ ናት!
መቸም ይህንን እያየና እየሰማ ኢንቨስት የሚያደርግ ዳያስፖራ ይኖራል/አይኖርም ባይባልም፣ ኢንቨስት የሚያደርገው ግን ከባንክ ገንዘብ ለመበደር እንጂ ለመሥራት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ከእንግዲህ ይመለከተኛል የምትል የመ/ቤት ኃላፊ ሁላ፣ ወይ ፍረድ ወይ ውረድ ማለት ግድ ነው።
ጎበዝ፤ በሀገርና በትውልድ እድሜ አንቀልድ!

___________________________________

                     የሰንበት ትዝታዎች
                        በእውቀቱ ስዩም


             ለመጀመርያ ጊዜ ሲኒማ የገባሁት አስራአንደኛ ክፍል ሳለሁ ይመስለኛል፤ እሁድ ቀን ደብረማርቆስ ውስጥ ነው፤ ብቸኛው ሲኒማ ቤት ተከፍቶ ካስራምስት የማንበልጥ ሰዎች ታድመናል፡፡ ፊልሙን በቴክኒክ የሚቆጣጠረው ሰውዬ፣ የጤና እህል ማለቴ እክል ገጥሞት አልመጣም፤ ስለዚህ፥ የሲኒማ ቤቱ ዘበኛ ጋሽ ይትባረክ ሰውየውን ተክተው ለመስራት ወሰኑ፤ ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ በጊዜው የነበረው የፊልም ፕሮጀክተር ከገጠር ወፍጮ ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ ከዚያ ውስጥ የባውዛ መብራት የሚመስል ነገር እንደዚህ እየተመዘዘ ይወጣና ግድግዳው ላይ ተአምር ይሰራል፡፡ ያን ቀን፥ ጋሽ ይባረክ ያለሙያቸው ያልሆነ ነገር ሲነካኩ ምን የመሰለውን የህንድ ፊልም ባፍጢሙ ዘቅዝቀው ማሳየት ጀመሩ፤ እነ አሚታብ ፥እነ ኩማር፥ እግራቸው ወደ ጣራው ተሰቅሎ፥ አናታቸው ወደ ምድር ተዘቅዝቆ ግድግዳው ላይ ውርውር ይላሉ፡፡ ታዳሚው ‘የዛሬው ፊልም ደሞ ካቀራረቡ ጀምሮ ለየት ያለ ነው” ብሎ በጽሞና መከታተሉን ቀጠለ፡፡ እኔ የሆነ ችግር እንዳለ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም፤ እልል ያልሁ አይናፋር ስለነበርሁ ደፍሬ ለመናገር አልቻልኩም፤ ቢቸግረኝ አጠገቤ ያለውን አብሮአደጌን አንተነህ ይግዛውን በክርኔ ጉስም አደረኩትና፤ “ እረ ባብማይቱ ይህን ነገር አንድ እንዲሉት ንገራቸው” ብየ አንሾካሾክሁ፤
አንተነህ በታላቅ ደምጽ፤ #ጋሽ ይትባረክ” ብሎ ተጣራ፤
“ምናባህ ሆንህ?” አሉ ጋሽ ይትባክ፥
“ትንሽ ድምጽ ይጨምሩበት! ድምጽ ይጎድለዋል”
ቆይቶ ቆይቶ ዘመን አልፎ ዘመን መጥቶ፣ የሆነ ሰንበት ላይ አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ወደሚገኘው ሚውዝየም ከባልንጀራዬ ጋራ ጎራ አልሁ፡፡ አስጎብኚው ድብርት የጎበኛቸው ሽማግሌ ናቸው፤ አንዱን ጦርና ጋሻ የተሰቀለበት የግድግዳ መአዘን ተደግፈው ሲያንጎላጁ አገኘናቸው ፤ ከዛ ኮሌታቸውን ይዘን ቀስቅሰናቸው ስናበቃ ጉብኝቱ ተጀመረ፤
“ይሄ የንጉሱ አልጋ ነው” አሉን፤
“የትኛው ንጉስ?”
“እሱን እንግዲህ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የወርድና የቁመቱን ሰብሰብ ማለት በማየት የቀዳማዊ ሀይለስላሴ መሆኑን መገመት ይቻላል” ሲሉ መለሱ፤
ከጥቂት ቆይታ በሁዋላ አንዱ ክፍል ውስጥ ደርሰናል፤
“እስቲ ስለዚህ ወንበር ይንገሩን?” አላቸው ባልንጀሬ፤
“ይሄ ወንበር!? ይሄ ወንበርማ እንግዲህ እንደምታዩት አራት እግር አለው፤ ሙሉ በሙሉ ከንጹህ ቀርቀሀ የተሰራ ነው”
አስጎብኛችን ስለ ወንበሩ በረጃጅም ሳሎች የታጀበ የአርባ ደቂቃ ገለጻ አደረጉልን፥
“ምን ያህል እድሜ አስቆጥሯል ?” ስላቸው፥
“ከተገዛልኝ ሳምንት አልሞላውም! አስጎብኝቼ ሲደክመኝ አረፍ እልበታለሁ፡፡”

______________________________________
                      ኑ! አማርኛን እናጥፋ!
                             ዩኑስ ናሲር

              አንድ በጣም የሚያስቀኝ ነገር አለ። የብዙዎቹ የአውሮፓ ሃገራት (ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ወዘተ...) ኮንሰርቫቲቭ ፖለቲከኞችና ቀላል የማይባለው ሰው የእንግሊዝኛ ቋንቋን ይጠየፋል። ይሄ በግሌ በተለያየ አጋጣሚ ያየሁት ነው። ቢችሉ እንግሊዝኛን ከሃገራቸው ከነስሩ መንቀል ይፈልጋሉ። ነገር ግን አልቻሉም!
ከብዙ ኢንቨስትመንትና የብሔርተኝነት ፕሮሞሽን በኋላም አውሮፓ ውስጥ እንግሊዝኛ በመኮሰስ ፋንታ እየፋፋ፣ አሁን አብዛኛው ከተሜ ህዝባቸው እንግሊዝኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋው የመጠቀም ደረጃ ላይ ደርሷል።
እንግሊዝኛ አልችልም ያለኝ ጀርመናዊ እንግሊዝኛውን ከእኔ በላይ አቀላጥፎ ሲናገር፣ እንግሊዞችን የምትጠየፍ ፈረንሳዊት የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተርጓሚ ሆና ተመድባልኝ ገጥሞኛል። የእንጀራ ነገር! በጣም የሚገርመው፦ አስተርጓሚ የሚመደበው ለወጉ ነው እንጂ በስራ አጋጣሚ ያገኘኋቸው ጀርመናዊያን፣ ፈረንሳዊያን፣ ጣሊያናውያን፣ በሙሉ እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። አውሮፓውያን ከሀገራቸው ውጪ ቢዝነስ ለመስራት ሲወጡ እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ተሰናብታም የህብረቱ ዋና ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው።
በአንድ ወቅት ከቻይናውያን ጋር ስንደራደር፣ የድርድሩ ቡድን መሪ እንግሊዝኛ እንደማይችል ተናግሮ በቻይንኛ እየተናገረ በአስተርጓሚ በኩል እየተደራደርን ለሁለት ሳምንታት ያህል ከቆየን በኋላ ወደ ቁልፍ የድርድር ነጥብ ስንገባ አስተርጓሚውን “በቃህ! ከዚህ በኋላ እኔ በቀጥታ እናገራለሁ” ብሎ በጠራ እንግሊዝኛ መናገር ሲጀምር ደንግጠናል። ከዚያ ቀን በኋላ የነበረውን ድርድር ያለ አስተርጓሚ ቀጥለናል።
ቋንቋ ላይ ያለው ፖለቲካ በአብዛኛው ውሸት ነው። ሂፖክረሲ - አስመሳይነት ይበዛዋል። የማይሰራ የከሸፈ ማስመሰል ነው። “አውሮፓውያን እንግሊዝኛን እንዲህ ተጠይፈውትም ሊያጠፉት ያልቻሉት ለምንድን ነው?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
እንግሊዝኛ የዓለም ቋንቋ ነው። የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ማሳለጫ ፣ የንግድ ማካሄጃ ቋንቋ ነው። ዓለም አቀፍ ውሎች የሚረቀቁት በእንግሊዝኛ ነው። እንግሊዝኛ የሳይንስና ምርምር ቋንቋ ነው። አሁን እንግሊዝኛ የእንግሊዞች ቋንቋ አይደለም። እንግሊዞችን ስለጠላህ እንግሊዝኛን ልታጠፋው አትችልም። የዓለም ህዝቦች የጋራ ቋንቋ ነው።
***
ወደ እኛም ሃገር ስንመጣ አማርኛ የሃገራችን የስራ፣ የትምህርት፣ የገበያና የማህበራዊ ግንኙነት ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከዳር አስተሳስሮ ያያያዘን አማርኛ ነው። ዛሬ አማርኛ የአማሮች ቋንቋ ብቻ አይደለም። ከአማራ ጋር ያለህን ፖለቲካ እዚያው አማራው ጋር ጨርስ። ነገር ግን ለአማራ ያለህን ጥላቻ በአማርኛ በኩል አታምጣው። አማርኛን ማጥፋት ብትፈልግም አትችልም። በአሁን ሰዓት አማርኛ ከአማራ ውጪ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች የአፍ መፍቻ ቋንቋም ጭምር ነው። ቋንቋ መግባቢያ ነው። የፖለቲካ ስሜትህን መወጫ scapegoat ልታደርገው አትችልም። አሁንም የሚያስቀኝ፦ አንዳንድ ሰዎች ለአማርኛ ቋንቋ ያላቸውን ጥላቻ በአማርኛ የሚገልፁት ነገር ነው። አየህ! የቋንቋ ኃይል! ሳትፈልገው እንድትጠቀመው ያስገድድሃል። ጠልተኸው ትፅፍበታለህ። ፌስቡክ ላይ ለቅልቀህ ላይክ ትለቅምበታለህ፣ በዩቲዩብ ለፍልፈህ ትሸቅልበታለህ።
ሃገራችን ቢያንስ አንድ ወይም ከዚያም በላይ ከዳር እስከዳር የምንግባባበት ቋንቋ ያስፈልጋታል። በታሪክ አጋጣሚ ደግሞ አማርኛ ይህን እድል አግኝቷል። አማርኛ የረጅም ዘመን የስነፅሑፍ ታሪክ ያለው፣ በግእዝ ፊደል የሚፃፍ፣ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ተዋውሶ የዳበረ፣ በመላ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ብዙ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ በመሆኑ ለወደፊቱም ቢሆን የሃገሪቱ የጋራ ቋንቋ ሆኖ እንደሚቀጥል መካድ አይቻልም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ቋንቋ እየተማረና በዚሁ እየተግባባ መሄድ አለበት።
ሁሉም ክልል አማርኛን እየገፋ በብሔሬ ቋንቋ ብቻ ነው የምጠቀመው ማለት የቋንቋ አፓርታይድን ለማስፈን ከመሞከር ተለይቶ አይታይም።
በቋንቋ የማይግባባ ማህበረሰብ እንዴት አብሮ መኖር ይቻለዋል? መጤ ተብሎ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ እየተገፋ ያለው ህዝብ ቢያንስ በህይወት የመኖር ዋስትና እንዲኖረው አንድ ቁልፍ መሣሪያ የሆነውን ቋንቋ እንዳይጠቀም እንቅፋት ማብዛት ነውር ነው።
ሀኪም ፈልጎ ሆስፒታል የመጣን በሽተኛ "የብሔሩን ቋንቋ ካልቻልክ አትታከምም" ከማለት በላይ ዘረኝነት የለም። እንደ ቀልድ “ሱቅ መጥተው በብሔሩ ቋንቋ ካልጠየቁ አትሽጡላቸው፣ ቋንቋችሁን ከማይናገር ሰው ጋር አትጋቡ፣ ቋንቋችንን ካልተናገራችሁ ወደ ክልላችን አትምጡ፣ ማን ጠራችሁ፣ ወዘተ...” የሚሉ የዘረኝነት ቀንዘሎች እዚህም እዚያም ሲያቆጠቁጡ እያየን ነው።
አብዛኛው በሰለጠነ አማርኛ የሚፖተልከውም ሆነ ፌስቡክ ላይ እየፃፈ አማርኛን ለማጥፋት የሚታትረው አክቲቪስት ትንሽ ቆም ብሎ የሚሰራውን ማየት አለበት። አማርኛዋ ከመጥፋቷ በፊት የኛን ማህበራዊ ግንኙነት በጣጥሳ እንዳትለያየን እንጠንቀቅ።
________________________________________

                     “መንሱሪዝም Vs. ኤርሚይዝም”
                              ጠይም ጽጌረዳ ጎንፋ

                ሁለቱም ባለሐብቶች ናቸው! መንሱሪዝም ውድ ውድ ሆቴሎች በቀን ሶስቴ ይበላል። በአንፃሩ ኤርሚይዝም በ24 ሰአት አንዴ ራሱ በትእዛዝ ያሰራውን ምግብ ብቻ ይበላል።
መንሱሪዝም የሚበላውንና የሚጠጣውን ፎቶ እያነሳ ዛሬ ምን በላችሁ?...ብሎ የሚጠይቅ ግሩፕ ላይ ይለጥፋል። ኤርሚይዝም በቀን አንዴ ተመጋቢዎች ላይ እንኳ እንዳይለጥፍ ማህበራዊ ሚዲያ አይጠቀምም፡፡ የሚበላው ነገርም ሲያዩት የሚያምርና የሚያስጎመዥ አይመስልም። መንሱሪዝም ውድ ሽቶ ይቀባል፤ ከንፈሩን አሁንም አሁንም በምራቁ ያረጥባል። ኤርሚይዝም በቀን 4 ሊትር ውሃ ስለሚጠጣ ረዥም ሰአት ቢያወራም ከንፈሩ አይደርቅም።
መንሱሪዝም ሮሌክስ ውድ ሰአት ያስራል፤ እድሜውን ግን 30+ ብሎ ያድበሰብሳል እንጂ እቅጩን አይናገርም። ኤርሚይዝም ያለ አላርም ይነቃል። እንደነቃ ብርሃን ያያል፤ 67 አመት ሆነኝ ብሎ አፉን ሞልቶ ይናገራል።
የመንሱሪዝም ጣት ውድ የዳይመንድ ቀለበት አጥልቋል፤ በኤርሚይዝም እጅ የብረት ካቴና ጠልቆ ነበር።
መንሱሪዝም ለመጀመሪያ ጊዜ ጫማ ያጠለቀው በ17 አመቱ ነው። ኤርሚይዝም በ6 አመቱ ፎቶግራፍ ነበረው። መንሱሪዝም ፀጉሩን በውድ ሻምፖና ቅባት ይንከባከበዋል፤ ኤርሚይዝም መላጣ ነው።
መንሱሪዝም ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር “እስከ መተቃቀፍ የደረሰ” ፎቶ አለው። እንደውም ከ10 አመት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር እሆናለሁ ይላል፡፡ ኤርሚይዝም አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር አግኝቷቸውም አያውቅ።
መንሱሪዝም ባንክ ይጠቀማል። ኤርሚይዝም ባንክ ይመሰርታል። መንሱሪዝም ኢንዶኔዥያ 7 አመት ቆይቷል። ኤርሚይዝም ከ20 አመታት በላይ በአሜሪካ ኖሮ ግሪን ካርዳቸውን መልሶ ነው የመጣው።
ለወጣቶች “ምን ልስራ?” ጥያቄ መንሱሪዝም ብር ይሰጣል፤ ኤርሚይዝም ሐሳብ ይሰጣል።
መንሱሪዝም ውድ መኪና ይነዳል። መንገድ ግን የሚያውቅ አይመስለኝም። “አይሱዙ” ለማለት “አይዙዙ” ይላል። ኤርሚይዝም ቦሌ መንገድ አስፓልት ሳይነጠፍበት አቧራ እያለ ሞተር ሳይክል ተለማምዶበታል።

________________________________________


                    "አባ እንሂድ"
                          ታሪክ አሳታሚ/Tarik Publishers

            የዚህ ሰውዬ አድናቂ ነኝ፤ደሞዝ ጎሽሜ ይባላል። ደራሲ ነው፤ የታሪክ ድርሳናትን እያገላበጠ፣ ከራሱ እሳቤ ጋር በማዛመድ የሚያካፍል፣ ከሰሩት በላይ በዝና ሰክረው እንደሚፋንኑት እንዳብዛኛዎቹ የሃገራችን ዝነኞች፣ እዩኝ እዩኝ የማይል፣ ድምጹን አጥፍቶ ስራውን የሚከውን ምርጥ ተዋናይ ነው። (ፈላስፋ በሉት)
በሰራቸው ስራዎች ላይ ሁሉ መስሎ ሳይሆን ሆኖ በመተወን ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል። ለኔ ይህ ሰው በጦቢያ ምድር ከተፈጠሩ ተዋናዮች ከዋንኞቹ መሃከል ነው።
ደሞዝ ጎሽሜ እስካሁን "አስራ ስድስት" እና "ሶስተኛው ኪዳን" የሚል እስ ያላቸው መፅሐፍትን ለአንባቢ ያቀረበ ሲሆን፤በ DSTV አቦል ቻናል ላይ "አስኳላ" የሚል ተከታታይ ድራማ ላይና በተለያዩ ፊልሞችና ድራማዎች ላይ ይሳተፋል። ለዛሬ "ሶስተኛው ኪዳን" በተሰኘ መፅሐፉ ላይ ስለሚገኙት፣ መልካምነታቸው መልካም ቦታ ስላደረሳቸው፣ ስለ አባ እንሂድ ከተጻፈው ቁምነገር ይህችን ወሰድን፡-
ሰውየው አባ እንሂድ ይባላሉ። በሚኖሩበት መንደር ሰው በመርዳት ይታወቃሉ፤ ሰዎች ወደ ወንዝ ሲወርዱ ካዩ “ወዴት ትሄዳላችሁ?” ይላሉ።
“ውሃ ልንቀዳ” ይመልሱላቸዋል፡፡
"እንሂዳ!" ይሉና አብረዋቸው ይቀዳሉ። በሌላ ጊዜም፤
“ወዴት ትሄዳላችሁ ? “
“እንጨት ለቀማ “
“እንሂዳ ! “
ሲለቅሙ ውለው ይገባሉ።
በዚህ ሁኔታ እየኖሩ ሳለ አንድ ቀን ቅዱስ ሚካኤል በሰው ተመስሎ ከመንገድ ያገኙታል።
“ወዴት ትሄዳለህ ? “ አሉት
“ወደ ገነት “
“እንሂዳ! “
ሄዱ፤ አልተመለሱም!

Read 1856 times