Saturday, 12 February 2022 12:32

ግሪን ቴክ አፍሪካ በኤሌክትሪክና በጸሐይ የሚሰሩ መኪኖችን ለገበያ ሊያቀርብ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በታዳሽ የሃይል ምንጮችና ቴክኖሎጂዎች ዘርፍ የተሰማራው ግሪን ቴክ አፍሪካ የተባለ ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክና በጸሐይ ብርሃን ሃይል የሚሰሩና በአይነታቸው ለአገሪቱ አዲስ የሆኑ የተለያዩ አይነት ዘመናዊ መኪኖችን በቅርቡ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
ግሪን ቴክ አፍሪካ በቅርቡ ለገበያ የሚያቀርባቸውን 6 አይነት ሞዴል ያላቸው መኪኖቹን ከትናንት በስቲያ ማለዳ ለመገናኛ ብዙሃን ባስተዋወቀበት መርሃ ግብር ላይ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍፁም ደሬሳ እንደተናገሩት፣ በኤሌክትሪክና በጸሃይ ብርሃን ሃይል የሚሰሩት እነዚህ መኪኖች ለነዳጅ፣ መለዋወጫና ጥገና ከሚውል ወጪ የሚገላግሉ ሲሆን፣ በዋናነት የቀረቡትም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰቡ ክፍሎች ነው፡፡
ኩባንያው በአለም ላይ በኤሌክትሪክ መኪና አምራችነታቸው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ከያዙ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር በፈጠረው አጋርነት የሚያስመጣቸው እነዚሁ መኪኖች፤ በአውሮፓ የጥራት ደረጃ የተመረቱና አገሪቱ ከምትከተለው የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ ጋር የሚጣጣሙ ሲሆኑ፣ ከነዳጅ ተጠቃሚ መኪኖች ጋር ሲነጻጸር፣ እጅግ አነስተኛ በሆነ ወጪ በቤት ውስጥና በቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት የኤሌክትሪክ ሃይል እየተሞሉ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉ መሆናቸውም ተነግሯል።
ግሪን ቴክ አፍሪካ የስራ ፈጠራን ለማበረታት፣ ተጠቃሚዎችን ትርፋማ ለማድረግና በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል አሰራር ቀይሶ ከሚንቀሳቀሰው እህት ኩባንያው ግሪን ትራንስፖርት ጋር በመተባበር ለአገሪቱ አዲስ የሆኑ እና ለማህበረሰቡ የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክና በሶላር ቻርጅ የሚሰሩ የተለያዩ አይነት መኪኖችን  ለገበያ እንደሚያቀርብም ኢንጂነር ፍፁም ደሬሳ ተናግረዋል፡፡
ግሪን ትራንስፖርት ለገበያ የሚያቀርባቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለከተማ ታክሲ አገልግሎት የሚውሉ 5 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው፣ 23 ሰው መጫን አቅም ያላቸው መካከለኛ አውቶብሶች፣ ፒክአፕ እና አገር አቋራጭ አውቶብሶች ሲሆኑ፣ ኩባንያው ከአፍሪካ ቪሌጅ ማይክሮ ፋይናንስ እና ከሌሎች ባንኮች ጋር በመተባበር መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ብድር የሚያገኙበትንና የመኪና ባለቤት ሆነው የተሻለ ገቢ በማግኘት ህይወታቸውን የሚቀይሩበትን አዲስ አሰራር መቀየሱም ተነግሯል፡፡
ግሪን ቴክ አፍሪካ በቅርቡ የኤሌክትሪክ መኪኖቹን በአገር ውስጥ በራሱ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ እየገጣጠመ ለገበያ ማቅረብ እንደሚጀምር የተነገረ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ መኪኖች በነዳጅ ከሚሰሩ ተሽከርካሪዎች አንጻር ምንም የጥገናና የመለዋወጫ ወጪ ባይኖርባቸውም፣ ኩባንያው ለአጋር ደንበኞቹ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተስማሚና ምቹ የጥገና እና የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላትን በስፋት እንደሚያቋቁምም ተገልጧል፡፡


Read 1377 times