Monday, 14 February 2022 00:00

“ለዛውም ሩቅ ናት፤ ደሞም መራራ ናት” አለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ለአቅመ -ሄዋን የደረሰች የደረሰች ሴት ልጅ የነበረቻቸው እናትና አባት በአንዲት መንደር ይኖሩ ነበር፡፡ ልጅቱ ከቀን ቀን እየወፈረች ሆዷ እየሞላ ትሄዳለች፡፡ የመንደሩ ሰው ሊጠይቃቸው ሲመጣ ጥያቄው አንድ ዓይነት ሆነ፡፡
አንዷ ትመጣና፤ “እንዴት ዋላችሁ?”
“ደህና እግዚሃር ይመስገን”
“ጤናዎትን እንዴት ከረሙ?”
“አልፎ አልፎ ይጫጫነኝና እተኛለሁ እንጂ ብዙውን ጊዜ ተመስገን ነው፤ ጤናዬን ደህና ነኝ”
እንግዳዋ ትንሽ ታመነታና፤ “እንደው የዚች የልጅዎ ነገር እንዴት ነው?”
እናትየው እንዳላወቀ ሆነው፤ “ምኗ?”
“እንዲያው አወፋፈሯ የጤና ነው ይላሉ?”
“አይ እንዲሁ የልጅ ገላ ሆኖ ባንዴ ወፍራ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤ “እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላማረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤ “እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላመረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
እንዲህ በተከታታይ ሲመልሱ፣ ለመጣው ሁሉ የልጅ ገላ ነው ሲሉ፤ እዳር ሆነው የሚያስተውሉት አባት በመጨረሻ ተነፈሱ፤ “እናንተ ይሄን ያህል ምን አስጨነቃችሁ? የምግብም ከሆነ ሲቀንስ እናየዋለን፡፡ የልጅም ከሆነ ሲገፋ እናገኘዋለን!” አሉና ገላገሏቸው፡፡
* * *
“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደማለት ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር መደበቅ፣ መሸፋፈኑ አይጠቅምም - ሁሉንም ጊዜ ይገልጠዋልና፡፡ ግልፅነት ዛሬ ወቅታዊ ወረት (fashion) የሆነ ይመስላል፡፡ ስንቶች በአደባባይ እየተናገሩ ጓዳ ጓዳውን ግን የልባቸውን እንደሚሰሩ ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ They shout at most against the vices they themselves are gulity of ይላሉ ፈረንጆች፡፡ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ” እንደምንለው መሆኑ ነው በአማርኛ። ስለመልካም አስተዳደር ያወራሉ። ግን መልካም አያስተዳድሩም፡፡ ስለፍትህ ያወራሉ ግና የህግን መርህ አይከተሉም። ስለዲሞክራሲ ይናገራሉ፡፡ ግን ዲሞክራት አይደሉም፡፡ ስለእኩልነት ያወራሉ ግን ወግነው ሰው ይበድላሉ፡፡ በእኩል አያኖሩም፡፡ ስለ እጅ ንፅህና ያወራሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ከሙስና የፀዱ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ግልፅነትን እንደሽፋን ነው የሚጠቀሙበት፡፡ ከእነሱ ጋር መከራከር ከንቱ ነው፡፡ አንድም “ዜጋና ሹም ተሟግቶ ደንጊያና ቅል ተላግቶ” ነው፡፡ አንድም ደግሞ ማርክ ትዌይን፤- “ከደደብ ሰዎች ጋር አትከራከር፡፡ ወደ እነሱ ደረጃ ያወርዱህና በልምዳቸው ያሸንፉሃል” የሚለን ለዚህ ነው፡፡ (Don’t argue with stupid people, they will drag you down to their level and then beat you with experience) በትክክለኛው ሜዳ ተጫወት እንደማለት ነው፡፡
ብልህነት የሌለበት ግጭት ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ “ተምረህ ተምረህ ደንቆሮ ሆነሃል” ይላሉ መንግሥቱ ለማ፡፡ በዚያው ጽሑፋቸው:- “አንድ ዓለም ተሰጠ ለአዳም ለሄዋን ለሁለቱ፤
ተረቱ እንደሚነግረን …ምንስ ልጆቻቸው ቢረቡስ ቢራቡ
ጥቂቶቹ ጠግበው ብዙዎች ይራቡ ጥቂቶች ሲያምራቸው ያንሱ ጦርነት
ብዙዎችም ይሂዱ ለመሞት ለዕልቂት!” ይላሉ፡፡
ስለ ብዙኃኑ እናስብ ዘንድ ማስገንዘባቸው ነው፡፡ ጥቂቶች በሀብት የናጠጡበት፤ ብዙሃን ይልሱት ይቀምሱት ያጡበት ሥርዓት መቼም በጅቶን አያውቅም፡፡ የናጠጡት የበደሉ የማይመስላቸው ሲሆን ደግሞ የባሰ መደናቆር ነው፡፡ ዳቦው ሳይኖር ለሰልፉ ሲሉ ብቻ ይሰለፉ ነበር እንደሚባሉት ምስኪን ሩሲያውያን እንዳንሆን መጠንቀቅም ብልህነት ነው፡፡ ለአገራዊ ምክክር ዝግጅት እየተደረገበት ባለበት ባሁኑ ሰዓት፣ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከወዲሁ ራሳቸውን ለውዝግብና ለንትርክ እያዘጋጁ ያሉ ይመስላል።   ወደ ምክክር ጠረጴዛው ከመደረሱ በፊት ብዙ እንቅፋቶች፣ ብዙ መሰናክሎች፣ ብዙ ፈተናዎች፣ ብዙ ውጣ ውረዶች፣ ብዙ አለመግባባቶች --- እንደሚከሰቱ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡ ለሁሉም ግን ሆደ ሰፊነትና ልበ ቀናነት ያስፈልጋል፡፡ ከግል ጥቅም ይልቅ የሕዝቡንና የአገር ጥቅም ማስቀደም ይገባል፡፡ በአገራዊ ምክክሩ አሸናፊና ተሸናፊ የምንጠብቅ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ዓላማው ተፎካክሮ ማሸነፍና መሸነፍ አይደለም። ተነጋግሮ መግባባት ነው፡፡ አንዳንዶች ከአገራዊ ምክክሩ እነሱ የሚፈልጉት ዓይነት ድል የማያገኙ መስሎ ከታያቸው ማጥላላትና ማጠልሸት መጀመራቸው አይቀርም፡፡ የጀመሩም አሉ፡፡ ነገራችን ሁሉ -- ድል እንደ ዛፉ ብስል ፍሬ ስትርቅ፤ ቀበሮዋ ዘላ ዘላ ፍሬዋን መያዝና ማውረድ ሲያቅታት፤ “ለዛውም ሩቅ ናት፤ ደሞም መራራ ናት” አለች እንደተባለው እንዳይሆን፣ ቆም ብሎ ማሰብ ለሁላችንም ይበጀናል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!!

Read 2912 times