Monday, 21 February 2022 00:00

ዋና አሰልጣኝ ውበቱ ከዋልያዎቹ ጋር ይቆያሉ!?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ‹‹አዲስ አሰልጣኝ ማምጣት ብሄራዊ ቡድኑን አይለውጥም›› - ፌደሬሽኑ


            የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና አሰልጣኙን በማሰናበትና በምትኩ አዲስ በማምጣት ብሔራዊ ቡድን አይለውጥም በሚል አቋሙን ከመግለፁም በላይ ፤ በሃላፊነቱ ለመቆየት በፈረሙት የኮንትራት ውል ላይ ሰባት ወራት እንደሚቀራቸው አስታውቋል፡፡ ከወር በኋላም ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድር የሚያግዛቸውን የወዳጅነት ጨዋታ ፌደሬሽኑ እንደሚያዘጋጅላቸው ገልጿል፡፡
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከምድብ  የማለፍን እቅድ ይዘው ከቡድናቸው ጋር የመጀመርያው ተሰናባች የነበሩት አሰልጣኙ በደካማው ውጤታቸው ላይ ይቅርታ ሳይጠይቁ በሃላፊነቱ ላይ መቀጠላቸው ብዙዎችን አላስደሰተም፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ የሚዲያ ተቋማት፤ የስፖርት ባለሙያዎች፤ ደጋፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዋና አሠልጣኙ ሃላፊነት ዙርያ የተለያዩ ትችቶችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ዋልያዎቹ የነበራቸውን ጠንካራ የቡድን ስብስብ በመጠቀም  በአፍሪካ ዋንጫው ላይ የተሻለ ውጤት ያልተመዘገበው በዋና አሰልጣኙ ብቃት ማነስ መሆኑን የሚገልፁ አስተያየቶች፤ በተጫዋቾች የአሠላለፍ ውሳኔ ላይ የታዩት ችግሮች፤ ቡድኑ  በኳስ አደረጃጀት ያለበትን ድክመት  እንዲሁም ኳሶቹን ወደ ኋላ መመለስ የሚያበዛበት አጨዋወቱ ላይ ለውጥ ማድረግ አለመቻላቸውን ሲተቹ ሰንብተዋል፡፡ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በየወሩ በሚያወጣው ደረጃ  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ1081 ነጥብ 138ኛ ላይ ሲሆን፤ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ለመጨረሻው ዙር ባለመብቃቱ እና በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያስመዘገበው ደካማ ውጤት ከደረጃው አውርዶታል፡፡
ካሜሮን ባስተናገደችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ከካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ዋልያዎቹ ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ዙርያ ዋና አሠልጣኙ ያቀረቡትን ሪፖርት ከሰሞኑ ፌደሬሽኑ እንደገመገመው ታውቋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ የያዘውን እቅድ ባለማሳካቱ ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያውያንን በይፋ ይቅርታ ቢጠይቅም ዋና አሰልጣኙ ግን በተመሳሳይ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው  ለደካማ ውጤታቸው የተለያዩ ሰበቦችን እየደረደሩ ቀጥለዋል፡፡ ለፌደሬሽኑ ባቀረቡት ሪፖርት ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት በቂ የወዳጅነት ጨዋታ አለማግኘታቸው፤ ካሜሮን ላይ ብዙ ተጨዋቾች በኮቪድ-19 ምክንያት ተሟልተው ልምምድ አለመስራታቸው ተፅእኖ ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡ የክለቦች መዋቀራዊ ችግር፣ የተጫዋቾች ልምድ ማጣት፤ የሊጉ ኋላ ቀር መሆንና የተጋጣሚ ቡድኖች ወቅታዊ አቋም የተሻለ ስለነበር በውድድሩ መቆየት አልቻልንም የሚሉ ምክንያቶችንም ዘርዝረዋል፡፡ በሌላ በኩል  በካሜሩን ስለነበራቸው ቆይታ ከቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ 16 ክለቦች ጋር  በድሬዳዋ በተደረገው ውይይት ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው በነበረበት የአካል ብቃትና ቴክኒካዊ ችግሮች  እንዲሁም ክለቦችም በጋራ መሥራት ያሉባቸው ሁኔታዎች ተነስተዋል፡፡ በአክሲዮን ማኅበር ከተደራጁ ሁለት ዓመት የሆናቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በቀጣይ ዘመናዊ አደረጃጀትን መከተል እንደሚገባቸው ያመለከተው ፌደሬሽኑ በኩባንያው አስተዳደር ውስጥ እየተወዳደሩ ለመቆየት ሁሉም ክለቦች የራሳቸው ቢሮ፣ ኦዲተር፣ የፋይናንስ ባለሙያና ሌሎች መሠረታዊ የተቋም መገለጫዎችን በማሟላት በአዲስ የአደረጃጀትና መዋቅር እንዲሰሩ አሳስቧል። ክለቦች  በአደረጃጀታቸው ውስጥ የተጫዋቾችን አካላዊ ብቃት እንዲሁም የአመጋገብ ሥርዓትን የሚከታተሉ ባለሙያዎች በቡድን ውስጥ ማካተት እንደሚያስፈልጋቸውም መክሯል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከአሰልጣኙ ሪፖርት ካደረገው ግምገማ በመነሳት እና ከቤትኪንግ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ጋር ያደረገውን ውይይት መነሻ በማድረግ ብሄራዊ ቡድኑ ወደፊት የሚጓዝባቸውን  አቅጣጫዎች እንዳስቀመጠ ተወስቷል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ2023 እኤአ ላይ የአፍሪካ ዋንጫን በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት እንደሚያካሂድ የሚታወቅ ሲሆን ዋልያዎቹ በቅርቡ የሚገቡበት አህጉራዊ ውድድር ነው፡፡  ወደ 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ለማለፍ የሚደረገው ፉክክር በቅድመ ማጣርያ መጋቢት አጋማሽ ላይ የሚጀመር ሲሆን  ኢትዮጵያ የለችበትም፡፡ምክንያቱም በቅድመ ማጣርያው የሚሰለፉት በወቅታዊ ደረጃቸው  ከ43 እስከ 54ኛ ላይ የሰፈሩት 12 ብሄራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ ከ1­ እስከ 42ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ግን በቀጥታ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ40ኛ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ የምድብ ማጣርያው ላይ መሳተፍ ይችላል፡፡  
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳተፉት 24 አገራት መካከል 15ቱ ብሄራዊ ቡድኖች የአገራቸውን ተወላጅ በዋና አሰልጣኝነት ቀጥረው ማሰራታቸው ልዩ ክስተት ሆኖ ተዘግቧል፡፡ 33ኛው አፍሪካ ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት  ከ4 ብሄራዊ ቡድኖች ሞውሪታኒያ፤ ጊኒ፤ ሱዳንና ናይጄያ ከአገራቸው ውጭ የቀጠሯቸውን ዋና አሰልጣኞችን አባርረው ነበር፡፡ ከውድድሩ በኋላ ደግሞ ጋና ሰርቢያዊውን አሰልጣኝ ሚሉቫን ራጄቪች ከምድብ በመሰናበታቸው፤ ቱኒዚያዊው ዋንድሜሄት ካቢሌር ከካርታጌ ንስሮች ከሩብ ፍፃሜ ማለፍ ባለመቻላቸው፤  የቡርኪናፋሶው ማሉ ካማዎ ከፈረሰኞቹ ጋር በ4ኛ ደረጃ ከጨረሱ በኋላ፤ እንዲሁም ናይጄርያዊው ኦገስቲን ኦጉቬን በጥሎማልፍ በመውደቁ ከየሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የአገራቸውን ተወላጅ ዋና አሰልጣኝ አድርገው ከቀረቡትና ከተለያዩ የውጭ አገራት አሰልጣኞችን በከፍተኛ ደሞዝ ከቀጠሩት ብሄራዊ ቡድኖች  የትኞቹ የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል የሚለው አጀንዳ  አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውና 9 የተለያዩ የአፍሪካ ቡድኖችን ያሰለጠኑት ፈረንሳዊው ክላውድ ዲለሮይ ከአህጉሪቱ ውጭ የሚመጡ አሰልጣኞች ብዛት እየቀነሰ መጥቷል በሚል የቀረቡ አስተያየቶች እንደማይዋጥላቸው ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ አንዳንድ ብሄራዊ ቡድኖች
በአገራቸው ተወላጅ እየሰለጠኑ መቅረባቸውን በጥርጣሬ የተመለከቱት ክላውድ ዲለሮይ፤ ዋንጫውን ያሸነፈው ሴኔጋላዊው አሊው ሲሴ እና የአልጄርያው ዲጄሜል ቢማዲ ምንም እንኳን ትውልዳቸው በአፍሪካ ቢሆንም ኑሮና እድገታቸውን በፈረንሳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ አሰልጣኞች የእግር ኳስ ዘመናቸውን እንዲሁም የአሰልጣኝነት ዲፕሎማቸውን ያገኙት በፈረንሳይ እንጅ አፍሪካ ውስጥ እየሰሩ አይደለም በማለት  ዲለሮይ ይሟገታሉ፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ የየአገራቸው ተወላጅ ሆነው በያዙት ቡድን ትክክለኛ ውጤት ያስመዘገቡት 3 የአፍሪካ ዋንጫዎችን ከፈረንኦቹ ጋር ለማሸነፍ የቻሉት ግብፃዊው ሃሰን ሺሃታ እና ጋናዊው ቻርልስ ጊያምፊ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከአገር ተወላጅ  ወይም ከውጭ አገር ተቀጥሮ የመጣ አሰልጣኝ የቱ ይሻላል በሚለው ክርክር ዋናው ጉዳይ  የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግበው ማነው? በሚለው ጥያቄ እንደሚወሰን የተለያዩ የእግር ኳስ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ባለፉት 10 ዓመታት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንና ዓለም  አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በአፍሪካ ውስጥ ያሉ  አሰልጣኞችን የሙያ ደረጃና ብቃትን ለማሳደግ ተከታታይ ኮርሶችን በማዘጋጀት ሲሰሩ ቆይተዋል። በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ መስፈርት መሰረት አንድ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከሀ21 የዲ ላይሰንስ ጀምሮ እስከ ኤ ላይሰንስ እንዲኖረው ይጠየቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር በአፍሪካ ውስጥ የሚገኝ አሰልጣኝ የቢ ላይሰንስ ካገኘ በኋላ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሚሰጣውን የኤ ላይሰንስ ኮርስ በመውሰድ ብቃቱን ማሳደግ ቢችልም በቅርብ ዓመታት ይህን አሰራር ካፍ እንዲቀጥል ባለማድረጉ በርካታ አሰልጣኞች በየአገራቸው ብሄራዊ ቡድኖችን ለመያዝ የሚኖራቸውን እድል አጥተዋል፡፡ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አፍሪካዊያን አሰልጣኞች በብዛት መሳተፋቸው ለወደፊቱ በአህጉሪቱ ያለውን የአሰልጣኞች አቅም እያሳደገ እንደሚሄድ የሚያረጋግጥ ልምድ ይሆናል፡፡
የቡርኪናፋሶው ካሞው ማሉ፤ የማሊው መሃመድ ማጋሲባ፤ የኮሞሮሱ አሚር አቡው በተሳትፏቸው ምርጥ ብቃታቸውን በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው ያሳዩ ዋና አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ሴኔጋላዊው አሊው ሲሴ ደግሞ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከቡድኑ ጋር ሻምፒዮን በመሆን ያገኘው ስኬት ደግሞ ተምሳሌት ሆኖ መጠቀስ ጀምሯል፡፡ ዋና አሰልጣኝ አሊው ሲሴ በሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ሃላፊነት ለአምስት አመታት የሰራ ሲሆን ለሴኔጋል በታሪክ የመጀመርያውን የአፍሪካ ዋንጫ ድል በማስመዝገብ ያገኘው ስኬት በአፍሪካውያን አሰልጣኞች ውጤታማነት ላይ እምነት ማሳደርና በቂ የስራ ዘመን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አመልክቷል፡፡

Read 1067 times