Saturday, 19 February 2022 12:36

በረሃ ላይ ብቻውን ምግብ ሲያበስል የታየው ህጻን ትኩረት ስቧል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   በረሃ ላይ ብቻውን ምግብ እያበሰለ የነበረውን ታዳጊ ፎቶ ያነሳው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ከፎቶው ጀርባ ስላለው ታሪክ ለቢቢሲ ተናግሯል። ፎቶውን በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ብዙዎች ያጋሩት ሲሆን ለልጁ ገንዘብና የተለያዩ እርዳታዎችም ተሰባስበውለታል።
ፎቶውን ያነሳው ጋዜጠኛ ቦሩ ኮንሶ ይባላል። በፎቶው ላይ ታዳጊው ብቻውን በረሃ ላይ ምግብ እያበሰለ የሚታይ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያ ለተመለከቱትም ከፍተኛ ኃዘኔታን አሳድሯል። ጋዜጠኛው በሞተር ሳይክል ሚዮ ወደተባለች ገጠራማ ሰፈር ሪፖርት ለመስራት እየሄደ በነበረበት ወቅት ነው ልጁን ያገኘው። በጣም መሽቶም ነበር።
“ትንሽ ልጅ ነው፤ ምናልባትም ዕድሜው ከ10 ዓመት በታች ቢሆን ነው። ብቻውን እሳት አንድዶ ምግብ እያበሰለ ነበር። ብቻውን በረሃ ውስጥ እያበሰለ ሳየው ደነገጥኩ። በ10 ኪሎሜትር ርቀት ካልሆነ በአካባቢው ምንም አይነት ቤት የለም። ሞተር ሳይክሌን አቁሜም ፎቶ አነሳሁት” ይላል ቦሩ። ቤተሰቦቹ በሌላ ወረዳ ውስጥ እንደሚኖሩና እሱ ውሃና ግጦሽ ፍለጋ፣ ከብቶቹን ይዞ ከቦታ ቦታ እንደሚንቀሳቀስ ነው ታዳጊው ለጋዜጠኛው የነገረው። የልጁን ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራቱን ተከትሎ፣ በርካቶች ታዳጊውን መርዳት እንደሚፈልጉም ነገሩት። ህፃኑን ከጎበኙት መካከልም ነጋዴዋ ሙና ባካሬ ትገኝበታለች። ለልጁ፣ ለቤተሰቦቹና ለጎረቤቶች የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጋለች።
“የዚህን ትንሸ ልጅ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማየቴ ልቤን ነክቶታል። መተኛት አልቻልኩም ነበር። ልጄ እንደሆነ ተሰማኝ፣ ያለበትን ማፈላለግ ጀመርኩ” ብላለች ሙና።
ሙና የልጁን የትምህርት ወጪ፣ ኮሌጅ እስኪያጠናቅቅ ድረስ ለመሸፈን ቃል መግባቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዘንድሮ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ የከፋ ድርቅ መከሰቱ ተገልጿል።

Read 2924 times