Saturday, 19 February 2022 12:51

"በአሜሪካ የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ ተግባራዊ ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የአካባቢውን ሰላም ይጐዳል"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ባለፈው ሃሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  እንደገለጹት፤ ኤች አር 6600 በሚል በአሜሪካ የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ አላስፈላጊና በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም የሚያቀጭጭ፣ የአካባቢውን ሰላምም የሚጎዳ ነው ብለዋል።
ረቂቅ ህጉ እንዳይጸድቅ የተለያዩ ጥረቶች በተለያዩ አካላት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሀመድ፤ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልል ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ለሰላም የሚደረገውን ጥረት እንደሚያደንቁትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ያደረጋቸው ስብሰባዎችና ጫናዎች ችግር ፈጥረው እንደነበር አስታውሰው፤ሆኖም ጫናዎችን በመቋቋም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ማካሄድ እንደተቻለ ገልጸውላቸዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቶ ሀገራዊ ውይይት ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋቸዋል።
የአለማቀፉ ማህበረሰብ በድርቅ የተጐዱ ወገኖችን እንዲደግፉ ጥሪ እንዳቀረቡላቸውም አንስተዋል።
35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ጉባኤው የሰላምና የጸጥታ ችግርን፣ የኮቪድ ወረርሽኝን እንዲሁም ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና መሰል ጉዳዮች ላይ መወያየቱን አስታውሰዋል።
መሪዎቹ በአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚደረገውን ጣልገብነትና ማእቀብ ማውገዛቸውንም ገልጸዋል።
ህብረቱ ከስዋህሊን ተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ አድርጐ ማጽደቁን ጠቁመው፣በኢትዮጵያ በኩል አማርኛን የህብረቱ የስራ ቋንቋ ለማድረግ ስራዎች ይጀመራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፤፡፡
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በተመለከተ ኢትዮጵያ የኢነርጂ ግዥን አስመልክቶ ከኬንያ ጋር መዋዋሏን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ህዳሴ ግድቡ ከተቋጨ በኋላ ኤሌክትሪክ በሽያጭ ከሚቀርብላቸው ሀገራት አንዷ መሆኗንም አመልክተዋል፡፡  
(ኢፕድ)

Read 3030 times