Saturday, 19 February 2022 12:52

"ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ የማስመጣቱ ሂደት ዘግይቷል"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት ለማስመጣት የሚደረገው ጥረት “በወቅታዊ ሁኔታዎች” ምክንያት መዘግየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ተናገሩ። የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን የመመለስ “ግዴታም፤ ኃላፊነትም ስላለበት” በዚያ አቅጣጫ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።  
ቃል አቀባዩ ባለፈው ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤አሁን በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ለሚገኙ ዜጎች “የመጨረሻ መፍትሔ” ተደርጎ እየተሰራ ያለው እነርሱን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ብሔራዊ ኮሚቴ መስርቶ የ“ቴክኒካል” ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለማምጣት በመንግስት በኩል ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ቃል አቃባዩ ቢናገሩም፤ ሂደቱ ላይ ግን የመዘግየት ጥያቄ ሊነሳበት እንደሚችል አምነዋል። “በአንዳንድ ወቅታዊ ሁኔታዎች ሊዘገይ ይችላል። ነገር ግን የመጨረሻ መፍትሔው ዜጎችን ማምጣት ነው” ቢሉም፤ “ወቅታዊ ሁኔታዎች” ያሏቸውን ጉዳዮች ሳያብራሩ ቀርተዋል።
ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት በማምጣት ረገድ፤ በሳዑዲ አረቢያ በኩልም ያለው አቋም ፤“ውሰዷቸው፤ መልሷቸው” የሚል መሆኑን ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ግን “አያያዛቸውና ጉዳት እንዳይደርስባቸው” ከሚመለከታቸው የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር ምክክር መደረጉንም ተናግረዋል።
በውይይቶቹ ላይ፤ በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚደርሰው “ስቃይ” የሁለቱን ሀገራት “ግንኙነት አይመጥንም” የሚል ነጥብ መነሳቱንም ቃል አቃባዩ አስረድተዋል። ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያለውን “ግንኙነት” በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ “መነጋገር ይቻላል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ በማህበራዊ የትስስር ድረ ገጾች ተከታታይ ዘመቻዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ያስታወሰው "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር"፤  ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ መልዕክት ያዘሉ መግለጫዎችን በማውጣት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው እያሳሰቡ መሆኑን ጠቁሟል - በሰሞኑ ሰፊ ዘገባው፡፡

Read 6978 times