Saturday, 19 February 2022 00:00

የሳምንቱ ዜና

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

"የጋዜጠኞች በነፃነት የመስራት መብት እየተሸረሸረ ነው"
                               አለማየሁ አንበሴ


            በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋዜጠኞች በነጻነት የመስራት መብት እየተሸረሸረ መምጣቱንና በርከት ያሉ ጋዜጠኞች ከሙያቸው ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ መፈጠሩን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር አስታውቋል።
ማህበሩ “ለዜጎች መብት መከበር የሚሟገተው ጋዜጠኛ መብት ይከበር” በሚል ከሰሞኑ ባወጣው  መግለጫ፤ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት መሻሻል እያሳየ እንደነበር ማህበሩም ሆነ አለም አቀፍ ተቋማት ያረጋገጡት እውነታ መሆኑን አስታውሶ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የፕሬስ ነጻነት እየተሸረሸረ ባለሙያውን አሸማቃቂ እርምጃዎች እየተወሰዱ መምጣታቸውን አስታውቋል - አብነቶችን በመጥቀስ፡፡ የሚዲያ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ታስረው ከተለቀቁ ባለሙያዎች መካከልም በቅርቡ ከበርካታ ወራት እስር በኋላ የተለቀቀው የአሀዱ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ፣ የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር ተመስገን ደሳለኝ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከቢሮው ተወስዶ ከታሰረ ከቀናት በኋላ መለቀቁ፣ የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፣ ታስሮ ለወራት ከቆየ በኋላ መፈታቱንና የሚዲያ ተግባር የሚያከናውንባቸው ንብረቶቹ በፖሊስ መወሰዳቸውን፣ የአሶሺየትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች አሚር አማን፣ የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳና የፋና ብሮድካስቲንግ ጋዜጠኛው አዲሱ ሙሉነህ እንዲሁም የተራራ ኔትዎርክ ዩቲዩብ አዘጋጁ ታምራት ነገራ በመግለጫው ተጠቅሰዋል፡፡
በተለይ ጋዜጠኞችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አፍኖ በመውሰድ ፍ/ቤት ባለማቅረብ አግቶ ማቆየት ከህግም ሆነ ከሞራል ያፈነገጠ መሆኑን የጠቆመው ማህበሩ፤ #ጋዜጠኛ የህዝብ አንደበትና ጆሮ እንደመሆኑ የሚያራምዳቸውን ሃሳቦች ከተለያዩ ምንጮች ሊያገኝ ስለሚችል የግል አቋሙ ተደርጎ መወሰዱ አግባብ አይደለም” ብሏል።
የጋዜጠኞችን መብት በእንዲህ ያለ መልክ ማፈኑ የሚቀጥል ከሆነ፣ አዲሱ ትውልድ የጋዜጠኝነትን ሙያ እንደ ወንጀል እየቆጠረ ከሙያው እንዲሸሽ፣ ባለሙያው ሥራውን በነፃነት ከመስራት ይልቅ እንዲሸማቀቅ የሚያደርግ እንዲሁም የፕሬስ ነፃነትና የሃገር ብልፅግናን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ መንግስት የሚዲያና የጋዜጠኛውን ነፃነት በማክበርና በማስከበር ረገድ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማህበሩ ጠይቋል፡፡  


______________________________________


                       ብልፅግናን ጨምሮ 26 ፓርቲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያደርጉ ታዘዙ
                            አለማየሁ አንበሴ


             የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ብልፅግናን ጨምሮ 26 የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤዎቻቸውን አካሂደው ሪፖርት እንዲያቀርቡ አሳሰበ፡፡
ከዚህ ቀደም ቦርዱ ከምርጫው በፊት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ማካሄድ ያልቻሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከምርጫው በኋላ አካሂደው ሪፖርት እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ቢያስቀምጥም፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ስብሰባዎች በመከልከላቸው ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንዳልቻሉ ተመልክቷል፡፡
ከሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ፣ ጉባኤዎቻቸውን ያካሂዳሉ ብልጽግናን ጨምሮ 13 ሀገር አቀፍና 13 ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶች በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሂደው ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
በወር ውስጥ ጉባኤ እንዲያደርጉ ቀነ ገደብ ከተቀመጠላቸው 13 ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስት (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ይጠቀሳሉ፡፡
ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ከተሰጣቸው ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ደግሞ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ትዴፓ)፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት (አረና) እንዲሁም የሲዳማ  አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ይገኙበታል፡፡
ፓርቲዎቹ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እስከ መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አከናውነው እንዲያጠናቅቁ  የጊዜ ገደብ የተቀመጠላቸው ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ የማያከናወኑ ከሆነ በቦርዱ ህግ መሰረት ከፖለቲካ ድርጅትነት ሊሰረዙ ይችላሉ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ቢያንስ በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሚደነግግ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ማካሄድ ካልቻሉ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚሰጣቸው የጊዜ ገደብ የማካሄድ ግዴታ አለባቸው፡፡
ቦርዱ በምርጫ ማግስት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ አስቀድሞ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣  ጉባኤያቸውን በወቅቱ  ያደረጉት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (አብአፓ) መሆናቸው ታውቋል፡፡


________________________________________________


                 የዳሎል ኦይል ኩባንያ የቦርድ አባላትና ባለ አክስዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ እንዲጠራ ጠየቁ
                      አለማየሁ አንበሴ

              ከ13 ዓመት በፊት 1255 አባላትን ይዞ የተመሰረተው ዳሎል ኦይል አክስዮን ማህበር በቅርቡ ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ህግና ደንቦችን የጣሰ ነው ያሉት የቦርድ አባላትና ባለ አክስዮኖች፣ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ጠየቁ፡፡
ታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው የኩባንያው 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የንግድ ደንብ የጣሰ ነው ሲሉ ለአዲስ አድማስ የገለጹት የቦርዱ አባላት፤ ስብሰባው ምልዐተ ጉባኤ መሟላቱ ሳይረጋገጥ፣ቃለ ጉባኤ መዝጋቢ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት በእለቱ ከተገኙ አባላቱ ሳይመረጥ፣ የመምረጥ መብት የሌላቸው አካላት በመራጭነት የተሳተፉበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከኩባንያው መስራች የቦርድ አባላት መካከል፡- አቶ አብሼ ብሩ፣ ኢ/ር አግዘው አድማሴና አቶ ጫልቺሳ አቤሳ ስለ ጉባኤው  ለአዲስ አድማስ ሲያስረዱ፤ የጉባኤው ስብሳባ በንግድ ህጉ አንቀፅ 370 መሰረት፤ 24 ተከታታይ ቀናት ሲቀረው ለቦርድ አባላትና ለባለ አክስዮኖች ጥሪ መደረግ ሲገባው አለመደረጉን ጠቁመው፣ በዚህም ምክንያት በቂ የአባላት ተሳትፎ እንዳይኖር መደረጉን እንዲሁም የቦርድ አባላት ሳይመረጡ የአስመራጭ ኮሚቴ በሰብሳቢው ብቻ ተዋቅሮ ማስመረጡን ጠቁመዋል፡፡  
በእለቱ በስብሰባው አካሄድ ላይ የታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙ በተሰብሳቢዎች ቢጠየቅም ቅሬታው ተቀባይነት አጥቶ ውሳኔዎች ከህግና ደንብ ውጭ መወሰናቸውን የሚገልጹት የቦርዱ አባላቱ፤ ይህ ሁኔታ የአክስዮን ማህበሩን ህልውና ከመፈታተኑ በፊት አፋጣኝ እርምት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
አክስዮን ማህበሩ ካሉት ከ1300 በላይ ባለ አክስዮኖች መካከል በጉባኤው የተሳተፉት ከ4 መቶ እንደማይበልጡ የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢያዎቹ፤ ምልአተ ጎባኤ ሳይሟላ በተካሄደ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች ተቀባይነት ስለማይኖራቸው በአስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ የተሟላለት ስብሰባ በድጋሚ እንዲካሄድ ጠይቀዋል። የቦርድ አባላቱን ቅሬታ አስመልክቶ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
  ታህሳስ 23 ቀን 2014 በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ፣ በቦርድ ሊቀመንበርነት የተመረጡት አቶ ታደሰ በቀለ ስለቀረቡት ቅሬታዎች  ጠይቀናቸው፤ “ሁሉን አጣርቶ መርምሮ ምላሽ መስጠት የሚችለው ኹነቱን ሲታዘብ የነበረው የንግድ ቢሮ ተወካይ፣ የሰነዶች ማረጋገጫ ቢሮ ነው፤ እኔ በወቅቱ አንድ ተመራጭ ነን፤ ስለ ጉባኤው ትክክለኝነት መናገር የሚችለው ታዛቢ ነው” ብለዋል፡፡
_________________________________________
                  በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ለሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጠ


             በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የስነልቦና፣ የማህበራዊና የአዕምሮ ጤና ድጋፍ አገልግሎቶችን ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና ከሰኞ የካቲት 7 አንስቶ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ሰጠ፡፡
ስልጠናውን በይፋ የከፈቱት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ፣ ርእሰ አካዳሚ ዶ/ር ምህረት ደበበ፤ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ተደራሽ የሚያደርግ የማህበራዊ፣ የሥነልቦናና የአእምሮ ጤና ስልጠና ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልጸው፣ የአመራር ልህቀት
አካዳሚውም ሥልጠናው በተገቢው መንገድ እንዲከናወን ድጋፉን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
 የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት የተከሰቱት ችግሮች፣ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ካሳደሩት ተጽእኖ
በተጨማሪ በዜጎች ላይ እጅግ የከፋ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳደረሱ፣ በተለይም በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴት የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከደረሰባቸው አሰቃቂ ጉዳት ተላቀው ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ የሁሉንም አካላት ርብርቦሽ እየጠበቁ እንደሆነ ጠቁመው፣ በስነልቦና፣ በማህበራዊና በአዕምሮ ጤና ድጋፍ ላይ ያተኮረው የአሰልጣኞች ስልጠና፣ ይህንን ግዙፍ ሀገራዊ ችግር ለመቅረፍ የራሱን አበርክቶ ይወጣል ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (UNICEF) የኢትዮጵያ ተወካይ ጂያን ፍራንኮ
ሮቲጂሊያኖ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በስነ ልቦና፣ በማህበራዊ እንዲሁም በጤና ዘርፍ የሚገኙ
ባለሙያዎች አቅም እንዲጎለብት የማድረግ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝና በቀጣይም ድርጅታቸው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በተለያዩ ዘርፎች ማለትም፡- በጤና፣በማህበራዊ፣በሴቶችና በህጻናት የሚከናወኑ ስራዎችን በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
 የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፤ የስልጠናው ዓላማ በቂ ባለሙያዎችን አስፈላጊ በሆነው እውቀትና ክህሎት አስታጥቆ ማሰማራት መሆኑን አመልክተው፣ የአሰልጣኞች ሥልጠናው ከአማራ ከአፋር፣ ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም  ከፌዴራል ለተውጣጡ 270 ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ጠቁመው ነበር - በሥልጠናው መክፈቻ ዕለት፡፡ ሥልጠናው በአምስት ዘርፎች ለአምስት ተከታታይ ቀናት መሰጠቱ ታውቋል፡፡

_____________________________________________


 በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩ ዜጎች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ተጠየቀ
                           አለማየሁ አንበሴ

                የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ አዋጁን ምክንያት በማድረግ የታሰሩ ዜጎች በሙሉ በአፋጣኝ  ከእስር እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጠይቋል።
የአስቸኳይ  ጊዜ አዋጁ ወቅቱን ጠብቆ መነሳቱ፣ በተለይ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስር እንዳይፈጸም ጥበቃ በማድረግ በኩል ሚናው የጎላ መሆኑንና ለማህበራዊ ይዞታዎች መሻሻል አስተዋፅኦ እንዳለው ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ በዚህ አዋጅ መነሻ የታሰሩ ሁሉ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ  ሊለቀቁ ይገባል ብሏል።
በአዋጁ መነሻ ታስረው የነበሩ ግሰቦች በእስራቸው ወቅት ማህበራዊ ኑሮአቸው መቃወሱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውም አደጋ ላይ መውደቁን የጠቆመው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ አብዛኛዎቹ ተከትሎ ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን ይህም የሆነው ግለሰቦቹ በአስቸኳይ አዋጁ መታሰራቸው ለየመስሪያቤቶቻቸው ሪፖርት ባለመደረጉ  ነው ብሏል።
ስለዚህም በቀጣይ ወደ ስራ ገበታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት በመግለጫው ተመልክቷል።
በተመሳሳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት በአድናቆት እመለከተዋለሁ። ሀገሪቱ ሰላምና የፀጥታ ሁኔታ ያሻሽላል የሚል እምነት አለኝ ያለው የአሜሪካ መንግስት በዚህ አዋጁ መነሻ የታሰሩ ግለሰቦች በሙሉ ከእስር በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል ብሏል።


Read 420 times