Print this page
Sunday, 20 February 2022 00:00

የምክር ቤቱን አባላት ያወዛገበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት ውሳኔ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 • 63 የምክር ቤቱ አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል
      • “መንግስት ለዜጎች ህይወትና ንብረት ዋስትና መስጠት በማይችልበት ሁኔታ አዋጁን ማንሳት ተገቢ አይደለም” አብን
           
          የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ያፀደቀውንን ለስድስት ወራት የሚዘልቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለጊዜው እንዲነሳ የሚንስትሮች ምክር ቤት ጥር 18 ቀን 2014 ያሳለፈውን ውሳኔ ለማጽደቅ ሰሞኑን ያካሄደው ጉባዔ ከወትሮው ለየት ያለ ተቃውሞ አስተናግዷል። ምክር ቤቱ አዋጁን በ63 የተቃውሞ ድምጽና በ21 ድምጸ ተአቅቦ አጽድቆታል።
ምክር ቤቱ በ6ኛው ዙር በ1ኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ በአገሪቱ ላለፉት 3 ወራት ተግባራዊ  ሲደረግ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማንሳት ካሄደው ጉባኤ በምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል።
ምክር ቤቱ” አገሪቱ የተደቀነባትን የህልውናና የሉአላዊነት አደጋ በመደበኛው ህግ ማስከበር የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁበአሁኑ ወቅት ያለው የአደጋ ስጋት አነስተኛ በመሆኑና በመደበኛው የህግ ማስከበር ተግባር መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተፈጸሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል። በዚሁ መሰረትም የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ድምጽ እንዲሰጡ አድርጓል። በዚህ ወቅትም፤ አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ፈጽሞ ያልተረጋጋና በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎችም በወረራና በሽብር ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ አይገባም የሚል ጠንከር ያለ ተቃውሞ ከበርካታ አካላት ቀርቦ ነበር።
በምክር ቤቱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ባቀረቡት ተቃውሞ፤ “መንግስት ለዜጎች ህይወትና ንብረት ዋስትና በማይሰጥበት ሁኔታ አዋጁን ማንሳት አግባብነት የለውም” ብለዋል።
በምክር ቤቱ የብልጽግና ተወካይ የሆኑ አንድ  አባል በሰጡት አስተያየት ከፓርቲ ጉዳይ ወጥተን ለህሊናችን ብለን ይህ የአዋጁን መነሳት የሚያጸድቅ ውሳኔ ከማጽደቅ መቆጠብ ይኖርብናል ብለዋል። በዕለቱ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወስኖ የቀረበውን አዋጅ ማጽደቅ የለብንም ሲሉ ተከራክረዋል።
በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱም አዋጁ በ63 የተቃውሞ ድምጽ እና በ21 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቃቸው ጅምር ስራዎች ካሉ ውሳኔው ከጸደቀበት የካቲት 8 ቀን 2014  ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያደርግም ምክር ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል።
በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የሕግና የፖለቲካ ምሁሩ አቶ አህመድ ኢሳ፤ እንደሚናገሩት መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በዚህ ወቅት ማንሳቱ የተሳሳተ ውሳኔ ነው ብለዋል። የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ዛሬም ድረስ በአፋር ክልል በርካታ አካባቢዎች ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ አድርገውና በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ባሉበት፣ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በተሰደዱበት፣ ኦነግ ሸኔ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በየዕለቱ ንፁሃንን በግፍ እየገደለ ባለበት በዚህ ወቅት  አዋጁ እንዲነሳ የተላለፈው ውሳኔ አግባብነት የለውም ሲሉ ተቃውመዋል።
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ መነሻ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ባልተፈታበት የንፁሃን ሞት፣ ስደትና መከራ በየዕለቱ እየጨመረ ባለበት፤ እንኳንስ አዋጁ ተነስቶ ሳይነሳም ችግሩን መቆጣጠር ባልተቻለበት ሁኔታ ውስጥ እያለን ችግሩን በመደበኛ ህግ መከላከል ይችላል በሚል አዋጁ እንዲነሳ መደረጉ ትልቅ ስህተት ነው” ያሉት አቶ አህመድ በተለይ አሁን የአፋር ህዝብ ከወራሪው ሃይል ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቀ ባለበትና ሺዎች  በተፈናቀሉበት ጊዜ ላይ አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ መተላለፉ መንግስት ለዜጎቹ በተለይም ለአፋር ህዝብ ያለውን ግድየለሽነት የሚያመለክት ነው  ሲሉም ምሁሩ ተችተዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም፣ ህውሃትና አጋሮቹ የአገር ሉአላዊነት ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመከላከል እንዲያስችል በማለት የወሰነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ማጽደቁ የሚታወስ ነው።

Read 9367 times Last modified on Sunday, 20 February 2022 15:23