Sunday, 20 February 2022 15:25

አድማስ ትውስታ

Written by  ሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

   መልስ የሚሹ ሁለት መሰረታዊ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች

   (የብሔረሰቦች ሕዝቦችን እንነጣጥል ወይስ እንደራርብ?)
                         
               ፌደራሊዝም ነጻ አስተዳደር ባላቸው ግዛቶች ሕብረት የሚመሰረት፤ በማዕከላዊ መንግሥትና ግዛቶቹ መካከል በሕግ የሚደነገግ የስልጣን እርከን ያለበት የአንድ ሉዓላዊ አገር ቅርጸ-መንግሥት ነው፡፡እንደ ኢትዮጵያ ያለ ለዘመናት አብረው የኖሩ የበርካታ ብሔረሰቦች ሕዝቦች አገር፤ የአስተዳደር ግዛት አወቃቀር በጥናት ላይ ተመስርቶ በሕዝበ-ውሳኔ መሰረት በጥንቃቄ ካልተፈጸመ በስተቀር የግዛት ውቅሩ በዘላቂነት ሊጸና አይችልም፡፡
ማህበረሰቦችን በአስተዳደር ክልል እንደገና የማዋቀር ሂደት ከሁለት አንዱን መርህ መከተሉ አይቀርም። አንዱ መርህ ከዚህ ቀደም ተበታትነው የቆዩትን ማህበረሰቦች፣ የአንድ ብሔረሰብ ሕዝቦች አባላት ናቸው በማለት በብሔረሰብ ገመድ ከዚያም ከዚህም አሳስቦ፣ ከነበሩበት የማህበረሰብ ዘውግ በመለያየት፣ አገጣጥሞ አዲስ የአስተዳደር ክልል መፍጠር ነው፡፡ ከተለያየ ጣቃ ጨርቅ ቆራርጦ ፣ቁራጮችን አገጣጥሞ ኮት እንደሚሰፋ ልብስ ሰፊ፣ ለዘመናት የተሳሰሩና ተደምረው የኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከየነበሩበት ዘውግ እንዲፈናቀሉ ማድረግ፣ የጠራ ብሔረሰብ ሕዝብ የአስተዳደር ክልሎች ለመፍጠር ማሰብ ይቻላል፡፡ ይህ ሕዝብን የመለያየት (Ethnic sorting) መርህ ሲሆን መርሁ የግዛት ማስፋፋት ድብቅ ዓላማ ማሳኪያ ስልት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ሌላው መርህ ለዘመናት አብሮ የኖሩ የማይለያዩ ማህበረሰቦች መሆናቸውን ተቀብሎ፣ ቀድሞ በነበሩበት ዘውግ ተነባብረው/ተደራርበው ዕኩልነታቸው ተከብሮ በመደመር እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህኛው በመደራረብ/በመነባበር ተደምሮ አብሮ የመኖር (Ethnic nesting/Ethnic clustering) መርህ ነው፡፡
የመለያየት መርህን የሚከተል ክልላዊ መንግሥት አወቃቀር፤ ሕዝቦችን በብሔረሰብ መስፈርት ለያይቶ በምንነቴ ይታወቅልኝና በመሬት ይገባኛል ጥያቄ፣ ዘወትር እርስበርስ ሲያናቁር፣ የመደራረብ አወቃቀር መርህ ግን ሕዝቦችን ድርና ማግ አድርጎ፣ ብሔረሰቦችን በጋራ አስተሳስሮ፣ በመዋደድ የሚያኖር የአንድነት ዋስትና ነው፡፡ ከሁለቱ አማራጮች የትኛው የአስተዳደር አወቃቀር ብሔረሰቦችን ወደ አንድነት ያመጣል፤ የትኛው ብሔረሰቦችን ይለያያል የሚለውን ጥያቄ በጥሞና መርምሮ አንዱን መምረጥ ይቻላል፡፡ ብሔረሰቦችን የሚነጣጥል የግዛት አማራጭ የግጭት መንስዔ ነው ተብሎ ተገልጿል። መልክዓምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ባደረገው የቀድሞው የጠቅላይ ግዛት/ክ/ሐገር የአስተዳደር አወቃቀር፤ በብሔረሰቦች መኻል ይቀሰቀስ የነበረው ግጭት ቢበዛ በውሃና ግጦሽ ሳር የሚከሰት ጤናማ ግጭት እንጂ በመሬት ይገባኛል አልነበረም፡፡ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ፤ የግዛት አስፋፊ ገዥ መደቦች መሬት የመቆጣጠር ጥያቄ እንጂ የተፈጥሮ ሐብት ተጋሪ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ጥያቄ አይደለም፡፡
በቀድሞው የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ዜጎች ይታወቁ የነበሩት በየግላቸው በየሚናገሩት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ሳይሆን በሚጋሩት የጋራ አገር እና ክ/ሐገር ነበር። አወቃቀሩ በድክመቶቹም ላይ ተደምሮ ሕዝቡን ሆድና ጀርባ አላደረገም ነበር፡፡ በአገራችን ሰውን በቋንቋ፤ በደም/በዘር ለይቶ ለመመደብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በሌለበት ጸጉር በመሰንጠቅ ማንም ሰው አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ሲዳማ፤ ወላይታ፤ ሱማሌ፤ አፋር፤ ጋምቤላ ወዘተ እየተባለ በቋንቋ ግድግድ አጥር ውስጥ ገባ። ዳሩ ግን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች በረዥም ዘመን የማህበረሰባዊ ለውጥ ሂደት በተፈጠረ በአንድነት የመኖር ዕድል በፈጠረው የማያቋርጥ ውስብስብ ማህበራዊ መስተጋብር፣ በደም/በዘር የተዋሃዱ ሕዝቦች ስለሆኑ ነጣጥሎ፣ በትክክል ለመከለል ያስቸግራል፡፡ የማይነጣጠሉ ማህበረሰቦች በመሆናቸው አንለያይም ሲሉ ልዩነታቸውን ለማስፋት በመኻላቸው የርስ በርስ ጥርጣሬን ማስፈን፤ የቀድሞውን ትስስር ማላላት፤ የጋራ ታሪክን ማኮሰስ፤ ልዩነቶችን በማጦዝ የመለያየት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ማደፋፈር አጀንዳ ተደርገው ይወሰዳሉ። አሁን የሚታየው የአገራችን ችግር ይህ ሲሆን የአንድነቷ ህልውና የሚወሰነውም በዚህ ችግር አፈታት ዙሪያ በሚደረሰው ብሔራዊ መግባባት ነው፡፡
መፍትሔውን በዚህ ችግር አፈታት ዙሪያ መፈለግ ሲገባ ምስቅልቅሉ ሊፈጠር የቻለው ወጣቱን ስለ ፌደራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ በሚገባ ስለአላስተማርነው ነው በማለት፣ አንዳንድ ከፍተኛ የፖለቲካ ኃላፊዎች ሲያቧልቱ ይሰማሉ። በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ እንዲማር ያልተደረገውን፣ ወጣቱ ትውልድ ያገሩን የጥንት ታሪክና ባህል በገዛ ራሱ ጥረት በመማር ጥሏቸው ማለፉን ከሁኔታዎች ግምገማ መረዳት አልቻሉም፡፡ ፌደራሊዝሙን በአግባቡ ስለአልተረጎምነው ነው ቢሉ እንኳ ይሻል ነበር፡፡
በየትኛውም የአስተዳደር ክልል የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚጠቅመው በቋንቋ ግድግድ አጥር ውስጥ መካለል ሳይሆን በየሚኖሩበት ክልል ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብሮ፣ በዕኩልነት የሚኖሩበት የጋራ አገር ባለቤት መሆኑን ባለስልጣናቱ አይቀበሉም፡፡ ዜጎችን በቋንቋ ግድግድ አጥር ውስጥ ያስገባው የአስተዳደር ክልል አወቃቀር፤ ”የእርሱ ክልል አይደለም” በተባለ ክልል ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ዜጋ የቤተኝነት ስሜትን በማሳጣት፣ ከግዛቱ ርቆ እንደ ተሰደደ አውሬ፣ ዘላለም በስጋት እንደ በረገገ፣ ፊት ለፊቱ ያለውን አደጋ እየተጠባበቀ እንዲቆይ ያደርጋል፤ ለደከመበት ሐብት ዋስትና ያሳጣል። በመልክዓምድር ላይ የሚመሰረት የአስተዳደር ግዛት፤ በቋንቋ ልዩነት ላይ ተመስርቶ ስለማይከለል ዜጎች በጊዜያዊነትም ይሁን በቋሚነት በየትኛውም ክልል ሲኖሩ በቋንቋ ተጽዕኖ ምክንያት ለሚደርስ አደጋ አይጋለጡም። ቋንቋውን የሚናገሩ ዜጎች እዚህም እዚያም ስለሚኖሩ ዜጎች የሚታወቁት በየግላቸው በሚናገሩት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ሳይሆን በሚጋሩት የጋራ አገር/ክፍለ ሐገር ስለሚሆን የሚሰማቸው ስሜት በአንድ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ክፍል የሄዱ ያህል ብቻ ይሆናል፡፡ በቋንቋ ምክንያት መጤ በመባል የሚገለል ሰው አይኖርም፡፡
ቋንቋን መሰረቱ ባደረገ አዲስ የአስተዳደር ግዛት አወቃቀር፤ አንዱ ነባር አስተዳደር ክልል እውቅና አግኝቶ ከነበረው ግዛት በላይ ሲስፋፋ፣ በሌላ በኩል ሌላው የሕዝብን ይሁንታ ባላገኘበት ሁኔታ ፈራርሷል። ይህ አድልዖ በጥብቅ መገምገም ያለበት ችግር ነው፡፡ የአስተዳደር አወቃቀር ለውጡ የተደረገው ብሔረሰቦች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ለማገዝ ነው እንዳይባል፣ እስከ 54 ብሔረሰቦች በአንድ ክልል ውስጥ ታጉረው ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ለዚህ ጥቂት ብሔረሰቦችን ያካትቱ የነበሩት ነባር የአስተዳደር መዋቅሮች ለምን ፈረሱ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አዎ፤ ብሔረሰቦች በቋንቋ ግድግድ አጥር የተከለሉት ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ነው የሚሉ ዜጎች ካሉ፤ የአገራችንን የፖለቲካ ጨዋታ ያልተረዱ የዋሆች ናቸው።  
የአገራችን ዜጎች በተቀረው የአገራቸው ክፍል ዘንተው መኖር በትረካ የሚታወቅ ብቻ የሆነባቸው፤ ቀድሞ የነበረው ታህታይ ሕብረብሔራዊነት መክሰም የፈጠረው የቤተኝነት ስሜት መሸርሸር ነው፡፡ ነባርና መጤ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የሚል ለአገራችን የማይሠራ ፈሊጥ ለማህበረሰቦች መንግጎ በመጋት አንዱ ከሌላው የተለየ መብት ባለቤት ሲሆን ሌላው በባይተዋርነት አንገቱን ደፍቷል፡፡ በክፋት የተጋትነውን የመለያየት አባዜ ከውስጣችን ካስወጣን፣አገራችንን በጋራ አልምቶ “በአንድ ትልቅ ሞሰብ መመገብ” ይቻለናል። የሞትነው እኛው፤ ያለነውም እኛው ነን፡፡ “በትንንሽ ሳህኖች” ለየብቻ ለመመገብ የሚጓጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በጽናት ታግለን እናስተካክላቸው። ዜጎችንና ብሔረሰብ ሕዝቦችን የሚለያይ የማይረባ እርሾ ሲግቱ የቆዩትን አካላት፤ “ጌታ ሆይ! የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ሰፊ አገር ያወረሰንን ቀደምት ትውልድ በማመስገን፣ ብሔራዊ ዕርቅ በማውረድ፣ አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ እንገንባ። የሩቅ ባዕድ ኃይሎች በቀድሞ የባህር በራችን ላይ እያደረጉ ያሉትን የባህር በር መቀራመት እንደምታ፤ የግብጽን ያዙኝ ልቀቁኝ ድንፋታ፤ ሌሎችንም አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ አስገብተን በማየት ለስትራቴጅክ አገራዊ ጥቅሞቻችን ስንል ብሔራዊ መግባባት ላይ ብንደርስ የተሻለ ይሆናል፡፡
ክልላዊ አስተዳደርን በብሔረሰብ ማዋቀር፤ በድንበር ግራ ወይም ቀኝ የሚገኝ መሬትን በአካቶ ለመያዝ ለሚፈልጉ ቡድኖች አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ቢሆንም ከአገራዊ ጥቅም አንጻር ሲታይ የተጫወተው አፍራሽ ሚና እጅግ የጎላ መሆኑን ከሁኔታዎች ግምገማ ለመገንዘብና ለመስተካከል አሁንም በቂ ጊዜ አለ። የአስተዳደር ክልልን በብሔረሰብ መከፋፈል ለጋራ ትስስር መጠናከር የማይጠቅም ስለመሆኑ ካለፉት የሙከራና የመከራ ዓመታት በቂ ልምድ ተገኝቷል። ከተገኘውም ልምድ በመነሳት የአስተሳሰብ ቅኝትን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሕዝብ ችግሮች ምንጭ፣ ይህን መሰል ደንቃራ አስተሳሰብና የአስተሳሰቡ ባለቤቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ሕዝቦች ከረዥም ዘመን ጀምሮ የተዋሃደ ደም ያላቸው ሕዝቦች በመሆናቸው፣ አሁን ያሉት ትውልዶች በደም ሊጠሩ ወይም ከደም ሊነጹ እንደማይችሉ እየከፋቸውም ቢሆን ሊገነዘቡት ይገባል። የራሳቸው ቋንቋ አላቸው የሚባሉ ሕዝቦችን ከተዋሃዱ ብሔረሰቦች ደም ፍጹም የጸዱ ወይም ከሌላው ሕዝብ ጋር ፍጹም ዝምድና የሌላቸው አድርጎ በመውሰድ፣ ለመለያየት መሞከር ለአገዛዝ እንዲያመች የሚከናወን ከባዕድ (ጣሊያን) የተቧገተ የማህበረሰቦች ዘውግ የማፍረስ ስልት ነው፡፡
ቀደም ሲል ለአጼ ቴዎድሮስ መነሳት መነሻ የነበረው የዘመነ መሳፍንት አገዛዝን በከፊልም ቢሆን እንደገና የሚመልሰው፤ ብሔረሰቦችን በመለያየት ላይ የተመሰረተው አዲሱ የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ብዙም ርቀት ሳይጓዝ በቂ ትምህርት አስገኝቷል። ከዚህ ይልቅ ብሔረሰቦችን ያነባብር/ይደራርብ የነበረው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛት/ክፍላተ ሐገራት አወቃቀር፤ የተሻለ የብሔረሰቦች ሕዝቦች አንድነትና ሰላም ምንጭ እንደ ነበረ በመከሰት ላይ ያሉት ችግሮች በቂ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ በብሔረሰቦች ሕዝቦች መኻል እየተፈጠረ ባለው ሰው-ሠራሽ ችግር ምክንያት ከየብሔረሰቦቹ የአገር ሽማግሌዎች፤ ኡጋዞች፤ ሱልጣኖችና አባጋሮች እየተስተጋባ ያለው መልዕክት ይህንን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡ “ይህን የመሰለ ከባድ መከራ የወረደብን ከወቅቱ ጋር ተያይዞ በመጣብን የፖለቲካ ችግር የተነሳ ነው” የሚሉት፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ካለፈው ሁኔታ ጋር በማነጻጸር፣ የምስክርነት ቃል ለመስጠት ከእነርሱ የሚበልጥ አካል የለም፡፡
ከሰማንያ አምስት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ህዝቦች መኻል እጅግ በጣት ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች በየስማቸው የሚጠሩባቸው የአስተዳደር ክልሎችን በማቋቋም፤ የምንነታቸው መጠሪያ ክልላዊ ስም ያላገኙ በርካታ ብሔረሰብ ሕዝቦችን ዓይን እያቀሉ፣ በቅሬታ ውስጥ ረዥም ዘመን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መኖር አይሳካም፡፡ የቱንም ያህል ጠቃሚ ይሁን፤ የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ለውጡ በአንድ የአስተዳደር ክልል ውስጥ የተከለሉ ብሔረሰቦች ሕዝቦችን ፍላጎት እንኳ ማርካት አላስቻለም፡፡ ለዚህም ነው በአዲስ የአስተዳደር ክልል፣ ለየብቻችን እንዋቀር፣ የሚል የማህበረሰቦች ጥያቄ መቋጫ ሊያገኝ ያልቻለው። ያስገኘው ትርፍ በብሔረሰቦች ሕዝቦች መካከል ልዩነትን መፍጠር፤ ጥርጣሬን ማንገስና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና ልማት፣ ዕድገት ዘላለማዊ ፈተና የሚሆን በውርስ ለትውልድ የሚተላለፍ ፈንጂ መቅበር ነው፡፡
የችግሩ መንስዔ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ከሆነ “የማትታረድ ቅድስት ላም የለችም” እንዲሉ፤  የሕገመንግሥት ማሻሻያ ማድረግ የቅንጦት ነገር ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ በዓለም ላይ ምንም ቋሚ የሆነ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር የሚገኘው በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ነው፡፡ ከቀድሞውና ከአሁኑ የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ባህርያት፤ ጠቃሚዎቹን ባህርያት ለይቶ በመውሰድ፣ ለአገራችን አንድነት መጠበቅ በሚጠቅም መልኩ የአስተዳደር ክልሎችን እንደገና ለማዋቀር ሁኔታዎችን ማጤን ግድ ይላል፡፡ ሌላ ዓላማ ከሌለ በስተቀር በንጉሡ ወቅት የነበረውን በመልክዓምድር ላይ የተመሰረተውን የአካባቢ አስተዳደር ክልል አወቃቀር ክፍተት በመሙላት የየብሔረሰቦቹን ሕዝቦች ወደ የፈራረሱበት ዘውግ መልሶ በማሰባሰብ ዕኩልነት በሰፈነበት መልክዓምድር አብረው እንዲኖሩ ማድረግ ተመራጭነት አለው፡፡ ስለሉላዊነት እና የአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ፖለቲካ በሚያነበንብ የቀበሮ ባህታዊያን አንደበት በድንበር ተጋጭተው የማያውቁ የብሔረሰቦች ሕዝቦችን እርስበርስ ማጋጨት የትግል አጀንዳ ሆኖ ሲቀርብ ያሳፍራል፡፡ “በእኛነት ስሜት” ተሳስረው አብረው የኖሩ፤ በደም የተሳሰሩ፤ የነበረውን ጨቋኝ ስርዓት በጋራ ታግለው ያስወገዱ ብሔረሰቦች ሕዝቦችን በቋንቋ ተናጋሪነት አዲስ ዘውግ ያለ ፍላጎታቸው ከማጠር ይልቅ ነባሩን ታህታይ ሕብረብሔራዊነት በተገኘው ድል አጠናክሮ ወደ ላዕላይ ሕብረብሔራዊነት (ኢትዮጵያዊነት) መረማመድ ይሻላል። ይህ የግዛት አወቃቀር የብሔረሰቦች ሕዝቦችን አንድነት ለማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው።
ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና በጋራ ታግለው ያስወገዱ ሕዝቦች፤ በጨቋኝ ስርዓት ላይ ድል በተቀዳጁ ማግስት ያቀረቡት የመለያየት አጀንዳ የለም፡፡ በጋራ የገነቡትን እሴት በየግላቸው ለማፍረስ አይተጉም፡፡ ከጨቋኝ ስርዓት መገርሰስ በኋላ ከቀድሞው ይበልጥ በሰላም አብሮ ለመኖር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል እንጂ ለዘመናት በጋራ የገነቡትን የአብሮነት ጸጋቸውን ጥለው ለመነጣጠል ይገሰግሳሉ ተብሎ አይታሰብም። የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች በላያቸው ላይ በተጫነ ገዥ መደብ ወይም አሮጌውን ገዥ መደብ ጥሎ አዲስ ገዥ መደብ ለመሆን ሁልጊዜ አቆብቁቦ በሚሳካለት የተደራጀ ቡድን ጭቆና ሲደርስባቸው፤ ሰላምና ዕረፍት ሲያጡ፤ የተጫነባቸውን የጭቆና ቀንበር ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው ለመጣል ሲታገሉ፤ ከአንዱ የለውጥ ዘመን ወደ ሌላ የለውጥ ዘመን፤ ከአንዱ ገዥ መደብ ወደ ሌላ ገዥ መደብ መሸጋገርና ሁልጊዜ በስቃይ ውስጥ ለውጥን ሲናፍቁ መኖር ግድ ሆነባቸው። ፈጣሪ በቃ እስከሚላቸው ድረስ አማራን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች አሁን የሚገኙት በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነው፡፡
ብዝህነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ደረጃ ብቻ መታሰቡ እንደ ገና በቅጡ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ነው። ብዝህነት በብሔረሰብ ሕዝቦች ውስጥ አለ። የኢትዮጵያ ህዝቦች ብዝህነት ይከበር እንደምንለው ሁሉ በአንድ ብሔረሰብ ሕዝብ ውስጥ ያለው ብዝህነት፤ የባህል፤የታሪክና ስነልቦና ፋይዳ መከበር አለበት፡፡ ለምሳሌ በአማራነት ውስጥ ያለውን ወሎየነት፤ ሸዌነት፤ ጎጃሜነትና ጎንደሬነት አማራነትን ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ካስተሳሰረ የወሎየነት፤ ሸዌነት፤ ጎጃሜነትና ጎንደሬነት ድርና ማግ ለያይቶ ማየት ስህተት ነው፡፡ በቋንቋ ላይ ብቻ በተመሰረተ ማንነት ማህበረሰቦችን ነጣጥሎ በማካለል ልዩ ፍላጎት ልቡ የተነካ ቡድን ካለ ወደ ቀልቡ ይመለስ፡፡ ሁኔታው በሌሎች ብሔረሰቦች ሕዝቦችም ተመሳሰይ ነው፡፡ ዘርፈ-ብዙ ብዝህነት በተግባር ሲከበር ለኢትዮጵያ አንድነት የዘለቄታ ዋስትና ነው፡፡
አዲሱ የአስተዳደር ክልል አወቃቀር ለዋለልኝ መኮንን የብሔረሰብ ትግል ጥያቄ በቂ ምላሽ አላስገኘም። ዋለልኝ መኮንን፤ በብዕሩ ጽፎ ህዳር 17 ቀን 1961 ዓ.ም “ታገል” መጽሔት ላይ ያሰፈረው ሃሳብ፤ “ብሔራዊ መንግሥት ዕውን የሚሆነው፣ ሁሉም ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋቸው ሲከበርላቸው፤ በመንግሥት ጉዳዮች በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ ሲኖራቸው ነው” እንጂ በቋንቋ ግድግድ አጥር ለየብቻቸው ሲከለሉ ነው ጭራሽ አላለም። ኢብሳ ጉተማ “ኢትዮጵያዊው ማን ነው?” በማለት፤ ዕኩልነት ባልሰፈነባት አገር ስለሚኖሩት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ጭቆና “ታገል” መጽሔት ላይ ለዛ ባለው ግጥም ሲያቀርብ ኢትዮጵያውያን በድንበር ተከፋፍለው በብሔረሰብ ጥላቻ ዓይን እየተያዩ በጉርብትና እንዲኖሩ በነበረው ምኞት አልነበረም፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ ደም ያለው ዋለልኝ መኮንን በወሎየነቱ፤ አማራነቱ ብሎም ኢትዮጵያዊነቱ የሚከፋ አልነበረም፤ ኢብሳ ጉተማ በቄለም ወለጌነቱ፤ በኦሮሞነቱ ብሎም በኢትዮጵያዊነቱ የሚከፋ አልነበረም፡፡ ርዕያቸው በደም ስለተሳሰሩ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ከመደብ ጭቆና ስለመላቀቅ፤ ስለዴሞክራሲ መብቶች መከበርና በዕኩልነት አብሮ ስለመኖር ነበር። “ሕዝቦች በየነበሩበት የአስተዳደር ግዛት ማህበረሰባዊ ፍትህ ያግኙ”፤ በቋንቋቸው ይማሩ፤ ይዳኙ፤ በዕኩልነት ይኑሩ፤ መሪዎቻቸውን ራሳቸው ይምረጡ” የሚል ነበር እንጂ የብሔረሰቦች ሕዝቦችን በቋንቋ ግድግድ አጥር ስለመለያየት፤ የዘመናት የጋራ ታሪክና የተገነባ የእኛነት ስሜታቸውን ስለማክተም፤ ብሔረሰቦች ሕዝቦችን አጎራብቶ በጠላትነት እንዲተያዩ ስለማድረግ አልነበረም፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች የብሔረሰብ ትግል ጥያቄ ተዛብቶ ለኪራይ መሰብሰቢያ እንዲውል ተደርጓል፡፡ የፌደራሊዝምንና የዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነትን የመዝገበ-ቃላት ትርጉም የመወትወት ልክፍትን በመሻር፤ ሕዝቡን ከማታከት በቅድሚያ ጽንሰ-ሓሳቡን መረዳት፤ በጥርጊያ መንገዱ ላይ የተቸነከሩትን ዕንቅፋቶች መጠራረግና በተገቢው መንገድ በአዲስ መልክ ለመተግበር ከልብ መነሳሳት የአገራችን ሕልውና ጥያቄ ነው፡፡
አዎ! በአገራችን የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ፤ ጠረኑ እየሸተተ ነው፡፡ አገራችንን ከገባችበት አቆራኝ ቀለበት ለማውጣት የሁላችንንም ተሳትፎ ይጠይቃል። የተጋትነውን መነባንብ በማስወጣት በአዲስ የአስተሳሰብ ቅኝት ለመተካት የልቦና ውቅር ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ አሮጌ አስተሳሰብንና መንግሥታዊ መዋቅርን ጨምድዶ በመያዝ ወይም የብሔረሰብ ፓርቲ ልምድ ኮርጆ፣ እንደ ገና ወደ ኋሊት በመጓዝ፣ በአገራችን የሚታሰብ አንዳችም ገንቢ ለውጥ ሊኖር አይችልም፡፡ ከአሁኑ የለውጥ ነፋስ ሕዝቡ እየጠበቀ ያለው ውድ ስጦታ፤ ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ መስጠት ነው፡፡


Read 442 times