Monday, 21 February 2022 00:00

ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዋጋ ያስከፍላል

Written by  ወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ (አልታ ካውንስሊንግ)
Rate this item
(1 Vote)

(የጥቅሙን ያህል ጉዳትም ያስከትላል)
       
           ዴብራ ብራድሊ ሩደር የተባለች የኮሙኒኬሽን ባለሙያና የሃርቫርድ መፅሔት ጸሐፊ ስለ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ስትናገር በምሳሌ እንዲህ ብላለች፡-  “እሳት ምግብን ለማብሰል ትልቅ ግኝት ነው፤ ነገር ግን ማወቅ ያለብን እሳት የሚጎዳና የሚገድል መሆኑንም ጭምር ነው፡፡”  
የሰዎች አኗኗር ለውጥን ተከትሎ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎችና አይነቶች ይፈጠራሉ።  በቅርብ ጊዜያት ዲጂታል ቴክኖሎጂና ሚዲያ፣ በሰዎች ስነልቦናና አጠቃላይ አኗኗር ላይ የፈጠሩትን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያጠና የሳይኮሎጂ ዘርፍ ተፈጥሯል፡፡ ይህም የሳይኮሎጂ ዘርፍ ዲጂታል ሳይኮሎጂ ይባላል፡፡ Dr. Sreeroopa Sarkar (ዶከተር ሴሮፓ ሳርካር) የተባለች በዋልደን ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ የትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆነች ምሁር፣ ዲጂታል ሳይኮሎጂን ስትገልጠው፤ “ዲጂታል ሳይኮሎጂ፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂና ሚዲያ በሰዎች ስነልቦና ጉዳዮች ላይ ማለትም አመላካከት፣ ባህርይ፣መነሳሳት፣መማርና ባህርያት ላይ የሚፈጥረውን ተፅእኖ የሚያጠና የሳይሎጂ ዘርፍ ነው” ብላለች፡፡
ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ሚዲያ አካላዊ፣ ስነ አዕምሯዊ፣ ሞራላዊ፣ የስሜት፣ የጤና እና ፆታዊ የግንኙነት እድገቶች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚፈጥሩ በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በትምህርት፣ በሥራ፣ ፋይናንስና ማህበራዊ ግንኙነቶቻችን ላይ አፍራሽ ሚና ይጫወታሉ፡፡  በዚህ ዘመን SCREEN TIME እየጨመረ GREEN TIME እየቀነሰ መሄዱን እለት ተዕለት አኗኗራችን የሚነግረን ሲሆን ጥናቶችም ይጠቁሙናል። ስክሪን ታይም ሰዎች ኮምፒዩተር፣ ቴሌቪዥንና ፊልም እየተመለከቱ የሚያሳልፉት ጊዜ ሲሆን ግሪን ታይም ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር እና በአካባቢያቸው የተለያዩ ክንውኖችን እያደረጉ የሚያሳልፉበት ከዲጂታል ቴክኖሎጂና ከሚዲያ ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የስክሪን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳዩ ጥናቶችን ማየቱ ይጠቅማል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሰው በአማካይ በቀን 6 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ሰክሪን ላይ ያሳልፋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 3 ሰዓት ከ15 ደቂቃውን የሚያሳልፈው ሞባይሉ ላይ ነው፡፡ አንድ አሜሪካው በቀን በአማካይ 7 ሰዓት ከ11 ደቂቃ በስክሪን ላይ ያሳልፋል፤ እንግሊዛዊው ደግሞ በቀን በአማካይ 6 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ስክሪን ላይ ያሳልፋል። ስክሪን ላይ የማሳለፍን ነገር የፊሊፒንስ ዜጎችን የሚደርስባቸው የለም፡፡ ፊሊፒኖስ በቀን በአማካይ 11 ሰዓት በስክሪን ላይ ያሳልፋሉ፡፡ አንድ ሰው በቀን በአማካይ 8 ሰዓት የእንቅልፍ ጊዜ አለው ብለን ብንነሳ፣ የፊሊፒንስ ዜጎች 70% የሚሆነውን ንቁ ጊዜያቸውን በኮምፒዩተር ወይም በሞባይላቸው ላይ ያሳልፋሉ፡፡ ጃፓኖኝ 27.5% ንቁ ጊዜያቸውን በስክሪን ላይ በማሳለፍ ዝቅተኛውን መጠን ይይዛሉ፡፡
በዓለም ደረጃ ሰዎች በቀን በአማካይ 34.94% የሚሆነውን የስክሪን ጊዜያቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሳልፋሉ፡፡ ነገር ግን ሶሻል ሚዲያን በመጠቀም ግብፅ (40.7%) ሳውዲ አረቢያ (40.9 % ) እና ኢመሬትስ (34.94) ከፍተኛውን መጠን ይይዛሉ፡፡
በጥቅሉ ኤዥያና ደቡብ አሜሪካኖቹ ከሌላው በበለጠ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስክሪን ላይ  ያሳልፋሉ፡፡
ደቡብ አፍሪካውያን በአማካይ በቀን 10 ሰዓት ከ 7 ደቂቃ ስክሪን ላይ ያሳልፋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የተሰራ ጥናት አላገኘሁም፡፡
ዲጂታል ቴክኖሎጂን በገፍ ብንጠቀም ምን ይጎዳናል?
ዲጂታል ቴክኖሎጂና ሚዲያ ጎትጓች ነው:- እረፍት አይሰጥም፤ ከአንዱ ትዕይንት ወደ ሌላ ትዕይንት ያንከራትታል፣ “እዩኝ እዩኝ፤ ስሙኝ. ስሙኝ” የሚል ጎትጓችነት ስላለው ጊዜን ትርጉም ላለው ሥራና በዓላማ መር ህይወት ላይ እንዳናሳልፍ እንቅፋት የመሆኑ እድል ሰፊ ነው፡፡  ቆሎ ፊት ለፊታችሁ ሲቀመጥ አሁንም አሁንም እየዘገናችሁ ከመብላት ጋር ይያያዛል፤ አንዳንድ ሰዎች ቆሎው ከፊታቸው ካልተነሳ ቆሎ ጠግበው መብላታቸውን አያቆሙም፡፡
ጥገኛ ያደርጋል- ሞባይላችሁን ቤታችሁ ረስታችሁ ብትወጡ ምን እንደሚሰማችሁ አስቡ- ጭንቀት ጭንቀት ይላችኋል፤ ከአለም እንደተቆራረጣችሁ ያህል ይሰማችኋል፤ ቤታችሁ ደርሳችሁ እስከምታገኙት ትቸኩላላችሁ፤---እስቲ ሌላ እንዲህ የሚያደርጋችሁን አስቡ--የተዋችሁት ሥራ ነው? ቤት ትታችሁት የወጣችሁት የቤተሰብ አባል ነው? ወይስ ማንበብ የጀመራችሁት መፅሐፍ ነው? ---እርግጠኛ ነኝ የሞባይላችሁ ይለያል!
የአንጎል ቅርፅንና አሰራሩ መቀየር፡- አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በከፍተኛ ደረጃ ቴክኖሎጂ ላይ መጣድ የአንጎል ቅርፅንና አሰራሩን የመቀየር ሃይል አላቸው፡፡ ቴክኖሎጂው፤ በአንጎላችን መመረት ያለባቸው ሆርሞኖች በበቂ መጠን እንዳይመረቱ ያደርጋል፡፡
የማያቋርጥ መዘናጋት- አንድ ሰው በቀን ከ85 ጊዜ በላይ ሞባይሉን አን ሎክ (ይከፍታል) እንደሚያደርግ አንድ በእንግሊዝ አገር የተጠና ጥናት ይጠቁማል፤ ሁሉን ነገር በጣት በመንካት የምናገኝ ከሆነ አዕምሯችንን  የማሰብ  ዕድል እንነፍገዋለን፡፡ በዚህም ምክንያት ሳናላምጥ እናስገባለን፤ ሳናላምጥ እናስወጣለን፤  ልክ እንደ ኮምፒዩተሩ  (garbage in garbage out)፡፡ በጥልቀት ማሰብና ማገናዘብን እንዲሁም የማመዛዘን አቅማችንን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል፡፡
የእንቅልፍ መዛባት፡- አብዛኛው ሰው ስልኩን ይዞ ወደ መኝታው ይሄዳል፤ አንድ ነገር ለማየት ወይም ለመፃፍ ብድግ ያደርገውና ሳያውቀው ከአንድ ሰዓት በላይ የተለያዩ ነገሮችን ሲሰማና ሲያይ ይቆያል፡፡ ከዚያ ለመተኛት ሲሞክር እንቅልፍ እንቢ ይለዋል፤ ነገ ስራ አለ፤ ነገ ትምህርት አለ---በሚቀጥለው ቀን በሚኖረው  በብዙ ተግባሩ ላይ ውጤታማነቱን ይቀንስበታል፤ ለጭንቀትና ለስጋት ይዳርገዋል፡፡  ከእንቅልፍ በፊት ሞባይል ላይ ማሳለፍ የእንቅልፍ ሆርሞን እንዳይመረት ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም አንጎላችን ከስማርት ስልካችን በሚወጣው ሰማያዊ ጨረር ምክንያት የጨረሩ መኖር “ቀን ነው” ብሎ እንዲያምን ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የእንቅልፍ ሆርሞን ባለመመረቱ ቶሎ እንቅልፍ እንዳይወስደን ምክንያት ይሆናል፡፡
የስራና የማረፍን ሰዓት ያዛባል፡- ሞባይልና ኢንተርኔት በሌለበት ዘመን ከሥራ ቦታ ስትወጣ ስራውን ትተህ ትወጣለህ፤ አሁን ግን ከስራ ስትወጣ፤ ወደ ስራ ትገባለህ፤ ቤትህ ሆነህ ኢ ሜይል ትመልሳለህ፤ ሪፖርት ትፅፋለህ። የሥራና የእረፈት ሰዓትህ ክፉኛ ይዛባል፡፡
ከቤተሰብ ጋር የማሳለፊያ ጊዜ ታጣለህ፡- ልጅህን በወጉ አታጫውትም፤ አብረኸው አታሳልፍም፤ ልጅህን አንተ ማሳደግ ታቆምና ሌሎች ያሳድጉልሃል።
ከቴክኖሎጂ ለጥቂት ጊዜ ብትለያይ የጠፋህ ያህል ትፈራለህ፤ ይህም Fear Of Missing Out (FOMO) ይባላል፡፡  ከአንድ ትልቅ ክንውን፤ ከሥራ፤ ትልቅ ማህበራዊ ዕድል ፤ ማግኘት ካለብህ ሰው ወዘተ የጠፋህ ያህል ይሰማሃል፡፡ ስለዚህ ፎሞ እንዳይፈጠር ከሞባይል ስልክህ ላለመለየት ትታገላለህ------ የሚወራውን እንተም እንደሰማኸው፣ የሚታየውን አንተም እንዳየኸው፤ ዜናውን አንተም እንዳነበብከው፣ የተፈጠረውን አንተም እንዳወቅከው ለሌላው መግለፅ ትፈልጋለህ! በዚህን ጊዜ የፎሞ ሰለባ ሆነሃል ማለት ነው፡፡
ራሳችንን ከሌላው ጋር እንድናወዳድር ያደርገናል፡- በአሉታዊ መልኩ ራስን ከሌላው ጋር ማወዳደር ለጤና ጠንቅ ይሆናል፡- እገሌ ስንት ላይክ (Like) አገኘ? ---እኔስ?; የእገሌ ውሎው እንዴት ደስ ይላል? ----የኔስ? እገሌ ስንት ተከታይ አለው?---- እኔስ? አቤት እገሌ የደረሰበት ቦታ! --- እኔስ?  ----አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚንፀባረቁ ፅሑፎች እውነተኛነት ይጎድላቸዋል፤ ወይም ግነት ይኖራቸዋል፤ በዚህም ምክንያት ሰዎች ራሳቸውን በትክክል ካልተገለፀ ማንነት ጋር በማወዳደር ለስነልቦና ጤና መቃወስ ይዳረጋሉ፡፡
የሰውነት ክብደት መጨመር፡-ከኮምፒዩተርና ከስልኮች ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ የሰውነት ክብደት እንድንጨምር ያደርገናል፤ ምክንያቱ ደግሞ  እንቅስቃሴያችን በመገደቡ ብቻ ሳይሆን ስክሪን ታይም ላይ ሆነን ሳናስበው ብዙ ስለምንመገብና በማስታወቂያ ተፅእኖ ምክንያት የምግብ ምርጫችን ላልተፈለገ ውፍረት የሚዳርግ መሆኑም ጭምር ነው፡፡
ማህበራዊ ግንኙነታችንን በእጅጉ ይጎዳል፡- ከሰው ጋር ማሳለፍ፣ ማውራት፣ አብሮ መስራትና መጫወት እየከበደ ይሄዳል! በህፃናት ላይ ደግሞ የቋንቋ እድገታቸውንም ጭምር ይገድባል፡፡
የቴክኖሎጂ ሱሰኝነት- እንደሌላው ማለትም እንደ አልኮልና ሲጋራ ሲኮነን ስለማይታይ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ እንዳንድ ጥናቶች የቴክኖሎጂ ሱሰኝነት፣ አደንዛዥ ዕፅ ከሆነው ከኮኬን የማይተናነስ ክብደት አለው፡፡
ድብርት፤ ጭንቀትና ጫና ይፈጥራል
ጠብ ጫሪነትና ብስጭት ሊፈጥር ይችላል፡- የምናያቸው ፊልሞችና የምንጫወታቸው ጌሞች ባህርያቱን በተመልካቹ ላይ የማስተላለፍ ሃይል አላቸው፡፡ ይህ ደግሞ በልጆች ላይ ይበረታል፡፡
አካላዊ ጉዳት፡- ብዙ ስክሪን ታይም ለአይን ጉዳትና ራስ ምታት የሚዳርግ ሲሆን ከደም ብዛትና ከልብ ጋር ተያያዥነት ላለው ህመም፣ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ውፍረትና  ወዘተ ጋር ተያያዥነት አለው
ሌሎችም ተፅእኖዎችን ይፈጥራል። ለምሳሌ የትኩረት ማነስ፣ የፈጠራ ክህሎት ማነስ እንዲሁም የአዎንታዊ ስሜቶች ለምሳሌ ደስታ፣ ተስፋ፣ መደነቅ ወዘተ ስሜቶች መመናመንን ይፈጥራል፡፡
ብዙ የስክሪን ጊዜ ልጆች ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ደግሞ ከፍ ይላል፡፡
በመጨረሻም ልክ እንደ ዴብራ ብራድሊ ሩደር እኔም እላለሁ፤ “ዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀት ለማስፋት፣ ለፈጣን ግንኙነትና ሥራን ለማቅለል ትልቅ ግኝት ነው፡፡ ነገር ግን ማወቅ ያለብን ዲጂታል ቴክኖሎጂ የማሰብ አቅማችንንና የፈጠራ ክህሎታችንን የሚጎዳና ጤናችንን የሚገድል መሆኑንም ጭምር ነው”፡፡   መፅሐፍ እንደሚል፤  “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅምም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳን አይሰለጥንብኝም”
ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጉዳት ለመዳን ምን እናደርግ? የሚለውን ጥያቄ በሚቀጥለው ሳምንት አንስተን እናወጋለን፡፡ እስከዚያው ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በ ኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡

Read 2140 times