Sunday, 20 February 2022 16:51

ያልተገለጠው የውጭ ፖሊሲ ውጥንቅጥ

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ - ከቤተሳይዳ ሜሪላንድ፣ አሜሪካ
Rate this item
(1 Vote)

«ነገሮችን እንደራሳቸው (እንደነገሮቹ) አይደለም የምንመለከታቸው፡፡ ይልቁንም እንደራሳችን ነው የምናያቸው” የሚል አገላለጥ ከኪዩባ ፈረንሳዊቷ ጸሀፊ አንጄላ አናኢስ ኒን ነው የተገኘው፡፡ በ’አይሁዳውያን ጥንታዊው ታልሙድ የቀደመ ምንጭ አለው’ ይላሉ በሰሎቹ፡፡ እና የምናየው እንደምናየው ነገር ባህርይና ተፈጥሮ ወይም ይዘትና ምንትነት አይደለም፡፡ የምንተረጉመውም የምንመለከተውም - እንደ ራሳችን ይሆናል እንደማለት ያለ፡፡ በዚህም የተነሳ አንድ ክስተት ላይ ያለንና የሚኖረን አተያይና አተረጓጎም እየቅል ይሆናሉ፡፡ ድሮ (የእኔ ድሮ ማለቴ ነው) በኖርኩባት አዲስ አበባ፣ ‘ቤራንቲን’ የሚባል የጉንፋን ፈሳሽ ሲሮፕ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡ ጠርሙሱ ካልተሳሳትኩ ድርፉጭ ያለ ቡናማ ቀለም ያለውም ነበር፡፡ አንድ ከሰፈራችን ጠጅ የቀዳ (የውቤ በርሃ እድሜ ቀጥል ጠጅ ቤት ይመስለኛል) የጠገበ ሰካራም ወደ ፋርማሲ ይገባና፤ “ያንን ቢራ(ላ) ስጠኝ” ይላል ከመደብሩ ለቆመው አስተናጋጅ፣ ወደ ጉንፋን መድሃኒቱ ‘ቤራንቲን’ ጠርሙስ እያመለከተ። የመደብሩ አስተናጋጅም፤ “ይቅርታ ይሄ ቢራ አይደለም፣ ቤራንቲን ነው!” ቢለው “እሱ እንዳስተያየቱ ነው!” ብሎት አረፈ አሉ፡፡
ይሄ ‘እንዳስተያየቱ’ ይሉት አሰኛኘትን ያስታወሰኝ፣ ሰሞኑን የተገጫጩ ኹነቶችን በእኛው ዓውድ ውስጥ አስተውዬ ነው። የአፍሪቃ ህብረት መሪዎች 35ኛው ጉባኤያቸውን በኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ የማካሄዳቸው ዜና የቅርብ ነው፡፡ በጦርነት አጣብቂኝ ገብታ - ‘መያዣ መጨበጪያ ወደሌለው ቀውስ ሀገሪቱ ልትገባ ነው’፣ ‘የኤምባሲ ሠራተኞቻችንም ለቃችሁ ውጡ’ - ‘ዜጎቻችንም ከመጓዝ ተቆጠቡ’ እየተባለ የተወተወበት ሰሞን፣ የድምጹ ርግብግቢት ከእዝናችን ሳይጠፋ ነው ይህ ስብሰባ የተካሄደው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ፊኛ እንኳን ሳይፈነዳ የመሪዎቹ ስብሰባ ተካሂዶ፣ እንግዶቹ ተስተናግደው፣ በሰላም ተሰናበቱ፡፡ በስብሰባው ሰሞን ፌብሩዋሪ 3 ቀን 2022 የዩኤስ አሜሪካ ኤምባሲ ደግሞ ከወራት በፊት ጀምሮት የነበረውን ‘ሰማይ ሊወድቅ ነው’ ማስፈራራቱን የመቀጠሉን እወጃ ተመለከትኩ፡፡ ለእኛ ለዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ - “የአትጓዙ ፍርሃቱን” የማወጁን ነገር ስመለከት፤ የጉንፋን መድሃኒቱ ጠርሙስና የቢራው ታሪክ እየመጣብኝ ‘እንዳስተያየቱ’ ነው ማለቴ አልቀረም፡፡ ወይም ረቀቅ ጠለቅ እናድርገው ካልን - ወደ ቀደመው የአናኢስ ኢን አገላለጥ ልንሻገር እንችላለን፡፡
በእንግልጣሩ የልጆች ተረት ‘ሄኒ ፔኒ’ ወይም ‘ችክን ሊትል’ ‘ሰማይ ሊወድቅ ነው’ የሚል ተረት አለ፡፡ ሰማይ ሊወድቅ ነው የሚለው ማስፈራሪያ ዛሬ በውጭዎቹ ክፉ የሚተነበይልን ስለምን እንደሆነ ብዙ ግራ ሊያጋባን ይችላል፡፡ የዚህ ሳቢያው መረጃ ይሁን ምኞት ውስጡን መፈተሽ ይገባል። ሀገሪቱ ውስጥ ግጭትና መፈናቀል ሙሉ ለሙሉ የተወገደበትን ጊዜ በእኔ ዕድሜ ስላላየሁ - የማስፈራሪያ ደወሉ አብዝቶ ሲደወል ይሄ ‘እሳት ሊነሳ ነው እንዴ’ ከሚል ስጋት፣ ከቶ ማስፈራራቱ ምን ይዞ ይሆን? ብዬ ይጨንቀኛል፡፡ እንዲህ ያለው ማስፈራሪያ ደግሞ ከምዕራባዊ መንግሥታቱ ብቻ ሳይሆን ከኮርፖሬት ሚዲያዎችም ይበልጡኑ ሲናፈስ - ተንታኝ በተባሉትም አንደበት ሲበተን ስናይ ስጋት ቢያድርብን አይፈረድብንም፡፡
ዩኤስ አሜሪካ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት ወጣ ገባ አይነት ይመስላል፡፡ የግንኙነቱ ቀዳዶች የሚታዩ - ግን ደግሞ ቀዳዳ የማይመስሉ አይነት ናቸው፡፡ በዙሪያ የተከሰቱትን ኹነቶች ምክንያታቸውንና ወደየት ሊጓዙ እንደሚችሉም ማመላከት ይገባል፡፡ ቢያንስ ጉዳዩ ያገባኛል የሚሉ እንዲያጤኑትም ይረዳቸው ይሆናል፡፡ እርግጥ አሁን- አሁን እዚህ ዋሽንግተን የኢትዮጵያ መንግሥት ምንጮች፣ ከ’አሜሪካ’ ጋር ያለን ግንኙነት እያገገመ’ ነው ይላሉ፡፡ በሀገራት መካከል ያሉ ግንኙነቶች ከጥቅሞቻቸው የሚመነጩ ስለሆነ የተዛባው በምን ተቃና - የጎደለው በምን ተሟላ ብሎ መጠየቅ ይገባ ይሆናል፡፡ ወይም ለኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ ሥራ ሀላፊነት የተጣለባቸው - ‘ሠርተናል’ ለማለት ብቻ የሚያሰራጩት ወንዝ የማያሻግር ፉከራ እንዳይሆንም መጠርጠር ይገባል፡፡ የሆነው ሆኖ ጥቃቅን የመሻሻል ምልክቶች የሚመስሉት ጊዜያዊ ማባበያ እንደሆኑ ተገንዝቦ የውጭ ፖሊሲን ከብሄራዊ ጥቅሞቻችን ጋር መፍተልና ማቆራኘት ይጠበቅብናል፡፡ በዚህ ‘ግንኙነቱ’ ተሻሻለ በተባለበት ሰሞን ያሉትን እንቅስቃሴዎችና ወሬዎቹን በጥቂቱ እንፈትሽ፡፡
በዜናዎቹ መካከል እንደ ዘበት ተወሽቆ ያለፈ ኹነት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የዩኤስ አሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በግላቸው ፈቃድ ሌሎች ዕድሎችን ለመከተል ሲሉ ከሀላፊነታቸው ለመገለልና ጡረታ ለመውጣት የመወሰናቸው ዜና አብይ ነበረ። ዓመት ከምናምን ወሮች በአምባሳደርነት ያገለገሉት ፓሲ፤ በዚህ ፍጥነት ‘ሌሎች ዕድሎችን ለመከተል’ ያስወሰናቸው  ነገር ‘ምን ይሆን?’ የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ የሀላፊነት ደረጃ ዓመት ከስድስት ወራት ላልሞላ ጊዜ ብቻ አገልግለው ‘በቃኝ’ ለማለት የመፍጠናቸው ዜና በእርግጥ ጥቂት ግር ያሰኛል፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭትና በዚህ ዙሪያ ያሉትን ተግዳሮቶች በተመለከተ የአዲስ አበባው ኤምባሲ የነበረው ሚና ግን ምን ነበረ? ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ዋና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የሚመጣለትን ውሳኔ ብቻ በማስተናገድ ብቻ ኤምባሲው የተወሰነ ነበርን? ኤምባሲው ከመስኩ የሚያሰባስበውና ወደ ማዕከሉ የሚያሳልፈው መረጃ ዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቱባ ሹማምንቱ መስማትና ማየት ከሚፈልጉት ጋር የተጣረሰ ሆኖ ክፍተት ፈጥሮ ይሆን? ረዥም ተሞክሮ ያላቸው አምባሳደር እንዲህ ሲለዩ ግን ይገርማል፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ የውጭ ጉዳይ ምንጮች፣ ሰሞነኛው የአምባሳደሯን መልቀቅም ይሁን የልዩ መልዕክተኛውን መነሳት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ መልካም ‘አይቶታል’ የሚል ድፍን ግምጋሜ እንዳላቸው ሰምቻለሁ፡፡ ይሁንና በዩኤስ አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ የኢትዮጵያን አቋም በተወሰነ ደረጃ ከመስኩ እውነታ ጋር በማያያዝ ለማየት የሚሞክሩ ክፍሎች፣ ከሰሜነኞቹ ጋር ወዳጅነታቸው በጸኑት ዘንድ በጎሪጥ የመታየት አደጋ እንደገጠማቸው የሚጠቁሙ ደግሞ እንዳሉ ጭምጭምታ አለ፡፡ ከዩኤስ አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ሰብዕናዎች መካከል አምባሳደር ፌልትማንም ይሁኑ አምባሳደር ፓሲ የእነዚህ ኢላማ ይሁኑ አይሁኑ ግን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ የሆነው ሆኖ በመስኩ ላይ ኢትዮጵያ ባሳየችው ወታደራዊ ብልጫና ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅሟን ከማገናዘብ የመነጨ የመለሳለስና ፋታ የመስጠት አዝማሚያ በዩኤስ አሜሪካ በኩል ይታይ ይሆናል፡፡ ይሁንና ስጋቱ ጨርሶ ተገፏል ወይ? የሚለው አነጋጋሪ ነው።
ዩኤስ አሜሪካ በውጭ ፖሊሰ ዙሪያ ያሏት ዋነኛ አሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ነጻና ገለልተኛ ሆነው ለማየት ያላቸውን ፍላጎት እስከ መጨረሻው መጠርጠር ክፉ አይመስለኝም፡፡ ከኤምባሲው በሚወጡት የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች ዙሪያ ጥያቄ ይነሳል። በምላሹ  -›ይህ የሚሰራጨው ማስታወሻ የሚዘጋጀው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን የየዘርፉ ቢሮዎች ያጠናቀሩት ድምዳሜ ነው’ - ‘ይህ ለዜጎቻችን ደህንነት ሲባል የሚወጣ ነው’ የሚሉና የተለያዩ መግለጫዎችና ማብራሪያዎች በዋሽንግተን በኩል ይሰጣሉ፡፡ ከኢትዮጵያው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ጋር ዩኤስ አሜሪካ ያላት ግንኙነት፣ ከሰሜኑ ግጭት ጋር ተያይዞ የነበረው ክፍተት ተሞልቷል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ዩኤስ አሜሪካ ብሄራዊ ፍላጎቴ ብላ የያዘችውን ለማሳካት የምትጠቀምባቸው እጆቿ ረዣዥም እንደሆኑ ማሰብ ይጠቅማል፡፡
የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካዊ ፋይዳ ከወቅቱ የፖሊሲ ገበጣ ጋር ተያይዞና ተቆላልፎም ነው የሚታየው፡፡ ከሩስያና ከቻይና ጋር ያለው የመጎነታተልና የመጓተት ሁኔታ አፍሪቃን ልክ እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ዋነኛ አውደ ግንባር እንዳያደርጋት የሚሰጉ ብዙ ናቸው፡፡ ዩኤስ አሜሪካ ሩሲያንም ሆነ ቻይናን በሪጅናቸው የቤት ሥራ ለመስጠት የምትሞክርበት ሂደት እንዳለ ሆኖ፣ በዓለም ዙሪያ ያላቸውን ተፅዕኖ ለማለዘብ የምታደርገውም ሙከራ አብሮ ነው የሚታየው፡፡ ቻይናን በታይዋን፣ ሩሲያን በዩክሬይንና በሌሎች ችግሮች እንዲወሰኑና አቅማቸውን እንዲያጠፉ የማድረጉ ሂደትን ባየንበት፤ ዩኤስ አሜሪካን ደግሞ  በሌሎች ክፍለ ዓለማት ባላሰበችው ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ እንድትጠላለፍ ተቀናቃኞቿ በፊናቸው ማስላታቸውም አይቀርም፡፡
በኢትዮጵያ ሰሞነኛ ሁኔታ አንዳንድ ገላጭ አብነት የምናደርጋቸው፣ ይህን የርዕሰ ኃያሏንና የሌሎችን መጓተቶች የሚጠቁሙ ክስተቶችን ማንሳት እንችላለን፡፡ ዩኤስ አሜሪካ ለአፍሪቃ ንግድ ማበረታቻ ብላ ከመሰረተችው ‘አጎዋ’ ኢትዮጵያን ሰረዘች በተባለ ማግስት፣ ቻይና ለኢትዮጵያ ንግድ ገበያ በመፍጠሩ ረገድ ተመሳሳይ ውጥን ይዛ ብቅ ማለቷን ያጤኑዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የሩሲያ ፕሬዚዳንት የመካከለኛ ምስራቅና አፍሪቃ ልዩ መልዕክተኛ፣ በአዲስ አበባ ተገኝተው፣ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መነጋገራቸውና ስለ ሩሲያ-አፍሪቃ ጉባኤ መምከራቸው ተዘግቧል። አሜሪካም ሆነች የሪጅናል ኃይል የሚባሉት ተፎካካሪዎቿ፣ ለኢትዮጵያ ጥቅምና ፍላጎት ብለው ይደግፉናል ወይም ይቃወሙናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ጥቅሞቻቸውን አስልተው የሚያሳኩበትን መንገድ ቀይሰው ነው የሚንቀሳቀሱት። በዚህ መሀል ኢትዮጵያ ደግሞ የራሷን ጥቅም ለማሳካት የምትችልባቸውን ዘዴዎች ከዚህ ወይም ከዚያ ጠቃቅሳ አዋህዳ መጓዟን ግድ ይላታል። ከዚህ ወይም ከዚያ ጋር እንደቆረበች ሆና ‘በክፉም በደግም’ አልለይም ልትል አይገባትም፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ አጥፍተው ለመጥፋት በተነሱት አማጽያን የተነሳ እንደ ሀገር ከምንፈተንበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። ለውጭው ባዕድ ኃይል መጋለጣችንም አልቀረም፡፡ በእርስ በእርስ ግጭቶቻችን የባዕዳንን እጅ የሚያስገባ አደገኛ አጋጣሚም ተፈጥሮብናል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የአማጽያኑ የማግባባትና ተፅዕኖ የመፍጠር ዘመቻ፣ አሁንም የተለያዩ ስልቶችን ይዞ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ዘመቻ በጀርባ የሚያማክሩ አፍቃሬ-ህወሓት ባዕዳን፣ የየበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ እርግጥ ነው ቀደም ሲል ከነበረው ሕወሓትን ብቻ የማድመጥ አባዜ በመጠኑም ቢሆን ለውጦች እየታዩ ነው። ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የአሜሪካው ቤተ መንግሥት (White House) ያቀናጀው አንድ ዝግ ስብሰባ በምስጢር ስለመካሄዱ ተሰምቷል፡፡ ይሄ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ምስጢራዊ ስብሰባ ሲሆን ከቀደመው በስብጥሩ ለየት ያለ ነበር፡፡ ይሄ ‘ዝግ ስብሰባ’፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንና - የዚህም ሀገር ተወላጅ ዜጎች የተሳተፉበት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ አንዳንድ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለመግለጽ የሚችሉ ሰዎች ታድመውበታል ተብሏል፡፡  ምንም እንኳን እድል አግኝተው ባይናገሩም ለአብነት መካተታቸው በራሱ  አንድ እርምጃ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ስብሰባው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ላይ ያነጣጠረ እንደነበረ ተገምቷል። የአማጺው ደጋፊዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲያግለበልቡት የቆዩት የ’ዘር ጽዳት’ ውንጀላ ቀዝቀዝ ብሎ የተሰማበትም ነበር ተብሏል፡፡
ይህ የነጩ ቤተ መንግሥት ‘ዝግ ስብሰባ’ ዓላማው ምን እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች ቢመስልም፣ በ’በቃን’ ወይም  No More እንቅስቃሴ የተነሳሳውን ስሜት የማባረድ - ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን የመለየትና የመከፋፈል እንዳይሆን የሰጉ ወገኖች አልጠፉም፡፡ የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር በመጪው የስልጣን ዘመኑ አጋማሽ ምርጫ ላይ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ድምጽ ከኢትዮ-አሜሪካውያን እንዳይተጓጎልበት ከወዲሁ የዘየደው መላም ሊሆን ይችላል፡፡ በውጭ ፖሊሲው ዙሪያ ያለው መዘበራረቅን ተንተርሶ የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትር ክቡር አንቶኒ ብሊንከንም፣ ከዚያው የዲሞክራት ወገን ችግር ሳይገጥማቸው እንደማይቀርም አንዳንድ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የምዕራባውያንን በተለይ የአሜሪካንን እገዛና ይሁንታን የሚሹ የትህነግ ደጋፊና አባላቱ፣ እዚህ አሜሪካ የበዛ ገንዘብ እየበተኑና ለአግባቢ ድርጅት እየከፈሉ፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው ግጭት በሰላም እንዳይጠናቀቅ ለማድረግ ያላቸው እኩይ ፍላጎት፣ እንኳንስ ለወገን ለባዕዳኑም ግር የሚያሰኝ እንቆቅልሽ ነው፡፡ በውጭ ደጋፊዎች እገዛና  እርዳታ የሚንቀሳቀሱት አማፅያን - በዲያስፖራ ደጋፊዎቻቸው ‘ግፋ ወደፊት’ በሚል እየተሠራ ያለው ግፍ የብዙዎችን ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ባዕዳኑ ያላቸውን የውጭ ፖሊሲ ተጠየቅ ስንመረምር - በጥቅማቸው ላይ የተመረኮዘ አካሄዳቸውን ስናጤን - የእኛ ነገር ግን ለሰሚውም፣ ለተመልካቹም እንደገረመ አለ። እርግማን የደረሰብን ይመስል በእኛው መካከል አንዱ ከዚህ፣ ሌላው ከዚያ ተሰልፎ ለውጭ መናጆ የመሆኑ እውነታ አሳዛኝ ነው። በታሪካችን እንደታየውም፣ የውጭዎቹ ተጽዕኖ የሚበረታው ቤታችን ሲከፋፈል ብቻ ነው፡፡


Read 1832 times