Sunday, 20 February 2022 16:56

“የአፋችሁን ሳይሆን የልባችሁን...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- ኸረ ረጋ በል! ማነህ እንዲህ በቅጡ ሳይነጋ ከጣራ በላይ የሚያስጮህህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ኸረ ተው እንዲህ በቀላሉ አትርሳኝ! ተው አንድዬ፣ ተው!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፤ አንተም ይሄ በቅጡ ሰላም እንኳን ሳትል የምታማርረውን ነገር ተወኝ እያልኩህ አሻፈረኝ አልከኝ ማለት ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እያማረርኩ አይደለም፡፡ ደግሞስ አየሁት ለየሁት እኮ! ባማርርስ ምን እንዳላመጣ ነው! ከበሽታ በቀር ትርፍ እንደሌለው አየሁት እኮ! ልማድ ሆኖብኝ ነው የምለፈልፈው፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ አሁንም ድረስ እኮ እንዴት ከረምክ፣ በጎ ሰነበትክ ወይ... እህሉስ፣ ከብቱስ አላልከኝም እኮ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- እውነቴን እኮ ነው! እኔስ ብሆን ደግ ወሬ አያምረኝም! ሁልጊዜ የእናንተን ምሬት ስሰማ እንደው ትንሽ አንኳን አለሳዝናችሁም?
ምስኪን ሀበሻ፡- አን...
አንድዬ፡- ግዴለም ተወው፡፡ ይሄ እንደው በሠላሳ ጣታቸው የጨመደዱት መሀረብ የመሰለው ፊትህን ፈታ ላድርግልህ ብዬ ነው። ዝም ትለኛለህ እንዴ... አጨብጭብልኝ እንጂ ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ለምኑ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡- እናንተ ይሄ ምንድነው አራዳ ቋንቋ ነው ምናምን የምትሉትን ስለተናገርኩ፡፡ ተወው... እንደውም እናንተ ሊጨበጨብለት ለሚገባው ነገር ማጨብጨብ ትታችሁ፣ ቿ! ቿ! የምታደርጉት ለፍሬከርስኪው ከሆነ ስለከረመ፣ እኔው ለራሴ አጨብጭቤያለሁ። እስቲ ንገረኝ፣ ዛሬ ደግሞ ከወትሮው በተለየ ሆድ የባሰህ ነው የሚመስለው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፤ እኔ እንደውም እየፈራሁ ያለሁት፣ ባሰኝ የምለው ሆድ፣ ትንሽ ቆይቶ ከቦታው እንዳይሰወር ነው፡፡
አንድዬ፡- ቆየኝማ ምስኪኑ ሀበሻ፤ እኔ የማላውቀው ይሄን ያህል ምን ከባድ ነገር ተፈጥሮ ነው፣ እንደው ሁሉ ነገርህ እንዲህ ስብርብር ያለብኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ፣ አንድዬ! ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ! እንደው ብቻ እዚህም መጥፎ ወሬ ነው፣ እዛም መጥፎ ወሬ ነው፡፡ እዚህም ክፋት ነው፣ እዛም ሸፍጥ ነው፣ እወዲያ ማዶም ተንኮል ነው፡፡ አንድዬ እየኖርን ያለን እንዳይመስልህ፡፡ እንደው ቀፏችን ነው ወዲህ ወዲያ የሚንከላወሰው፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፤ አሁን እኮ እንዲህ ነው ብለህ ለይተህ የነገርከኝ ነገር የለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፤ ላስለፍልፈው ብለህ እንጂ ሳታውቀው ቀርተህ ነው!
አንድዬ፡- ባውቅ ለምን እጠይቅኻለሁ? ምስኪኑ ሀበሻ፤ ደግሞ የገባኝን የማስረዳት ያልገባኝን የመጠየቅ ዴሞክራሲያዊ መብቴን አታፍንብኛ፡፡...አየህ! አየህ አይደል! ትንሽ ፈገግ አስደረግሁህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ካልተቆጣኸኝ እዚህ ላይ እቃወምኻለሁ፡፡
አንድዬ፡- አልቆጣም፤ ደግሞ ተቆጥቼ ሌላ የብሶት ሰበብ ልስጥህ! ግን ምስኪኑ ሀበሻ፤ ተቃውሞህ እኔ ላይ ነው የተናገርኩት ነገር ላይ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድ...
አንድዬ፡- እሺ... እሺ...ቀጥል፡፡  
ምስኪን ሀበሻ፡- እኛ እኮ ጠዋት ማታ ወዳንተ የምንጮኸው፣ እኔም በተደጋጋሚ በርህን የማንኳኳው፣ ከአንተ የሚሰወር ምንም ነገር የለም ብለን ነው፡፡
አንድዬ፡- በእርግጥ ምስኪኑ ሀበሻ እዚህ ላይ ጥሩ የሚባል ነገር ተናግረሀል፡፡ ከእኔ የሚሰወር ነገር መኖር አልነበረበትም። እንደውም እኮ አንዲት ተረት አለቻችሁ አይደል... እኔን ገልጦ የሚያይ ነው ምናምን የምትሉባት!
ምስኪን ሀበሻ፡- ተሸፋፍነው ቢተኙ፣ ገልጦ የሚያይ አምላክ አለ፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ! አየህ፣ ሁሉም ነገር እንደሱ መሆን ነበረበት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እኮ አንድዬ፣ እኛም እኮ ይህንን ነው የምንለው፡፡ ሁሉም ነገር እንደዛ መሆን አለበት፡፡ ልክ አይደለሁም እንዴ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡- እዚህ ላይ እቃወምኻለሁ... የማትቆጣኝ ከሆነ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ተው እንደሱ እያልክ አታስደንገጥኝ!
አንድዬ፡- እኔ የምለው፣ እናንተ በስንቱ ደንግጣችሁ ትችሉታላችሁ? በሚያስደነግጠውም፣ በማያስደነግጠውም! ለዚህ ነው እኮ በሽታውም የሚያጠቃችሁ።
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኛ ዘንድ በሽታ የሚያመጣብን ድንጋጤው ብቻ ሳይሆን ሌሎች በበሽታ ላይ በሽታ የሚጎትቱብን ነገሮች መቶ እጥፍ ናቸው፡፡ እኔ አንድዬ አልዋሽህም አሁን፣ አሁን አንዳንድ ሰዎችን ማየቴ ብቻ በአንድ ጊዜ የጨጓራና የአንጀት በሽታ ነው የሚለቅብኝ፡፡ ደግሞ ትንሽ አመም አድርጎኛል ብለህ፣ ሌሊቱን ስታቃስት ብታድር ውሀ የሚሰጥህ የለም። አንድዬ፣ እመነኝ ትንሹም ትልቁም እኛን አስደንጋጭ ሆኖልሀል፡፡
አንድዬ፡- በዚህ ልከራከርህ ብል እዚቹ እንደቆምን መሰንበታችን ነው። ልመልስህና ተሸፋፍነው ቢተኙ ገልጦ የሚያይ አምላክ አለ ትላላችሁ አይደል?
ምስኪን ሀበሻ፡- እንዴታ አንድዬ! እንዴታ!
አንድዬ፡- ከዛም ሁሉም ነገር እንደዛ መሆን አለበት አልከኝ፡፡ እኔም እቃወምኻለሁ ያልኩህ ይህንኑ አባባልህን ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ?
አንድዬ፡- እኔ መሆን አለበት ሳይሆን መሆን ነበረበት ነው ያልኩህ፡፡ ስዋሶህን ረሳኸው እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አ..አንድዬ፣ አልገባኝም።
አንድዬ፡- መሆን ነበረበት ማለቴ አሁን እንደሱም ላይሆን ይችላል ማለቴ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አልገባኝም፡፡
አንድዬ፡- በፊት በምንም ይሸፈን በምን ገለጥ ሳደርገው እንዳለ ቁልጭ ይላል። ዘንድሮ ግን ገለጥ አድርጌ አየሁት ስል፣ ከስር ሌላ የሚገለጥ ይመጣል፣ እሱን ስገልጠው እንደገና ደግሞ ሌላ የሚገለጥ ብቅ ይልልሀል። እንዲህ እየሆነ እኔም መግለጡ እየሰለቸኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አየህልኝ አይደል አንድዬ፣ አንተንም እንዴት እያስቸገርንህ እንደሆነ አየህልኝ አይደል! አንድዬ፣ አትታዘበኝና እንደው አንዳንዶቻችንን ምን ስትል ፈጠርከን?!
አንድዬ፡- እየው እንግዲህ ምስኪን ሀበሻ ጀመረህ፡፡ እኔንም፣ ልታነካካኝ ጀመረህ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደሱ አይደለም፡፡ ግን ሁላችንም ግራ ግብት ነው ያለን፡፡ እርስ በእርስ ወሬያችን ሁሉ እሱ ብቻ ሆኗል፡፡
አንድዬ፡- እርስ በእርስ እየተደማመጣችሁ ማውራታችሁም ራሱ መሻሻል ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አይደለም፣ አይደለም አንድዬ፡፡ እኔ ስናገረው አበላሽቼው እንጂ እንደሱ አይደለም፡፡
አንድዬ፡- ታዲያ እንዴት ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን መሰለህ አንድዬ፣ እንነጋገራለን ሳይሆን እንለፋለፋለን ብል ይሻል ነበር፡፡ ሁሉም ይለፈልፋል እንጂ ማንም ራሱን ብቻ እንጂ ሌላ ማንንም አያዳምጥም፡፡ አንድዬ፤ ደግሞ ሌላው ነገር ምን መሰለህ፣ ዋነኞቹ ግራ አጋቢዎች፣ ራሳችን እኮ ነን መልሰን ግራ ተጋባን የምንለው፡፡
አንድዬ፡- ምስኪን ሀበሻ፣ ይህ እንኳን አሁን የመጣ ሳይሆን በፊትም የነበረ ነው። ራሳችሁ ጥፋቱን ፈጽማችሁ እኮ ራሳችሁ የፖሊስ ያለህ የምትሉ፣ ራሳችሁ ከሳሽና ዳኛ የምትሆኑ ናችሁ፡፡ ምስኪን ሀበሻ ደህና ስናወራ የቆየነውን አትነካካኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፣ ይቅርታ! አንድዬ፣ አትታዘበኝና እንደው አንዳንዶቻችንን ምን ስትል ፈጠረክን!?
አንድዬ፡- እዚሁ ይቅርታ ብለህ እንደገና እዛው ተመልሰህ ትገባለህ? ሁልህም እኩል ነው የተፈጠርከው፡፡ ይሄ ስወለድ እሱ ቀብቶኝ፤ እሱ ዳሶኝ፣ እሱ እንዲህ አድርጎኝ የሚሉትን እርሳቸው፡፡ ከተፈጠርክ በኋላ ያለው ጉዳይ የየራስህ ነው፡፡ ተግባብተናል፣ ምስኪን ሀበሻ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ አዎ፡፡
አንድዬ፡- በል አሁን ደህና ሁን፡፡ ደግሞ እኔ የምፈልገው እውነተኛ ልባችሁን እንጂ  የማይታመን አፋችሁን አይደለም፡፡ ምንም ነገር ባደርግም፣ ባላደርግም የልባችሁን ንጽህና አይቼ መርምሬ እንጂ የአፋችሁን ማማለል አዳምጬ አይደለም ብሏል፤ በልልኝ፡፡ ሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 1712 times