Tuesday, 22 February 2022 00:00

“ህዝቡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሲያገኝ ማየት ያስደስተኛል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - ከዳላስ ማህበረሰብ በአንድ ቀን ብቻ ከ350 ሺ ዶላር በላይ አሰባስበናል

          አቶ ዘውገ ቃኘው  ከዳላስ ቴክሳስ የመጡ እንግዳ ናቸው። በአሜሪካ  ለ40 ዓመት ግድም ኖረዋል። በሪል ስቴት ስራ ላይ የተሰማሩ የቢዝነስ ሰው ሲሆኑ፣ ጎን ለጎን በጋዜጠኛ ሙያ ይሰራሉ ከልጅነታቸው ጀምሮ ጋዜጠኝነት ምኞታቸው ነበር፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ደግሞ ታዋቂው ጋዜጠኛና ገጣሚ ሰለሞን ተሰማ የአባታቸው ባልንጀራ ስለነበር በልባቸው ውስጥ የለኮሰው ፍቅር ቀላል  እንዳልነበረ ይናገራሉ፡፡
በዳላስ የማኅበረሰብ ሬድዮ ውስጥ አሁንም ድረስ በጋዜጠኝነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በግዛቲቱ  የሚኖሩ ኢትዮጵያውንን የሚያገለግለው የሬድዮ ጣቢያው፤ በተለይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይገልጻሉ።… አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከአቶ ዘውገ ቃኘው ጋር በጋዜጠኝነት ሙያውቸው፣ በበጎ አድራጎት ሥራቸውና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።                ሬድዮ ላይ ስትሰሩ የተለየ ሁኔታ የተፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ?
 የአሜሪካ የአየር ጠባይ ተለዋዋጭ ነው። ሌላ የሬድዮ ጣቢያ የለንም። በአንድ ወቅት ወደ አንድ ቦታ እየተጓጓዝን ነፋስና ጎርፍ መጣና ሳናውቀው ጎርፍ ውስጥ ገባን። የቀጥታ ስርጭት-(ላይቭ) ፕሮግራም እያስተላለፍን ነበር፡፡ ከዚያ ቀጥታ ከጣቢያው ጋር በስልክ አያይዘን ቀጠልን። መኪናችን ግን በጎርፍ ላይ ተንጠልጥላ ነበር። ያ የማይረሳ አጋጣሚ ነው፤ ልንሰምጥም እንችል ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ አስተዳደር ላይ የምናቀርበው ትችት የማያስደስታቸው ቡድኖች የሚያስፈራሩን ጊዜ ነበር፡፡
በዚያም ምክንያት ለሃያ ሶስት ዓመታት ሀገሬን እንዳላይ ተገድጄአለሁ።  ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከታገዱ ዜጎች አንዱ ነበርኩ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹አገራችሁ ግቡ›› ሲባል ነው የገባሁት፡፡
በሬድዮ ጣቢያችሁ ላይ የስፖርት ፕሮግራም የምትሰሩት እንዴት ነው?
በዚህ ዘርፍ የምሰራው እኔ ነኝ፤ በዘርፉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች አቀርባለሁ፤ጤናን በሚመለከት፣ማኅበራዊ ጉዳዮችንም እንዲሁም እንግዶችን እጋብዛለሁ፡፡
እንግዶች ምን ያህል ይሳተፋሉ?
በጣም ይሳተፋሉ፤ አድማጮች አሉን። ዋሽንግተን ብትሄድ ሃያና ሰላሳ ሬድዮ አለ፡፡ ቴክሳስ ግን እኛ ብቻ ስለሆንን ማኅበረሰቡ ለምዶታል፤ እቤት ውስጥ ሆኖ መስማት ይችላል፤ መኪና ውስጥ መስማት ይችላል፡፡ አሁን ደግሞ የራሱ አፕሊኬሽን ስላለው ከቀድሞ በላይ ተደማጭ ሆኗል። በርግጥ ገንዘብ አናገኝበትም፤ ትርፉ ህዝቡን ማገልግል ነው፡፡ በወጪም በኩል ለጣቢያው የሚያስፈልገውን ማኅበረሰብ ይረዳል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተደራጀ ማኅበረሰብ ስላለን በደንብ ይረዳናል፤ በፊት ወጪውን ራሳችን ከሰው እየለመንን ነበር የምንሸፍነው።
በአሜሪካ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አሁን ኮቪድ ባያቋርጠን ኖሮ በእግር ኳስ 38ኛ ዓመታችንን ማክበር ነበረብን፡፡ ይሁንና በኮቪድ የተነሳ ሳይከበር ቀርቷል። የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፈዴሬሽን የተቋቋመው በ1984 ዓ.ም  የዛሬ 38 ዓመት ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ለሰላሳ አምስት ዓመታት ያህል ቆይቻለሁ፡፡ በነዚህ ሁሉ ዓመታት በስቴዲየም ውስጥ የፕሮግራሙ አስተዋዋቂ ሆኜ ሰርቼአለሁ። የፈደሬሽኑ የቦርድ አባል ነኝ። ቀደም ሲል የህዝብ ግንኙነት አባል ነበርኩ።
እውነት ለመናገር በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን የሚያህል ጠንካራ ድርጅት የለም፡፡ ይህ ፌደሬሽን ከሰላሳ በላይ ቡድኖች በስሩ አሉ፤ እነርሱ ውድድር ያደርጋሉ። በዚያ ሰበብ ከኢትዮጵያ፣ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት፤ ከአውሮፓና ከመላው አሜሪካ ኢትዮጵያውያን ይሰበሰባሉ፤ በስቴድየሙ ዙሪያ ድንኳኖች ይተከላሉ፤ አትራፊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሳይቀሩ ከኢትዮጵያ መጥተው ድርጅታቸውን ያስተዋውቃሉ፤ ምግብ ቤቶች ሌሎች ቢዝነሶችም አሉ። ዋናው ትልቁ ጠቀሜታ በስፖርት ስም ተሰብስበን ኢትዮጵዊነትን ማጎልበት ነው፡፡ በተለይ እዚያ አሜሪካ ለተወለዱ ልጆቻችን ትልቁ መድረክ ይህ ፕሮግራም ነው፡፡ ከህጻንነታቸው ጀምረው እዚያ ሲታደሙ ስለ ሀገራቸውና ወገናቸው የሚኖራቸው ፍቅር ጥልቅ ይሆናል፤ በስፖርቱም ተሳትፈው የጨዋታ ዘመናቸውን ያበቁ ሁሉ አሉ፡፡
በተለያዩ ችግሮች ወቅት ለአገር ቤት የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርጉ ይነገራል። እስቲ ስሱ ይንገሩኝ?
ለኢትዮጵያ አንድ መቶ ሺህ ዶላር በስጦታ የለገሰን ጊዜ አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች በደረሱ ጊዜ ሁሉ ፌደሬሽኑ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። ለአበበች ጎበና፣ መቄዶንያና ለመሳሰሉት ድርጅቶች እገዛ እናደርጋለን፡፡
ኅብረተሰቡን ሰብስቦ ኳስ መጫወትና ኢትዮጵያዊነትን ማጎልበት ብቻ ሳይሆን አገራችንንም በተቻለን አቅም ለመርዳት እንጥራለን፡፡ አሁን እንኳ በጦርነጹ ለተጎዱ ወገኖች የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፈዴሬሽን 350 ሺ ዶላር ለመለገስ ቃል ገብቶ፣ 100 ሺ ዶላሩን አሁን ይሰጣል፡፡ ቀሪውን በተከታታይ የተጎዱ ቦታዎችን እያየን እገዛ በማድረግ እንቀጥላለን። ይህ አንዲሆን ግን የኢትዮጵያ መነግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት፤ ቢሮክራሲዎችን መቀነስ አለበት፡፡ ችግሩ በ24 ሰዓታት ውስጥ ይፈታል እልኩ አይደለም፤ ደረጃ በደረጃ  ግን መስተካከል መሻሻል አለበት።
በአሁኑ ቆይታችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ታዘባችሁ?
ባሁኑ ሁኔታ ጥሪው የተደረገው ድንገት ስለሆነ በቂም ባይሆን ጥረቶቹ ጥሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሲስተሙ ያው በመሆኑ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡ በወልዲያ ዋና የሚባል  የመንግስት ሰው ቢሮ ውስጥ ስንገባ ያሳየን ነገር የሚያሳፍር ነው፡፡ “ለምን መጣችሁ? አታስቸግሩኝ” ዓይነት ነበር፤ በጣም አሳፍሮናል፡፡
በሌላ በኩል፣ በኮምቦልቻ ደሴና ሌሎች ከተሞች ያገኘናቸው የመንግስት ሃላፊዎች ያደረጉልን አቀባበል ከምንጠብቀው በላይ መልካም ነበር፡፡ ወደ ወልዲያ እህል ጭነን ስንሄድ፣ በመንግስት ወንበር የተቀመጡ ኃላፊዎች ሊተባበሩን ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ታዝበናል። አስቸጋሪ  ሰዎች በየቦታው መኖራቸውን አሳይቶናል፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
እርስዎ በውሃ ልማትም ላይ እንደሚሰሩ ሰምቻለሁ?
ከዳላስ ማኅበረሰብ ወጣ ብለን በግሌ የምደሰትበት ጉዳይ፣ ህዝቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሲያገኝ ማየት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ይህን የውሃ ልማት ፕሮጀክት የመሰረትኩት እኔ ነኝ፡፡ ቢሆንም መመስረት ብቻ በቂ አይደለም። አሁን ድርጀቱን የሚመራው እስክንድር ታምራት የሚባል ታታሪና መልካም ሰው ነው። የፕሮጀክት ልምድ ያለው ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ፍላጎትም ያለው  በመሆኑ  ሥራው በጥሩ ሁኔታ እተካሄደ ነው። መልካም ሆኗል፡፡ በፕሮጀክቱ  ላይ የምንሰራው በአኮላሆማ፣ ዳላስና ሂውስተን የሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያውን ተጨምረው ወደ ዘጠኝ ገደማ ነን፡፡ በዚህ የልማት ስራ ባለፉት አስር ዓመታት ያልሄድንበት ቦታ የለም፤ በደቡብ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ወጪ አድርገን እየሰራን ነው፡፡ አንድ ጊዜ ላይ ጋይንት ውሃ አስቆፍረን ለማስመረቅ በሄድኩ ጊዜ ያየሁት ሁሌም ከአእምሮዬ አይጠፋም፤ ልክ እኔ ስደርስ ተራራው ላይ የሚያምር ንጹህ ምንጭ ይታያል፡፡ ያንን ግን ሰው እንዴት አድርጎ ያምጣው! እሩቅ ነው፡ ያንን ውሃ ፍለጋ ሄደን ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ውሃ ፍለጋ ሀገር አቋርጠው ይሄዳሉ። እኛ ያንን ምንጭ ከተራራው ላይ በቧንቧ አድርገን፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ አመጣነው፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበትን ምክንያት ይንገሩን…?
የመጣሁት በሁለት ምክንያት ነው። አንዱና ዋነኛው፣ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችቻችን በምንችለው አቅም ለማገዝ ነው፡፡ በዳላስ ይህንን በሚመለከት ግብረ ሃይል.. አቋቁመናል። ያ ቡድን ከማኅበረሰቡ ገንዘብ አስባስቦ ዛሬ እዚህ መጥተን ወገኖቻችንን እያገዝን ነው፡፡ ከግማሽ ሚሊየን የማያንሱ መድኃኒቶችን አስጭነን ነው የመጣነው፣ እያንዳንዱ ሰው በግል ተጨማሪ ክፍያ እየከፈለ፣ ሁለት ሻንጣ የሚፈቀድለት ሶስት እያደረገ መጥቶ፣ ጤና  ጥበቃ ባዘጋጃው ስፍራ ላይ መድሃኒቶችን አስረክበናል። በሌላ በኩል ደግሞ እህል፣ ፒጃማ፣ የውስጥ ሱሪዎች፣ በተለይ ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እዚሁ ገዝተን ሰጥተናል። በቅርቡ ደሴ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ላይ ያየነው ሁኔታ ለሰው ህሊና የሚከብድ ነው፡፡ አፋርም ለመሄድ አስበን፣ ጸጥታው አስተማማኝ አይደለም ተብለን ተመልሰናል። ይሁን እንጂ እኔ በግሌ ሰመራ የመሄድ ዕቅድ አለኝ። አዲስ አበባ ሆስፒታል ለተኙ የመከላከያ አባላት የሚገባውን አድርገበናል፡፡ አሁንም ጦርሃይሎች ሄደን፣ ችግሮችን ለማገዝ የሚያስችል ስራ ለመስራት ቀጠሮ ይዘናል፡፡
ይህንን ሁሉ የሚያደርገው የዳላስ ማህበረሰብ ብቻ ነው?  ወይስ…
ያ! የዳላስ ማህበረሰብ ብቻ ነው፡፡ ባንድ ቀን ብቻ ከ300,000 ዶላር በላይ ሰብስበናል፡፡
በቁጥር ብዙ ናችሁ ማለት ነው?
በግምት ሰላሳና አርባ  ሺህ እንሆናለን። የሰው የመስጠት ፍላጎት ክፍ ያለ ነው፡፡ ሰው ሀገሩን ለማገዝ ያለው ፍላጎት ጨምሯል። እዚህ ከመጣን በኋላ አንዳንድ የፖለቲካ ውሳኔዎች ያስቀየማቸው ሰዎች ቢኖሩም፣ እንደገና ነገሩን በማጤን “እኛ የመጣነው ወገኖቻችንን ለመደገፍ ነው፤ የፖለቲካ ጉዳይ የትም ቦታ የተለያየ ነው፤ ትኩረታችን አናዛባው” በሚል ተመካክረን ያሰብነውን አድርገናል፡፡ ይህ ወገንን የመርዳት ተግባር በቋሚነት የሚቀጥል ነው፡፡ ፖለቲካውን ወደ ጎን ትቶ በሰብአዊነት ጉዳዮች ላይ በማተኮር መስራታችንን እንገፋበታለን።
ቅድም የጠቀስኩት ላይ ጋይንት፣ አንዲት እናት  ውሃ ፍለጋ ሄደው ነብር ሊበላቸው ሲል ሰዎች ደርሰው ህይወታቸውን እንዳተፈሩላቸው ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። ታዲያ  ከተራራ ላይ አውርደን ወደ ት/ቤት  በቧንቧ ያስገባነውን  የውሃ ልማት ፕሮጀክት ለመመረቅ ስንሄድ መንገዱ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ትራንስፖርት ስለሌለ በእግሬ ነበር የሄድኩት፤ ግን እዚያ ስደርስ ባየሁት ነገር ድካሜ ሁሉ ጠፋ። ተማሪዎች ተሰልፈው ሴቶች እየዘፈኑ እየዘመሩ ተቀበሉን፤ የቤተ-ክርስቲያን ሰዎች፣ ቀሳውስት ዣንጥላ ይዘው፣ የወረዳው ባለስልጣናት በኅብረት ሆነው ሲቀበሉን በጣም እረካሁ።
ይህ የሆነው በእኔ መሄድ አይደለም። ህይወታቸውን የሚለውጥ ነገር ስለተሰራ ሲደሰት ማየት ትልቅ ነው ሰው ነህና መቸም ትሞታለህ፡፡
የዚህ ሀሳብ አፍላቂ እኔ ብሆንም፣ አብረውኝ የሚሰሩትና በአቶ ታምራት የሚመራው ቡድን አባላት ከፍተኛ ትብብር ባይታከልበት የትም አይደርሱም ነበር። ሁሉም ትልልቅ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ስለሆኑ፣ ፍላጎታቸው ወገንን መርዳት ብቻ ነው፡፡ ገንዘቡም መቶ በመቶ ስራው ላይ ይውላል፡፡ የፈረንጅ ድርጅቶች ለስራ አስኪያጆች የሚከፍሉት ገንዘብ ብዙ ነው። እኛ ጋር እንደዚያ የሚባል ነገር የለም፡፡ የኛ ደሞዝ የኛ ክፍያ የህዝቡ ደስታ ነው፡፡
ባሁኑ ደረጃ ሁሉም ክልል ሄደናል፤ ጦርነቱ ባይጀመር ቀጣዩ ፕሮጀክታችን ትግራይ ነበር፡፡ አሁንም ነገሮች ቢስተካከሉ ለመሄድ ዝግጁ ነን፡፡ ድርጀቱ “strean of hope” ይባላል “የተስፋ ምንጭ” ይባላል። በዌብ ሳይታችን ላይ strean of hope.org) ሁሉንም ነገር ማየት ይቻላል፡፡    

Read 10291 times