Sunday, 20 February 2022 17:02

“የሰላም ሚኒስቴር”፣ ስሙ ቢቀየር ይሻላል።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  “የሰላም ሚኒስቴር” ስም ይለወጥ! ደግሞ ስሙ ምን ይወጣለታል? ሰላምን የመሰለ ውድ በረከት ከወዴት ይገኛል! በዚያ ላይ፣ የመንግስት ዋና ስራ፣ ሰላምን መፍጠር፣ ሰላምን ማስፈንና መጠበቅ ነው፤… አይደለም እንዴ?
እሺ፣ “የእያንዳንዱን ሰው ሕይወትና ነፃነት ማስከበር ነው፣ ዋናው የመንግስት ስራ”። ቢሆንም እንኳ፤ ሰላም በሌለበት፣ እንዴት ተብሎ ሕይወትና ነፃነት ይከበራል? ጤንነትና ትምህርት፣ ከመንግስት ውጭም ይኖራሉ፤ ለዚያውም በተሻለ ጥራት። ሰላም ግን፣ ያለ መንግስት አይገኝም። ቢገኝም አይዘልቅም።
ሰላማዊ አገርና ኑሮ፣ ያለ መንግስት (ወይም ያለህግ፣ ያለስርዓት) አይደላደልም። ቢሆንም ግን፣… “ሰላም”፣ የመንግስት ሥራ፣ ሃላፊነትና ግዴታ ቢሆንም፤ “የሰላም ሚኒስቴር” የሚለው ስያሜ፣ ከመንግስት ሥራ ጋር የተጣጣመ ቢመስልም፣ ….
ስሙ ቢቀየር ይሻላል። ለምን? “ሰላም” የሚለው ቃል፤ ኮስታራ ስላልሆነ? ቃሉ፣ ብዙ ሰው ለሰላምታ የሚጠቀምበት ቃል ስለሆነ? መንግስት እንዳይወርስብን? ጥሩ። ዋናው ችግር ግን፣ ሌላ ነው።
“የሰላም ሚኒስቴር” የሚለው ስም፣ ከባድ የጠባሳ ታሪክ የተሸከመ ስም ነው - በጆርጅ ኦርዌል ድርሰት። ከመሰሎቹ፣ “የፍቅር ሚኒስቴር” እና “የእውነት ሚኒስቴር” ከሚሉ ስያሜዎች ጋር፣ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ገብቷል።
ሰዎችን ለማሰቃየት የተቋቋሙ እስር ቤቶችና የማጎሪያ ጣቢያዎች፣ “የፍቅር ሚኒስቴር” ንብረቶች ናቸው - “1984” በተሰኘው የኦርዌል ድርሰት። ማሰቃያ ቤትን፣ “የፍቅር ቤት” ብሎ እንደመጥራት ነው። ድርሰቱ ውስጥ፣ “የሰላም ሚኒስቴርም”፣ ስሙ መቼም እንዳይነፃ ሆኖ ጠቁሯል።


          ሰላም በጎ ነው። ጥርጥር የለውም። ኑሮ ነው፤ ሕይወት ነው። ሰላም የሚለው ቃል፣ ከለጋሾች ቸርነት፣ ከፍቅር ስብከቶች፣ ከሕብረ ዝማሬዎችና ከምኞት ዘፈኖች ጋር በጣም የተዛመደ መሆኑም አይገርምም። “የመንግስት ነገረ-ስራ” ግን፤ ሁሌም ኮስተር ቆፍጠን ማለት አለበት።
መንግስት ከተባለ፣ ስራው ሁሉ፣ በሕግ የሚፈፀም ግደታ መሆን ይኖርበታል። የእያንዳንዱ ሰው ነፃነት ፈፅሞ መነካት ስለሌለበት፤ ቆፍጣና የህግ ዋስት ያስፈልገዋል፤ የሕግ ጥበቃም ይታወጅለታል። “የሰውን ነፃነት የጣሰ፣ ጉዱ ይፈላል”፤ “ወዮ! ለወንጀለኛ!”… የሚያስብል መሆን አለበት። ኮስታራነቱን አያችሁ!
“የመንግስት ነገረ-ስራ”፣ ለነፃነትና ለፍትህ ኮስታራ ካልሆነ፤ ወንጀለኞች ያልፍላቸዋል።
ደግሞስ፣ የመንግስት ምንነት፣ ኮስተር ቆፍጠን ባለ አገላለፅ፤ “ሕግና ስርዓት” ማለት አይደል! የመንግስት ተቋማት “በሥርዓት” የሚዋቀሩት፣ ሃላፊነታቸው በግልጽ እየተዘረዘረ፣ ስልጣናቸው በህግ እየተገደበ ነው - በአዋጅ። ፓርላማ (ምክረ ቤቶች)፤ ርዕስ መስተዳደር (ካቢኔ ሚኒስትሮች)፤ ፍርድ ቤት
(ዳኖች)፤ ...እንዲህ ስንዘረዝረው፣ “ሥርዓት”ነቱን አጉልተን ለመመልከት ይረዳናል።
ሕጋዊነቱን አበክረን ለማገናዘብስ?
“ሕግ መምሪያ (መወሰኛ)”፤ “ሕግ ማስፈፀሚያ”፤ “ህግ መተርጎሚያ” የሚሉ የዘርፍ ፈርጆችን መጠቀም እንችላለን። ፓርላማ፣ ካቢኔና ፍርድ ቤት… መሆናቸው ነው። የሁሉም ተቋማት ሥራ፤ በሕግ ዙሪያ ያጠነጠነ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙም አይቸግርም።
በአጭሩ፣ የመንግስት ነገረ-ስራ ሁሉ፣ የህግና የስርዓት ጉዳይ ነው - ኮስተር ቆፍጠን ያለ።
በሕይወትና በንብረት ላይ መፍረድ፣ “ኮስታራ” ስራ ነው።
“ፍርድ ቤት” የሚባለውን ስያሜ ተመልከቱ። ወለም ዘለም የሚያስብል አይደለም። በሞትና በሕይወት ላይ ይፈርዳል። አቃቤ ህግ እና ተጠርጣሪ ወንጀለኛ፣ ከሳሽና ተከሳሽ፣ ምስክርና ማስረጃ፣ …. የህግ ሥርዓትንና የእውነትን መንገድ ተከትሎ፤ ጥፋተኛ የሆነና ያለሆነ ተለይቶ ይበየናል። የንጹህ ሰው ነፃነት ይከበራል። ወንጀለኛው ደግሞ ለጥፋቱ የሚመጥን ቅጣቱን ያገኛል - በፍርድ ቤት ውሳኔ። ይሄ ሁሉ ነው የዳኝት ሕጋዊ ስርዓት (የስህተት አጋጣሚዎችን ለመከላከል የሚረዳ የይግባኝ አሰራርንም ጨምሮ)።
ታዲያ፣ በሕይወትና በንብረት ላይ የሚፈርድ የህግ ሥርዓት፤ ኮስታራነቱ ያጠራጥራል?
“የጦር ሚኒስቴር”፣ “የጦርነት ሚኒስቴር” የሚባለው የድሮ አጠራር፤ ዛሬ አስገራሚ ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን፤ ስያሜው፣ የስራውን ኮስታራነት ለመገልጽ መሆኑን ማስታወስ አለብን።
ለነገሩ፤ ዛሬም ቢሆን፤ “የጦር ሚኒስቴር” የሚል ስያሜ የተረሳ ቢመስልም፤ “መከላከያ ሚኒስቴር” ተብሎ ቢለወጥም፣ ሙሉ ለሙሉ ተለሳልሷል ማለት አይደለም። “የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ”፣ “የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም”፣ “የምድር ጦር አዛዥ”፣ “አየር ሃይል”፣ “የዘመቻ መምሪያ”፣… የሚሉ አገላለጾች ዛሬም ድረስ አሉ። ነገሩ የዋዛ አይደለም። ያ ሁሉ የጦር መሳሪያ ታጥቆ፤ እንዴት የዋዛ ይሆናል!
ከዚህ አንጻር ስናየው፤ “የሰላም ሚኒስቴር”፣… ከመንግስት ምንነት ጋር አብሮ ይሄዳል? ወታደሮችን ሰማያዊ ቆብ አልብሶ፣ ታንኮችን ነጭ ቀለም ቀብቶ፣ ወደ አፍሪካ አገራት ከሚመጣ የተባበሩት መንግስታት ልዑክ ይመሳሰላል?
ነጭ ቀለም የተቀባ ታንክ? አፈሙዙ ላይ ሰማያዊ ባዲንራ የሚያውለበልብ መትረየስ? የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሰራዊት፤ ሸምጋይ ገላጋይ ልዑክ ተብሎ የሚሰማራ? እንቆቅልሽ ይመስላል። በእርግጥ፤ የተባበሩት መንግስታት (ዩኤን)፤ ይህን እንቆቅልሽ የሚፈታ ማብራሪያ ሊያቀርብ ይችላል።
አንደኛ ነገር፣ የዩኤን ጦር ሰራዊት፣ ወደ ሆነ አገር የሚያሰማራው ለጊዜው ነው (ቋሚ ሕጋዊ ስርዓት እስኪደላደል ድረስ፣ ትንሽ ለማገዝ ብቻ)።
ሁለተኛ ነገር፣ ሰላም ለመፍጠር ሳይሆን፣ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ፣ አስተማማኝ ሕግና ስርዓት እስኪዋቀር ድረስ፣ ድጋፍ መስጠት ብቻ ነው - የሰላም አስከባሪ ኃይል ጊዜያዊ ሃላፊነት።
በሌላ አነጋገር፣ “የጦር ሰራዊት ነው፤ ግን ለጦርነት አይዘመትም” እንደማለት ነው ነገሩ (“ታንክ ይዟል፤ ግን ነጭ ቀለም የተቀባ ነው”)። የሚያስኬድ ማብራሪያ ይመስላል።
ነገር ግን፤ በተደጋጋሚ እንደታየው፣ “ሰላም አስከባሪ” ተብሎ በዩኤን የሚሰማራ የጦር ሰራዊት፤ ከጦርነትም ከሰላምም ሳይሆን ይቀራል።
ነጭ ቀለም የተቀባ ታንክ፤ ወይ የህክምና አምቡላንስ አይሆንም፤ ወይ ተዋግቶ የሚያሸንፍ ታንክ አይሆንም። ሁለቱን ወድዶ ሁለቱን ያጣ ነው።
ሰላም ሚኒስቴርስ፤ ከዚህም ከዚያም ሳይሆን በመሃል አይቀርም ወይ? ዩኤን መቼስ፤ “የኔ ሃላፈነት ጊዜያዊ ነው፤ የኔ ድርሻ ሰላምን የመፍጠርና የማስፈን ቋሚ ስራ ሳይሆን፤ ለጊዜያዊ እፎይታ ማገዝ ነው” ሊል ይችላል።
የመንግስት ድርሻና ሃላፊነት ግን፣ ጊዜያዊ አይደለም፤ ቋሚ ነው። የማገዝ ጉዳይ አይደለም፤ ህጋዊ ግዴታ ነው።
በእርግጥ፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማገናዘብ፣ የረብሻና የነውጥ አደጋዎችን ለመሻገር፤ ወደ ሰላምና ወደ እርጋታ ለመድረስ፤ ለአጣዳፊ ስራዎች የሚያገለግል ጊዜያዊ የተቋማት ስያሜ ያስፈልግ ይሆናል። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ለጥቂት ወራት ብቻ አይደል? ልክ እንደዚያው፣ “የሰላም ሚኒስቴር” የሚል ስያሜም፣ ለሁለት ለሶስት ዓመት፣ ተገቢ ሊሆን ይችላል (የደፈረሰ እስኪጠራ፣ የተናወጠ እስኪረጋጋ ድረስ ብቻ)።
ቋሚ ስያሜ ከሆነ ግን፤ ችግር አለው። ሰላም የሰፈነበት አገር ውስጥ፣ ህግና ስርዓትን ማስከበር ነው - የመንግስት መደበኛ ሃላፊነት፣ መደበኛ ስራ። “የሰላም ሚኒስቴር”፣ እንደ “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ”፣ ለአጭር ጊዜ ብቻ መሆን አለበት።
ሰላምታችንን ይመልስልን?
እውነት ለመናገር፣ በተቻለ መጠን፣ አገርኛ ቃላትን መጠቀም ጥሩ ነው። የፕላን ኮሚሽን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣… የሚሉ ስያሜዎች፣ በአገርኛ ቃላት፣ ሌላ ተስማሚ ስም አይገኝላቸውም? በዚህ በዚህ፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ በከፊል አገርኛ ስም ነው።
ቢሆንም ግን፣ የዘወትር የሰላምታ መለዋወጫ ቃላችን፤ መንግስት ባይወርስብን ይሻላል።
ዛሬ ዛሬ “ጤና ይስጥልኝ” የሚል የሰላምታ አባባል ጠፍቶብናል። የጤና ጉዳይ በመንግስት ስለተወረሰ ሊሆን ይችላል - በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር።
“ሰላም አደራችሁ፣ ሰላም እደሩ”፤ “በሰላም አውለኝ፤ በሰላም አሳድረኝ” ብለን ስንናገር፤ የውስጣችንን መልካም ምኞት ነበር የምንገልፀው። አሁን ግን፣ “በሰላም ያገናኘን” ብለን ብንናገር፣ ለሰላም ሚኒስቴር አቤቱታ ምናቀርብ ያስመስልብናል።
“ሰላም አደርሽ?” ብትሉ፤ “ኧረ ምን ሰላም አለ!” የሚል መልስ ብታገኙ አስቡት። የሰላም ሚኒስቴርን ለመውቀስና ለማሳበቅ አንዳች ሰበብ የምትፈልጉ ያስመስልባችኋል።
በዚህ ባትስማሙ፤ ችግር የለውም። ያን ያህል የሚያጣላ አይደለም። ያለ ቅሬታ በመልካም መንፈስ መቀጠል እንችላለን። ዋናው ነገር፤ ሰላምና ጤና ነው። አይደለም እንዴ? በቅንነት መነጋገር እንችላለን -ሰላምና ጤና ከሰጠን። ማለቴ ከሰጡን። የሰላምና የጤና ሚኒስቴሮች ማለቴ ነው።
ግን፤ ቁምነገር ነው የያዝነው አይደል?
የሰላም ሚኒስቴር የሚለውን ስያሜ፤ ከምር ልንለውጠው ይገባል። ወቅታዊውን የአገር ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ለጊዜው “እሺ ይሁን” ማለት ይቻላል። ለወደፊት ግን፣ ሌላ ስም ቢፈለግለት ይሻላል።
ላይነፁ የተጠቆሩ ስሞች።
አንዱ ትልቅ ችግር፤ ስያሜው ከመነሻው የስም ጠባሳ የተሸከመ መሆኑ ነው። የታሪክ ጠባሳው ምንኛ አስከፊ እንደሆነ ለማየት ከፈለጋችሁ፤ “1984” ላይ ተመልከቱ።
ምኞት የሚያምርለት፣ እውነትን ለያዘና ለጥረት ለተዘጋጀ!
“1984” በሚል ርዕስ የተሰራው፣ አዲሱ የ”Wonder Woman” የጀብድ ፊልም ማለቴ አይደለም። በእርግጥ፣ ፊልሙ፣ ድንቅ የፍልሚያ ትዕይንቶችን፣ ከአስገራሚ ሃሳቦች ጋር አዋህዶና አሳምሮ የያዘ የጥበብ ስራ ነው። ብትመለከቱትና ብታጣጥሙት፤ ትደሰቱበት ትመሰጡበት ይሆናል።
እውነትና ምኞት በልካቸው ተመጥነው፣ በጥበበኞች ጥረት እርስ በእርስ ካልተዋደዱ፣... ለካ አገር ምድሩ ይተረማመሳል። ለካ፣ ለጊዜው ያማረ መስሎ ሕይወትና ኑሮ ይቃወሳል። ከእውቀት ከእውነት ጋር የተጣላ ምኞት፣ ከጥበብ ከጥረት ጋር የተፋታ ጉጉት፤ በአንድ ጎኑ የሰመረ ቢመስል እንኳ፤ ሌላውን እየሰበረ እያኮላሸ፤ ያጠወልጋል፤ ፍሬ ያሳጣል። መከበርን ተመኝተው፣ ውርደትን፤ የተሟላ ኑሮን ፈልገው፣ መጉደልን ያገኛሉ። ይሄ ጥሬ የሃሳብ ገለፃ ነው። ፊልሙ ደግሞ ሕይወት ይዘራበታል፤ በእውን የኖርንበት ያህል እንዲታየን ያደርጋል።  
ተፈጥሮአዊውን እውነታ በአዎንታ የመቀበል፤ ለእውነታ ታማኝ የመሆን፣ እያገናዘቡ እውቀትን የመጨበጥ ሃላፊነት፣… ትልቁ የሰው ሃላፊነት ነው፤ ትልቁ የሰው አቅም ነውና። ከዚህ ውጭ ምንም የለም። ምኞትም፣ ስኬትም፣ የሰብዕና ክብርም፣ ከ”እውነት” ውጭ፣ ጤናማ አይሆንም።
“Truth is all there is!... No true hero is born from lies.” እንዲል ፊልሙ።
ለምኞት ሲጓጉ፣ አላማ ሲመርጡ፣… ህይወትን የሚያለመልምና መልካም ፍሬ የሚያመጣ እንዲሆን በጥንቃቄና በእውቀት ይምረጡ። አለበለዚያ መዘዝን ይጋብዛሉ። እውነት ላይ ካልቆሙና ለጥረት ካልተዘጋጁም፣ ምኞት ብቻ፣ አንድም ሕፃንነት፣ አንድም ሞኝነት፣ አልያም የክፋት ቁልቁለት ይሆናል።
“Beware what you wish for!” ትላለች የፊልሙ ዋና ባለ ታሪክ፣ ጀግናዋ ተፋላሚ፣ አስተዋይዋ ዳያና።
በባዶ የሚሳካ ምኞት የለም። በአቋራጭ የሚደርሱበት ከፍታ፣ አየር ባየር የሚዘግኑት ጣፋጭ ፍሬ፣ በየትም ቦታና ጊዜ አይኖርም። በባዶ ዝም ብሎ የሚገኝ ሊመስል ይችላል። ግን፣ ትርፍ የሚገኘው፣ በጥበበኛ ጥረት ብቻ ነው።
በባዶ፣ አንዳች ትርፍ አገኘሁ የሚል ሰው፣ እንደ ሕፃን፤ የእናት ጡት ወተትን ወይም የአባት የፍራፍሬ እርሻን እያሰበ ነው። ወይም ሞኝነት ነው። የወላጆችን እንክብካቤና የጓደኞችን እገዛ፣ ከባዶ አየር ተትረፍርፎ የሚገኝ ሲሳይ ይመስለዋል - ውለታቢስ አላዋቂ።
ከአንድ ጎኑ እየተቆረሰ ለሌላ ጎኑ የሚቀልብ፣ ለመጪው ክረምት ያስቀመጠውን የእህል ዘር ዘንድሮ የሚቆረጥም፤ ከነገ አጉድሎ ዛሬ የሚሰክር ሰው፤ አየር ባየር በነፃ የተመገበና የበርታ፣ በአቋራጭ መንገድ የተደሰተና ምኞቱ የተሟላ ይመስለዋል።
አልያም፤ በነፃ ትርፋማ የሆነ የሚመስለው፣ የሌላ ሰው የጥረት ፍሬዎችን እየሸመጠጠ ነው። ያለ ጥረት በአቋራጭ የሚገኝ እውነተኛ ጥቅምና ትርፍ የለም። ከተገኘም፤ በሌላ ሰው ጉዳትና ኪሳራ ነው።
የውሸታም ሽንገላ፣ የሸረኛ ሸፍጥ፤ ወይም የለየለት የሽፍታ ዝርፋያ ሊሆን ይችላል - አቋራጩ መንገድ። በሀሰት ማሳመን፣ በማታለያ ማዘናጋት፣ በዛቻ ማስፈራራት፣ … ከዚያስ?
ሦስቱ ሚኒስቴዎች - በ”1984” ድርሰት።
የምኞት ሦስት አቋራጭ መንገዶች፣ በሀሰት ማሳመን፣ በማታለያ ማዘናጋት፣ በዛቻ ማስፈራራት፣… ብቻ አይደሉም። የየራሳቸው ጓዝ አላቸው። አላምንም፣ አልዘናጋም፣ አልፈራም የሚል ይኖራል። በቃ? አይበቃም።
አላምንም ካለ፤ እውነትን እንዳይናገርና አፉን ይዞ እንዲቀመጥ ማፈን፣ የተረነገረውን ብቻ እየሰማ እንደ ድምፅ ማጉያ እንዲያስተጋባ ማስገደድ።
ከኑሮ አላማው አልዘናጋ ካለ፤ በተቀናቃኝ ጎራ አቧድኖ የጠላትነት ስሜት እንዲነግስ፣ ጠላትነት ዋና የኑሮ አላማ እንዲመስል ማድረግ፣ …. “የመደብ ጠላቶችና የውስጥ ከሃዲዎች”፤ “ቅኝ ገዚዎችና የውጭ ወረራዎች” በሚል ጭፍን ፍረጃ አማካኝነት፣ የትንቅንቅና የፀበኝነት ቅኝቶችን እያቀነቀኑ፣ ለጦርነት  ማዝመት።
በሃሰት ማሳመንና ማፈን፣ ከኑሮ ማዘናጋትና ለጦርነት ማሰለፍ-በቂ አይሆንም።
ከማስፈራሪያና ከዛቻ ጋር የሚመጣ የማሰቃየትና የመግደል ጥቃት ይኖራል።
እንግዲህ፣ ሦስቱን ዘርፎችና የሚመሩ ግዙፍ ተቋማት፤ ምንና ምን እንደሆኑ በእውን የሚያሳይ ነው -1984 የተሰኘው ድርሰት።
ሰዎች፣ እውነትን እንዳይናገሩ ለማፈን፣ አገር ምድሩን በሃሰት ወሬ ለማጥለቅለቅ፣ እለት ተእለት፣ ቀን ከሌት ውሸትን እየፈበረከ ለማሰራጨት የተደራጀው ትልቅ ተቋም፣ “የእውነት ሚኒስቴር” ይባላል። “Ministry Of Truth”። በጣም አስፈሪ፣ የሳንሱርና የፕሮፓጋንዳ ተቋም ነው።
ሰዎች፣ ኑሮን የማሻሻል አላማቸውን እንዲዘነጉ፣ በጥላቻ ስሜት እንዲወናበዱ፤ “የውስጥ ከሃዲ፣ የውጭ ሃይሎች ተላላኪ” ከሚል ውንጀላ ለማምለጥ ብለው፣ በወዶ ዘማችነት እንዲመዘገቡ የሚያስገድድ፣ የጦርነት ሰበቦችን የሚፈበርክና ጦርነቶችን የሚቆሰቁስ ትልቅ ተቋምም አለ - “Ministry Of Peace” ተብሎ ተሰይሟል - የሰላም ሚኒስቴር።
የመግረፊያና የማሰቃያ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ፣ የስለላና የክትትል፣ የእስርና የቅጣት፣ የግዞትና የማጎሪያ ድርጅቶችን የሚመራ ተቋምም፤ ሌላ ስም ወጥቶለታል - “Ministry Of Love” ተብሏል። የፍቅር ሚኒስቴር።
እንግደህ አስቡት። “1984” የተሰኘው ድርሰት፤ በስፋት ከሚታወቁ ድንቅ ድርሰቶች መካከል አንዱ ነው (Nineteen Eighty-Four፣ George Orwell)።
የሦስቱን ሚኒስቴሮች ምንነት የሚገልፅልን፣ በስላቅ ስሜት አይደለም። ከምር ነው- ፍቅር ሚኒስቴር፤ ከምር “የስቃይ ማስተር” እንደሚሆን አትጠራጠሩም። በሐተታ በትንተና አይደለም። የኖርንበት ያህል ነው በእውን የሚያሳየን።
የድርሰቱ ምናባዊ ዓለም ውስጥ ገብተን፣ በሕይወት በአካል የኖርንበት ያህል እንድናውቃቸው ብቻ አይደለም። በአእምሮና በመንፈስ እንዲቀረፁብና የሚያደርግ ነው - ሃያል የኪነጥበብ ብቃቱ። የማይጠፋ፣ ጨርሶ የማይደበዝዝ ምስል ነው የሚሆንብን - የደራሲው ፈጠራ።
በማስተባበያና በመከራከሪያ የሚለውጡት አይነት አይደለም - ምናባዊው ምስል።
በአጭሩ፣ ሦስቱ የሚኒስቴር ስሞች፣ የተጠቆሩ ስሞች ናቸው፤ በዘላለማዊ ጥቁር መዝገብ ውስጥ የተወቀሩ።
በሃያል የኪነጥበብ ብቃት የተፈጠረውን መዝገብ ለመቀየርና የተጠቆሩትን ስሞች ለማደስ መታገል፣ በጥቂት ዓመታት ወይም በቀላል ጥረት ብቻ፣ ምንም ውጤት አያስገኝም። ጊዜንና አቅምን ይበላል እንጂ።
ምን ይጠየቃል? “የሰላም ሚኒስቴር” የሚለው ስያሜ፤ በመላው ዓለም ለበርካታ ዓስርት ዓመታት የዘለቀ የጠባሳ ታሪክ የተሸከመ ስያሜ እንደሆነ አያከራክርም። ታዲያ፣ ይህ ብቻ፣ በቂ ምክንያት አይደለም? ስያሜ ለመቀየር!


Read 1336 times