Saturday, 26 February 2022 12:03

“ህብር ኢትዮጵያ” የሃገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎች ቢሆኑ ያላቸውን ጉዳዮች አመለከት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   ተፋላሚ ሃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል
                               
            በቀጣይ የሚካሄደው የሃገራዊ ምክክር መድረክ ዋነኛ ትኩረቱን ሀገራዊ እርቅ፣ብሔራዊ መግባባትት የህገ መንግስቱ ጉዳይ እና የሽግግር ሂደት በሚፈጥርባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲደረግ ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዎ ፓርቲ (ህብር) ጠይቋል፡፡
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጠው ህብር ኢትዮጵያ መሳሪያ አንስተው እየተዋጉ ያሉ ሃይሎች ወደ ሰላማዊ የትግል መንገድ እንዲመለሱ እንዲሁም ወደፊት የኢትዮጵያን አንድነት ከሚጎዳ የጥላቻና ከፋፋይ አስተሳሰቦች ኢንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
 ጦርነትና በዜጎች ላይ የሚፈፀም ጥቃት አሁንም የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈና እያጎሳቆለ ነው እንደሚገኝ የጠቆመው ፓርቲው፣ መንግስትም የዜጎችን ሠላም መጠበቅና የሃገሪቱን ፀጥታ ማስከበር አልቻለም ብሏል፡፡
የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ያለው ጦርነት አብቅቶ ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት ተአማኒና ሃቀኛ ድርድርና ሁሉን አቀፍ ምክከር በአስቸኳይ መጀመር አለበት ብሏል፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ሃይሎች ክፉኛ እየተፈተነች ነው ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ ፈተናው የበዛው በዋናነት የውስጥ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገርና መፍታት ባለመቻሉ መሆኑን በመግለጽ ሁሉን አቀፍ ሃቀኛ ምክክር እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታና ዘር ለይቶ የሚፈፀም ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን፤ መንግስት በክልሉ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ ተጠያቂ ነው ብሏል፡፡
የመንግስት ውሳኔ አሰጣጥ አቅም ማነስ፣ የተጠያቂነት አለመኖር፣ መንግስታዊ ሃላፊነትን ለመወጣት ያለመፈለግ፣ ግዴለሽነትና፣ የመጠላለፍ የፖለቲካ ባህል የፈጠራቸው ችግሮቹ የሃገሪቱንና የዜጎቿን መከራ ያበረቱ መሆኑን ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል፡፡


Read 1227 times