Saturday, 26 February 2022 12:03

በትግራይ ከፍተኛ የነዳጅ፣ የጥሬ ገንዘብና የመድሃኒት እጥረት መከሰቱ ተገለጸ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  ህውሓት በአፋር በኩል በቀጠለው ጦርነት ሳቢያ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ወደ ትግራይ መሰረታዊ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ማጓጓዝ አለመቻሉን ተከትሎ የነዳጅ፣ የጥሬ ገንዘብና መድኃኒቶች እንዲሁም የምግብ እጥረት መከሰቱን የተባበሩት መንግስታት ምግብ ፕሮግራም  ኤጀንሲ አስታወቀ።
የእርዳታ ቁሳቁሶች ይጓጓዝበት የነበረው የአፋርና ትግራይ አካባቢ ላይ ህውሓት አሁንም ጦርነት በመቀጠሉ ላለፉት 5 ወራት ምንም አይነት እርዳታ ወደ ትግራይ ማሳለፍ እንዳልተቻለ ኤጀንሲው ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቷል።
በዚህ ምክንያት በዋናነት የነዳጅ፣ የጥሬ ገንዘብ፣ የመድሃኒትና የምግብ እጥረት መከሰቱንና 40 በመቶ ያህሉ የክልሉ ነዋሪ ለከፋ ችግር መጋለጡን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ 14 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡሮችና የሚያጠቡ እናቶች ለእርዛት ተዳርገዋል ብሏል፡፡  
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ከመድኒሃትና ከህክምና ቁሳቁስ እጥረት ባሻገር በክልሉ የባለሙያዎችም እጥረት መኖሩን የጠቆመው የኤጀንሲው ሪፖርት፤ ከ87 በመቶ በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት በመውደማቸውም  ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውንም አመልክቷል።
ከ16 ወራት በላይ ባስቆጠረው የሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በትግራይ 5.2 ሚሊዮን፣ በአማራና በአፋር ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለቀጥተኛ እርዳታ ጠባቂነት ተዳርጓል ተብሏል፡፡
በትግራይ ክልል ሆስፒታሎችን ጨምሮ 2 መቶ ያህል የጤና ማዕከላት ሲወድሙ፣ በአማራ ክልል 30 ሆስፒታሎችን ጨምሮ 2,206 ያህል የጤና ተቋማት መውደማቸውን፣ በአፋር ደግሞ 2 ሆስፒታሎችን ጨምሮ 555 የሚደርሱ የጤና  ተቋማት በጦርነቱ እንደወደሙ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
የኤጀንሲው ሪፖርት ላይ እንደሰፈረው፤ ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት ሥራውን ለቀዋል አሊያም የሚኖሩበትን አካባቢ  ሸሽተዋል፡፡

Read 11262 times