Saturday, 26 February 2022 00:00

አስደንጋጩ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  • የነዳጅ ዋጋ ባለፉት 7 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ጭማሪ አሳይቷል
          • የኪያቭ ነዋሪዎች አገራቸውን ጥለው ፖላንድ እየገቡ ነው
          • ቻይና የሩሲያን ወታደራዊ እርምጃ አልተቃወመችም
          • በዩክሬን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በርሊን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲያሳውቁ ተጠይቋል
          • “ምዕራባውያን አጋፍጠውን ጠፍተዋል፤ ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን” የዩክሬን ፕሬዚዳንት
                   


         ሶስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የዓለም ትኩረትን ስቧል፡፡ የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን ዋና  ከተማ ኪያቭን የተቆጣጠሩ ሲሆን በጦርነቱ እስከ አሁን ከ137 በላይ ዜጎቿ መገደላቸውንና ወደ 200 የሚጠጉ መቁሰላቸውን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ “ምእራባውያን አገራት ብቻችንን ለጦርነት አጋፍጠውን ሸሽተዋል፤ አገራችንን ለመከላከል በብቸኝነት እየተዋጋን ያለነው እኛው ነን ብለዋል፡፡
“ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደተወን ነው የተሰማኝ፤ እንደሚደግፉን ቃል ሲገቡልን የነበሩት ሁሉ ትተውናል፤ ሞትን ለብቻችን እንድንጋፈጠው አድርገውናል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ በምሬት። ሃገራቸው ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗንም አክለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች በኋላ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ ሲሆን ጭማሪው ባለፉት ሰባት ዓመታት ከተስተዋሉት ጭማሪዎች ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ሩሲያ በዩክሬን ግዛት ላይ መውሰድ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ ምዕራባውያንና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሩሲያንና  ፕሬዚዳንት ፑቲንን እያወገዙ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከባለፉት 100 ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ እጅግ አስከፊ የሆነው ጦርነት እንዲጀመር አይፍቀዱ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንዳ ላየን፤ ድርጊቱን እናወግዛለን ፑቲን አውሮፓን ዳግም ወደ ጦርነት  ከቷታል፡፡ ከዩክሬናውያን ጎን ነን፤ ሩሲያ በህብረቱ አገራት በምታንቀሳቅሰው  ሃብት ላይ ከባድ ማዕቀብ እንጥላለን” ብለዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ለሚደርሰው  ጉዳት ኃላፊነቱን ትወስዳለች አለምም ተጠያቂ ያደርጋታል ብለዋል፡፡
ሩሲያ በተቆጣጠረችው የዩክሬን ዋና ከተማ ኪያቭ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ጥላው በመሸሽ ወደ ፖላንድ እየገቡ ነው። እስከ አሁን ከአንድ ሺ በላይ ዩክሬናውያን በድንበር አቅራቢያ ከምትገኝ የፖላንድ ከተማ በባቡር መድረሳቸው ተነግሯል፡፡
ሃንጋሪና ስሎቫኪያ የዩክሬንን ስደተኞች ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዩክሬን  የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያ ካሉበት ቦታ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በርሊን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲያሳውቁ ጥሪ ተነግሯቸዋል። ኢትዮጵያውያኑ ወደ ፖላንድ መግባት እንዲችሉ ከፖላንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ፈቃድ መገኘቱም ተገልጿል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ኔቶ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የወሰደችውን ወታደራዊ እርምጃ አጥብቀው የኮነኑ ሲሆን የተለያዩ ማዕቀቦችን መጣላቸውን ቀጥለዋል። የሩሲያ የረዥም ጊዜ አጋር የሆነችው ቻይና ግን የሞስኮን እርምጃ አልተቃወመችም፡፡ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን “ምንም እንኳን ቻይና የሀገራት ሉአላዊ የግዛት አንድነት ብታከብርም ምክንያታዊ የሆነውን የሩሲያ የደህንነት ስጋት ትገነዘባለች” ብለዋል፡፡
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የወሰደችውን ወታደራዊ እርምጃ አስመልከቶ አቋማቸውን ከመግለፅ የተቆጠቡ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያ፣ ጋና እና ጋቦን ሩሲያ በይኩሬን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ በይፋ አውግዘዋል። ከአፍሪካ አገራት መካከል ከሩሲያ ጎን መቆሙን በይፋ የገለፀ አገር የለም፡፡

Read 645 times