Saturday, 26 February 2022 00:00

አወዛጋቢው የመንግስትና የህወኃት ድርድር?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)


          • በኢትዮጵያ መንግስትና በህወኃት አመራሮች መካከል ተስፋ ሰጪ ውይይት እየተደረገ ነው - ተ.መ.ድ
          • ድርድሩ በአጭር ጊዜ ተፈፃሚ ካልሆነ ብዙ ልንታገስ አንችልም - የህወኃት ሃይሎች
          • እስሁን ከህወኃት ጋር የተጀመረ ምንም አይነት ድርድር የለም - ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
          • በአሸባሪነት ከተሰየመ ድርጅት ጋር የሚደረግ ድርድር ህጋዊ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም - የህግ ባለሙያ
          • ህወሃትን ከአሸባሪነት ስያሜ ለማሰረዝ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡
                                    በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው የህወኃት ታጣቂ ቡድንና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ላለፉት 16 ወራት ሲካሄድ የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ከተለያዩ ወገኖች የሚወጡ መረጃዎች ቢጠቁሙም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ “እስካሁኗ ሰዓት ድረስ  ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የተጀመረ ምንም አይነት ድርድር የለም ብለዋል።
ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በአጭር ጊዜ ውስጥ መንግስት በጦርነቱ የበላይነትን ተቀናጅቶትግራይ ክልልን ከተቆጣጠረና በርካታ የህወኃት አመራሮችን ደምስሶና የተወሰኑትንም በቁጥጥር ስር ካደረገ በኋላ አሜሪካና አጋሮቿ ድርድር እንዲካሄድ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ መንግስት “ሽብርተኛ ተብሎ ከተሰየመ ድርጅት ጋር የመደራደር ፍላጎት የለኝም” የሚል ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ከስምንት  ወራት በኋላ መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ ሰራዊቱንና ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ክልሉን ተቆጣጥረው የጥቃት አድማሳቸውን ወደ አማራና አፋር ክልል በማስፋት፣ በሁለቱ ክልሎች እጅግ ዘግናኝ ጥቃትን በማድረስ ወደ ሰሜን ሸዋ መገስገስ በጀመሩ ሰዓት ከእግዲህ የድርድር ጉዳይ አክትሞለታል ብለው ነበር። ጦርነቱን በአሸናፊነት እንዳጠናቀቁ በመግለጽ።
የህወኃት ታጣቂ ኃይሎች  ጦርነት ሲጋጋልና የሃይል ሚዛኑ ወደ እነሱ ያጋደለ መስሎ ሲታይ ድምጽ የማሰማው የአሜሪካ መንግስት በህወኃት የመንግስት ጥምር ሃይሎች ከፍተኛ ጥቃት ሲፈጽሙ “ጦርነቱ ቆሞ ድርድር” ይደረግ በማለት በተደጋጋሚ ሲወተወቱ ታይተዋል፡፡
በሁለቱም ወገኖች መካከል ለወራት የቀጠለውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ውይይትና ድርድር እየተደረገ  መሆኑን የጠቆሙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሰላም ጥረት እንደሚደግፍ ገልፀዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወኃት ታጣቂ ቡድኖች መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆምና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑ አስደስቶኛለ፤ ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ድርድር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ መሆኑንም አመልክተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወኃት ሊቀመንብር ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገ/ሚካኤል ሰሞኑን ህወኃት የተመሰረተበትን 47ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ ላይ፤ ህወኃት ለድርድር በማያቀርባቸው ጉዳዮች ላይ ሰጥቶ መቀበል የሚባል ነገር አይኖርም ብለዋል። ሕወኃት ለድርድር አላቀርባቸውም ካላቸው ጉዳዮች መካከል የትግራይ ክልል ሰራዊት የትግራይ ክልል ወሰን ጉዳይ፣የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ መውጣት፣ የትግራይ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ጉዳይና በትግራይ ህዝብ ላይ በደል የፈፀሙ ግለሰቦች ተጠያቂነት  የሚሉት ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደተናገሩት፤ ከህወኃት አመራሮች ጋር እስከአሁን ድረስ የተጀመረ አንዳችም ድርድር የለም ብለዋል፡፡
“በመንግስት በኩል ከህወኃት ሃይሎች ጋር የተደረገ ድርድር የለም፡፡ ይህ ማለት ግን ድርድር አያስፈልገውም ማለት አይደለም፤ ጦርነት ኢትዮጵያን ለማፅናት ነው፤ የድርድሩም አላማ በሚያፈረስ በማንኛውም መንገድ ድርድር አያደርግም” ብለዋል፡፡ የአገሪቱን ሉአላዊነትና ህልውና ኢትዮጵያንበማይፈታተን ሁኔታ ለሚደረጉ ንግገሮች በሩ ዝግ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።
ህወኃት የተመሰረተበትን 47ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሊቀ መንበሩ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በሰጡት መግለጫ ለችግሮቹ ሰላማዊ መፍትሔ ለመስጠት የምናደርገው ጥረት በአጭር ጊዜ መቋጫ እንዲያገኝ ቀነ ገደብ ማስቀመጣቸውን ጠቁመው በቀነ ገደቡ መጠቀም ካልተቻለ ግን ብዙ መታገስ አንችልም ብለዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀ ቡድን ጋር ሊደረግ የሚችል ምንም አይነት ውይይትና ድርድር አይኖርም፤ መንግስት ከእነዚህ ወገኖች ጋር የሚያደርገው ድርድርም ህጋዊ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ሲሉ የህግና የፖለቲካ ምሑሩ አቶ አህመድ ኢሳ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የህግ ምሁሩ “የሽብር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012ን ጠቅሰው እንደሚናገሩት፤ በዚህ አዋጅ  አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየመ ድርጅት ስያሜው ተፈፃሚ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ  የሚያደርጋቸው ግንኑነቶችና እንቅስቃሴዎች ህጋዊ ውጤት አይኖራቸውም፡፡
ድርጅቱ ህጋዊ ሰውነት የሌለውና በአሸባሪነት ሲፈረጅም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት የነበረው ህጋዊ ሰውነት የፈረሰ በመሆኑ መንግስት ህጋዊ ሰውነት ከሌለው አካል ጋር ምንም አይነት ንግግርም ሆነ ድርድር ሊያካሂድ አይችልም።” ብለዋል-ምሁሩ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ድርጅቱን ከአሸባሪነት ለማሰረዝ የተለያዩ ጥረቶች እየተዳረጉ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል። ይህ ሂደት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት እድል ይኖራል ወይ? ህጉስ ይህንን ጉዳይ እንዴት ይመለከተዋል? በሚል ለህግ ባለሙያው ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “ድርጅቱ ስያሜው እንዲሰረዝለት ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ ማመልከት የሚችል ሲሆን ዐቃቢ ህጉ  ጉዳዩን ካመነበት ስያሜው እንዲሰረዝለት የውሳኔ ሃሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ም/ቤቱ የቀረበውን የውሳኔ ሃሰብ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርቦ ድርጅቱን ከአሸባሪነት ስያሜው ሊያሰርዘው ይችላል፡፡ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 24 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት በአሸባሪነት ተፈርጆ የነበር ድርጅት ስያሜው ሊሰረዝለት የሚችለው ድርጅቱ፤ የሽብር ወንጀለ፤ መፈፀሙን ያቆመና በዚህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ ሊሳተፍ የማይችል ስለመሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ህወኃት ግን ዛሬም ድረስ በተለያዩ የሽብር ተግባረት የንጹሃንን ደም ያለ አግባብ እያፈሰሰ፣ ንብረት እየዘረፈና አስገድዶ  እየደፈረ ባለበት ሁኔታ በምን አግባብ ነው ከአሸባሪነት ስያሜ ሊሰረዝ የሚችለው? ይህ ፈፅሞ ሊደረግ የማይችል ህገ ወጥ አሰራር ነው” ብለዋል፡፡
ጦርነቱ ለማስቆምና ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ ነው በሚባልበት እንዲሁም መንግስት ለውይይትና ድርድር በራችን ዝግ አይደለም እያለ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት ህወሃት በአንዳንድ  የአማራና አፋር አካባቢዎች ውጊያ እያደረጉና ጥቃት እፈጸመ መሆኑ እየተነገረ ነው።Read 792 times