Saturday, 26 February 2022 00:00

“አንድን ግንድ አስር ዓመት ውሃ ውስጥ ብታስቀምጠው አዞ አይሆንም!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)


          ከዕለታት አንድ ቀን ተኩላ ቀበሮን አሽከር አድርጎ ይቀጥረዋል። ተኩላ ጉልበተኛ እና ክፉ ነው። ቀበሮ ደግሞ መልካም፣ ግን የጌታው  የአያ ተኩላ ክፋት የሰለቸው ነው።
አንድ ቀን አብረው እየሄዱ ሳለ፣ አያ ተኩላ፤
“ወዳጄ ቀበሮ ሆይ! አንድ የምበላው ነገር ካላገኘህልኝ፤ አንተኑ ልበላህ ነው። አንድ መላ ምታ” አለው።
ቀበሮም፤
“ጌታ ተኩላ ሆይ! እዚህ አካባቢ አንድ የገበሬ ቤት አለ። ገበሬው ባለጸጋ ሀብታም ነው። ለምን እዚያ ሄደን ከሁለቱ አንዷን ጠቦት አምጥተን አንበላም? አለው።
አያ ተኩላ ተስማማ።
ቀበሮ ከሀብታሞች ቤት አንድ ጠቦት ሰርቆ አመጣ። ጠገቡ።
አያ ተኩላ ግን አልጠገበም። ስለዚህ እራሴ ሄጄ  ሁለተኛዋን ጠቦት አምጥቼ እበላታለሁ ብሎ አስቦ ወደ ገበሬው ቤት ሄደ። ሆኖም ጀፍጃፋ በመሆኑ ተነቃበትና ተያዘ። ባለቤቶቹ  እንዳይሞት እንዳይሽር አድርገው ቀጠቀጡት።
ተኩላም ወደ ቀበሮ ተመልሶ፤
“እንዲህ ያለ መዓት ውስጥ እንዴት ትከተኛለህ” ሲል አማረረ።
ቀበሮም፤
“ጌታዬ ሆይ! እንዴት ተያዝክላቸው?” ሲል ጠየቀው።
መልስ አልነበረውምና ጸጥ አሉ አያ ተኩላ።
በሁለተኛው ቀን፣ ተኩላው፡-
“አንተ ቀበሮ፣ የምበላው ነገር ካላገኘህልኝ አንተኑ ነው የምበላህ” አለና አስፈራራው።
ቀበሮም፤
“ዛሬ ከሰዓት፣ ዳቦ የሚጋግሩ ሰዎች አሉ። እዚያ ሄደን የተወሰነ ሰርቀን ብንመጣ ረሀብህን ያስታግስልሃል” አለው።
አያ ተኩላ ተስማማ።
ቀበሮው ወደ ዳቦ ጋሪዎቹ ሄዶ የሚችለውን ሰርቆ ለአያ ተኩላ አስረከበው።
አያ ተኩላ ግን አሁንም አልጠገበም። ሊሰርቅ ሄደ። ሆኖም ሲንከረፈፍ ባለቤቶቹ አገኙት። አሁንም እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ደበደቡት።
አሁንም በቀበሮው አሳበበና “እሱ ነው ለዚህ የዳረገኝ!አለ።
ብዙ ሥጋ የተሰቀለበት ጓዳ ደረሱ!
ተኩላ ተደሰተና ዘና ብለው መብላት ጀመሩ!
ሙዳ ሙዳውን እየጎረሰ ነው!
ተኩላው እየበላ ሳለ፣ ቀበሮው መለሰ- ቀለስ እያለ ዙሪያ-ገባውን ያጣራል።
ተኩላ፤ “አንተ ቀበሮ፣ ምን ወዲያ ወዲህ ያሰኝሃል፣ አርፈህ አትበላም?” አለው።
“ማንም አለመምጣቱን  ማረጋገጥ ስላለብኝ ነው” አለ አቶ ቀበሮ። “ያም ሆኖ፣ የእኔ ምክር ግን እርሶ በምንም ዓይነት ብዙ እንዳይበሉ ነው!”
አያ ተኩላም፣
“የመስቀያው ስጋ ሳይጠናቀቅ፤ምንም አላርፍም” አለ ተኩላ።
በዚህ ቅጽበት ወዲያ ወዲህ የሚለውን ቀበሮ ኮቴ ሰምቶ፣  የስጋው ባለቤት ከች ብሎ ኖሯል!
ቀበሮው እንዳየ ዘሎ ጉድጓዱ ገብቶ አመለጠ!
ተኩላ ቀበሮውን ሊከተል ከንቱ ሙከራ አደረገ! ሆኖም የበላው ስጋ ሆዱን ቀፍድዶ ያዘውና፣ ያን ሆዱን ይዞ በቀዳዳው መሹለክ አልቻለም።
ገበሬው ተኩላው ባለበት በቆመጥ አናት አናቱን እያለ ጸጥ፣ እረጭ አደረገው። ተኩላ ተሰናበተ!
ቀበሮም ከአሽከርነት ነጻ ወጥቶ በደስታ ጫካው ውስጥ ኖረ።
*   *   *
የጌታና የሎሌ ግንኙነት ዘላቂነት የለውም። በመንግስት ደረጃም ቢሆን! በተለይም የሎሌው ሚና እንደ ዛሬው ጌታው ያለውን መፈጸም ብቻ ሲሆን፣ እሱም በተሰለቸ መንገድ ሲሆን አይጣል ነው!በቃኝ የማይል ሃብታም የአገር ዕዳ ነው፡፡ ዛሬም ነገም!
ሁሌ ´የምበላውን ካላመጣህ አበላሃለሁ´ የሚል ስርዓት ያላቸው ገዥዎች ነገ ተበዩ ናቸው!
ግፍም በተገፊው አብሮ የሚበላው በዚሁ ስርዓት ውስጥ ነው!
´የአሽከር እሺታ ጌታውን ያባልጋል´ ይባላል። ጌትየው ከባድ ባለጌ ከሆነስ? ማነው ዳኛው? የሾመው ስርዓት? ወይስ ሌላ? እግዚሃር ይወቅ!
የእነ እንዳይበቃኝ ፍልስፍና፣የመንግስት መርህ ነው ከተባለ ውሎ  አድሯል። እነ እንዳይበቃኝ ያጎረሱት የሚያስጎመዣቸው ናቸው።
የአይበቃኝም ፍልስፍና ጠላትን ወይም ባላንጣን ወደ መናቅ፣ በስልትና በመላ ከመመካት ይልቅ በጉልበት ወደ መመካት፣ ማዘንበልን ያስከትላል።
ጌትነት ብዙ መልክ አለው። የሀብት ጌትነት አለ። የጉልበት ጌትነት አለ። የስልጣን ጌትነት አለ። የጌታ ታካኪ በመሆን የሚገኘው የአሽገር ጌትነት አለ። የአለቅነት ጌትነት አለ!
እነዚህ ሁሉ የጌትነት መልኮች ዞሮ ዞሮ፣ የበላይ የበታች ግንኙነት አጥር ውስጥ የተቀነበቡ ጉዳዮች ናቸው!
እየሰረቁ የሚያበሉት ጌታ፣ እሱን ያጠገበው ስርዓት ብቻ የዓለም መጨረሻ ይመስለዋል።
- ሙስና
- ስርቆት
- ጭፍራ ማበጀት /Network/
- ዘረፋ
- ንብረት ከአገር  ማሸሽ
- ያለጨረታ ማሸነፍ
- ኢ-ፍትሃዊነት
- ያላግባብ ሰራተኛ ማባረር
እኒህ ሁሉ የሚጠቃለሉት፤
“አዘለም፣ አንጠለጠለም፤ ያው ተሸከመ ነው”
በሚለው ነው። ሞሳኝ ያው ሞሳኝ ነው! አለቀ።
ንግዳዊ ሙስናም ሆነ ቢሮክራሲያዊ ሙስና፣ አሊያም በስልጣን መባለግ፤ ገና ከዐይነ-ውሃው እዚያው እጅ-በጅ መፍትሄ ይፈልጋል። “ሳይቃጠል-በቅጠል”ን ይሻል።
አበው፤ “በመስከረም የሚቆስል እግር፣ በክረምት ዝምቦች ያርፉበታል” ይላሉ አበው። ፈረንጆቹ /Coming events cast their shadows/ የሚሉት ነው። መጪው ነገር ወደድንም ጠላንም ዛሬ ላይ ጥላውን ይጥላል።
ይህም ሆነ ያ፣ በወንጀለኛው ዳፋ ንጹሁ እንዳይጠቃ፣ ሃይለኛው ደካማውን እንዳያጠቃ (እንዳይጫን)፣ ጊዜ የሰጠው፣ ቀን- የጎደለበትን ከጨዋታ ውጪ እንዳያደርገው፣ ትክክላዊ ፍርድና ዲሞክራሲያዊ አሰራርን ፈር ማስያዝ ሁነኛው መላ ነው! ከወሬና ከወረቀት ባሻገር እናስብ! ደምብ መመሪያና ህግ ከሁሉ በፊት ሰብዕናን ይፈልጋል! ግብና ዒላማችን ተቋም፣ አሊያም ፓርቲ አይሁን።
ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ ብዙ ጊዜ ብለናቸዋል። ሆኖም ብዙ ጊዜ ብለናቸውም የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ያለው ህብረተሰባችን፣ ዛሬም ጆሮውን ዘግቶ ተኝቷል፡-
“አንድን ግንድ አስር ዓመት ውሃ ውስጥ ብታስቀምጠው አዞ አይሆንም!”
የሚለውን ተረትና ምሳሌ ደግመን የምንናገረው ለዚህና ለዚሁ ብቻ ነው!!




Read 9315 times