Saturday, 26 February 2022 00:00

ብሔራዊ ምክክሩ የሁሉም መፈተኛ ነው

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

አገርና መንግስት አንድም ሁለትም ናቸው፡፡ መንግስት ይኖር ዘንድ አገር፣አገር ይሆን ዘንድም መንግስት አስፈላጊ ነው፡፡ መንግስታት ይወጡና ይወርዱ ዘንድም አገር የግድ መኖር  አለበት፡፡
የንጉሱ መንግስት ወድቆ ደርግ ሲተካ፣ ደርግም በመሳሪያ ትግል ተወግዶ ትሕነግ መራሹ ኢሕአዴግ፤ የኢትዮጵያን መንግስት መጨበጥ የቻለው ኢትዮጵያ በሀገርነት በመቀጠሏ ነው፡፡
“የአራት ድርጅቶች ጥምረት ነው” የተባለው ኢሕአዴግ፣ የኢትዮጵያን የመንግስት ሥልጣን እንደጨበጠ የፈለገውን ውሳኔ መወሰን  የሚያስችለው ድምፅ ይዞ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የሽግግር መንግስት ተመሰረተ፡፡ የሽግግር መንግስቱ ግን የተፈለገውን ውጤት  ሳያመጣ  ቀረ፡፡ ስልጣን ሙሉ በሙሉ ኢሕአዴግ ወደ ተባለው ይበልጡንም ወደ ትሕነግ እጅ ተጠቃሎ እንዲገባ ተደረገ፡፡ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ፍፁም የትህነግ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነው አረፉ፡፡
ሥልጣን የያዘው “ኢህአዴግ” ይበልጥ የከፋ አስተዳደር እየሆነ በመምጣቱ፣ አሸናፊ ነን፤ተዋግተን ባመጣነው ድል ማለትም ሥልጣን ማንም  ጠያቂ ሊሆን አይችልም፤መብት ማለት በእኛ ፈቃድ የሚወሰን ጉዳይ ነው; የሚል ትምክህት በበዛ ጊዜ፤ “ማሸነፍ ልብን ነው፣ ያሸነፋችሁት ደርግን እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ አይደለም" የሚል ተቃውሞ ተጀመረ፡፡ በወቅቱ ለህትመት በበቁ ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ የተቃውሞ ሃሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ። የፖለቲካ ድርጅቶችና የሙያ ማህበራት የኢህአዴግን መንገድ መቃወምና አጥብቀው መተቸት ያዙ፡፡
መንግስት ጠንካራ የነበሩትን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እና የሰራተኞች ማህበርን እያፈረሰ በራሱ አምሳል በተቀረጸ አካል ተካቸው፡፡ ብዙ የተወራለት በአዲስ የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚመራ መንግስት የመመስረቱ ተግባርና ተስፋም ውሃ በላው፡፡
ወቅቱ በአፍሪካ ምድር ትላልቅ ጉዳዮች የተፈጸሙበት ነበር፡፡ አንደኛው ለአመታት በቀለምና በዘር ልዩነት ስትታመስ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ምርጫ አካሂዳ፣ ለአመታት በእስር የቆዩትን ኔልሰን ማንዴላን በመምረጥ ፕሬዚዳንቷ አደረገች፡፡ በዚህ አላቆመችም፡፡ በአቤን ዴዝሞንድ ቱቱ የሚመራ፣የእውነትና የፍትህ አፈላላጊ ተቋም በማደራጀት፣ በደቡብ አፍሪካ ምድር የተፈፀሙ ግፎች ወደ አደባባይ እንዲወጡ፣ ጥፋተኞች ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ በሕዝብ መካከል ሰላም እንዲሆንም  አድርጋለች፡፡
ሁለተኛው ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ የዘለቀውና ስምንት መቶ ሺህ ሰዎች ያለቁበት የሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ነው፡፡ በአሁኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በፖል ካጋሜ የሚመራው የሩዋንዳ ሕዝባዊ ጦር የዘር  ማጥፋቱ በተፈፀመበት ጊዜ ሥልጣን ላይ የነበረውን መንግስት በማስወገድ ወንጀለኞች እንዲጠየቁ፣ በአገሪቱ እርቅና ሰላም እንዲወርድ አድርጓል፡፡
እነዚህ ሁለት የታሪክ አጋጣሚዎች በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ጥያቄ እንዲነሳ አደረጉ፡፡ ብሔራዊ እርቅ ይደረግ የሚል ጥያቄ፡፡ መንግስት ግን #ማን ከማን ጋር ተጣላና ብሔራዊ እርቅ ይደረጋል" በማለት  ጥያቄውን በአደባባይ ውድቅ አደረገው። ይባስ ብሎም #ተወዳድረው ማሸነፍ ያቃታቸው ሥልጣን ፈላጊዎች  ዘዴ ነች; ማለት ጀመረ፡፡ እርቅ የሚለው ቃል ላልተመቻቸው ወገኖችም “ብሔራዊ መግባባት” በሚል አጀንዳውን ለማሳመን ቢሞከርም፣ በስልጣን ላይ የነበረው መንግስት "በአይኔ አትምጡብኝ" ብሎ አሻፈረኝ አለ፡፡
መንግስት የተቀናጀ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አዘጋጀ፡፡ ይህን ፕላን በመቃወም በአዲስ አበባ ዙሪያ አመፅ ተቀሰቀሰ፤ አመፁም እየሰፋ ሄደ፡፡ የኦሮሚያ ክልልን አልፎ ሌሎችንም ክልሎች አዳረሰ፡፡ የአማራ ተወላጆች ጎንደር ላይ “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው” በማለት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ደግፈው ቆሙ፡፡ መንግስት ተንገዳገደ፤ ተብረከረከ፡፡ ሳይወድ ተገዶ ትሕነግ፣ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን የበላይነት ተነጥቆ ወደ መቀሌ ገሰገሰ፡፡
ወደ ስልጣን የመጣው በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት፣ ከሕወኃት/ኢሕአዴግ  የፀዳ ነው ለማለት ያዳግታል። አጋር የሚባሉ ክልሎችንና የክልል ገዢ ፓርቲዎችን ከአጋርነት አውጥቶ እኩል ወንበር የሰጣቸው ቢሆንም፣ ከብልፅግና መሥራቾች አንዱ ቢያደርጋቸውም፣ አሁንም እየተጠሩ ያሉት በቅርንጫፍነት ሳይሆን እንደ ቀደመው ሁሉ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የቤኒሻንጉል ወዘተ ብልፅግና ፓርቲ እየተባሉ ነው፡፡ ይሄ የብልጽግና ትልቁ ጥፋት ነው፡፡
ምንም ይሁን ምን የዘር ፖለቲካ መሪዎች ነገ አይኖሩም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስትም ዕጣ ፈንታው ከሌሎች መንግስታት የተለየ አይሆንም፡፡ በሥራው ይመሰገናል፤ ይወቀሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፄ ኃይለ ሥላሴን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዳመሰገኗቸው ሁሉ እሳቸውንም የሚያመሰግንና የሚያወድስ ትውልድ ይመጣል፡፡ በቀጣዩ ትውልድ ጠ/ሚኒስትሩ ከሚመሰገኑባቸው ሥራዎች አንዱ ደግሞ አሁን ሊካሄድ የታቀደው የአገራዊ ምክክር መሳካት ነው፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽነርነት 632 ሰዎች መጠቆማቸውን ገልጧል፡፡ ማን ጠቆመ፣ ማን ተጠቆመ የሚለውን ይፋ ባያደርግም። ከተጠቆሙት ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 75 እንደተያዙ አመልክቶ፣ ከእነዚህም ውስጥ 42ቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና የአገር ሽማግሌዎች አስተያየት እንዲሰጡ ማድረጉን አሳውቋል፡፡ ከ42ቱ ውስጥ ደግሞ አስራ አንዱን በኮሚሽነርነት፣ በምክትል ኮሚሽነርነትና በአባልነት መርጦ በምክር ቤቱ አሹሟል፡፡ ይህ ግልፅነት የጎደለው አሰራር ነው ተብሎ እየተተቸ ነው፡፡ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፣ አሠራሩን ግልፅ በማድረግ ረገድ አስቀድሞ ማሰብ እንደሚኖርበት ከወዲሁ ሊገነዘብ ይገባል፡፡
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ በትግሬ በአማራና በኦሮሞ የተያዘ ወይም የተቀነበበ ሆኗል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። አንድ አማራና ኦሮሞ ለብሔራቸው ሊደርሳቸው የሚገባው አንድ ከሰማኒያው (1/80) መሆን አለበት፡፡ የኮሚሽኑ አባላትም ሆነ የኮሚሽኑ አሠራር፣ ሰውን በሰውነቱ እንጂ በዘሩ ከመለካት መራቅ ወይም መታቀብ ይኖርባቸዋል። ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ ጥያቄዎችም ሆኑ ሃሳቦች ከዘር አንጻር እየተያዩ እንዳይመዝኑ አጥብቆ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
በአሸባሪነት የተፈረጁት ትህነግ እና ኦነግ ሸኔ በሀገራዊ የምክከር መድረኩ ላይ ተሳታፊ እንደማይሆኑ መንግስት አስታውቋል፡፡ መሳሪያ ያላነሱ፣ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ጫካ ያልገቡ ግን ደግሞ የሁለቱን ድርጅቶች ሃሳብ የሚያራምዱ ብዙዎች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ በነዚህ  ግን በሩ እንዳይዘጋባቸው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እንዲያውም መንግስት ፈልጎ ወይም ጠርቶ በምክክሩ ተሳታፊ ቢያደርጋቸው የበለጠ ተመራጭ ይሆናል፡፡
መንግስታት እነሱ የሚሰሩት ሁልጊዜም ትክክል ነው፡፡ ብልፅግና እና መንግስትም በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ትክክለኛነታቸውን ለማስረዳት ላባቸው ጠብ  እስኪል መልፋታቸው አይቀርም። አገራዊ ምክክሩ ይሳካ ዘንድ ብልፅግና መንግስት ከዚህ አይነቱ ልማድ መታቀብ አለባቸው፡፡ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ ለሚገጥሙት  ጥያቄዎች የህግ በፖሊስና በደንቦች መፍትሔየ ለመስማት መንግስት መፍጠን እንዳለበት መገንዘብ አለበት፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችንና መሪዎቻችን የተለመደ ዓመል ማኩረፍ ነው፡፡  የማያኮርፉበት ሰበብና ምክንያት በትክክል ስለመኖሩ ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠርቷቸው የሚቀሩ ብዙ ፓርቲዎች እንዳሉም እናውቃለን፡፡
“የእኛ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ተጠርተው የማይቀሩት የእንግሊዝና የአሜሪካ አምባሳደሮች ከሚያዘጋጁት  የሻይ ግብዣ ነው” የሚለው የአንድ ጓደኛዬ የሰላ ትችት ሁሌም አይረሳኝም፡፡
በአገራዊ ምክክሩ አንሳተፍም የሚል አቋሙን በይፋ በመግለፅ ኦፌኮ ቀዳሚው ነው፡፡ ሌሎችም ይህን መንገድ የሚከተሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ኦፌኮም ሆነ መሰሎቹ በምክከሩ ቢገኙ መልካም ይሆናል፡፡ ሌላው እንኳን ቢቀር እዚህ ድረስ ተጉዘን አቃተን ለማለት ይመቻቸዋል፡፡ ይህን ለማለት ደግሞ በቅን ልቦና ወደ ጉዳዩ መግባትን ይጠይቃል። አገራዊ ምክክሩ ለአዘጋጁም ሆነ ለተጋባዡ መፈተኛ መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡


Read 446 times