Sunday, 27 February 2022 00:00

“ብርሃን ሆነ” አለ - አበበ። “ጨለማ ይሆናል” ይላል - ከበደ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  (በቲፎዞ ሞድ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ቅኝቶች ናቸው፡፡)
                          
              ጨልሞበት የሚያጨልም ሰው አለ። “ፍቅሯ  ቀለለ ስል፤ እሷን አዘዘብኝ፤ ልታንገላታኝ ነው” ብሎ ያንጎራጉራል። የፍቅር ሃያልነትን ለመግለፅ የተዘፈነ አይመስለውም። “ፍቅር ሲታደስ”፣ መንፈስን የሚያስደስት ሳይሆን፣ ሕይወትን የሚያጨልም ይሆንበታል፡፡ ይሄ፣ ጭፍን የተቃውሞ ቅኝት-(setting) ነው።
ሌላ ደግሞ አለ። ቅንጣት የፍቅር ምልክት ባያይም፣ “ሱሪዬን አጥቤ ደጅ ላይ ባሰጣው፤ ወዳኝ ነው መሰለኝ ተራምዳው አለፈች” ብሎ ደስታውን ያዜማል። ዓመቱን ሙሉ፣ “እዮሃ አበባየ” እያለ፣ በየቀኑ የፌሽታ ርችት ሊያፈነዳ፣ በየእለቱ የምርቃት ድግስ ሊያበላ የተዘጋጀ ይመስላል። ይሄ ጭፍን የድጋፍ ቅኝት(setting) ነው፡፡
 
ሁልጊዜ፣ ሁሉም ነገር፣ ብሩህ ሆኖ የሚታየው ሰው መኖሩ ይገርማል። ግን አለ። ዘወትር፣ አበባ ነው። ታዲያ፣ ብርሃናማ መንፈስን ለመስበክ ብሎ፣ እናንተን ለማሳመን አስቦ አይደለም። ሰዎችን ለማበረታታትና ለማፅናናት፣ ወይም ፏ ብሎ ለመታየትና ለማስመሰልም አይደለም። በቃ፤ የመንፈሱ ብርሃን፣ ከሁለት ፀሀይ ይበልጣል። ቀንም ማታም፣ ፀሀይ አይጠልቅበትም።
የደበዘዘው ኑሮ ፈክቶ፣ የጨፈገገው ዓለም ደምቆ ይታየዋል። ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖም፣ ብርሃን አለ ይላል። በእርግጥ፣ ፀሀይ መጥለቁና መምሸቱ አይቀርም። ነገር ግን፣ ከቁብ አይቆጥረውም።
“ጨለማው፣ የብርሃን ማረጋገጫ” እንደሆነ ያብራራል። “ያለጨለማ ብርሃን አይኖርም፤ ብርሃንነቱም አይታወቅም” ብሎ ያስረዳል።
ለሙግት ብቻ አስቦ የተናገረ ይመስላል። ግን አይደለም። እንዲያውም፣ ሙግት አይወድም። ተከራክሮ የማሳመን ጥማት የለውም።
ማሳመን ቢፈልግማ፣… “ይመሻል፣ ይነጋል። ይዘንባል፣ ያባራል። ቀንና ማታ፣ ሃዘንና ደስታ ይፈራረቃል” በማለት፣ እንደመተኛትና እንደመንቃት፣ የፈረቃ ሕይወትን አስውቦ ለማሳየት ይሞክር ነበር። መንፈሱ፣ ይህን አይቀበልም። ግማሽ ሕይወትንና ግማሽ ሞትን በፈረቃ እንደማስተናገድ ሆኖ ይታየዋል።
“ብርሃን ለማግኘት ጨለማን በፀጋ እንቀበል” ለማለትም አይፈልግም። ይሄማ፣ ብርሃናማ ሃሳብ አይደለም። የቅይጥ ሃሳብ ግራጫ መንፈስ ይሆንበታል::
“የጨለማ ጊዜ ያልፋል” ብሎ ቢናገር ደግሞ፤ ደካማ የመፅናኛ እሽሩሩ ሆኖ ይሰማዋል።
ምንም ኑሮ ቢጨፈግግ፣ ምንም ዓለሙ ቢጨልም፣ “ብሩህ ዘመን እየመጣ ነው፤ ጊዜው ቀርቧል፤ ከደጃፋችን ደርሷል” ብሎ ያምናል። ሌሎች ሰዎች ባያምኑ ይደንቀዋል። እንዴት ብርሃናማ ዘመን አይታያቸውም ብሎ ይገረማል።
ለነገሩ፣ የጠወለቀ ቅጠል እንጂ የደመቀ አበባ ባይታያቸውም፣ መንፈሱ አይረበሽም። ዓለም ሁሉ ብርሃን ባይላበስ፣ ሁሉም ቤት በደስታ ባይሞላ፣ እንዳሰበው ባይሳካ፣ ትንቢቱ ባይፈፀም እንኳ፤ ፊቱ አይጨፈግግም።
ችግር ባይቃለልም፤ ይባስ ብሎ መከራ ቢበረታም፤ ጨለማው ቢጠቁርም፤ ምናቡ አይደበዝዝም፣ መንፈሱ ጥላ አያርፍበትም።
ሰዎች፣ ጨልሞባቸው ሲጨነቁ፤ “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” ብሎ ያስታውሳቸዋል።
“ሰማዩ ቀላ!” ብለው ሰዎች ሲሰጉ፤ “ሰማይ ደም መሰለ፤ ሊነጋ ነው ሌቱ!” የሚል ዜማ ይመጣለታል።
ችግር ሲበዛ፣ የመፍትሔ ግብዣ ሆኖ ይታየዋል።
ህመም ሲያድርበት፣ የጤንነት ዋዜማ ነው ይላል።
መድሃኒት፣ ላይ ላዩን ሲቀምሱት ይጎመዝዛል፤ ቀጥሎ ግን ያድናል። ይሄ ምኑ ይጠየቃል? መድሃኒት፣ መጎምዘዙ ለበጎ ነው። ለመዘዝ አይደለም። ሁሉም ነገር ለበጎ ነው፤ አይንህን ብትገልጥ ይታይሃል ብሎ ያስባል።
ምንም ቢሆን፣ ምንም ቢያስቀይም፣ ቢያሳምም፣ የቱንም ያህል የከፋ ቢሆን፣ “ሁሌም የሚያምር ገፅታ፣ በጎ ጎንና አንዳች እርካታ አለው” ብሎ ያምናል። “ሁሉም መልካም ይሆናል” እያለ በፈገግታ ያዜማል።
ሕንፃ ቢፈርስ፣ በቅጽበት የሚከሰትለት ሃሳብ፣ ምን ያህል ረዝሞና ተስፋፍቶ እንደሚታነፅ ነው። የሚያጓጓ የስራ ብዛት፣ ሰማይ ጠቀስ ዲዛይን፣ የግንባታ ምኞትና አዲስ እቅድ ይታያችሁ፤ ሕልም ይኑራችሁ፤ ባለራዕይ ሁኑ ይላል።
የሰዎችን ሕልፈት ሳይሆን፣ የህፃናትን ልደት ያልማል፤ ዋይታን ሳይሆን እልልታን። ከመርዶ ውስጥ፣ የምስራችን ፈልቅቆ ያወጣል። “ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ እንኳኩ ይከፈትላችኋል” የሚለው ስብከት ይማርከዋል።
“ብሩህ ራዕይ፣ ትልቅ ምኞት ይኑርሽ፣ ትልቅ ሕልም ይኑርህ፣. ታያለህ ይሳካል፤ታያለሽ ኑሮሽ ይሟላል። ምንም አትጠራጠሩ” ይላል።
ባይሟላና ባይሳካም፤ ችግር የለውም። “ውድቀት የመነሳት መጀመሪያ ነው። ይህን ማወቅ፣ የጥበበኛ ሰው ምልክት ነው” ብሎ ያስባል። ያምናል። “ውድቀትን ወደ መልካም እድል መለወጥ” የሚል መፅሐፍ ማንበቡን ያስታውሳል።
ምንም ቢሆን፤ መንፈሱ አይሸነፍም። እናንተም አትሸነፉ ይላል።
“አሁን ባይሳካም፤ አትጨነቁ፡ ይ.ሳ.ካ.ል.”።
“እንዴታ! ይሳካል!”… ይላል ንፁህ ህልመኛ። ለጭፍን ድጋፍ የተዘጋጀ የቲፎዞ ቅኝት ነው፡፡
“ይሳካል? እንዴት?”… ይላል የባነነ ህልመኛ። ክፉውን ለመለየት በጎውን ለመቀበል የተዘጋጀ የሚዛን ቅኝት ነው፡፡
“እንዴትም አይሳካም! ቢሳካም አይረባም”… ይላል ሕልም የጨለመበት፡፡ ይሄ ለጭፍን ተቃውሞ የሚቅበዘበዝ የቲፎዞ ቅኝት ነው፡፡
ሕልም ጠፍቶበት፣ ሕልም የሚያጠፋ ሰው፣…
“ሕልም ሞኝነት ነው፤ ስኬት ተረት ነው”፤ ይላል፡፡
“ኑሮ የማያልቅ መከራ ነው። ሕይወት ከማህፀን እስከ መቃብር፣ መራራ ነው፤”… ይላል የጨለመበት ሰው  (የጨፈገገውን ብቻ ሳይሆን፣ ብርሃንንም በሚያጨልም መንፈስ)።
“በእርግጥ፣ አላማህ የተሳካልህ፣ ኑሮሽ ያማረልሽ ይመስላችኋል። ስኬት መሳይ አጋጣሚ ይከሰታል፣ ቆንጆ መሳይ ኑሮ ይታያል። ሞልቷል። ግን፤ ሁሉም አይረባም። ሁሉም ከንቱ ነው።” ብሎ ይዘረግፈዋል፡፡
“ስኬትም አላፊ፣ ውበትም ጠፊ ነው። የፈካው አበባ፣ ጠውልጎ ይደርቃል። የበሰለው ፍሬ፣ ወድቆ ይበሰብሳል”… እንግዲህ እያለ ጨልሞበት ያጨልማል። ፀሀይ ወጥቶ የሚያውቅ አይመስላችሁም - ስትሰሙት።
ለንፁህ ሕልመኛ ግን፣ ኑሮ ቀላልና ጣፋጭ ነው። ስኬትም ወዲያው የሚመጣ፤ ከቤት ደጃፍ ላይ የሚገኝ  ይመስላል። ኑሮና ስኬት፣ ወጣ ብሎ የጠዋት ፀሀይ እንደመሞቅ ነው - ያለወጪ ያለ ድካም፣ እዚያውና ወዲያው።
ግን፣ አሁን ባይሳካም፤ አትጨነቅ። ይሳካል። ይላል ንፁህ ሕልመኛ፡፡
የሚዛን ቅኝት፡፡ ሕልም፣ አለው፡፡ ግን በንቃት ነው፡፡
እንዴት? ብሎ የሚጠይቅ ሰው፣ ንፁህ ሕልመኛ አይደለም። ግን ሕልም የጨለመበትም አይደለም።
በእርግጥ፣ በአንድ በኩል፣ የህይወት ዓለም ውስጥ፣ ጨለማና ችግር መኖሩን አይጠራጠርም። ያምናል። የጨለመበት ይመስላል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጨለማ ውስጥ መቅረትን አይፈልግም። ብርሃንን ይመኛል። ስኬትን ያልማል። ሕልመኛ ይመስላል።
ግን፣ የስኬት ሕልም፣ አየር ባየር፣ ስኬትን አይወልድም። ታዲያ፣ “ይሳካል” ሲሉት፣ አልሰማም አይልም። እንዲያውም፣ ለመስማት ይጓጓል።
“ይሳካል? እንዴት?” ብሎ ይጠይቃል።
ይሳካል? በብዙ መከራ? በዓመታት ልፋት? እና ያኔ ይሳካል? ብሎ ይመረምራል። ያመዛዝናል፡፡ ውጤቱስ፣ የዚያኑ ያህል ይጣፍጣል? ድምፃዊቷ እንዳለችው፣ በእሳት እንደተሰራ ወርቅ፣ የጥረት ስኬትም ያምራል?
የጥረት ውጣውረድ ቀላል አይደለም። ከባድ ነው፡፡ ወይም ብዙ ይሆናል። አልያም፤ ይረዝማል፡፡ ቢሆንም ግን፣ ደራሲው እንዳለው፣ “Nothing Is Ever Easy” የሚያሰኝ ቢሆንም፤ ውጤቱ የከበረ፣ እንደወርቅ ያማረ ከሆነ፤ ሕይወትና ጥረት ግሩም አይደል!
 የነቃ ሕልመኛ እንዲህ ነው። ታዲያ፣ እንዲህ አይነት ንቁ  መንፈስ፤ “ብርሃናማ ነፍስ፣ ደማቅ መንፈስ ነው” ማለት አይቻልም?
 ለንፁህ ሕልመኛ፣ ይሄ ሁሉ፣ ብሩህ አይደለም። ግራጫማ ሆኖ ይታየዋል።
በብዙ ጥረት፣ በረዥም ጉዞ፣ በአድካሚ ውጣ ውረድ፣… በመከራ ምኞት ተሳክቶ፤ ለውጤት ደርሶ….
“ይሄማ ብሩህ መንፈስ አይደለም” የሚሉ የስኬት ሃዋሪያት አሉ።
 የውጣ ውረድ ጉዞ፤ “የጭጋግ መንፈስና የጨለማ ምልክት” እንደሆነ ይናገራሉ። ደግነቱ፣ መፍትሄው አላቸው። “ጨለማ መንፈስ፣ በቀላሉ በቀላሉ ይጠገናል። እንዲያውም፤ ስለ ህክምናና ስለ ጥገና ማሰብ የለብንም” ይላሉ።
“ስለ ህክምናና ስለ ጥገና ማውራት፣ የህመምና የስብራት እስረኛ እንደመሆን ነው። የጤንነትን ውበትና የኑሮን እርካታ፣ የመታነጽና የመበልፀግ ሕይወትን ነው ማሰብ ያለብን” ብለው ያስረዳሉ።
“በብዙ ጥረት፣ በረዥም ጉዞ…ምናምን አትበሉ። ደርሻለሁ በል፤ ተሳክቶልኛል ብለሽ እመኚ። እንደ እምነትሽ ይሆንልሻል፤ እንዳልከው ይፈፀምልሃል።”
“ባይሆንልሽ፤ ባይፈፅምልህ…. አትጨነቁ። ለበጎ ቢሆን ነው። መጨናነቅ ጭንቀትን ይጠራል። በእጃችሁ ያለውን ፀጋ ሁሉ አስቡ። ደስም ይበላችሁ፤”...ይላል ብርሃናማው የቲፎዞ ቅኝት፡፡ አይኑን ጨፍኖ፣ በምናቡ የማያልቅ ብርሃንን መፍጠር ይችላል፡፡
“ዋይታ፣…የተሳሳተ እልልታ ነው” ይላል- ንፁህ ሕልመኛ፡፡
የአንዳንድ ሰው ብሩህ መንፈስ፤ ድንቅ ነው። ምንም ቢሆን፣ ርችት ለመተኮስ ሰበብ አያጣም። ምን ይሄ ብቻ። ምንም ቢሆን፣ ምንም ቢከሰት፣ የእልልታና የድግስ ሰበብ ይታየዋል። ሰበብ ባይታየውም፣ በምናብ ይፈጥራል።
ሱሪውን አጥቦ፣ ቆንጅየዋ ወጣት በምትመላለስበት መንገድ ላይ ያሰጣል።  የልብስ ማስጫ ገመድ ያኔ ድሮ አልነበረም? መሬት፣ሳር ላይ ተዘርግቶ ነበር የሚደርቀው። ብርሃናማው ወጣት መንገድ ላይ ነው ልብሱን የዘረጋው፡፡ ቆንጆዋ ወጣት ምን ታድርግ? ተሻግራው ሄደች፡፡ ደግ አደረገች፡፡
“ወዳኝ ነው መሰለኝ፣ ተራምዳው አለፈች” ብሎ ይዘፍናል።
የታጠበውን ሱሪ ረግጣ ብታልፍስ? እሰየው ነው። “ወዳኝ ነው መሰለኝ፣ ነካክታው አለፈች” ብሎ ይዘምራል።
ከሱሪው አጠገብ ደርሳ፣ ወደ ቤቷ ተመልሳ ብትሄድ፣ “አይታው ተመለሰች” ይላል - “ይህም የፍቅር ምልክት ነው” ለማለት።
ሱሪውን አይታ ብትስቅስ? ተገኝቶ ነው? የፍቅር ማረጋገጫና ማህተም ይሆንለታል - “ወዳኝ ነው መሰለኝ፣ በፈገግጋታ ሳቀች” ብሎ ነገሩን ለማሳመር ይሞክራል።
ውቢቷ ወጣት፣ ምንም ብታደርግ፣ የጎረምሳውን ብሩህ መንፈስ ማድመቅ እንጂ፣ ማደብዘዝ አትችልም።
ያጠበውን ልብስ ረግጣ ብታቆሽሽ፣ ከዚያም አልፋ፣ ሱሪውን ብታቃጥለው እንኳ፤ የመዋደድ ችቦ የተለኮሰ ይመስለዋል። የፍቅር ሙቀት የተቋደሱበት ክብረ በዓል ሆኖ ይታየዋል።
ቀኑን የሚያጨልም የቲፎዞ ቅኝትም ይመጣል- ሕልምን የሚያጠፋ፡፡
 ንፁህ ሕልመኛ፣ሁልጊዜ፤ በድጋፍ ቅኝት ይዘምራል፡፡ ደግ ደጉ ይታየዋል - በምናብ እየፈጠረም ቢሆን። እሳት ቢያቃጥለው፤ “አይበርድም” ይላል። በረዶ ቢዘንብበት፤ “አያቃጥልም” በማለት አወንታዊ ገፅታ ያላብሰዋል።
እስከመቼ እንደሚዘልቅ እንጃ።
“እና በረዶ፣ ፀሀይና እሳት ጠመዱኝ፤ ብዬ እርግማን ላውርድባቸው? እድሌ ጠማማ እያልኩ ማዘን፣ ማማረርና መኮራመት ይሻላል? ሃዘን ካልተዉት፣ ውስጥ ዘልቆ ይጸናል፣ ተጨማሪ ሃዘንም ይጠራል። ሲያማርሩ ሌላ የመረረ ይመጣል። ይሁን ብለው በፀጋ ቢቀበሉት ይሻላል። “አያድርስ” ነው ነገሩ። የባሰም እንዳለ አለመርሳት ነው - ደጉ። እንዲህ እየተናገረ፣ ኑሮን የሚያጠቁር ይሻላል? የጨፈገገ መንፈስ ይሻላል?” ይላል-ንፁህ ሕልመኛ፡፡
 እውነትም፣ ጨፍጋጋ መንፈስ፣ እንኳን ሰበብ አግኝቶ ይቅርና፤ የንጋት ብርሃን ላይ ቆሞ፤ ዓለምን ማጨለም አይከብደውም። ፀሀይዋ ስትወጣ እያየ፣ መምሸቱ መጨለሙ እንደማይቀር ይናገራል - ሌሊቱ ቀርቧል ይላል።
እውቀት ሲበራከት፣ ትምህርት ሲያብብ ቢያይ፤ “ምን ዋጋ አለው! እውቀት ዳቦ አይሆንም” ይላል።
የከዋክብትን ርቀት፣ የዓለማትን ብዛት፤ የውቅያኖስን ጥልቀት መመርመር፣ የህዋሳትና የንጥረ ነገሮች ረቂቅነት ላይ ቀመርና ስሌት እየሰሩ፣ በሃተታ መምጠቅና መራራቅ፣… የማታ፣ ማታ፣… ቅንጣት የሚላስ ቁራሽ፣ የሚቀመስ ጠብታ አያመጣላችሁም ይላል።
የእለት ጉርስ፣ መጠለያ ዳስ፣ የአመት ልብስ አይሆንላችሁም። ሃተታና ሃሳብ ቢትረፈረፍ፣ አይጋግሩትም፤ ጎተራ አያስገቡትም ይላል። እውቀት ሌላ ኑሮ ሌላ፣ ሃሳብ ሌላ ተግባር ሌላ…በማለት፣ብርድ ይጋግርባችኋል፡፡
በተግባር የተሳካ፣ በኑሮ የበለፀገ አጋጣሚ ቢያይ፣ መንፈሱ የሚፈካ ይመስላል። ግን፣ አይፈካም። “የዓለም ስኬት አላፊ ነው፤ ተድላና ፀጋ ጊዜያዊ ነው፤ እንደጤዛ። ለዚያውም የአንድ ትንፋሽ ጤዛ። ስኬት ቢያጋጥም፤ የአጋጣሚ  ጉዳይ ነው። ከዚያ አያልፍም። እንደ አጋጣሚ ይመጣ ይሆናል። በእርግጠኝነት ደግሞ፣ ከአመጣጡ ፈጥኖ ይሄዳል። አላፊ ጠፊ ነው - የሰው ስኬትና የዓለም ሃብት” ይላል።
ስኬትና ሃብት፣ ዘላቂና ቋሚ ቢሆኑም እንኳ፤ መንፈሱ አይደምቅም። ለምን?
 “ደስታና ፍቅር በሃብት ብዛት አይገኝም” ይላል። “የህይወት ትርጉም በብር አይሞላም፤ የህይወት ጣዕም በገንዘብ አይገኝም” ይላል ጎዶሎነቱ እየታየው።
“ደግሞስ፣ መች ነው ክብር ለአዋቂ የሆነው? የት ነው ሃብትና እርካታ፣ ለጥበበኛውና ለትጉህ ሙያተኞች የሆነው? መቼ ነው እውነትን የሚናገር ሰው፣ መውደድን ያተረፈው? ሸንጋይና አስመሳይ ነው ዝነኛ የሚሆነው።” እንዲህ እያለ፤ ሁሉንም ያጨልማል።


Read 378 times