Sunday, 27 February 2022 00:00

ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጉዳት ለመዳን ምን እናድርግ?

Written by  ወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ (አልታ ካውንስሊንግ)
Rate this item
(1 Vote)

  “ባለፈው ሳምንት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዋጋ ያስከፍላል” በሚል ርዕስ ስር ከመጠን በላይ ዲጂታል ቴክኖሎጂንና ሶሻል ሚዲዲያን መጠቀም ሊፈጥር የሚችለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለማየት ሞክረናል፡፡ በዚህ ሳምንት “ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጉዳት ለመዳን ምን እናደርግ?” በሚለው ርዕስ ስር እንነጋገራለን፡፡
ዲጂታልና ሶሻል ሚዲያን “ከመጠን በላይ” መጠቀም ስንል ምን ማለታችን ነው? ከመጠን በላይ በሁለት መለኪያዎች ልናየው እንችላለን፡፡ አንደኛው ለቤተሰብ ግንኙነት፣ ለማህበራዊና መንፈሳዊ ህይወት ጊዜ ማጣትና ለግል የሚደረግን እንክብካቤ ክፉኛ ሲጎዳ (ለምሳሌ ንጽህና መጠበቅ፣ በአግባቡ መመገብን፣ አካላዊ እንቅስቃሴ መግታትን ያካትታል)፤ በዚህም ምክንያት ግንኙነቶች ችግር ውስጥ ሲገቡ፤ ሥራን በአግባቡ እንዳናከናውን እክል ሲሆን ከመጠን ያለፈ ይሆናል፡፡ ሌላው የምናየውና የምንሰማው ነገር ሃሳባችንን በአብዛኛው አሉታዊ ሲያደርገው፣ ስሜታችንን ሲጎዳ፣ የእንቅልፍ ስርዓታችንን ሲያዛባ፣ ድርጊታችንን አላግባብ ሲያደርገው (ለምሳሌ ሱሰኛ ሲያደርገን) ዲጂታል ቴክኖሎጂና ሶሻል ሚዲያ ከመጠን በላይ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡
ጥብበ ማለት ሚዛናዊነት እንደሆነ የጥንቱ ፈላስፋ አርስቶትል  ይነግረናል፡-“Virtue is the golden mean between two vices, the one of excess and the other of deficiency”  ይህ ፈላስፋ ሰዎች ደስታን እንኳን ለማጣጣም በሁለት ፅንፎች መካከል የሚገኘውን መካከለኛ ምርጫ ማድረግ እንደሚገባቸው ይገልፃል። ይህ የአርስቶትል ንግግር በስነልቦና ሳይንስ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው፡፡  ነገሮችን በሚዛናዊነት ማየትና ማድረግ ለአዕምሮ ጤንነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ለምሳሌ አራት የህይወት አቅጣጫዎችን በሚዛናዊነት መከወን ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም አካላዊ (physical) (በአግባቡ መመገብ፣ ንጽህናን መጠበቅ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አካላዊ ጤናን መንከባከብ)፤ ሥራና ስኬት (Achievement) (የሥራና  የትምህርት ህይወት)፤ ማህበራዊ -(Social) (ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ማህበራዊ ግንኙነት ማድረግ) እና መንፈሳዊ (Spiritual) (ሃይማኖታዊ ተግባራትን መከወን፤ የማሰላሰያ ጊዜ መውሰድ) ናቸው፡፡ አንድን ፊኛ ከመጠን በላይ በአየር ብንሞላው በመጨረሻ ይፈነዳል፡፡ በመጠኑ ብንሞላው ግን ለምንፈልገው ዓላማ እናውለዋለን፡፡  ንዴት እቃ ካሰበረ፣ በራስ እና በሌሎች ላይ ጉዳት ከፈጠረ ከመጠን ስላለፈ አሉታዊ ውጤትን ያመጣል፡፡ ንዴት ግን በመጠኑ ከሆነ ንዴት የፈጠረውን ሁኔታ ለማስተካከልና ለሰብዕና ቀረፃ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ዲጂታልና ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንም እንዲሁ በመጠኑ ካልሆነ ባለፈው ሳምንት በዝርዝር ያየናቸውን ችግሮች ያመጣል፡፡  
ከዲጂታል ቴክኖሎጂና ማህበራዊ  ሚዲያ ጉዳት ለመዳን የሚከተሉትን ማድረግ ያስፈልጋል፡-
የምናየውን እና የምንሰማውን መምረጥ፡- የምናየው የዲጂታልና ሶሻል ሚዲያ ይዘት ለስነልቦናና ለማህበራዊ ጉዳት ሊዳርገን ይችላል፡፡ አንዳንድ በፊልም የሚታዩ ትዕይንቶች ለአሉታዊ አስተሳሰብና ለመጥፎ ባህርያት የሚዳርጉ ናቸው፡፡ አንዳንድ ወጣቶችና አዋቂዎች የሚያዩዋቸው ፊልሞች ለብስጭት፣ ለንዴትና ለጠብ አጫሪነት ባህርይ ሲዳርጓቸው እናያለን። ከዚህም በተጨማሪ ሱስ ይሆኑባቸዋል፡፡ በመሆኑም የሚያዩትን መምረጥ አለባቸው፡፡
በዲጂታልና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምናሳልፈውን ጊዜ መገደብ፡- የሥራ ክንውንና የቤተሰብ ጊዜን እንዳይሻማ እንዲሁም ለራሳችን የምንሰጠውን ጊዜ እንዳያሳጣን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
በስራ ቦታ እና በስራ ሰዓት ሶሻል ሚዲያ አለመጠቀም፡- በዓለም ደረጃ ብዙ አሰሪዎች ይህንን ክልከላ ያደርጋሉ። ክልከላውን የሚያደርጉት ምርታማነት እንዳይቀንስ፣ የኔትወርክ ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅና ሰራተኞች ከሌላኛው ወገን ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል ጭምር ነው፡፡ ይህ ክልከላ መኖሩ ሰራተኛው ከሥራውና ከማህበራዊ ግንኙነቶች ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳል፡፡ አሰሪዎች ይህንን ባያደርጉም ግለሰቦች ለራሳቸው ደህንነትና ሥራ ላይ ትኩረት ለማድረግ ሲሉ “በስራ ሰዓት ሶሻል ሚዲያ አልጠቀምም” ብለው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ በራሳቸው ተነሳሽነት እንደዚህም የሚያደርጉ ሰራተኞች አሉ፡፡
ዘመናዊ ስልኮችን (ስማርት ፎንስ) ከእንቅልፍ ሰዓት አስቀድሞ መጠቀም ማቆም፡- አልጋ ላይ ተኝቶ መጠቀም በቂና የተረጋጋ እንቅልፍ እንዳንተኛ ያደርጋል። ከተጀመረ ማቆሚያው ያስቸግራል፡፡ ሳይታወቅ ማረፍ የሚገባንን ያህል ሳናርፍ ሌሊቱ ይጋመሳል፡፡ ይህም በቀጣዩ እለት ከሃይላችንና ከንቃታችን ጋር እንዳንሆን ያደርጋል፡፡
በዲጂታልና በማህበራዊ  ሚዲያ ዙሪያ የቤተሰብ ህግ ማውጣት፡- የአልታ ካውንስሊንግ መሪ ሃሳብ (Motto)፤ “ቤተሰብ የትውልድ መሠረት!” የሚል ነው፡፡ ቤተሰብ ስለ ዲጂታልና ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ህግና ደንብ ሊያወጣ ይገባል፡፡ እድሜያቸው ከሶስት ዓመት በታች ለሆኑት ልጆች በተቻለ መጠን ስክሪን ላይ እንዳያሳልፉ ማድረግ፣ ለታዳጊዎች- ለትምህርታዊና ለመዝናኛ የሚጠቅሙ ቪዲዮዎችን እንዲመለከቱ በቀናትና በጊዜ የተገደበ ጊዜ መስጠት፤ ለወጣቶች ደግሞ ጥቅምና ጉዳቱን እንዲለዩ፣ እንዲያውቁና እንዲረዱ በማድረግ ራሳቸው መጠን እንዲያበጁለት መምከርና ከዓላማቸው ጋር ተያያዥነት ያለው የዲጂታልና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መርህዎች እንዲኖራቸው ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡
ወላጆች ራሳቸው ለልጆቻቸው አርአያ የሚሆን የዲጂታል ቴክኖሎጂና ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መርህ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ባልና ሚስት ተመሳሳይ የሆነ የአጠቃቀም አቋም ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም አንዱ ለልጆቹ ፈቃጅ ሌላው ደግሞ ከልካይ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ልጆቹም የቤቱን ህግ እንዲያውቁና እንዲገዙ ይረዳቸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በዲጂታልና በማህበራዊ ሚዲያ ዙሪያ ሲነጋገሩ ልበ ሰፊ በመሆን ጥቅሙንና ጉዳቱን በማስረዳትና በሂደት የሚሻሻል ባህርይ እንደሆነ በማሰብ ሊሆን ይገባል፡፡ አንዳንድ ወላጆች በዚህ ዙሪያ የተፃፉ የቴክኖሎጂ ጉዳቶችን ተመልክተው የእለቱ እለት ልጆቻቸው ላይ ክልከላ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መልክ ከማድረግ ተቆጥቦ በመምከርና ከመጠን ሲያልፍ የሚያመጣውን ተፅእኖ በማሳወቅ፣ በሂደት እንዲያሻሽሉ ማበረታታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 4605 times