Thursday, 03 March 2022 06:35

ከባዶ ላይ መዝገን...

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  "--ለምንም ነገር ልመና ማቅረብ ትቻለሁ፡፡ የኀዘን እንጉርጉሮ ማሰማት አቅቶኛል፡፡ በተቃራኒው በጣም ጥንካሬ ይሰማኛል፤ እኔ ከሳሽ ስሆን ተከሳሹ እግዚአብሔር ነበር፡፡ ዓይኖቼ ተከፍተዋል፡፡ ብቻዬን ነኝ፤ ያለ እግዚአብሔርና ያለ ሰው በአስፈሪ ሁኔታ ብቻዬን ነኝ፡፡ ያለ ፍቅር ወይም ያለ ምሕረት፡፡--"

             መጣሁ አየሁ፡፡ ሁሉንም መረመርኩ። ሁሉም ባዶ ነበር፡፡ ዘመኑ ዘመኔ ሆነ፡፡ ከየትኛው ጥልቅ ጉድጓድ ወደዚህ ጨካኝ ዓለም እንደተጣልኩ አላውቅም፡፡ ምናልባት ማወቄ የመሆን አለመሆን ዕጣፋንታዬን መወሰን ካላስቻለኝ፣ ልዩነት አያመጣም ይሆናል፡፡ ግን ዙሪያዬ በሙሉ በምልዓት የተንሰራፋ ባዶነት ተወሯል፡፡ ሁሉ ምንም ነበር፡፡ ከባዶነት የሚገዝፍ የሆነ ነገር ቢኖርስ ስንኳ ሕመም ነበር፡፡ የሚበላ አልጠፋም፣ ጣዕም ግን ምንም፡፡ ንግግር፣ ቋንቋ እንደ ጉድ ፈልቷል፤ ለዚያውም ሰማኒያ፣ ሁለት ሺህ፣ ከሀያ ሺህ በላይ... ግን መግባባት ጨርሶ አልተቻለም፡፡ መገናኘት ነበር፤ የነፍስ ተግባቦት ግን ፈጽሞ የማይታሰብ ሆነ። ሕዝብ ነበር፤ ኅብረተሰባዊነት ከጅምሩ መክኗል፡፡ ሰው እንኳን ከሰው ከጥላው ተኳርፏል፡፡ ኪነት ነበር፤ ግን የበረከተው በጅምር የቀረ፣ ሊሆን ያለ፣ ቁንጽል ብቻ ሆነ... ባለታሪክ የናቀው፣ የሚዘምረው ያጣ ታሪክ ነበር፤ ትርክት ግን ምንም! ሀይማኖት ሰልጥኗል፤ እምነት ግን ተራቁታለች፡፡
ሺህ ዘመናት ወደ ኋላ አየሁ፡፡ ሺህ ዘመናት ወደ ፊት ተነበይሁ። ትከሻዬን ይከብደኛል። ክርስቶስ በኖረበትም ዘመን የሆነው እንዲህ ይመስለኛል፡፡ ቢሆንም የመለኮትን ትንፋሽ ተሸካሚ ነውና ሰብዓዊነትን አልተጠራጠርሁትም። ሰው ሰብዓዊነቱን የቀረፀባቸው መንገዶች ስህተት እንደነበሩ ግን አምናለሁ፡፡ ሰው ራሱን ከመግራት ይልቅ ሌሎችን ለመግዛት ሰልጥኗል፡፡ ሰብዓዊነት መክኗል። ተኮላሽቷል፡፡ ገጣሚው እንዳለው፤ ሰው በሰው ሲታደን አያለሁና ከሰው ይልቅ ሰዎች ሲበልጡባቸው አይቻለሁና፣ ሰው ከመሆኔ ውጭ አዳኞቼ ስለምን እንደሚያሳድዱኝ ኩነኔዬን አላውቅምና፣ ሰብዓዊነትን መጠራጠር ጀምሬያለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ስለራሴ ብቻ አይደለም፡፡ እኔማ የትም ባክና ባክና አበባ ብታጣ ኩስ ላይ ከምታርፍ መድረሻቢስ ቢራቢሮ ባንስ እንጂ አልበልጥ...
ለሰው ልጅ ግን ከሰው ልጅ በላይ ጠላት ሊኖረው አይችልም፡፡ በፍጹም! ሁላችንም በዳይ፣ ሁላችንም ተበዳዮች ነን፡፡ የሰውን ልጅ የሚያድነው ትልቁ አውሬ፣ ራሱ የሰው ልጅ ነው፡፡ አሁን የት እንዳነበብኩት ላስታውሰው በተቸገርኩት የሆነ ጥናት መሰረት፤ ባለፉት ሦስት ሺህ ዘመናት፣ በበሽታዎችና በወረርሽኝ ከሞተው የሰው ልጅ ይልቅ በግጭትና ጦርነቶች የተሰዋው በልጦ ተገኝቷል፡፡ እንደገና ኒውስ ዊክ መጽሔት ላይ ባነብኩት አንድ ሌላ ጥናት መሰረት፤ (The Bible so misunderstood it’s a sin, Newsweek magazine Jan 9, 2015) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ውስጥ ብቻ በእግዜሩ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሞተው ሰው ብዛት እስከ 25 ሚሊዮን ይገመታል፡፡
ቢሆንም ‹ሰው መቻያውን ሰጥቶታልና› ከቆቅ የባሰ ስጋት እየሰጋሁ፣ እንደ ዶሮ በአንድ ዓይኔ እያንቀላፋሁ አለሁ፡፡ ችዬዋለሁ፡፡ እኔና ሌሎች ቢሊዮናት መሰሎቼ ይሄን መቸንከር ተቋቁመነዋል፡፡ ከኦሽዊትዝ የሕማም ጥልቅ በነፍሱ ረቂቅ ጣቶች ‹logo therapy› የተሰኘ ግሩም የስነልቦና ፈውስ መላ የነደፈው ቪክቶር ፍራንክል (Man’s search for Meaning)፤ ‹‹ሰው ማንኛውን ነገር [መራር ሰቆቃ] ይላመዳል፡፡ ይቋቋማል፡፡ እንዴት አድርጎ የሚለውን ግን አትጠይቁኝ...›› ይላል፡፡
ፈረንሳዊው ፈላስፋ ዣን ፓል ሳርትረ ‹Existentialism and Human Emotions› በተሰኘ መጽሐፉ፤ ‹‹Man is condemned to be free; because once thrown into the world, he is responsible for everything he does. It is up to you to give [life] a meaning.›› ይላል። ሰው የነጻነቱን፣ የዕጣፋንታውን አክናፋት በእጆቹ ሲሠራ መንታ ስነልቦናን አዳበረ። ስለ አብሮነት ከሚሰብኩ ትውፊቶቹ እኩል ስለ መለያየት የሚያትቱ ትርክቶችን ፈበረከ፡፡ ቅዱሳቱን መጻሕፍት በተለይም ‹ብሉይ ኪዳን›ን የሚያነብ ሰው፤ በዚህ ሁሉ የመከፋፈል የመለያየት መቅበዝበዝ ውስጥ መለኮታዊ መሻት እንደነበር ቢጠረጥር ልንፈርድበት አንችልም፡፡
በአስራ አምስት ዓመቱ ከናዚ የሰቆቃ ማጎሪያ የተረፈው አይሁዳዊው ኤሊ ዊዝል፣ በሰው ልጆች ላይ፣ በመለኮቱ ላይ ያስተናገደው ተስፋ መቁረጥ ሕማም የተለየ ነበር፡፡ #ሌሊት; ከተሰኘ መጽሐፉ ላይ አብዝቼ እጠቅሳለሁ...
‹‹በእግዚአብሔር አመንን፡፡ ሰውን ታመንን፡፡ እያንዳንዳችን ከመለኮት የክብር እሳት ላይ አንዳች ቅዱስ ፍንጣሪ ተሰጥቶናል። በእያንዳንዳችን ዓይኖችና ነፍስ ውስጥ የእግዚአብሔርን ምስል ይዘናል በሚል በማይጨበጥ ሀሳብ ኖርን፡፡ የመከራችን ምንጭ ይኸው ነበር፡፡ ያውም መንስዔው ካልሆነ፡፡[...] ዓለምንም መቼም ይቅር አልልም፡፡ መፈናፈኛ ወደሌለበት አጣብቂኝ ገፍተውኛልና፤ ወደ እንግዳ ፍጡርነት ቀይረውኛልና፤ ወራዳና ያልሰለጠነ ደመነፍስ በውስጤ ቀስቅሰዋልና፡፡[...]
ለምንም ነገር ልመና ማቅረብ ትቻለሁ። የኀዘን እንጉርጉሮ ማሰማት አቅቶኛል፡፡ በተቃራኒው በጣም ጥንካሬ ይሰማኛል፤ እኔ ከሳሽ ስሆን ተከሳሹ እግዚአብሔር ነበር። ዓይኖቼ ተከፍተዋል፡፡ ብቻዬን ነኝ፤ ያለ እግዚአብሔርና ያለ ሰው በአስፈሪ ሁኔታ ብቻዬን ነኝ፡፡ ያለ ፍቅር ወይም ያለ ምሕረት። አሁን ዐመድ ነኝ እንጂ ምንም አይደለሁም። ሆኖም ከዚህ ለረጅም ጊዜ ተቆራኝቼው ከነበረው ኃያል አምላክ ይበልጥ መጠንከሬ እየተሰማኝ ነው፡፡››
ዊዝል ይሄን ይበል እንጂ ከኦሽዊትዝ አሰቃቂ ልምምድ በኋላ ዓለምን ይቅር ብሎ በድኑንም ቢሆን ተጨማሪ ሰባ አንድ ዓመታት ኖሯል፡፡ የስነ-ሰብዕ (Humanities) ተመራማሪ ሆኖ አስተምሯል፡፡ ሰብዓዊነት በምድር ላይ እንደገና ያብብ ዘንድ ዘመኑን ሙሉ ሰውቷል፡፡ ለዚህ ጠንካራ ሰብዕናው የሰላም የኖቤል ሽልማትን ተቀዳጅቷል። ዛሬም ግን ከኢትዮጵያ እስከ ማሊና ካምቦዲያ፣ በመላው ዓለም፣ ሰው በሰው ይታደናል፡፡ ክርስቶስ አሊያም ነብዩ መሐመድ በነበሩበት ዘመን የሆነውም እንደዚህ ነው፡፡ ወደፊትም ሰው፣ ራሱን ሰው መሆንን እስካስተማረ፣ የሚሆነው ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡
ይሄንን የተናገሩት የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ሺሞን ፔሬዝ ናቸው አሉ፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው በፊት ‹World Economic forum› ስዊዘርላንድ ዳቮስ... የዘገበልን ደግሞ በቦታው ነበርኩ የሚለው የብራዚሉ ዝነኛ ደራሲ ፓውሎ ኮኤልሆ ‹በLike a flowing river› መጽሐፉ...
   እንዲህ አሉ፡፡
 ታላቁ የአይሁድ ሐይማኖት መምህር ራቢ ተማሪዎቻቸውን ሰበሰቡና ጠየቁ፤
‹‹ቀኑ ከሌሊቱ ቦታውን መረከቡን የምናውቅባት የንጋት ትክክለኛዋ ቅጽበት የትኛዋ ናት?››
መጀመሪያው ተማሪ መለሰ፡፡
‹‹ውሻውን ከበግ መለየት የሚያስችል ብርሃን ባገኘን ጊዜ››
ሌላኛው ተማሪ ቀጠለ...
‹‹በፍጹም ንጋቱን የምናውቀው ወይራውን ከሾላው በቅጡ መለየት
የሚያስችል ብርሃን ሲለግሰን ነው፡፡›› አለ፡፡
‹‹ሁለቱም እውነት አይደሉም!›› የመምህሩ መልስ ሆነ፡፡
‹‹እንኪያስ የመዓልቱን መገለጥ እንዴት እናውቃለን?›› ታዳጊዎቹ ተማሪዎች በጋራ ጠየቁ፡፡
ራቢው ቀጠሉ፤
‹‹የመዓልቱን መጀመር የምናውቀውማ የሆነ እንግዳ ሰው ሲቃረብ አይተን ወንድማችን እንደሆነ ስናስብና ጠቦች፣ ልዩነቶች ሲከስሙ ነዋ፡፡ በእርግጥም ያኔ ሌሊቱ ተሸኝቷል፡፡ ብርሃንም ሆኗል፡፡››
ይህችን ሚጢጢ ጥልቅ አስተውሎት የተሸከመች ታሪክ አንብቤ ስጨርስ ዙሪያዬን ተመለከትኩ፡፡ ለሀገሬ፣ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ውድቅት ነበር፡፡ ይሄ ጨለምተኝነት አይደለም፡፡ እውነት ጨለምተኛ አድርጎ አያውቅም፡፡ ‹‹Having been is also a kind of being, and perhaps the surest kind›› እንዲል ቪክቶር ፍራንክል፤ በነፍሴ የዳሰስኩት እውነት እሱ ከጨበጥኳት እፍኝ ጥሬ እንኳን ይበልጥ ዕውን ይሆንብኛል፡፡    
ቢሆንም... ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ሕይወት ከአመጽ፣ ከሕመም ትፈልቃለችና እኔም የከሸፈውን የሰው ልጅ ዕድገት በመርገም አልተወሰንኩም፡፡ በመሰጠት ተፋለምኩ፡፡ ከከበበኝ ባዶነት ላይ እፍኜ የቻለችውን ያህል ኦና ነገር ዘግኜ በነፋሱ አቅጣጫ በተንኩኝ። ገሚሱ ቀለመ፡፡ ከፊሉ ተነነ፡፡ የቀለመ ከመሰለኝ ሀቲት መሀል ጥቂቱን ትፈትኑት ዘንድ በእነዚህ ገጾች ላይ አንብሬዋለሁ። ግን እሱም ያው ከንቱ መቃተት ነበር፡፡ ባዶ ገረወይናን እንደማንከባለል የሚታክት ኑባሬን እያባበሉ ምልዓቱን መሻት፡፡
በእርግጥስ ሙሉ ባልሆነ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ምልዑነትን መሻት ምን ዓይነት ሞኝነት ነው? ይህንን ጎደሎነት ታባብል ዘንድስ ኪነትን ታህል ደካማ ጣዖት ታክኮ መታገል ምን ይሉት ጀብደኝነት፣ ምን ዓይነት ስንፍና ነው? እንግዲህ ይህንን ስንፍና ተክኜበት ተገኘሁ፡፡ የነፍሴ መሻት የነበረችውን ኪነትን ተወዳጀሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ፣ በሕይወት ለነበሩ 10 ዝነኛ ደራሲያን፣ ለወጣት ደራሲያን የሚመክሯቸውን አስር አጫጭር ምክሮች እንዲጽፉ ጋበዘ፡፡ ከተጋባዦቹ አንዷ የZadie Smith አስረኛው ምክር ትንሽ ለየት ይላል። ድርሰትን ካልህ አለች ዛዲዬ ‹‹[ድርሰትን ካልኽ] በፈቃደኝነት ራስህን ፈጽሞ ካለመርካት ለሚመነጭ የሕይወት ዘመን ሕማም፣ መከፋት አዘጋጀው፡፡›› ይቻት እንግሊዝኛዋ... ‹‹Resign yourself to the lifelong sadness that comes from never being satisfied.›› በዚህ ላይ የዘመን ስካር መደነጋገር ሲታከልበትማ፣ የሕመሙን ጥልቀት አስቡት፡፡ በዕውቀቱ ሥዩም ‹ለስብስብ ግጥሞች› መድበሉ በጻፋት መግቢያ፣ ገጣሚው (ጠቢቡ)፣ ‹‹ለሰው ልጆች የሚገደው ልባም መሆኑን እናምናለን።›› ያላትን ሀቅ ስትደርቡበት ደግሞ የስቃዩ ጥልቀት የሚደረስበትም አይመስል፡፡
አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ በ#አልቦ ዘመድ; መጽሐፋቸው፣ ‹ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው› በሚል ብሂል መነሻነት ስለ ኪነት የሚሰነዝሩት ሀቲት ደግሞ እጅጉን የተለየ ነው...
‹‹ሥነ-ጽሁፍ የሌለው ሕዝብ ሐሪሶት (culture) ሊኖረው አይችልም፡፡ ሐሪሶት ወይም ባህል የሌለው ሕዝብ አንድነት የለውም፡፡ ከዚህም የተነሳ ነጻነቱን ያጣል። ሌላ ምሳሌ መጥቀስ አያስፈልግም፡፡ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ መመልከት ይበቃል። የዛሬው ትውልድ ሐሪሶት የለውም - ሥነ ጽሁፍ የለውም - ነጻነት የለውም፡፡ ከባህሉ ውስጥ ማቆየት የቻለው እንጀራና ወጥ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ለኢኮኖሚው ወይ ለቁጠባ ሲል ብቻ ነው እንጂ ባህሉን ለማክበር አይደለም፡፡ [...] አንድን ሕዝብ ታላቅ የሚያደርገው ባህሉ እንደሆነ የሚክድ አይገኝም፡፡›› ሰው ቅን ቀልብን የሚማርባት አንደኛ መንገድ ኪነት ነች፡፡ የመማማሪያ የመሰባሰቢያ ጃንጥላ ነች... በዚህ መጽሐፍ ገጾች ላይ የምታነቧቸው ሀቲቶች ለመተከዢያ የሚሆኑ ጥቂት ኮርኳሪ የነገር ሰበዞች ማቀበል ከተቻለ በሚል ቀና ምኞት የተሰነዘሩ የአንድ ጀብደኛ ወጣት ትንፋሾች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ ልዩ ልዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተስተናግደዋል፡፡ ወደ መጽሐፍ ቅርጽ ሲመጡ ለማሻሻል፣ ለማበልጸግ ጥረት ማድረጌንም ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ መልካም ንባብ!!
("ከባዶ ላይ መዝገን" ከተሰኘው የያዕቆብ ብርሃኑ መጽሐፍ፣ እንደ መግቢያ የተጻፈ ቀዳሚ ቃል ላይ ተወስዶ ለጋዜጣ እንዲመች ተሻሽሎ የቀረበ)


Read 401 times