Tuesday, 01 March 2022 00:00

“‘ፍ‘ ይዘሀል?;

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "--እኔ በህልሙ ላይ የታየኝ መሬቱ ላይ ተዘርሬ ነው፡፡ በዙሪያችን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ወዳድቀዋል፡፡
በገደሉ መውጫ ኩርባ ላይ የእንግሊዝ ወታደሮች እየመጡብን ነው፡፡ ቀና ብዬ ስመለከት መይሳው ከጎኔ እንደ መንጋለል ብለዋል፡፡ ትከሻቸው ላይ የጣሉትን ሹሩባ የወረሰው ጭንቅላታቸውን ቀና አድርገው…’ገዝዬ’ አሉኝ፡፡ ስሜን ያውቁታል፡፡ ከጀግናው ጎን በመጨረሻዋ ሰአት የተገኘሁ እኔ ብቻ ነኝ፡፡"
              ግራገቢቶ          ቢሮ ተከራይተናል ካለኝ ወደ አንድ ወይ ሁለት ሳምንት ገደማ አልፏል መሰለኝ፡፡
መጀመሪያ ቢሮ መከራየት፣ ከዛ አነስተኛ እና ጥቃቅን ስራን መጀመር…ከዛ የኪራይ ክፍያ ሲደርስ ቢሮውን ቆልፎ መጥፋት…የተለመደ ሂደት ነው፡፡ ከዚህ በፊትም …ያለፈው አመት ተመሳሳይ ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ ከሸፈ፡፡ ሙከራው ጀዝባን አንድ ለአምስት ለማደራጀት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከሽፏል፡፡ ከዚህ በኋላም የሚሳካ አይመስለኝም፡፡
ቢሮ የተከራየውን ልጅ “አንዳችን “ብዬ ነው በውስጤ የምጠራው፡፡ ሌሎቹ አምስቶቻችን ማንም ልንሆን እንችላለን። ማንንም ብንሆን ጀዝባ መሆናችን ግን አይቀየርም፡፡
“ቢሮ ተከራየሁ” ሲለን ተሰብስበን እንመጣለን፡፡ ቢሮ የተከራየው ሰው ብሩ እስኪያልቅ የማስቃም አቅም አያጣም በሚል…ኪሳችን “ኮሽ” ያለብን ሁሉ ተጠራርተን እንመጣለን፡፡ ሁለት ጠረጴዛ እና የፕላስቲክ ዱካ ወንበሮች ተደርድረው ይጠብቁናል፡፡ የምናውቀው ነው፡፡ ቢሮውን መጥቶ ያየ ሁሉ ተቀምጦ ይቀራል፡፡ ማደርም ከተቻለ ያድራል፡፡ የጀዝባ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ የኛ ትውልድ ሁሉ አንድ አይነት ይዘት ያለው ግን ቅርጹን የሚለዋውጥ ጀዝባ ነው፡፡
የአሁነኛው ቢሮ ቆጥ ላይ ነው፡፡ እንደ ዘንዶ በተጠመጠመ የብረት መሰላል…የቢሮው ባለቤት እየመራ እኔ እየተከተልኩ ወጣን፡፡ በጥንቃቄ፡፡ የመንደር በያጅ መሰላልን ወደ ደረጃ የመቀያየሪያ ምህንድስና አለው፡፡ ደግሞ ደረጃውን የወጣ ሰው ቆጡ ላይ እንዳይደርስ በርም ተበጅቶለታል፡፡ መሰላሉ ደረጃ …ደረጃው ደግሞ እስር ቤት መሆን ይችላል፡፡
ቆጡ ላይ ደርሰን ቢሮውን እጁን ዘርግቶ አሳየኝ፡፡ተደሰትኩኝ፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፤ መቃም እና ማጨስ የሚቻልበት ቢሮ ነው፡፡ እንደ እርግብ ቅንቅን እስክናወጣ ድረስ የጣራው ቤት ውስጥ ተኮልኩለን መቃም እንችላለን፡፡
ግን ለማረጋገጥ “በርጫ ገዝተሀል” ብዬ ጠየኩት፡፡ የቤቱ ባለቤት ራሱ ወለሉ ላይ እየቃመ ተራመደን፤ አልፈነዋል፡፡ ከጣራው ላይ ሆኜ ወደ ታች ስመለከት ብዙ ጫት መሸጫዎች ይታያሉ፡፡ “አዎን” አለኝ በአጭሩ፡፡
ወንበር ያዝን፡፡ ቢሮውን መውደዴን እየነገርኩት ሲጋራዬን ለኮስኩ፡፡ ክፍሉ ራሱ ተጠምቶ ነበር መሰለኝ፣ የመጀመሪያውን ሲጋራ ጭስ ከአፌ እየነጠቀ ዋጠው፡፡
“ይሄ ብቻ ሳይሆን በጀርባ በኩልም ሌላ ክፍል ተከራይተናል …ላሳይህ?” አለኝ። ተከተልኩት፤ ጣራውን ዞርነው፡፡ ዞረን መጨረሻ የምናጣ ልክ ሊመስለኝ ሲል፣ አንድ በር በድንገት ተፈጠረ፡፡ በበሩ ወደ ውስጥ አንድ የዘበኛ ቤት የመሰለች ዙሪያዋን በእርጥበት በወረዛ የኮምፔልሳቶ መዋቅር የተከበበች ክፍል ተከሰተች፡፡ “በጣም አሪፍ ነው” አልኩኝ፡፡ ለመግባት ሳልዳዳ። እዛኛው ክፍል እየቃምኩ የሚደብረኝ ሰው እንግዳን ተመስሎ ከመጣ፣ ለሽሽት ልቀመጥበት እችላለሁ ብዬ እያሰብኩኝ ወደ ኋላ አፈገፈግሁ፡፡
አንድ በር ብቻ ሳይሆን ሁለት በሮች መኖራቸውን የጠረጠርኩት ክፍሉ ውስጥ ማንም ሰው ባይኖርም የሚሰማኝ ድምጽ ስላለ ነው፡፡ ድምጽ እውነት ሰምቻለኁ ወይንስ ጆሮዬ ነው ብዬ ልወዛገብ ስል “ከጎን ያለው ቢሮ የስነልቦና አማካሪዎች ናቸው የተከራዩት” አለኝ፡፡
“የቱ ጋ?” ልለው ካሰብኩ በኋላ ማጣጣል እንዳይመስልብኝ ከአፌ መለስኩት። ክፍል፤ በርዝመትና በወርድ የሚለካ ተጨባጭ ስፍራ ሳይሆን ምናባዊ ግዛት ሊሆን የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ “የምክር አገልግሎት መስጫው ስፍራውና ሰጪዎቹ በአይን የሚታዩ ባይሆኑም…ድምጽ በመስማቴና ትልቅ የማስታወቂያ ፖስተር ጣራው ስር ተደግፎ በማየቴ የተባለው ነገር በእውን ስለመኖሩ ለመጠራጠር ድፍረቱን አጣሁ፡፡
መጀመሪያ ወደ አሳየኝ ቢሮ ተመለስኩኝ። ቅድም ያልነበሩ ሁለት አዲስ ፊቶች ጀዝባን ተመስለው ተቀምጠዋል፡፡ በክንፍ እንጂ በእግር በመሰላል ወደ ላይ እንዳልወጡ ጠረጠርኩ፡፡ ሁሉም ከሁሉም ጋር ሰላምታ ተለዋወጠ፡፡ ቦታ እየለቀቀ “ተቀመጡ” የሚል ግብዣ አዘዘ፡፡ ተቀመጥን፡፡
ሁለቱ ጀዝቦች በወሬ መሃል ናቸው። እያወሩ ያሉት ስለ አንድ ታላቅ ጀግና አሟሟት ነው፡፡ ታላቁ ጀግና ሽጉጣቸውን ጠጥተው የሞቱ ናቸው፡፡ አሟሟታቸውን የሳለውን ሰአሊ እየነቀፈ አንደኛው ጀዝባ ይናገራል፡፡
ተናጋሪው በሚናገረው አድማጩ እየተንፈራፈረ ይስቃል፡፡ እየተወራለት ያለው ሰአሊ ጫቱን ይዞ በመሰላሉ ብቅ ሲል፣ ተናጋሪው እና ሳቂው አንድ ላይ ጭጭ አሉ። ሰአሊው ገባ፡፡ ሰላምታ እና መተቃቀፍ…ወንበር መለቀቅ እና መገባበዝ ተከተለ። የተከታተሉት ድርጊቶች ተከናውነው አለቁ። ሰከኑ፡፡
ሰአሊውን ሲያማው የነበረው ሰው ስለ ስእሉ አነሳበት፡፡ ሸራ እና ቀለም መግዣ ከአነስተኛ እና ጥቃቅን ብድር ከቀበሌ ካገኘ ሰሞኑን ደግሞ ሊስለው እንዳሰበ ነገረን። የብድሩን ፎርም የመሙያ ወረቀቶች ከጉያው ወይንም ከጉራው ውስጥ አፍሶ አወጣ፡፡ ለመሙላት ይችል ዘንድ አበክሮ መቃም ጀመረ፡፡
ቅድም ሀሜቱን እየሰማ ሲስቅ የነበረው አዲስ ሀሳብ አፈለቀ፡፡ አዲሱ የአጼ ቴዎድሮስ ሞት ምን መምሰል እንዳለበት የሚጠቁም ሀሳብ ነው ያፈለቀው፡፡ “እንዲያውም ስእሉ እንደ ትያትር በወቅቱ እና በዛች ቅጽበት የተከሰተውን የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ እኔ የጀግናው አሟሟት ባለፈው ከለሊቱ አስራ አንድ ሰአት ላይ እንደታየኝ ልተርክልህ” አለው፡፡
ቀጥል ተባለ፡፡ ቀጠለ፡፡
“እኔ በህልሙ ላይ የታየኝ መሬቱ ላይ ተዘርሬ ነው፡፡ በዙሪያችን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ወዳድቀዋል፡፡ በገደሉ መውጫ ኩርባ ላይ የእንግሊዝ ወታደሮች እየመጡብን ነው፡፡ ቀና ብዬ ስመለከት መይሳው ከጎኔ እንደ መንጋለል ብለዋል፡፡ ትከሻቸው ላይ የጣሉትን ሹሩባ የወረሰው ጭንቅላታቸውን ቀና አድርገው…’ገዝዬ’ አሉኝ፡፡ ስሜን ያውቁታል፡፡ ከጀግናው ጎን በመጨረሻዋ ሰአት የተገኘሁ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ “አቤት አጽዬ” አልኳቸው፡፡…እየተጣጣሩ…አንገታቸውን ቀና አድርገው…’ይዘሀል ወይ?’ አሉኝ፡፡ ‘ ምን አጽዬ …ምን ይዣለሁ…ሽጉጥ ነው?...ምሽግ ነው…ምን?...ውሃ ነው’ አልኳቸው …አልመለሱልኝም። ጭንቅላታቸውን በትከሻቸው ላይ መልሰው ጥለዋል፡፡ ስማቸውን ደጋግሜ ጠራሁ፡፡ ልወዘውዛቸው አልደፈርኩም፡፡ እንግሊዞቹ እየመጡ ነው፡፡ ሳይደርሱባቸው እንደሚሞቱማ አውቃለሁ፡፡ ታሪክም ቢሆን በህልም አይቀየርም፡፡
“ግን ጀግናው አልሞቱም…አሁንም ቀና አሉ፡፡ ደም በለበሰ አይናቸው መቅደላን አንዴ ተመለከቷት፡፡ ደም በከንፈራቸው ጥግ ብቅ አለ፡፡ ዋጥ አደረጉት፡፡ አሁን እኔን አትኩረው አዩኝ፡፡ የመጨረሻ እይታቸው መሆኑን እርግጠኛ ነበርኩ። ‘…ይዘሃል?’ አሉኝ አሁንም፡፡ …’አጽዬ…ይንገሩኝ ምንድን ልስጥዎ…ምንድን ልያዝ?’ አልኳቸው፡፡ “ፍ…ፍ…ፍ…” ይላሉ፡፡ “ምን?...ፍርድ…ፍትህ…ፍቅር…ፍልጥ” በ ‘ፍ’ ፊደል የሚጀምሩ ቃላትን እየጠራሁ የፈለጉት ምን እንደሆነ ለማወቅ ጣርኩ፡፡ እንግሊዞቹ ደርሰዋል። የአምባውን አጥር ጥሰው ገብተዋል። በቃ ሳይሞቱ ሊደርሱባቸው ነው…እያልኩ ተጨነኩኝ፡፡ እጅ ሳይሰጡ መሞት አለባቸው፡፡ እንዲሞቱ ደግሞ ለ “ፍ” ጥያቄያቸው መልስ ማግኘት አለብኝ፡፡
“ፍሬ…ፍልስፍና…ፍርፍር…ፍጻሜ…ፍትሐብሄር… ያልጠራሁት ቃል የለም። አሁንም ጭንቅላታቸውን ቀና አደረጉና በታላቅ ትግል… ’ፍሞ ይዘሀል?’ አሉኝ፡፡ ወይ አንጀቴ ፍስስ ይበል!...ፍሞ ጨርሻለሁ ከመተኛቴ በፊት ሁለት የነበሩኝን ሲጋራዎች በስስት አጭሼ ሳልጠግብ እንደተኛሁ ትዝ ይለኛል፡፡
“…’አጽዬ አይ አልያዝኩም’ አልኳቸው፡፡ ፈርቻቸዋለሁ፡፡ ፈርቼላቸዋለሁ፡፡ ወዲያው ቁርጡን ስነግራቸው ክልትው ብለው አልሞቱም!”
ክፍሉ በሳቅ ተናጋ፡፡ ሰአሊው አኮረፈ፡፡ ”በጀግና አይቀለድም” በሎ በጣሪያው ዙሪያ ወዳለችው ሁለተኛዋ የማኩረፊያ ክፍል ጫቱን ታቅፎ…የብድር ፎረሙን አንግቦ ተጓዘ፡፡
ስቀው ሲጨርሱ አንድ ሴት ቢሮው ውስጥ ቆማ ድንገት ተገኘች፡፡ “የሲጋራው ጭስ እየረበሸኝ ነው… እኛ ጋር የሚመጡ ታካሚዎቻችንን ሲጋራ እንዳያጨሱ እየመከርን፣ ቢሯችን ግን በእናንተ የሲጋራ ጭስ ሲታፈን ምን ይባላል…ወይ ቢሮ ቀይሩን፡፡ እኛ ፊትለፊት እንሁን፤ እናንተ ወደ ጀርባ ግቡ” አለች፡፡ የስነልቦና አማካሪዋ መሆኑዋ ነው፡፡ ቢሮውን የተከራየው ልጅ፤ ጉዳዩን ከሷ ጋር ለመወያየት እንዲችል እያባበለ እጇን ይዟት ወጣ፡፡
ቅድም የአጼ ቴዎድሮስን ህልም አየሁ ያለው አልማጭ አረፍ ሲል ጓደኛው ደግሞ ይቀልዳል፡፡ አንዱ ሲቀልድ እረፍት ላይ ያለው ይስቃል…እና በተገላቢጦሽ፡፡
“የስነልቦና አማካሪ ናት አይደል?...የገንዘብ እጦት ችግር አለብኝ፤ አማክሪኝ ብላት ታማክረኛለች? መቶ ሺ ብር ማጣት የፈጠረብኝ ችግር ነው የሚያስጨሰኝ እና እንዳላግጥ የሚያደርገኝ…ብላት መፍትሄ ታፈላልግልኛለች?”
እተሳሳቁ ቆዩና ቀልድ አለቀባቸው። ቀልድ ከጫት በላይ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሚቀልዱበት ነገር ያጡ፣ ወደ እኔ አቅጣጫ መመልከት ጀምረዋል፡፡ …ወደ ውጭ ብወጣ ይሻለኛል፡፡ ሽንቴ ባይመጣም ወደ ሽንት ቤት በመሰላሉ ወርጄ ብመለስ…አዲስ አባል ተቀላቅሎ፣ አዲስ ወሬ ደርቶ ይጠብቀኛል፡፡
ቀልዳቸው ከጀርባዬም ቢሆን መሰንዘሩ አልቀረም፡፡ ደረጃውን ስወርድ ሳቃቸው እየተምዘገዘገ ሲጫንብኝ ትርጉም የማይሰጥ ህመም ሲያመኝ ተሰምቶኛል፡፡ ደግነቱ ህክምናውም ጎረቤታችን አለ፡፡ የስነልቦና ቁስለት ቢሮ እና ህክምና ቢሮ ጎን ለጎን ሆነው፣ ስብራት እና ጥገናን በአንድ ጣራ ስር ያከናውናሉ፡፡


Read 268 times