Tuesday, 01 March 2022 00:00

ሩስያ በአሜሪካና አጋሮቿ ማዕቀብ ተወጥራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከአውሮፓ የአስርት አመታት የከፉ ቀውሶች አንዱ ነው የተባለለት የሩስያና የዩክሬን ፍጥጫ ባለፈው ረቡዕ ሩስያ ጦሯን በዩክሬን ተገንጣይ ክልሎች ማስፈሯን ተከትሎ የባሰ መካረሩ የተነገረ ሲሆን፤ አሜሪካና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በርካታ አገራት በሩስያ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን መጣላቸው ተጠቁሟል፡፡
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ሰኞ፣ ከዩክሬን ለመገንጠል በሚፈልጉ አማጽያን ቁጥጥር ስር ለሚገኙ ሁለት ክልሎች እውቅና መስጠታቸውንና ወደ ዩክሬን ድንበር ካስጠጓቸው ከ150 ሺህ በላይ ወታደሮች መካከል የተወሰኑትን ባለፈው ማክሰኞ በእነዚህ ሁለት ክልሎች ማስፈራቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ ይህም አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራትን ክፉኛ ማስቆጣቱንና ለማዕቀብ ማነሳሳቱን አመልክቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ረቡዕ ባወጡት መግለጫ፣ ሩሲያ በይፋ ዩክሬንን መውረሯን የተናገሩ ሲሆን ሩሲያ ከምዕራባውያን የፋይናንስ ብድር እንዳታገኝ የሚከለክል ማዕቀብ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሜሪካ በሩስያ ላይ ከጣለቻቸው ሌሎች ማዕቀቦች መካከልም በሩስያ መንግስት ባለቤትነት የሚተዳደሩትን ሁለት ግዙፍ ባንኮች ሃብት ማገድና አሜሪካውያን በዩክሬን አማጽያን ቁጥጥር ስር በሚገኙት ሁለት ክልሎች የንግድ ስራቸውን እንዲያቆሙ መከልከል ይገኝበታል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የ23 ሩስያውያንን ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ማገድ፣ የጉዞ ክልከላ መጣልና ለሁለቱ የዩክሬን ክልሎች እውቅና በሰጡት 351 የሩሲያ ምክር ቤት አባላት ላይ ማዕቀብ መጣልን ጨምሮ በርካታ ማዕቀቦችን ለመጣል የተዘጋጀ ሲሆን እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳና ጃፓን በፋይናንስ ተቋማትና በሩስያውያን ባለጸጎችና ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦችን መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንግሊዝ በአምስት የሩስያ ባንኮች ላይ ማዕቀብ የጣለችና ከፑቲን ጋር ቅርበት አላቸው የተባሉ ሶስት ሩስያውያን ባለጸጎችን ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ያገደች ሲሆን ጀርመን የሩሲያን ነዳጅ ወደ አውሮፓ አገራት የሚያስተላልፈው ትልቅ መስመር ስራ እንዳይጀምር ማገዷና ይህም በአውሮፓ አገራት ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ መናር ሊያስከትል እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ሩስያ በዩክሬን ላይ ይፋዊ ጦርነት የምታውጅ ከሆነ፣ ተጨማሪ ጠበቅ ያሉ ማዕቀቦችን እንደሚጥሉ ያስጠነቀቁ አገራት ቁጥር እየተበራከተ እንደሚገኝም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የሩስያን እርምጃ ተከትሎ ዩክሬን ባለፈው ረቡዕ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደምታውጅ በመግለጽ ዜጎቿ በአፋጣኝ ሩስያን ለቅቀው እንዲወጡ ያስታወቀች ሲሆን አሜሪካ የጦር ሃይሏን በሩሲያ አቅራቢያ ወደሚገኙት ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ እና ሊዩቲኒያ ማስጠጋት መጀመሯን የዘገበው ቢቢሲ፤ ጣሊያን በበኩሏ የጦር ጀቶችንና ሄሊኮፕተሮችን በፖላንድ በማስፈር ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡
ቻይና በበኩሏ፤ አሜሪካ በሩስያና በዩክሬን መካከል ፍርሃትና ውጥረት እንዲነግስ እያደረገች፣ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በመስጠት አገራቱ ወደ ጦርነት እንዲገቡ ሆን ብላ እየገፋፋች ነው ስትል መወንጀሏንና ሁሉም አካላት ከጦርነት ይልቅ የዲፕሎማሲ አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ ማቅረቧን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡


Read 1133 times