Wednesday, 02 March 2022 00:00

50% የአለማችን ወላጆች የታሸገ የዱቄት ወተት ማስታወቂያ ሰለባ ናቸው ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ግማሽ ያህሉ የአለማችን ወላጆች አግባብነት በሌለውና የተሳሳቱ መረጃዎችን በያዙ የታሸጉ የዱቄት ወተት ምርቶች ማስታወቂያ አስገዳጅነት፣ ለልጆቻቸው ጤና አስፈላጊ የሆነውን የጡት ወተት በአግባቡ እንደማይሰጡ ተመድ አስታውቋል፡፡
የአለም የጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በጋራ በሰሩት ጥናት ያገኙትን ውጤት ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ በአለማችን የታሸጉ የዱቄት ወተቶች ኢንዱስትሪ ባልተገባ የገበያ ማስታወቂያ ሳቢያ ከፍተኛ ገቢ የሚያካብት ባለ 55 ቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ ለመሆን መብቃቱን አስታውቀዋል፡፡
የዱቄት ወተት አምራች ኩባንያዎች አለማቀፍ የማስታወቂያ ህግጋትን በመጣስ ነፍሰጡሮችና ወላዶች ለልጆቻቸው ተገቢውን ምግብ ከመስጠት ይልቅ በዱቄት ወተት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ እያደረገ ሲሆን፣ አምራች ኩባንያዎቹ በድረገጽ አማካይነትና በሽያጭ ወኪሎቻቸው በኩል እናቶችን እያማለሉና በሽልማትና ስጦታ እያባበሉ ሰለባ እንደሚያደርጉም ሪፖርቱ ያብራራል፡፡
የዱቄት ወተት ምርቶች ያልያዙትን ንጥረ ነገር እንደያዙ አድርገው በየሚዲያው ማስታወቂያቸውን በስፋት የሚያሰራጩ ኩባንያዎችን መንግስታት ትኩረት እንዲሰጧቸው የጠየቀው ሪፖርቱ፤ ከልካይ ህጎች ወጥተው መተግበር እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡ ኩባንያዎች አዋላጅ ነርሶችንና የጤና ሰራተኞችን በስጦታና በማማለያ በመደለል እንዲሁም ኮሚሽን በመስጠት፣ ምርቶቻቸውን አገልግሎት ለሚሰጧቸው እናቶች አግባብተው እንዲሸጡ እንደሚያደርጉም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡



Read 1095 times