Thursday, 03 March 2022 06:52

የዓድዋ ገሞራ ፍንጥርጣሪዎች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 መላው ዓለም ከታሪካችንና ስማችን ጋር የሚያነሳው አንጸባራቂ ዐምድ አለን። እኛ ያለ ፍርሀትና ሽንፈት፣ ያለመሸማቀቅና ማጎንበስ የምንተርከው፣ ባላንጣዎችን በምሬትና በሰቀቀን በእንባ ለውሰው የሚያስቡት ወርቅ ንክር ማስታወሻ ጽፈናል።
ታሪክ የጻፍነው እንባ በሚያንጠበጥብ  ብሪር አይደለም፤ በማይከስም የደም ነበልባል ነው። ይህ የታሪክ ነበልባል፣ የነጻነት ፍም፣ የማያባራ ገሞራ፣ “ዐድዋ” ተብሎ ይጠራል። “ዐደዋ” የቦታ ስያሜ ይሁን እንጂ በመላው ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ተዘርቶ፣ በታሪክ ምዕራፍ ጎመራ የጀግንነት ትዕምርት፣ የነጻነት ምስል ነው።
በየዓመቱ በወርሃ የካቲት የምንዘክረው ይህ የጀግኖች መስዋዕትነት፤ ብዙ ጀግኖቻችንን እንድናስብ ይቆሰቁሰናል፣ የታሪክ ጸሐፍትን ገጾች ስንገልጥ፣ የሚገነፍል የተጋድሎ ድምጽ እንደ አዲስ ያስተጋባብናል።… ወደ የግል ስናመጣቸው፣ ከዚያ  የታሪክ ዛላ ላይ የተንጠለጠሉ የአጥንት ዘንጎች በእኛ ልብ ውስጥ ተሰንቅረው ይነድዳሉ።… በዚያ ዐውደ ውጊያ፣ ቅድመ አያቶቻችን ወድቀው፣ ባንዲራችንን አስከብረዋል፤ ደምተው ህይወት  ጽፈውልናል!
ለዚህ ተጋድሎና መስዋዕትነታቸው እገሌ ሕዝባዊ ከያንያን በምጥ የወለዱትን ሕዝባዊ ቅኔ ተቀኝተውላቸዋል፤ እኛም እንደየአቅማችን በግጥምና በዜማ፤ በወግ ሁሌም በታሪክ መሰዊያዎች ላይ ጥበባችንን እናጣጢሳለን። ከጸጋዬ ገብረመድህን ጀምሮ፣ በርካታ ገጣምያን፣ ዐድዋን ሲዘክሩ፣ ዲጄ ደግሞ በዜማ ነክራ ታሪክን በሕዝብ ጆሮ እንደጅረት አፍስሳለች።
በዐድዋ ጦርነት ከጦርነቱ መሪ ከአጼ ምኒልክ ጀምሮ ጀግኖቻችን ብዙ ናቸው።  በጊዜው የጦሩ ዋና አዛዥ ከሆኑት ልዑል ራስ መኮንን ጀምሮ፣ ራስ አሉላ አባነጋ፣  ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ አባተ ቧ ያለውና ሌሎችም ይገኙበታል።
እውነት ለመናገር፣ በዚያ ዘመን ጦርነት የኢትዮጵያውያን ፍላጎት አልነበረም። ስለዚህም አጼ ምኒልክ ጣሊያን የትግራይን መሬት በከፊል ሲይዝ እንኳ ዝም በማለታቸው፣ በአፍሪካና በአውሮፓ እንደ ፍርሀት ተቆጥሮባቸው እንደነበር ሬይሞንድ ጀናስ ጽፈውት፣ ኤፍሬም፣ እንዳለ ወደ አማርኛ በመለሰው መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን።
ኤክ ፒተር ፔትሪዲስ ደግሞ በሌላ መጽሐፋቸው፣ ይህንን ሰላም ፈላጊነታቸውን ሲጽፍ፡- አፄ ምኒልክና ራስ መኮንን፣ ብልጽግና እንጂ ጦርነት ምርጫቸው እንዳልነበር አበክረው አስታውሰዋል። እንዲህ ይነበባል። በነሱ ዘመን ኢትዮጵያ ከሁሉ ይልቅ ሰላምን ፈለገች። በመጥፎ በሽታና በየጊዜው በተደረገው ውጊያ ከመጣው ጉዳት ሀገሪቱ እንድታንሰራራ ወደ ብልጽግና ወደ ስልጣኔ ዕድገትና ደስታ ዘመን እንድትራመድ መንገድ  ጠርጎ ማዘጋጀት የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነበር። ሁለቴ ዘመዳሞች በማናቸውም አኳኋን ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ተስማሙ። ጦርነት የሚያደርጉት በብዙ መንገድ ለመቃወምና ለመከራከር መክረው በመጨረሻ ያለሱ የማይሆን  ሲሆን ብቻ እንዲሆን ወሰኑ።
ይህ ምኞት ስላልተሳካ፣ ዐድዋ ላይ ጦርነት ተደርጎ፣ ብዙ ጀግኖች መስዋዕትነት ከፍለው ሲያልፉ፣ አያሌ ጀግኖች በጦር ሜዳ ተወለዱ። … በእሳት ተፈትኖ እንደሚወጣ ወርቅ፤ ነፀብራቃቸው ዘመንንና የታሪክን ገጾች አሳመሩ።
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን “ታሪካዊ” ተውኔቶች በሚል፣ በዐፄ ምኒልክ የተውኔት ጽሑፍ፣ ከምኒልክ ቃለ ተውኔት እንደማሳያ ብንወስድ፡-
ስልጣኔስ እኮ ጽንስ ነው/ የወላድ እኮ ጭንቅ ነው/ የትውልድ አእምሮ በስልት፣ አገር በሕብር የሚያምጠው።/
አገር ነው የታሪክ ደሙ/ ስልጣኔ ነው አውሙ።/ ምኒልክ ምስጢር የለኝም- የአንድ እናት ወገን ለወገን፤ የኛ መድሃኒት እኛ ነን።/
ኢትዮጵያ ማለት ሰላም ናት- ለጦርነት አንቸኩልም/ ገፍቶ የመጣን ጠላት ግን፣ ቴዎድሮስ ይሙት አልምርም/ ለዓለም መቀመጫ እስኪሆን፣ ሳልሰብረው አልመለስም።/
…እንዳሉት ጠላት ያለማቸውን ህልሞች፣ የዘገናቸውን ቅዠቶች አቡንነውበታል።
ጦርነት መጨረሻው በጀግኖቻችን በድል ቢቋጭም ጣሊያንን በኩራት ያሳበጠ፣ የምኒልክን ወገኖች ያሰጋ ብርቱ ጥርጣሬ ነበር። በንጉሱ ያኮረፉ፣ ክፉ ቀን ጠብቀው ፊታቸውን ያዞራሉ የተባሉ መኳንንትና የጦር መሪዎች ጥቂት አልነበሩም። በተለይ ራስ አሉላ አባነጋ፣ ራስ መንገሻ ዮሀንስና ንጉስ ተክለሃይማኖት፣ ራስ መኮንን አባ ቃኘው በእጅጉ ተፈርተው ነበር።
ይሁንና ነገሩ ጣሊያንን በሚያስደነግጥ ሁኔታ አቅጣጫውን ቀየረ። እናም ዐድዋ፣ መራራ ኮሶ ሆኖ ተጠጣና በአንድ ጀንበር፣ በሽታውን ጠራርጎ አሻገረው። ሕዝብ በየግንባሩ ቆሞ ከመፋለም ባሻገር ከጦር ሜዳው ውሎ ማግስት ስንኝ እየቋጠረ፣ ዜማ እያዜመ ጀግኖቹን አሞገሰ።
ሲጀምርም ግጥም ጀግኖችን በሚወልድበትና የተወለዱትንም ከፍ በሚያደርግበት ሀገር ዐፄ ምኒልክና የጦር አበጋዞቻቸው፣ ቅኔ ጠገቡ፤ ዜማ ዘነበላቸው። ከነዚያ ጀግኖች ከዘነበ ግጥም ለዘንድሮው ዐድዋ በዓል ማሟሻ መምዘዝ የዛሬ የኔ ፋንታ ነው። ጦርነት ብርቃቸው አይደለም፤ ከንጉሥ ተክለሃይማኖት ሰራዊት ጋር ባደረጉት ጦርነት፣ ሁለት ጊዜ ፈረሳቸው በጥይት ተመትቷል። መጀመሪያ ጠጣው በሚባለው ፈረሳቸው ላይ  እንደወጡ ፈረሱ አንገቱን ተመትቶ ሲወድቅ፣ በሌላ ፈረስ ቢወጡም ይኼኛውም በጥይት ቆስሎ ነበር። የተክለሃይማኖት ጦር ተኳሾች ለዣንጥላው አልመው እንዳይመታቸው ጥላ ያዡ ሲያጥፍ “የኔ ጥላ አይታጠፍም፤ ዘርጋው” ብለው መቆጣታቸውን፣ ተከለጻድቅ መኩሪያ ጽፈዋል። እስቲ ለአባዳኛው ከተገጠሙት ግጥሞች ስንኞች እንዋስ፡-
ጣልያን ገጠመ ከዳ፣ ሙግት
አግቦ አስመለሰው ሥራው ጥይት
አሁን ማን በዚህ አለም
ጣሊያን አስደንጋጭ ቀን ሲጨልም
… ወዳጁም ሳቀ ጠላቱም ከሳ
አራቱ አህጉር ለሱ እጅ ነሳ ተንቀሳቀሰ ዳኛው ነሳ።
“አፄ ምኒልክ፣ ያለ ጣይቱ ነጠላ ናቸው” እንደሚስት ብቻ ሳይሆን እንደ ጦር አማካሪ እንደ ጄኔራል፣ እንደ ሃይማኖት እናትም ነበሩ። ስለዚህም ሕዝብ እንዲህ ብሎ ገጥሟል፣ (ታደለ ገድሎ ዶ/ር)
ፈረሱ ዳኘው ሚስቱ ጣይቱ፤
ምጥም ወርዳ ቀዳች ወጥ ቤቱ።
ዳኛው በደሞትፌር በለው በለው ሲል፤
የቃኘው መኮንን ደጀኑን አፍርሶ ጦር ሲያደላድል፤
አባተ በመድፍ አምሳውን ሲገድል፤
ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል፤
የጎጃሙ ንጉስ በለው ግፋ ሲል፤
እትዬ ጣይቱ እቴጌ ብርሃን፤
ዳዊቷን ዘርግታ ስምዐኒ ስትል፤
ለቆሰለው ጀግና ውሃ ስታድል፤
ተማራኪው ጣሊያን ውኃ ውኃ ሲል፤
ቃኘው ስጠው አሉ ሠላሳ በርሜል፤
እንዲህ ተደርጎ ነው የዓድዋችን ድል።
እውነትም ንግስቲቱ፣ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ርኅራኄም ስለነበራቸው፣ ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን በእጃቸው የወደቀን ጠላት በሰው ልጅነቱ ርኅራኄ አሳይተዋል። ውኃ የሰጡት ለወገናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለተሸነፈ ጠላትም ጭምር ነበር። ይህ ደግሞ ጀግንነትን፣ ከስልጣኔ ጋር ያጣመረ መልካምነት ነበር። ጀግናው ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል በጦር ሜዳ ሞቱ። የጦር መኮንኖችን በክብር እንዲቀበሩ ሲያደርሩ፣ ዓለምን የሚያስተምር የስልጣኔ ማሳያ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት መስክረውላቸዋል። ቅብጥብጡን የጣሊያን መኮንን ቶሲሊን ሳይቀር አስክሬኑ ክብር እንዲያገኝ አድርገዋል።
ራስ መኮንን ለጀግንነታቸው ስንኝ ከተቆጠረላቸው ያገር ልጆች አንዱ ናቸው።
ልክ እንዲገባ ያጎበጎበው፤
የዳኘው ቀኝ እጅ አንተ ና ቃኘው።
ሄደ ዘለቀ እስከ ጠረፉ።
ካለኔ አንስቶ ምጥዋ ድረስ፣
ቃኘው ይሉታል የዚያን ሰው ፈረስ።
ልዑል ራስ መኮንን ግጥሙ የሚገልጠውን ያህል ብቻ አይደሉም። ለዐድዋው ድል ከጦርነቱ እጅግ ቀድሞ ከተለያዩ ሀገር ዜጎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በማሰባሰብና ዘመናዊ ጦር በማደራጀት፤ ከዚያም ባሻገር በጣሊያን ሀገራቸው ባደረጉት ጉብኝት፣ የጣሊያንን ጦር ቁመና በመገምገም ፣ ለዓድዋው ድል  ወሳኝ ሚና ነበራቸው። ታላቅ ሰው ናቸው።
ሌላኛው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) ናቸው። እኒህ ጀግና በተለይ በአምባላጌው ጦርነት ይወሳሉ። የአምባላጌው ጦርነት ለዐድዋው ድል ትልቅ ሚና ነበረውና ጠላትን አስደንግጦ ፣ ከጠላት ወገን የተሰለፉ ወላዋዮችን ወደ ንጉሠ ነገሥታቸው የመለሰ ነበር።
የዚህ ጦርነት ጀማሪ ደግሞ ፊታውራ ገበየሁ ናቸው። ይሁንና ጦርነቱን ከጦሩ አዛዥ ትዕዛዝ ሳይቀበሉ በመጀመራቸው ለተወሰኑ ቀናት በእስራት ቆይተው ነበር። ከዚያ በኋላም በዐድዋው ጦርነት ቀይ ለብሰው በጀግንነት የተሰው ደፋርና ብርቱ የጦር መሪ ነበሩ። ለዚህም ነው፤
“አታድርስብን ያን ሰው ሲቀጣ፤
የዳኘው አሽከር ገበየሁ መጣ” የተባለው።
እኒህ ሰው የአምባላጌውን ጦርነት የጀመሩት እርሳቸውና የወገን ሰራዊት ሲጓጓ ከፊት ለፊት በባንዳ የሚመራ የጠላት ጦር አይተው መታገስ ስላቃታቸው እንደነበር አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት ይናገራሉ።
የንጉስ ፊታውራ የጎራው ገበየሁ፤
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፤
ለምሳም አልበቁ ቁርስ አደረጋቸው።
የተባለውም ለዚህ ነው። ፊታውራሪ ገበየሁ በዐድዋው ጦርነት ከሞቱ በኋላ በምትካቸው የገቡትን መድፈኛ ባልቻ ሳፎ (አባነፍሶ)
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።
ተብለዋል።
ባልቻ ሳፎ (አባነፍሶ) በዐድዋው ጦርነት ጉዞ ላይ፣ የጣይቱን በቅሎ የሚመሩ ታማኝ ረዳት፣ የቤተ-መንግስቱን ግምጃ ቤት ሃላፊና ዋና መድፍ ተኳሽ ነበሩ። እኚህ ታላቅ የጦር ሰው ከአርባ ዓመታት በኋላ ለበቀል ኢትዮጵያን ከወረረው ፋሽስት ኢጣልያ ጋር ጦርነት ገጥመው፣ በመጨረሻ ለሀገራቸውና ለባንዲራቸው ክብር የወደቁ ታላቅ አርበኛ ናቸው።
አሻግሮ ገዳይ ዲብ አንተርሶ
የዳኘው አሸብር ባልቻ አባነፍሶ።
የተባለላቸውም፣ የላቀ ጀግንነታቸውን ዋቢ በማድረግ ነበር።
ይህ የጥቁር ሕዝቦችና የነጻነት ተጋድሎ ተምሳሌትና የኢትዮጵያውያን አትንኩኝ ባይነት ማሳያ የሆነው ድል ከጦርቱ በፊትና ዋዜማ- በዓድዋ ጉዞ ላይ የነበሩ እረኞች እንደ ትንቢት ሲናገሩት እንደነበር የዓይን እማኝ የነበሩት ትንሹ የዐድዋ ዘማች ተክለሃዋርያት ተክለማርያም በኦቶባዮግራፊያቸው እንዲህ አስፍረውታል፡-
በየካቲት ጣጣችንን ክትት
በመጋቢት እቤታችን ግብት
በሚያዝያ -ያገግም የከሳ
እያሉ ይተነብዩ ነበር። ነገሩ እንዳሉት ሆኖ፣ በየካቲት ወር 1888 ዓ.ም ጣጣችንን ክትት ብሎ፣  ታላቅ ታሪክ፣ በታሪክ ገጾች ላይ ተጽፏል፣ በርካታ ከያንያንም በማይረሳ ቀለም ስለውታል…



Read 1139 times