Thursday, 03 March 2022 06:49

የጂጂ አድዋ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "--ጂጂ የመጨረሻ ደረጃ የደረሰች የወርቅ ንጥር ነች። የአንጣሪውን መልክ የምታንፀባርቅ ወርቅ። የለፋባትን፣ መስዋዕትነት የከፈለላትን መልክ የምታሳይ ወርቅ። በየቀኑ ኩራትን፣ ክብርን፣ ደስታን፣ ፍቅርን፣ ድልን የምታንፀባርቅ ወርቅ። መከራውንም ጭምር።--"
              ቢኒያም አቡራ    



            ፈረንሳዊው ጉስታቬ ፍሎበርት “ታሪክን መፃፍ ውቅያኖስ ጠጥቶ በስኒ እንደ መትፋት ነው” ይላል። የአድዋ ታሪክ ከውቅያኖስ ይገዝፋል። ተጠጥቶ አያልቅም። በምንም ያህል ቀለምና ጥራዝ ቢከተብ ስኒ ላይሞላ ይችላል። የአድዋ ታሪክ ነጠላ ታሪክ አለመሆኑን ለማተት በደርግ ዘመነ መንግሥት የተከሰተውን ገጠመኝ እንመልከት፡፡ ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ አድዋን በሚመለከት ደንበኛ የታሪክ መጽሐፍ እንዲከተብ ፈልገው ነበር። በሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ መመሪያ መሰረት፣ ተክለፃድቅ መኩሪያ እንዲያሰናደው ትዕዛዝ ተሰጠ። አንጋፋው የታሪክ ምሁሩ ተክለፃድቅ፣ ለጥቂት ቀናት ከቆዳቸው ሲማከሩ ሰንብተው፣ አድዋ ከኢትዮጵያ የታሪክ ሰፌድ ብቻውን የሚመዘዝ ሰበዝ አለመሆኑን አመኑበት። ወደ ሻምበል ፍቅረስላሴም ሄደው ነገሩን አስረዱ። በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ የአፄ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ እና ምኒሊክ (የኢትዮጵያ አንድነት) የተሰኙ መጻሕፍት በተክለፃድቅ መኩሪያ የተዘጋጁት። አድዋ ጋ ለመድረስ ጉዞውን ከአፄ ቴዎድሮስ ነበር የጀመሩት። አድዋን ለመተንተን ጋሽ ተክለፃድቅ ሶስት ቅፅ ቢያሰናዱም ቅሉ፣ የአድዋን ውቅያኖስ በስኒ ቅንብብ ውስጥ ከማኖር እንደማይዘል መካድ የለበትም። ዳሄራ ወቃጮች፣ ወጥ ወጥዋጮች፣ ጆሮ ጠቢዎች፣ አዝማሪዎች፣ ጋሻ ጃግሬ አንጋቢዎች፣ ፈረሰኞች፣ እግረኞች፣ ገበሬዎች፣ ባንዳዎች፣ የእነዚህ ሁሉ ታሪክ ቢካተት ከውቅያኖስ ይልቃል።
በታሪክ አፃፃፍ ውስጥ ውቅያኖስ ሙሉ ውጦ፣ የስኒን ያህል ብቻ የመትፋት ግዴታ አለ እንዴ? ውቅያኖስ ሙሉ ተጠጥቶ ውቅያኖስ ሙሉ መትፋት የማይቻል ከሆነ፣ በምርጫ ብዛት እርግማን ላይ መውደቅ ግድ ይላል። በርግጥ ያልተገለፀውን ሊያመላክት የሚችል ውክል (Symbol) መጠቀሙ ስራን እንደሚያቀል እሙን ቢሆንም።
 እንግዲህ ጂጂ ከዚህ እውነታ ጋር ነው የተፋጠጠችው። ጨርሳ ከማትችለው የታሪክ ውቅያኖስ ጠጥታ፣ ስኒን በምታህል ገለፃ የመትፋት መስክ ላይ ነው የተገኘችው። ስለ አድዋ ለማተት ሶስት የመፅሐፍ ጥራዞች ያልበቁትን ተክለፃድቅ፣ ከግዙፉ የአድዋ ታሪክ አንፃር የስኒን ታህል ነው ካልን፣ የጂጂን 22 ስንኞች ምን ልንል ነው?
የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆን ክቡር
ሰው ሞቷል፣ ሰው ሊያድን፣ ሰውን
ሲያከብር
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ
በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ
በጥራዝ-ጠለቅ ስኒ ለመትፋት ሙሉ ውቅያኖስ መጠጣቱ ግዴታ ነው። ጂጂ ግን ውቅያኖሱን ሙሉ የጠጣች አይመስለኝም። የታሪክ ተመራማሪ አለመሆኗን ልብ ይሏል። በከፍተኛ የግል የንባብ ክምችት ከታቆረ ኩሬ የተጨለፈ ነው ለማለትም ላለማለትም ያዳግታል። ነገር ግን በአንዲት ጠብታ ደም፣ ሙሉ የሰውነት ክፍል የጤንነት ሁኔታ እንደሚመረመር ሁሉ፣ የውቅያኖሱን ሙሉ ይዘት ሊያሳውቅ ከሚችልበት ማዕከል ቀድታ በመጠጣቷ የአድዋን እምብርት ልታገኝ የቻለች ይመስለኛል። ቅድመ አያቷ አድዋ ዘምተዋል፣ አያቷ ማይጨው ተዋግተዋል። አባቷ የአባቶቹን ገድል አውግቷታል። ቅድመ አያቷ ሰው፣ አያቷ የሰው ልጅ፣ አባቷ ክቡር ሰው መሆናቸውን እያወቀች ነው  ያደገችው። ታዲያ የአድዋን የእሽክርክሪት ዘንጉን ብታገኝ ምን ይደንቃል?
የጂጂ አድዋ፣ ከወትሮው ያፈነገጠ ድባብ የረበበበት የቲያትር መድረክ ነው። ደራሲውና አዘጋጁ ከመድረኩ ጀርባ ሆነው ሰው በተባለ ገፀባህሪ ተወክለዋል። መብራት አፈንጣቂው፣ ድምፅ አዋሃጁ በመርኃ-ግብሩ መዝጊያ ስማቸው አይጠቀስም። የማስታወቂያ ሰሌዳ ግርጌ ላይም አልሰፈሩም። ሰው በሚል ውክል ውስጥ ግን ተሰድረዋል። የገፀ ቅብ ባለሙያዎቹ የሚታዩት በተዋንያኑ ፊት ላይ ነው። በአድዋ መድረክ ላይ የሚመደርከው ገፀባህሪ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ ስም አልባ ተዋናይ ነው። ምንም ነገር የለው፤ ከሰውነት በቀር። ብሄር የለ፣ በምናልባተኝነት የተዋቀረ ብሄር ጠቋሚ ስም የለ፣ አንፋሮ ያጠለቀ የግለሰብ ጀግና የለ፣ በፈረሱ ስም ጌታውን የሚያስተዝተን አባ እከሌም የለም፡፡
ጂጂ በአድዋ መድረክ ያሳየችን ክቡርን የሰው ልጅ ነው። ተረኩም የሚያውጠነጥነው በሞቱ ሕይወትን ስለሚሰጥ ክቡር አክባሪ ነው። በቃለ ተውኔቱም “ሰው ክቡር ነው፤ የሞተውም ለክብር ነው፤ ክብሩ ተነጥቆ ክብሩን ሊያስመልስ ሳይሆን የሞተው፣ ሊመጣ ያለውን የክብር ነጠቃን ሊያድን ነው። የክብር እጦት ከሞት እኩል ነው። ክቡር ሰው፣ የሌላውን ክብር አክባሪ ነው። የሌላውን ክብር የማያከብር ክቡር ሰው መሆኑ ያጠራጥራል። የተከበረ ሰው የሌላውን የሚነጥቅ ሳይሆን የሌላውን ክብር ሊያድን የሚሞት ነው።  ለሌላው ክብር ሲጠራ፣ ለሌላው መኖር ሲፈለግ በክብር ይሄዳል” የሚሉ ሀሳቦችን እናገኛለን። ገፀባህሪው የተዋቀረው ብሄሩን ሳይሆን ደግነቱን፣ ፈረሱን ሳይሆን ፍቅሩን፣ አንፋሮውን ሳይሆን አክብሮቱን ባማከለ መልኩ ነው።
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር
ትናገር አድዋ ትናገር ትመስክር
ትናገር አድዋ ትናገር አገሬ
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ
“በቆሎ ወደ ወፍጮ ቤት የምንወስደው የበቆሎውን ዱቄት ፈልገን ነው። ወፍጮው እንዴት እንደፈጨው አያስጨንቀንም። በመኪናው ተሳፍሮ መሄድንና ካሰብንበት መድረሳችን እንጂ መኪናው በምን ስልት እንደሚሽከረከር ለማወቅ ደንታ የለንም። #በቆሎውን አስገብቶ ዱቄቱን መውሰድ ብቻ ሳይሆን ወፍጮው እንዴት እንደሚፈጨው ማወቅ አለብን!” ይላሉ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ #ሰበዝ; በተሰኘው መፅሐፋቸው። በነፃነት መኪና ተሳፍረን መጓዝ እንጂ፣ የነፃነት መኪናው በምን አይነት ስልት ተሽከርክሮ እዚህ እንዳደረሰን ለማወቅ አለመፈለግ፣ የነፃነት መኪና አምራቾቹን አለማመስገን ነው። የነፃነት በቆሎ ምን ያህል ዋጋ ተከፍሎበት እንደተፈጨ አለማወቅ፣ የነፃነት በቆሎውን ዋጋ ከማራከስ አይተናነስም። የነፃነት በቆሎውን ጣዕም ከማጉደልም በዘለለ የውለታ ቢስ ቁንጮ ያደርገናል። የጠለሸ ስያሜ ያከናንበናል።
ጂጂ “የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣ ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት” ብላ ለነፃነት መኪናችን የተከፈለውን ዋጋ ታወሳለች። በሞታችሁ ሕይወት ሰጣችሁኝ ትላለች። የነፃነት እህል ያገኘነው በምን ያህል ተጋድሎ እንደሆነ በማስተጋባቷ፣ የውለታ ቢስነታችንን መጋረጃ ትገፈዋለች። እዚህ ጋ ተዋናይ ግሩም ዘነበ የሙዚቃ ጠበብቱን ኤልያስ መልካን ባደነቀበት አገላለፅ እኔም ልጠቀምና፤ “ጂጂ አድዋን በመፈከር በኩል ያለብንን የትውልዳችንን ክስ ሰርዛልናለች!” ለማለት እገደዳለሁ።
“ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር ...” ስትል አንዳች ሆድን የሚያንቦጫቡጭ ነገር ትጥልብናለች። አድዋ ታላቅ እውነት ናት። ለወደቀውም ለቆመውም የምትመሰክር ታላቅ እውነት። ለወደቁ ወገኖቿ ምስክርነት አድዋን ትጠራብናለች። በነሱ መውደቅ ለመቆሟም ምስክሯ እሷው ራሷ አድዋ ናት።
በልጅነቱ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበረውና ተዓምር በሚባል ደረጃ በሕይወት ተርፎ የሰላም ኖቤል ሽልማት የወሰደው ኤሊ ዊዝል “Night” በተሰኘ መፅሐፉ እንዲህ ይላል፦ “ፅዮን፥ ከሬሳ ማቃጠያው መካከል ነፍስ ዘርታ እንደገና ነው የተነሳችው። አዲስ ሕይወት የሰጧት እነርሱ ናቸውና!” የኤሊ ዊዝል ምልከታና የኛዋ ጂጂ እይታ በሆነ በኩል ይጋጠምብኛል። እንደሚታውቀው ስድስት ሚሊዮን አይሁዳዊያን በናዚ ጀርመን በግፍ እስከሚገደሉ ድረስ አይሁዳውያን አንቀላፍተው ነበር። ከሬሳ ማቃጠያው የወጣው ወላፈን ነው አንቅቷቸው፣ ኃያሏን እስራኤልን እንደገና ያቆሟት። ኤሊ ዊዝል እስራኤል የቆመችው በስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን ጭፍጨፋ ምክንያት ነው ሲል፤ ጂጂ ደሞ አድዋ ላይ በወደቁ ወገኖቻችን እኛም ቆመናል ትላለች። በሰው መውደቅ የቆምን ሰዎች ነን፤ ሞታችን በሌሎች ሞት ስለተከፈለ ነው የኖርነው፤ እያለች የነፃነት አምዶቻችንን ታወሳለች።
በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን በቀን
በቀን
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን
ወርቅ አንጣሪ ወርቁን ሲያነጥር የመጨረሻ ደረጃ መድረሱን የሚያውቀው መልኩን አንፀባርቆ መመልከት ሲችል ነው። ጂጂ የመጨረሻ ደረጃ የደረሰች የወርቅ ንጥር ነች። የአንጣሪውን መልክ የምታንፀባርቅ ወርቅ። የለፋባትን፣ መስዋዕትነት የከፈለላትን መልክ የምታሳይ ወርቅ። በየቀኑ ኩራትን፣ ክብርን፣ ደስታን፣ ፍቅርን፣ ድልን የምታንፀባርቅ ወርቅ። መከራውንም ጭምር።
አምባሳደር ዘውዴ ረታ “የኤርትራ ጉዳይ” በተሰኘ መፅሐፋቸው፤ ታላቁ ዲፕሎማት ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተነፈጋትን ፍትሕ ያስመለሱበት ንግግርን እንዲህ ባለ መልኩ አስፍረው ነበር፦
“ሀገሬ ኢትዮጵያ በአለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ አይደለም። ... ኢትዮጵያ ያለፉት ታሪኮች በትክክል እንዳስረዱት ለነፃነቷና ለመብቷ በኮሎኒያሊስት ጣልያን ጋር በየጊዜው ስትዋጋ ያሸነፈችው ብቻዋን ነው፡፡ የተጠቃችውም ብቻዋን ስለሆነ፣ አገሬ መቼውንም ለሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም። ዛሬም ሆነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅ፣ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያለባት እሷ ራሷ ብቻ ነች።”
እዚህ ንግግር ውስጥ ኩራት፣ ክብር፣ ለብቻ የመቆም ምንምነት፣ ነፃነትና ድል በሚገባ ተንፀባርቋል። ያለፉ አባቶቻችንን መልክ የሚያንፀባርቅ ነው። ይህ ንግግር በ1949 ዓ.ም የተደረገ ሲሆን የአለም መሪዎችን አብረክርኮ አቋማቸውን የፈተሸ ድንቅ ንግግር ነው። ይህን ንግግር ሌላ የአፍሪካ ሀገር ዲፕሎማት ተናግሮ ቢሆን ድምፅ የታከለበት የቻርሊ ቻፕሊን ኮሚክ ሊመስላቸው ይችላል። ምክንያቱም በሰዓቱ አብዛኛው የአፍሪካ ሀገር በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ እየዳከሩ የሚገኝበት ወቅት ነበር።
የፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ንግግር ባዶ የቃላት ናዳ አይደለም። ብቻውን የቆመ ምርጥ የቃላት አሰካክ አይደለም። ከንግግሩ ጀርባ ታሪክ አለ። ንግግሩን መሬት የሚያወርድ ሕዝብ እንዳለ አሳምረው ያውቁታል።  ዳግማዊ አድዋ ሊከሰት የማይችልበት እድል ጠባብ እንደሆነ ያውቁታል። ስለዚህ በዚህ ንግግርና ከንግግሩ ጀርባ ባለው የአድዋ ትዝታ ምክንያት፣ በተባበሩት መንግስታት አባል ሃገራት ዘንድ ትልቅ ድንጋጤ ፈጥሮ አቋማቸውን እንዲፈትሹ አድርጓል።
ጂጂም ይኼ ገብቷታል። “በድል እኖራለሁ ያውም በቀን በቀን” የምትለው ለዛ ነው። የአድዋ ድል በ1888 ዓ.ም የተገደበ አይደለም። ድሉ የፈጠረው የአሸናፊነት ስነ-ልቦና በዓመታቶች አይደበዝዝም። በተሸናፊዎችም ዘንድ ያለው የአድዋ ትዝታ የሚፈጥረው ቁስል በቀላሉ አይሽርም።
በኩራት እንድንኖር ተዋድቀውልን፣ በሃፍረት ማቅ ብንጠቀለል፤ በክብር እንድንመላለስ ተጋድለውልን፣ በውርደት ጥጋጥጉን ብንይዝ፤ በሐሴት እንድንከርም ተዋግተውልን፣ በሀዘን ቋያ ብንለበለብ፤ በፍቅር እንድንጋመድ ደምተውልን፣ በጥላቻ ብንፋታ፤ በድል አድራጊነት ስሜት እንድንሰነብት ሞተውልን፣ በሽንፈት መንፈስ ብንዋጥ፤ ወርቅ አልባ ድንጋይነት ነው። የወርቅ አንጣሪውን ልፋት መና ማስቀረት ነው። ነጥሮ ነጥሮ ድንጋይነት ነው።
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት
ምስጋና ለእነርሱ ለአድዋ ጀግኖች
ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች
የጥቁር ድል አምባ አድዋ
አፍሪካ እምዬ ኢትዮጵያ
ተናገሪ ተናገሪ
የድል ታሪክሽን አውሪ
ፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጆናስ #The battle of Adwa; በተሰኘ መፅሐፉ፤ አድዋ ላይ ከተዋጉ ጀግኖች አባቶቻችን መሃል የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አለመቀበራቸውን፣ በየሜዳው ወድቀው መቅረታቸውን ዘግቧል (ይህ ታሪክ አከራካሪ መሆኑን ልብ ይሏል)።
ጂጂ ይህን ሁሉ ነገር ማካተቷ ድንቅ ነው። የአድዋ ጀግኖች ያደረጉት የተጋድሎው አበርክቶት፣ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ተርፏል። መኃሉ ላይ ጠጠር የተወረወረበት ኩሬ፣ የክቡ ይዘት እየተለጠጠ ዳር እንደሚደርስ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ላይ የተወረወረው የጦር ጠጠር፣ በአድዋ የክበብ ውክል፣ ከዓለም ጫፍ እስከ ዓለም ጫፍ ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል።
የአንዳርጋቸው ጽጌ “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር” በተሰኘ ባለወፍራም ጥራዝ መፅሐፉ፣ ሬይሞንድ ጆናስን ዋቢ አድርጎ ባስቀመጠው ኅዳግ ላይ እንዲህ ይላል፦ “አድዋ ላይ ኢትዮጵያ ተሸንፋ ቢሆን ኖሮ የአለም ታሪክ ይቀየር ነበር። አፍሪካ እንደ አውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድና፣ ሰሜን አሜሪካ የነጮች መኖሪያ ክፍለ አለም ትሆን ነበር። አብዛኛው አፍሪካዊ በበሽታ፣ በጦርነት በባርነትና በማግለል ቁጥሩ ተመናምኖ እንደ አሜሪካን ሕንዶችና የአውስትራሊያ አቦርጂኒዎች አይነት ይዞታ ውስጥ ይወድቅ ነበር። ይህ የነጮች መስፋፋት ከአፍሪካም አልፎ ወደ እስያ ለመሄድ የልብ ልብ ይሰማው ነበር። የነጮችን በአለም ላይ የመስፋፋት ሕልም፣ ሕልም ሆኖ እንዲቀር ያደረጉት፣ ኢትዮጵያውያን ጣሊያንን አድዋ ላይ በማሸነፋቸው ነው።” እውነትም ጂጂ የጥቁር ድል አምባ ብላለች። እናንተዬ! ይኼስ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የተደረገ ተጋድሎም አይደል?!
በመጨረሻም በ"ጉዞ አድዋ" ተጓዦች ምርጥ አባባል እንሰነባበት፤ “አድዋ ለመድረስ አምስት ወር የተጓዘው ሰራዊት ጦርነቱን የጨረሰው በስድስት ሰዓት ነው። የአምስት ወር መንገድ በስድስት ሰዓት የተጠናቀቀው፣ ጦርነቱን መንገድ ላይ ጨርሰው ስለገቡ ነው።”


Read 1228 times