Saturday, 05 March 2022 11:56

ግሎባል የስፖርት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ይካሄዳል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    በዓለም ዙርያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያሳትፍ ግሎባል ስፖርት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡ ኢትዮ ፈርሰት ኢቨንትስ፤ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ትናንት በሸራተን አዲስ ፌስቲቫሉን በሚያዘጋጁበት የመግባቢያ ሰነድ ላይ ተፈራርመዋል፡፡ የስፖርት ፌስቲቫሉ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራችን በማስመጣት  በተለያዩ ስፖርቶች አወዳድሮ ለመሸለም ተዘጋጅቷል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባሪያ ጽ/ቤት ዋና ዲያሬክተር ክቡር ዶክተር አረጋዊ በርሄ የዚህ ትውልድ አድዋ የህዳሴው ግድብ መሆኑን አመልክተው ፤ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከኋላቀርነት ለማላቀቅ ፤ ከድህነት ለማውጣት እና ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለማድረስ የሚሰሩት ታሪክ  ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮፈርስት ኢቨንትስ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በስፖርት አስተባብሮ ለአገራቸው አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ በመስራት ትልቅ ሚና መጫወቱን ያደነቁት ዶክተር አረጋዊ በአድዋ የታየውን ትብብራችን በመድገም በጋራ የኢትዮጵያን ገፅታ መቀየር ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ዲያሬክቶሬት ዲያሬክተር አቶ ጎሳዬ አለማየሁ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ቢሯቸው የከተማው ነዋሪ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጤናውን እንዲጠብቅ እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚሰራ አስታውሰው፤ ከውድድር እና ስልጠና በተጨማሪ በማህበራዊ ልማት እንደሚሳተፍም ገልፀዋል፡፡ የስፖርት ቢሮው በስፖርት ኢንቨስትመንት እና በስፖርት ኢንዱስትሪው ከሚሰሩት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ የጠቀሱት ዲያሬክተሩ የባለሙያ እና የምክር ድጋፍ በመስጠት እገዛ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ኢትዮፈርስት ኢቨንትስ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እና ህብረብሄራዊ አንድነታችንን የበለጠ እንዲያጠናክሩ ዋና አላማው አድርጎ የተቋቋመ  የአክስዮን ማህበር ነው፡፡ በግሎባል የስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እና ተያያዥ ሁነቶች ላይ እንደሚሳተፉ የገለፁት ከኢትዮፈርስት ባለድርሻዎች አንዱ የሆኑት ኢንጅነር የሱፍ መሃመድ ፌስቲቫሉ  በአገር አንድነት ላይ የተሻለ ገፅታ የምንፈጥርበትና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ገቢ ለማሰባሰብ መልካም አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስፖርትን በተመለከተ ከከተማው ምክር ቤት ስፖርት ለማስፋፋት፣ ለማሳደግ፣ ለመቆጣጠር ሙሉ ሃላፊነት የተሰጠው በመሆኑና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባሪያ ጽ/ቤትም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያበረክቱ ለማስተባበር ሃላፊነት በመያዙ ፌስቲቫሉን በማዘጋጀት ዋና አጋር ሆነው የመግባቢያ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡  ኢትዮ ፈርሰት ኢቨንትስ ስለተዘጋጀው የስፖርት ፌስቲቫል ዝርዝር  መርሀ ግብሮችን አስመልክቶ በቅርቡ ጋዜጣዊ መግለጫ እነደሚሰጥም አስታውቋል፡፡


Read 463 times