Saturday, 05 March 2022 11:59

አለም ወደ 3ኛው ጦርነት?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ሩስያና ዩክሬን በመሰንበቻው


          ነገሩ እያደር መክፋቱንና መስፋቱን ተያይዞታል፡፡
እየተባባሰ የመጣው የሩስያና የዩክሬን ጦርነት እንደተፈራውም የ3ኛው የአለም ጦርነት መባቻ ሳይሆን አይቀርም፤ ለጦርነቱ ዋነኛ ሰበብ ተደርጋ ስትወቀስ የሰነበተችው ሩስያ ባለፈው ማክሰኞ የኒዩክለር ጦሯን በተጠንቀቅ እንዲቆም ቀጭን ትዕዛዝ መስጠቷም አለምን በድንጋጤ ክው አድርጓል፡፡
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፤ ይሄኛው የአለም ጦርነት የኒውክሌር ጦር መሳሪያን የሚያጠቃልል ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ያስተላለፉት መልዕክትም አለምን ጭንቀት ውስጥ ከትቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተጀመረው ጦርነት ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ የመጣ ሲሆን፣ የሩስያ ጦር ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ደግሞ ደቡባዊቷን የዩክሬን ስትራቴጂክ ከተማ ኬርሰንን መቆጣጠሩና መዲናዋን ኬቭ ጨምሮ የተለያዩ ከተሞችን በቅርብ ርቀት በከባድ ድብደባ በማውደም ላይ እንደሚገኝና ጦርነቱ ተባብሶ መቀጠሉ ተነግሯል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዜለንስኪ ባለፈው ማክሰኞ ለአውሮፓ ፓርላማ በቪዲዮ ባሰሙት ንግግር፤ ሩሲያ ልታጠፋን ቆርጣ ተነስታለች ሲሉ አምርረው የተናገሩ ሲሆን፣ ጀግናውን የዩክሬን ህዝብ ማንም እንደማያሸንፈው የገለጹት ሰውዬው፣ ያም ሆኖ ግን መላው አውሮፓ ከዩክሬናውያን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ዩክሬን ያቀረበችውን የአባልነት ጥያቄም መቀበሉ  ተነግሯል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረቡዕ ዕለት ባካሄደው ልዩ አስቸኳይ ስብሰባ፣ በ73 በመቶ አብላጫ ድምጽ የሩስያን ወረራ ያወገዘ ሲሆን፣ አገሪቱ ጦሯን በአፋጣኝ ከዩክሬን ክልል ሙሉ ለሙሉ እንድታስወጣም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሩስያ ጦርነቱን የሚቃወሙ የአገሬው ድምጾች ከእለት ወደ እለት ቢበራከቱም፣ ፑቲን ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት አልበቃቸው ብሎ የተቃወሙትን ሁሉ በገፍ ወደማሰር ተሻግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እትብታቸው በተቀበረባት ሴንት ፒተርስበርግ ሳይቀር መንግስታችን ዩክሬንን መውረር የለበትም ብለው የተቃወሙ በርካታ ዜጎች ለጅምላ እስር በመዳረግ ላይ እንደሚገኝ ነው የተነገረው፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን አውዳሚውን ጦርነት በጊዜ ለማስቆምና ግጭታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የሚያስችል የመጀመሪያ ዙር ውይይት ባለፈው ሰኞ ያካሄዱ ሲሆን፣ ጦርነቱ ግን ባለፉት ቀናትም እየተባበሰ መቀጠሉ ነው የተነገረው፡፡ የሁለቱ አገራት ተወካዮች ረቡዕ ዕለት የሁለተኛ ዙር ውይይታቸውን በቤላሩስ አድርገው ቢለያዩም፣ የማያባራ የተኩስ ድምጽ እንጂ አንዳች ተስፋ ሰጪ ወሬ ሳይሰማ ሳምንቱ ተገባዷል፡፡

ማዕቀቡ ቀጥሏል
ሩስያን በኢኮኖሚ ለማሽመድመድ የታሰበው የማዕቀብ ዶፍ አሁንም ከያቅጣጫው መዝነቡን የቀጠለ ሲሆን አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ሳምንቱን ተደራራቢ ማዕቀብ ሲጥሉ ገፍተውታል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረትና መሰል አለማቀፍ ተቋማትም በሩስያ ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ተያይዘውታል፡፡
የአለም ባንክ ሩስያ በዩክሬን ላይ ያወጀችውን አስከፊና አውዳሚ ጦርነት በጽኑ እንደሚቃወመው በመግለጽ በሩስያ ተግባራዊ የሚያደርጋቸውን ፕሮግራሞች ሙሉ ለሙሉ ማቆሙን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረትም የአየር ክልሉን ለሩሲያ አውሮፕላኖች ሙሉ ለሙሉ ዝግ ለማድረግ ወስኗል፡፡
የአለማችን ቁጥር አንድ የመኪና አምራች ኩባንያ የጃፓኑ ቶዮታ ምርቶቹን ወደ ሩስያ እንደማይልክና በሩስያ ውስጥ ያሉትን ፋብሪካዎች እንደሚዘጋ ከትናንት በስቲያ በይፋ ማስታወቁን የዘገበው ሮይተርስ፤ ሌሎች የመኪና አምራች ኩባንያዎች ሆንዳ፣ ማዝዳ፣ ሚስቲቡሽም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸውን አስነብቧል፡፡
አለማቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ ሩስያ ለአለም ዋንጫ የምታደርጋቸውን ቀጣይ ጨዋታዎች ያለ ብሔራዊ መዝሙርና ሰንደቅ አላማ እንድታካሂድ ከሰሞኑ የወሰነ ሲሆን፣ አለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ፣ በቤጂንግ የ2022 ፓራኦሎምፒክ የክረምት ውድድሮች የሚሳተፉ የሩሲያና የቤላሩስ አትሌቶች ውጤታቸው እንዳይያዝላቸው መወሰኑ ተሰምቷል፡፡

የአሜሪካ ነገር
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ማክሰኞ ለፓርላማቸው ባደረጉት ንግግር፣ ጦራቸውን ወደ ዩክሬን ያዘመቱት ቭላድሚር ፑቲን የእጃቸውን እንደሚያገኙ የዛቱ ሲሆን፣ አሜሪካ የአየር ክልሏን ለሩስያ አውሮፕላኖች ሙሉ ለሙሉ ዘግታለች፡፡
አሜሪካ ለዩክሬን 350 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲሁም የ54 ሚሊየን ዶላር የሰብዓዊ እርዳታ ማድረጓን ያስታወቁ ሲሆን፤ በበርካታ የሩስያ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን መጣሏንም አብራርተዋል፡፡
ቦይንግ እና አፕልን የመሳሰሉ የአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች ከሩስያ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ማቋረጣቸውን በይፋ ማስታወቃቸውም ተዘግቧል፡፡
የባይደን አስተዳደር መቀመጫውን በኒውዮርክ ባደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤት የሚሰሩ 12 ሩሲያውያን ዲፕሎማቶችን "ለብሔራዊ ደህንነቴ አስጊ መሆናቸውን ደርሼበታለሁ" በሚል ባለፈው ማክሰኞ በአፋጣኝ ከአገሪቱ እንዲወጡ ቁርጥ ትዕዛዝ ማስተላለፉም ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ አካሄድ ያላማራት ቻይና በአሜሪካ ለሚገኙ ዜጎቿ #ለደህንነታችሁ ጥንቃቄ አድርጉ; ስትል ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች፡፡

ሞት እና ውድመት
ሩስያ ዩክሬንን በወረረች በአንድ ሳምንት ውስጥ ሆስፒታሎች፣ መኖሪያ ቤቶችና መዋዕለ ህጻናትን ጨምሮ ሲቪሎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ2 ሺህ በላይ ዩክሬናውያን መገደላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ የሩስያ ወታደሮችን ገድያለሁ ማለቷ የተሰማ ሲሆን፣ በሩስያ 30 አውሮፕላኖችና 31 ሄሊኮፕተሮች፣ 211 ታንኮችና ሌሎች በርካታ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሷንም አስታውቃለች፡፡
ሩስያ በበኩሏ በጦርነቱ በደረሰባት ጉዳት ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል ሃሙስ ዕለት በሰጠችው መግለጫ፤ በጦርነቱ 498 ወታደሮቿ መሞታቸውንና 1 ሺህ 597 ያህልም መቁሰላቸውን ብትናገርም፣ ብሪታኒያ ግን ቁጥሩ ከሚባለው በእጅጉ እንደሚልቅ መረጃ አለኝ ብላለች፡፡
የሩስያ መከላከያ ሚኒስትር በዩክሬን ላይ ያደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ በሰጠው መረጃም፤ ከ2 ሺህ 870 በላይ የዩክሬን ወታደሮችን መግደሉንና ተጨማሪ 3 ሺህ 700 ያህል ወታደሮችንም ማቁሰሉን አስታውቋል፡፡
ጦርነቱ 18 ሚሊዮን ያህል ዩክሬናውያንን ተጎጂ እንደሚያደርግና 4 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎችን ለስደት ይዳርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ እርዳታ ኮሚሽን ማስታወቁን የዘገበው ቢቢሲ፤ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራትም የዩክሬን ስደተኞች በግዛታቸው ለ3 አመታት ያህል ጥገኝነት ሳይጠይቁ መኖር እንዲችሉ ለመፍቀድ መስማማታቸውን አስነብቧል፡፡

የክፍለ ዘመኑ አስከፊ ስደት
ሩስያ በዩክሬን ላይ ያወጀችው ጦርነት ያስከተለው ቀውስ የፈጠረው ስደት በዚሁ ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ የክፍለ ዘመኑ እጅግ አስከፊ የስደት ቀውስ ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡ ወረራውን ተከትሎ ለደህንነታቸው በመስጋት አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ዩክሬናውያን ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ ሲሆን፣ የዩክሬናውያን ስደተኞች ቁጥር ከትናንት በስቲያ ከ1 ሚሊዮን ማለፉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የስደተኞቹ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ4 ሚሊዮን ያልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ አብዛኞቹ የዩክሬን ስደተኞች ወደ ፖላንድ መግባታቸው የተነገረ ሲሆን፣ ወደ ሃንጋሪና ሌሎች የአውሮፓ አገራት የሚጎርፉ ዩክሬናውያንም እጅግ በርካታ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
በዩክሬን የሚገኙ የተለያዩ አገራት ዜጎችም በአፋጣኝ አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት እየተረባረቡ ሲሆን፣ በተለይ አፍሪካውያን ከአገሪቱ ለመውጣትና ራሳቸውን ለማዳን ሲሞክሩ፣ በአገሬው የተለያዩ ዘረኝነት የሚታይባቸው ጥቃቶችና እንግልቶች እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ የአፍሪካ ህብረት በዩክሬን የሚኖሩ አፍሪካውያን ደህንነት እንዳሳሰበው በመግለጽ የሚፈጸምባቸው ጥቃትና እንግልት በአፋጣኝ እንዲቆምና ከአገር የሚወጡበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው አሳስቧል፡፡

ዳፋው ለአለም የተረፈ ጦርነት
ሩሲያ የገባችበት ጦርነት በዋናነት የራሷን ኢኮኖሚ ተጎጂ እያደረገ ቢሆንም፣ ዳፋው ግን ለተቀረው አለምም መትረፉ እየተነገረ ነው፡፡ ጦርነቱ መፋፋሙን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ የነዳጅ ዋጋ በአለም አቀፍ ገበያ ካለፉት 10 አመታት ወዲህ ከፍተኛው ነው የተባለው በበርሜል 119.84 ዶላር ላይ መድረሱና ይህም በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪን ያስከትላል፤ በአለም ኢኮኖሚ ላይ የከፋ ተጽዕኖን ያሳድራል ተብሎ መሰጋቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጦርነቱ መፋፋሙን ተከትሎ አለማቀፉ የሸቀጦች ዋጋ ባለፉት 14 አመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጭማሪ ማሳየት መጀመሩን የዘገበው ፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ፤ የታላላቅ ኩባንያዎች የአክሲዮን ዋጋም በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን አስነብቧል፡፡ የዩክሬንና የሩስያ ውጥረት በተባባሰበት ያለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ አለማቀፉ የስንዴ ዋጋ በ40 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱ የተነገረ ሲሆን፣ ለአለማቀፍ የውጭ ገበያ ከሚቀርበው ስንዴ መካከል 30 በመቶ ያህሉ ከሁለቱ አገራት የሚገኝ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሩስያ ከመላው አለም የሚጣልባት ማዕቀብ እየተበራከተ መምጣቱን ተከትሎ የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር የመግዛት አቅሙ በ30 በመቶ ያህል ቅናሽ ማሳየቱ የተነገረ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም ቭላድሚር ፑቲን ሩስያውያን ከውጭ አገራት ገንዘብ እንዳያንቀሳቅሱ መከልከላቸው ተዘግቧል፡፡
ሩስያ በተለይ ከፋይናንስ ዝውውር ጋር በተያያዘ የተጣሉባት ማዕቀቦች ክፉኛ እንደሚጎዷት እየተነገረ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ባንኮቿ በ200 የአለማችን አገራት የሚገኙ 11ሺህ ያህል ባንኮችን ከሚያገናኘው ስዊፍት የተሰኘ አለማቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ሲስተም መታገዳቸው እንዲሁም ማዕከላዊ ባንኳ አለማቀፍ ስራውን እንዳይቀጥል የተጣለበት ክልከላ እጅግ የከፉ ቅጣቶች እንደሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሩስያን ወረራ በመቃወም ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ማቋረጣቸውን የሚያስታውቁ አለማቀፍ ኩባንያዎች ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየተበራከተ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በነዳጅ ዘርፍ የተሰማሩት ግዙፎቹ ኩባንያዎች ቢፒ፣ ሼል፣ ኤክሶን ሞቢልና ኢኮይናር ይገኙበታል፡፡ ከሩስያ ጋር ንግድና ኢንቨስትመንት ማቆማቸውን ካስታወቁ ሌሎች ኩባንያዎች መካከልም ኤች ኤንድ ኤም፣ ጄኔራል ሞተርስና ሮልስ ሮይስ ይጠቀሳሉ፡፡
ጦርነቱ የከፋ ውድመት እንዳደረሰባት የተነገረችዋ ዩክሬን በበኩሏ፤ የጦር ሃይሏን ለማጠናከር ልዩ የጦርነት ቦንድ መሸጥ ልትጀምር ማሰቧንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ የአለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በማሳየት ባለፉት 10 አመታት ከፍተኛው ሆኖ ቢመዘገብም፣ አለምን ከነዳጅ ቋታቸው በማዳረስ የሚታወቁት ዋነኞቹ የነዳጅ አምራች አገራት ግን ገበያውን ለማረጋጋት ሲሉ የነዳጅ ምርታቸውን የሚጨምሩት በትንሹ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እስከ ሃሙስ በነበሩት ቀናት የ20 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 119.84 ዶላር የደረሰው የነዳጅ ዋጋ፣ ከሳምንታት በፊት ወደነበረበት ለመመለስ የወራት ጊዜ ሊፈጅበት እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን፣ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ከአለማችን አገራት 3ኛዋ ግዙፍ የነዳጅ አምራች ከሆነችው ሩስያ ጋር ያላቸውን ንግድ ማቋረጣቸውም በቀጣዮቹ ቀናት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ተዘግቧል፡፡
የአለም አሰላለፍ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባለፈው ረቡዕ ባደረገው ልዩና አስቸኳይ ስብሰባ የሩስያን ወረራ ያወገዘ ሲሆን፣ ከድርጅቱ 193 አገራት መካከል 141 ያህሉ ወይም 73 በመቶ ያህሉ የሩስያን ወረራ በማውገዝ፣ ጦሯን በአስቸኳይ ከዩክሬን ሉዐላዊ ግዛት ሙሉ ለሙሉ እንድታስወጣ ድምጻቸውን መስጠታቸው ነው የተነገረው።
አብዛኞቹ ምዕራባውያን አገራት የሩስያን ወረራ ያወገዙ ሲሆን፣ ውግዘቱን ከተጋሩት የአፍሪካ አገራት መካከልም ግብጽ፣ ጋና፣ ኬንያና ሶማሊያ ይገኙበታል፡፡ በተመድ የሩስያ አምባሳደር ባዝሊ ኔቤንዚያ ግን ምዕራባውያን መንግስታት በሌሎች አገራት ላይ ሩስያን እንዲያወግዙ ግልጽ ጫና ከማሳረፍ አልፈው ዛቻ ሲሰነዝሩ ነበር ሲሉ ከስሰዋል፡፡
ሩስያ ምዕራባውያን መንግስታት በተመድ ስብሰባ ውግዘት እንዲያደርሱብኝ በአገራት ላይ ጫና አድርገዋል ስትል ያቀረበችውን ትችት የሚያጠናክር ዘገባ ያወጣው አል አይን፤ ፓኪስታን ሩስያን እንድታወግዝ በ22 አገራት ዲፕሎማቶች መጠየቋን ያስነበበ ሲሆን፣ ከአገራቱ መካከልም ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ኦስትሪያና ጃፓን እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመቃወም ቅድሚያውን የያዘችው ራሷ ተወጋዧ ሩስያ ስትሆን፣ ጎረቤት ቤላሩስ፣ ሶርያና ኤርትራ ጉዳዩን በየራሳቸው መነጽር በመገምገምና ከግራና ቀኙ የትኛው አሰላለፍ እንደሚያተርፋቸው በማስላት ከሩስያ ጎን ቆመውላታል፡፡
እነ አሜሪካን ተከትዬ በሩስያ ላይ ያልተገባ የፋይናንስ ዝውውር ማዕቀብ አልጥልም ስትል የሰነበተችው ቻይና፣ በተመድ ስብሰባ ሩስያን ለማውገዝም ውግዘቱን ለመቃወምም ሳትደፍር፣ ድምጽ ሳትሰጥ የቀረች ሲሆን እንደ ቻይና ሁሉ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው እንዲህም እንዲያም፣ ወዲህም ወዲያም ሳይሉ ከቀሩ 35 የአለማችን አገራት መካከልም ህንድ፣ ኢራቅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ሞሮኮ እና ቶጎ ይገኙበታል፡፡
ሱዳን በተመድ ስብሰባ ላይ ድምጽ ባትሰጥም፣ ከሰሞኑ ሩስያን የጎበኙት የአገሪቱ ሉዐላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ግን አገራቸው ብሔራዊ ፍላጎቷን እስካልተጋፋት ድረስ ሩስያም ሆነ ሌላ አገር በቀይ ባህር ዳርቻ በሚገኙ ወደቦቿ የባህር ሃይል የጦር ሰፈር ቢገነባ ፈቃደኛ እንደሆነች አስታውቀዋል፡፡
ሩስያን ከማውገዝ አልፈው ዩክሬንን በጦር መሳሪያ የሚደግፉ አገራት እየተበራከቱ እንደሚገኙ የዘገበው ቢቢሲ፤ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያ፣ ግሪክና ስዊድንን ጨምሮ ከ25 በላይ አገራት የጦር መሳሪያና የሰብአዊ እርዳታዎችን ለመላክ ቃል መግባታቸውን አስነብቧል፡፡
አገራቸው በሁለቱ አገራት ጉዳይ ገለልተኛ መሆኗን ያስታወቁት የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ጃየር ቦልሶናሮ በበኩላቸው ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የዩክሬን ህዝብ በኮሜዲያን ላይ ተማምኖ ወደ ጦርነት መግባቱ ያሳዝነኛል ሲሉ በዩክሬኑ መሪ ዜለንስኪ የቀድሞ ሙያ ላይ መሳለቃቸው ተነግሯል፡፡
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሩስያ በዩክሬን ላይ የጦር ወንጀሎችን መፈጸሟን ለማረጋገጥ ምርመራ መጀመሩን ባለፈው ሃሙስ ያስታወቀ ሲሆን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማትም ሩስያ በተለይ በሳምንቱ ባደረሰቻቸው ጥቃቶች የፈጸመቻቸውን ወንጀሎች እያነፈነፉ ማጋለጣቸውን ተያይዘውታል፡፡

Read 11362 times