Saturday, 05 March 2022 11:58

"ተጣጥሮ መቅደም ነው እንጂ፣ የሩጫ መልክ አለው ወይ?"

Written by 
Rate this item
(5 votes)

      ከዓመታት በፊት የሚከተለውን ብለን ነበር፡- ከዕለታት አንድ ቀን ታላቅ ጦርነት ይካሄድ ነበር ይባላል፡፡ ተዋጊው ንጉስ በርካታ ወታደሮች ነበሩት፡፡ ግን ለወታደሮቹ የሚከፍላቸው ደሞዝ እጅግ ዝቅተኛ ነበር፡፡
ከወታደሮቹ መሀል ሦስቱ ሊከዱ ተስማሙ፡፡ ከተያዙ እንደሚሰቀሉ ስለሚያውቁም፣ ለመደበቂያቸው ባሻገር ወደሚታየው  ጫካ ሊሄዱ ወሰኑ፡፡ በተግባርም ወደዚያው ጫካ ገቡ፡፡ ጫካው ውስጥ ሶስት ቀንና ሌሊት እንደቆዩ ከፍተኛ ረሃብ ያዛቸው፡፡ “ንጉስ ደሞዝ   አሳነሱን ብለን፣ ጦሩን ከድተን ወጥተን፣ እዚህ በረሃብ መሞት ጅልነት ነው!” እየተባባሉ፣ መልሰው እጃቸውን ለመስጠት ሲያመነቱ፤ ድንገት ሰይጣን በትልቅ አጋዘን ተመስሎ ይመጣል፡፡ ችግራቸውንም ይጠይቃቸዋል፡፡ የሆነውን ሁሉ ነገሩት፡፡ ሰይጣኑም፤
“ቀላል  ነው ነገሩ፤ እኔ ከዚህ ጫካ አውጥቼ በደስታ ወደ ምትኖሩበት ቦታ እወስዳችኋለሁ፡፡ የንጉሡ ሠራዊት እንዳያያችሁ በአየር ላይ አሻግራችኋለሁ። ሆኖም በአንድ ነገር ከተስማማን ነው፡፡  ከሰባት ዓመት በኋላ አንድ ዕንቆቅልሽ እጠይቃችኋለሁ። መልሱን ካላገኛችሁ የእኔ ሎሌዎች ትሆናላችሁ፡፡”
በሃሳቡ ተስማሙ፡፡ ሰይጣኑ የጠቀሰው ሰባት ዓመት በጣም ሩቅ ጊዜ መስሏቸዋል። መዝገቡን አምጥቶ አስፈረማቸው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ሶስት የአስማት አርጩሜዎች ይሰጣቸውና በአርጩሜዎቹ ፈረሶቻቸውን ሲገርፉ በአየር ተንሳፍፈው ወደ ሌላ አገር ይሄዳሉ። ሀብት፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ተድላና ደስታ በእጃቸው ይገባሉ፡፡ መልካም ኑሮም ይኖሩ ጀምር፡፡
ሰባት ዓመት እንደ ቀልድ ነጎደ፡፡ ሰይጣኑ፣ በቀጠሮው መሰረት መጣ፡፡ ሁለቱ ወታደሮች በሀዘን ተዋጡ፡፡ አንደኛው ግን፤
“አይዟችሁ ጎበዝ! እንደምንም ብለን ዕንቆቅልሹን እንፈታዋለን” አላቸው፡፡ ሁለቱ ግን ከጭንቀታቸው አልወጡም፡፡
አንደኛው በጫካው ውስጥ ሲዘዋወር፣ እንጨት ተሸክመው፣ ከብዷቸው ሊወድቁ የደረሱ አሮጊት ያገኛል፡፡ እንጨቱን አውርዶ ይሸከምላቸዋል፡፡ እጎጇቸው ሲደርሱ ስለማንነቱ ጠየቁት፡፡ ታሪኩን በሙሉ ይነግራቸዋል፡፡
አሮጊቷም፤
“በጣም ደግ ሰው በመሆንህ ውለታህን እከፍልሃለሁ፡፡ ቃል ያስገባችሁ ሰይጣን የልጅ ልጄ ነው፡፡ ማታ ሲመጣ እኔ ዕንቆቅልሹን እጠይቀዋለሁ፡፡ አንተ ጓዳ ተደብቀህ መልሱን ታዳምጣለህ፤” አሉት፡፡
ጓዳ ተደብቆ ሲጠብቅ ሰይጣኑ መጣ፡፡ አሮጊቷም ስለ ሶስቱ ወታደር ልጆችና ስለ እንቆቅልሹ ጠየቁት፡፡
ሰይጣኑም “ሶስቱን ወታደሮች በጭራሽ የማይመልሱት ዕንቆቅልሽ ነው! ይኸውም
ወደ ፊት ምን ትመገባላችሁ?
በምን ትመገባላችሁ?
ምንና በምንስ ትጠጣላችሁ? የሚል ነው;
አሮጊቷም፤ “ታዲያ መልሱ ምንድን ነው?”
ሰይጣኑም፤ “በሰሜን ባህር ውስጥ የሞተ አንድ ጥንቸል - አሳ አለ፡፡ ለረዥም ጊዜ ቢመገቡት የማያልቅ ነው! ያንን ሾርባ ይመገባሉ፡፡ ለማንኪያ የሚጠቀሙበትም የዓሳ ነባሪ ጎድን ነው፡፡ ለወይን መጎንጫቸውም የፈረስ እግር መጫሚያ ተዘጋጅቶላቸዋል” አላቸው።
ሠይጣኑ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንቅልፍ ወሰደው፡፡
አሮጊቷ ወደ ተደበቀው ወታደር ዞረው፤
“እህስ ወዳጄ! ሁሉንም ነቅተህ አዳመጥክ አይደል?” አሉት፡፡
“አዎን፤ በደምብ አዳምጫለሁ” አላቸው፡፡
“በል እንግዲህ መጥቶ ሲጠይቃችሁ፣ በደንብ መልሱ፡፡ ለወደፊት የሚጠቅሙህን ሶስት ምክሮችን ግን ልለግስህ እፈልጋለሁ፡፡”
ወታደሩም፤
“ምን ምንድናቸው እማማ?”
“የመጀመሪያው፤ ከአንድ ቦታ ከድቼ እወጣለሁ ብለህ ስታስብ አስቀድመህ  ማረፊያህን አስብ፡፡
“ሁለተኛው፤ ምንም ቢርብህ ከሰይጣን ጋር ውለታ አትፈራረም!”
“ሶስተኛው፤ ባጋጣሚ ተሳስተህ ውለታ ከተፈራረምክም፤ እንዴት እንደምትወጣው ቀኑ ሳይደርስ አስብበት፡፡” ብለው  አሰናበቱት፡፡ አመስግኗቸው ሄደ፡፡
በነጋታው አይምሬው ሰይጣን መጥቶ ዕንቆቅልሹን አቀረበ፡፡ ብልሁ ወታደር ሶስቱንም ጥያቄ በልበ ሙሉነት መለሰ። ሰይጣንም ፀጉሩን እየነጨ ጥሏቸው ጠፋ፡፡
***
ችግር በገጠመን ሰዓት መፍትሔውን የምንሰጠው፤ አውጥተን አውርደንና አቅደን፣ መነሻና መድረሻችንንም አውቀን መሆን ይኖርበታል፡፡ በብሶት ግፊት ሆ ብለን፣ በድንጋጤ ግፊትም ለዘመቻ ተነስተን፣ መሆን የለበትም፡፡ ትርፉ መራኮት ነውና፡፡ አሁን የምንሰጠው ችኩል መፍትሔ ለሌላ ችግር መነሻ ሊሆን ይችላልና መጠንቀቅ ተገቢ ነው። ሲርበንና ሲጠማን በጥድፊያ ከሰይጣን ጋር ለመፈራረም አለመቸኮል- “አትሩጥ አንጋጥ” እንደሚባለው፤ ብልኅነት ነው፡፡ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል”ን አለመዘንጋት ነው፡፡ ምንጊዜም ችግሮቻችንን በሁለት መድቦ ማስቀመጥ፤ ቢያንስ የቱ ይቅደም የቱ? የሚለውን- ቀዳማይ-ድኅራይን መለየት ወሳኝ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ ነባራዊና ህሊናዊ (objective and subjective እንዲል ፅሑፉ) ለመለየት ይበጀናል፡፡
በአንድ አገር የኑሮ ውድነት ሲበረታ ሰው ለሰው ይጨካከናል፡፡ ይሄ በተደጋጋሚ ያየነው፣ የመሰከርነው ዕውነታ ነው፡፡ ምንዝር ላለቃው አይታዘዝም፡፡፡ ሰራተኛ ይለግማል። አለቃ ለኢኮኖሚ ድቀቱ ምላሽ መስጠት ሲያቅተው ቁጣ ቁጣ  ይለዋል፡፡ ኢኮኖሚስቱ ወደ ጥንቆላ  ይሸጋገራል፡፡ አስተማሪው ጥያቄ የሚጠይቀን ተማሪ ይጠላል! የኑሮ ውድነት የአእምሮ ድህነትን ማስከተሉ ግድ ይሆናል፡፡
የፖለቲካም፣ የኢኮኖሚም፣ የሰብዕናም፣ የፍልስፍናም ንቅዘት የዕለት የሰርክ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ከሃዲ ይበዛል፡፡ አጭበርባሪ ሸቃይና ሸቃጭ በሁኔታው ይጠቀማል። ተስፋ መቁረጥ ይበረታል፡፡ ኢኮኖሚና በጀት ከዕቅድ ውጪ ያፈነግጣል! ማህበራዊ ቀውስ እየተባባሰ፣ ይለመድና “ምን ይደረጋል?” “እሱ ያመጣውን! ወይም  ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው”…ማለት ይዘወተራል!
ቀውስ ናፋቂው፣ ቀጣፊው፣ ምላሳሙ ሰርጎ ገቡ ለሙስና ይሹለከለካል- “በራቸውን ሳይዘጉ፣ ሌባ ሌባ ይላሉ” አለች የተባለችውን ውሻ አለመርሳት ነው፡፡
ምንም ዓይነት ገለፃና ማብራሪያ ብንሰጥበት ከነባራዊ ሁኔታ በላይ ማሳመን አይቻልም፡፡ “ካልታዘልኩ አላምንም! “ ያለችው ሙሽራ ይሄ ሁኔታ የገባት ሳትሆን አትቀርም” (experience is better and richer than knowledge ይላሉ ጠበብት)።
አንድ  መሪ በጣም ጣፋጭ ´ድገመኝ ድገመኝ!´ የሚያሰኝ ንግግር አደረገ አሉ፡፡
ያንን ንግግር ያደመጡ አንዲት ምስኪን የራባቸው አሮጊት፤ “ምነው ይሄ ንግግር ዳቦ በሆነልኝ?” አሉ፤ አሉ። ያገራችን ፖለቲካል-ኢኮኖሚ እናቱም አባቱም ይሄው ነው!
የዓለምን ገበያ ከኢትዮጵያ ጉልት ችርቻሮ የሚያመለክት አሃዝ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የቻይናን የኮንስትራክሽን ማቴሪያል ፍጆታ መብዛት ከሀገራችን ህንጻና መንገድ ግንባታ የፍጆታ ዕቃ እጥረት ጋር አነፃፅሮ፣ ሰበቡ ይሄና ያ ነው ብሎ ለማብራራት፣ በታሳቢነት ግብዓት የሚሆኑት ነቁጦች እንኳን ተዘርዝረው አያልቁም! በኢትዮጵያ ውስጥ የታየው ግሽበት፣     “ደም ብዛት ነው!” “የለም ጉንፋን ነው!” ብሎ እንደመሟገት ያለ ጨዋታ አይደለም። የአሁኑ የኢኮኖሚ ሁኔታችንና ኑሮ ውድነት ከዓለም ገበያ  ዋጋ መጨመር ጋር ጨርሶ አይያያዝም፣ ብሎ ዐይንን መጨፈን ዩክሬንም፣ ሩሲያም፣ አሜሪካም፣ ቱርክም ሰሜን ዋልታና ደቡብ ዋልታ ላይ ነው ያሉት የማለት ያህል ዳፍንተኝነትን (obscurantism) መቀፍቀፍ ይሆናል፡፡
አንድ ኪሎ ስጋ ለመብላት ሶስት ኪሎ እህል እንፈጃለን ዓይነት ምሁራዊ ትንተና መስጠትም መሬት ለረገጠው ድህነት የመፍትሔ አቅጣጫ አይሆንልንም፡፡
ባይሆን፤ የችግራችንን ሥረ መሰረት (´መንቀሊያ´ እንዲሉ) በጋራ እንወያይና አንፃራዊ መፍትሔ እንጠቋቀም፤ ማለት ያባት ነው፡፡ ሙስና በተለያየ መልኩ ሲገለፅ ቢከርምም፤ ሰሚ አጥቶ ቆይቶ፣ ይፋ ገፅታው መታየት  የጀመረው ገና አሁን ይመስላል። "አጭበርባሪ ነጋዴና ተባባሪ የመንግስት ሠራተኛ አለ፡፡ ከድርቅ ጋር  የከብት ዋጋ አለመውደቁ ዘንድሮን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ፐርሰንቴጁ ታይቶ ኢኮኖሚያችን ጤናማ ነው፡፡
85%ቱ ገበሬ ኑሮ አልተወደደበትም” እየተባባልን ለጥያቄዎች እጅ በእጅ መልስ ለመስጠት ብቻ የምንሞክር ከሆነ፣ ለሚዲያ ፍጆታ እንጂ ወደ መፍትሔው ንፍቀ ክብብ እያመራንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ዕቅዴን ካሳካሁና የመገምገሚያ ነጥቤን ካሟላሁ፣ ሌላው ምንም ፋይዳ የለውም ካልን "ተጣጥሮ መቅደም ነው እንጂ የሩጫ መልክ አለው ወይ?” “እንደማለት ነውና፤ የትኛውም ፍሬ ሠናይ ዘንድ አያደርሰንም። “አካሄዱን አይተው፣ ጭብጦውን ቀሙት” እንደሚባልም እናስተውል!

Read 11804 times