Print this page
Saturday, 05 March 2022 12:04

በግጭትና ጦርነት ሳቢያ ነፍሰ ጡሮችና ህፃናት ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በኢትዮጵያ በተለያዩ ግጭቶችና ጦርነት ምክንያት ነፍሰ ጡሮችና አራስ ህጻናት ተገቢውን ክትትልና ህክምና እያገኙ አለመሆኑን፣ በዚህም እናቶችና የሚወለዱ ህጻናት ለሞትና ለተለያዩ የጤና እክሎች እየተጋለጡ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት አመልክቷል።
በኢትዮጵያ የነፍሰ ጡሮችና የወላጆች ጤና ክትትል ቀውስ አጋጥሟል ያለው ሪፖርቱ፤ በተፈናቃይ ካምፖችና መጠለያ ውስጥ ሴቶች በቀላሉ ይደፈራሉ፣ ይህን ተከትሎም ያረግዛሉ፣ ያለምንም የጤና ክትትልና እርዳታ እንዲወልዱ ስለሚገደዱ በመውለድ ላይ የሚሞቱ እናቶችና ህጻናት ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል-ብሏል።
ባለፉት አመታት የግጭት ቀጠና ሆኖ በቆየው የደቡብ ክልል ኮንሶ አካባቢ የተደረገው ጥናት፤ በርካታ ሴቶች በተፈናቃዮች ጊዜያዊ ጣቢያ ውስጥ የወለዷቸው  በጤና ክትትል እጦት ሳቢያ እንደሞቱባቸው ያመለክታል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የጥናት ቡድን በኮንሶ ዞን ገርጪ የተፈናቃዮች መንደር ውስጥ ከአራስ ልጇ ጋር አግኝተው ያነጋገሯት የ25 አመቷ አስናቀች፤ “ከሁለት ዓመት በፊት በአካባቢያችን የብሔር ግጭት ሲቀሰቀስ የወለድኩትን የወራት እድሜ  ያለውን ልጄን ይዤ ከግጭቱ ስሸሽ መንገድ ላይ በምግብ እጥረት ሞተብኝ” ብላለች።
ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ እዚያው መጠለያ ውስጥ እያለች በድጋሚ ማርገዟን የምትናገረው አስናቀች፤ “በእርግዝናዬ ወራት ሁሉ አንድም ህክምና አግኝቼ አላውቅም፤ የመውለጂያ ጊዜዬ ሲደርስ ምጥ መጣብኝ፣ ነገር ግን በአቅራቢያችን የሕክምና ተቋም ስለሌለ ወደ ህክምና ቦታ እየወሰዱኝ ሳለ ለመውለድ ሰዓታት የቀሩት ፅንስ ተጨናገፈ፣ ሞቶ ተወለደ” ትላለች። “ብዙ ተስፋ ያደረኩበትን ሁለተኛ ልጄንም በዚህ መልኩ አጣሁት” ብላለች አስናቀች።
እንደ አስናቀች ሁሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነፍሰ ጡርና ወላድ እናቶች ባለፉት ግጭት የበረታባቸው ዓመታት ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንዳጋጠማቸው የሚገልፀው ሪፖርቱ፤ በአካባቢው አሁንም ምንም አይነት የነፍሰ-ጡሮችና ወላጆች  ህክምና አገልግሎት አለመኖሩን ይጠቁማል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በአሁኑ ወቅት ከ110 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነፍሰ-ጡር ሴቶች ምንም አይነት የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው አለመሆኑን፣ ከእነዚህም ውስጥ 17 ሺህ ያህሉ በእርግዝናቸው ወቅት የተወሳሰበ የጤና ችግር እያስተናገዱ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል። ከነፍሰ-ጡር ሴቶች መካከል 55 ሺህ ያህሉ ደግሞ እርግዝናው የተፈጠረው ያለፍቃዳቸው በተፈፀመ ወሲባዊ ጥቃት መሆኑም በጥናቱ ሪፖርቱ ተጠቁሟል።
ጥናቱ በዋናነት ባተኮረበት የኮንሶ አካባቢ 17 የጤና ተቋማት ቢኖሩም፣ በጌድዮ ዞንና በጉጂ ዞን ባሉ ግጭቶችና የታጠቁ ሃይሎች እንቅስቃሴ የተነሳ ተገቢውን የሕክምና ቁሳቁስ ማሟላት እንዳልተቻለ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ መ፣ጀ ችግሩ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ ጉዳዩም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁሟል።
በተመሳሳይ ግጭትና ጦርነት በበረታባቸውና ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ነፍሰ ጡሮች፣ ወላዶችና ጨቅላ ህጻናት ተገቢውን የህክምና ክትትል እያገኙ ባለመሆኑ የወላጆች የጤና ቀውስ በከፋ ሁኔታ እያጋጠመ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል።


Read 11103 times