Sunday, 06 March 2022 00:00

የኛ አሉላ አባነጋ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

   የፈረሳቸው ስም ከተፀውኦ ስማቸው ጋር ተቋጥሮ “አሉላ አባ ነጋ” እየተባሉ የሚጠሩት ጀግና፤ የጥቁር ሕዝቦች ድል፣ የነጻነት ፈላጊዎች ትጋት ውጤት በሆነው፣ የዐድዋ ድል ተዘውትረው ቢነሱም በዶጋሊና በሌሎችም ግንባሮች በፈጸሙት ጀብድ ስማቸው በክብር ይወሳል።
አሉላ የተገኙት፣ ከአባታቸው ባሻ እንግዳ ቑቢና፣ ከእናታቸው ወይዘሮ ገረዳማርያም ናጊድ በትግራይ፣ ደጉን ተምቤን ተብሎ በምትጠራ፣  ውስጥ ዝቋላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው። በጊዜው በሀገሪቱ የነበረው የትምህርት ተቋም የቤተክህነት ብቻ ስለነበረ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ትምህርት ቤት ተልከው ነበር። ትምህርት ቤቱ መነዌ ሚካኤል ሲሆን መምህሩም የኔታ ወልደጊዮርጊስ ይባሉ ነበር።
የአሉላን የትውልድ ዘመናቸውን ቁርጥ አድርጎ መናገር ባይቻልም፣ በሁለት ነገሥታት የአስተዳደር ዘመን የሚዋዥቅ ግምት ነበረ። አንዳንዶች በደጃዝማች ሰባጋድስ ዘመን ተወልደዋል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ በደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ዘመን መጨረሻ አካባቢ ተወለዱ ይላል።
ለእነዚህ ማመንታቶች የተሻለም ደጋፊ ሀሳብ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው አውጉስተስ ዌልድ የተባሉ እንግሊዛዊ ዲፕሎማትና የታሪክ ጸሐፊን ሀሳብ ነው። ምክንያቱም እኚህ ሰው አሉላ አባነጋን በ1888-1889 ዓ.ም በአካል አግኝተዋቸው ስለነበር ነው። እኚህ ሰው እንደሚሉት፤ በዚህ ጊዜ አሉላ ዕድሜያቸው በ60ዎቹ መጨረሻ ነበር፤ቢበዛ እንኳ ከ70 አይበልጥም።
ሌሎች እንደሚሉትም፤ አሉላ በጉንደትና በጉራጌ በተደረጉ ጦርነቶች ሲፋለሙ፣ ዕድሜያቸው በ40ዎቹ ውስጥ ነበር።… በርግጥ ከ25-30 ዓመት የሚገምቷቸውም ነበሩ።  
በሌላ በኩል፤ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ተብለው ዙፋን ላይ ሲወጡ፣ አሉላ ዕድሜያቸው 12 ዓመት እንደ ነበረ መምህር ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርም ጽፈዋል። ይሁንና ከሁሉም የዕድሜ ግምቶች የበለጠ ቦታ የሚሰጠው የአውግስተስ ዋይልድ ሀሳብ ነው። አሉላ፣ የተወለዱት ገጠር ሰሆን ወላጆቻቸውም ገበሬ ስለነበሩ፣ በዘመኑ መኳንንትና መሳፍንት ተብለው ከሚመደቡት ወገን አልነበሩም። ይህን እንኳ ከንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ፍልሚያ (ጦርነት) የቀኝ እጅ የሆኗቸው በዝብዝ ካሣ ምርጫ ለአሉላ የሻለቃነት፣ የሊጋባነትና የጦር አበጋዝነት ሹመት ሲሰጧቸው፣ ብቃታቸውን እንጂ የቤተሰባቸውን ዝና አልመዘኑም። እንዲያውም የዘመኑ መኳንንት  “እንዴት እኛ እያለን?” በማለት በቅናት ሲቅበጠበጡ፣ ካሣ ምርጫ ግን ጆሮ አልሰጧቸውም ነበር። ይሁንና አሉላ ግን አሉላ ነበሩ።
አባታቸው እንግዳ ቑቢ ጀግንነት የሚያንሳቸው አልነበሩም። አሉላ ብቻ ሳይሆን ሁለቱ ልጆቻቸው በጦር ግንባር የተዋደቁ ነበሩ። ባሻ ገብረማርም በጉራጌ ጦርነት ተፋልመው ሲወድቁ፣ ሌላኛው ልጃቸው ባሻ ተሰማ እንግዳ ፣ በመረብ ጉንደትና ጉንዳጉንዲት ሲዋጋ ክፉኛ ቆስሎ ነበር።
በርግጥም የእንግዳ ስም “ቑቢ”ም ትርጉሙ በትግርኛ ቀላል አልነበረም። “ቑቢ” ማለት የአንበሳ ጅራት ማለት ነው። ታዲያ የአንበሳን ጅራት የሚነካው ማነው?... አባትየው ጀግና ወዳድ፣ ቆፍጣናና ጀግና ናፋቂ እንደሆኑ የሚታወቀው የአሉላ  የክርስትና ስም “ገብረ ሚካኤል” በመሰኘቱ ቅር ተሰኝተው፣ “ወልደ ገብርኤል” በሚል ለውጡልኝ በማለታቸው ነው። የአሉላ-ባሻ አባት ቑቢ፣ ያልናቸው፣ የአሉላ የክርስትና ስም ገብረሚካኤል “ወልደ ገብርኤል” በሚል እንዲቀየር ያደረጉት ጥረት ወታደርና ጦረኛ ወዳድነታቸውን የሚያጎላ ነው -ይባላል። ይህንንም ብዙዎች በልማድ እንደሚያስቡት ገብርኤል ቁጡና ሀይለኛ፣ ሚካኤል ለስላሳና ገራገር ተደርጎ ስለሚታይ ነው።
ታዲያ አሉላም ዝንባሌያቸው ወደ ጦርነቱ አዘንብሎ፣ የኔታ ጋር ሄዶ ፊደል ከመቁጠሩ ይልቅ ባሩድ ማጤስ እያማራቸው ወደ ቄስ ትምህርት ቤታቸው ሲሄዱ መንገድ ላይ በሶናድራቸው የተኩስ ልምምድ (ኢላማ) ያደርጉ ነበር። አጎታቸው ባሻ ፈንጃይም “እንኳንስ እኔ ፊት ይቅርና ከኔ ኋላ እንኳን ተኩስ ሳተ የሚል ወሬ እንዳልሰማ” ይሏቸው እንደነበር ይነገራል።
ወጣቱ አሉላ በመጀመሪያ ቀን ሙከራቸው አምስት ጥይት ተኩሰው፣ ሁለቱ ዒላማቸውን አግኝተው የበሬ ቀንድ ሲመቱ ሶስቱን ስተው ነበር። በዚህም ምክንያት አጎታቸው ተቆጥተው “እንዴት ሦስት ጥይት ታባክናለህ” በማለት በኩርኩም አድምተዋቸዋል እየተባለ ይነገራል።
በልጅነታቸው ፈረስ መጋለብ፣ የውሃ ዋና፣ ከዱር አራዊት ጋር መሯሯጥ፣ ጥንቸል ሽኮኮ፣ ጦጣ ወዘተ ማሯሯጥ ይወድዱ ነበር። ከባልንጀሮቻቸው ጋር ጋራ ሸንተረር ላይ መሯሯጥ ፣ ዝላይና ድንጋይ ውርወራም ጨዋታቸው እንደነበር ይነገራል። የወደፊቱ ታይቷቸው ጓደኞቻቸው ብዙ ጊዜ የቡድን መሪና አለቃ ያደርጓቸው ነበር፣ ታዲያ ማንም ሮጦ አያመልጣቸው! አሳድደው ቀብ ነው።
ይሁንና ሃይለኛ  በመሆናቸውበ በሌሎችም ሰዎች ክስ፣ በየኔታ ወልደጊዮርጊስ ፊት እየቀረቡ በቁንጥጫ ሳይመዠለጉና በኩርኩም ሳይጋጩ የሚውሉበት ጊዜ ስላልነበረ ትምህርቱን ወደ መሸሹ ያመጣቸው  ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይገመታል።

በደጃዝማች
(ባልገዳ) አርአያ ድምፁ ቤት
ደጃዝማቹ በርካታ ወጣቶች በአሽከርነት ሲገቡላቸው፣ አደን ተኩስና መሳሪያ መፍታትና መግጠም የተለማመዱት አሉላ፣ ወደኚሁ ጎበዝ ቤት መግባት ፈለጉ። ይሁን እንጂ ሌሎቹ በሚገቡበት መንገድ በዘመድ አዝማድና በቤተሰብ በኩል ሳይሆን ራሳቸው  በቀጥታ ሄደው ጠየቋቸው። ቤተሰባቸውን የሚያውቋቸው አርአያ ድምፁም ሊቀበሏቸው አላቅማሙም።  የደጃዝማች አርአያ በደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም አልገዛም ባይ ናቸው ተብሎ ከታሰሩበት መቅደላ እስር ቤት ከተመለሱ በኋላ አሉላ የዚያ መኳንንት እልፍኝ አገልጋይና አሽከር ሆኑ።
አሉላ እዚህ ቤት ከገቡ በኋላ ዝናቸው ናኝቶ፣ በቤተሰቡም ተወዳጅ ሆነው ነበር። ቆቅ እያጠመዱ፣ ድኩላ፣ ሚዳቋና ሰስ እያደኑ ስለሚያመጡ በደጃዝማቹ ሴት ልጅ በወይዘሪት አምለሱ ይበልጥ ተወዳጅ ሆነው ነበር። በመሆኑም እንዲህ ስንኝ ቋጥራ፣
የምበላው ስጋ የድኩላ፣
ያመጣልኝ ወንዱ አሉላ፣
ይመረጣል ስጋ ከሆነ የሰስ፣
አሉላ ወንድ ነው የልብ የሚያደርስ።
…ታደንቃቸው ነበር።
ወጣቱ አሉላ፣ እዚህ ቤት ከገባ በኋላ አደን እየወጡ ድኩላ መግደል፣ ሰስና ሚዳቋ ተኩሶ መጣል፣ ቆቅ ማጥመድ የዕለት ተዕለት ሥራቸው ሆነ። በዚህም ተግባራቸው፣ በተለይ በደጃዝማቹ ሴት ልጅ  በወይዘሪት አምለሱ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ሆነ። የእርሷ ወንድም ደበብ በቅናት  ቢንገበገብም፣ እርሷ ግን ግጥም ትገጥምለት ገባች። እናም፡-
የምበላው ስጋ የድኩላ፣
ይምጣልኝ ወንዱ አሉላ።
ይመረጣል ሥጋ ከሆነ የሰስ፣
አሉላ ወንድ ነው የልብ የሚያደርስ።… በማለት ታደናንቀው ነበር።
በአሉላ ጀግንነትና አልሞ ተኳሽነት የቀናው የደጃዝማች አርአያ ልጅ በተለያየ ዘለፋና ተረብ በሰላም እንዳይኖር እያወከው ቆይቶ፣ አንድ ቀን አሉላ ከአቅሙ በላይ ሲሆን፣ ሰማይ አድርሶ መሬት አፈረጠው። ነገሩ በዚያ ዘመን፣ ያን የሚያህል የመኳንንት ልጅ መደብደብ ከባድ ነበር። ይሁን እንጂ አሉላ ጫንቃው ከዚያ በላይ ሊሸከም ስላልቻለ እርምጃ ወሰደ።
ከዚያ በኋላ የገጠመው ዕጣ እስር ቤት መግባት ነበር። የደጃዝማቹ አጋፋሪዎች “የጌታችንን ልጅ ተዳፍረሃል” በሚል አሰሩት። ይሁን እንጂ በአምለሱ ዘንድ ግን አሉላ ያኔም ተወዳጅ ነበር። እታሰረበት ድረስ ምግብ አሰርታ፣ ሄዳ ጠይቃዋለች። አሉላ፣ “አንቺ እኔ ጋ መምጣት አይገባሽም ነበር” ብሎ፣ የደረጃ ልዩነታቸውን ሊናገር ቢዳዳም፣ በአምለሰት ዘንድ ያልተገባ መሆኑ ተነግሮት፣  ይዛለት ከሄደችባቸው ምግብ እርሷ ጎርሳ ነበር። አሉላ “ከኔ ጋር ልትበደይ አይገባም!” ብሎ በርሷ ላይ ሊያመጣ ስለሚችለው ወቀሳና ንቀት ተቆርቁሯል፣ እሷ ግን ፍቅሯ ከመደብ ልዩነት በላይ ነበረና አልሰማችውም… ፍቅሯም ሩቅ ነበር። ይሁንና አሉላ ወደ ሕልሙ በፍጥነት እየተጓዘ ስለነበር ፣ የተሰረቀ ልቡን፣ የሚሮጥ ሀሳቡን ማስቆም አልቻለችም!...

ሕይወት ወደ
ደጃዝማች በዝብዝ ካሣ
ደጃዝማች አርአያ ቤት እሮሮና ክስ የበዛበት አሉላ፣ ተረጋግቶ ወደተመኘው ሕይወት መድረስ ስላልቻለ፣ ቤታቸው ያስገቡት ደጃዝማች አርአያ ሕልሙን ያሰምሩለታል ብለው ወዳሰቡት አባ በዝብዛ ካሳ (በኋላ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ) ቤት ወሰዱት። እናም “ይህ ልጅ ይጠቅምሃል፤ ጎበዝ ነው!” ብለው ለበዝብዝ ካሣ አሥረከቧቸው።
በኋላም አባ በዝብዝ ካሣ ጦርነት በገጠሟቸው አፄ ተክለጊዮርጊስ የጦር ዝግጅት ወቅት አሉላ የበለጠ የጦር ስልጠና የሚያገኝበት ዕድል አገኘ። ለካሣም አስተማማኝና ፈርጣማ ጡንቻ ሆኖ ቆመ። በተለይ ከጆን ሌዊ ኪርከሃም (የአባ በዝብዝ ካሣ የጦር አማካሪ) ጋር በመሆን የተክለጊዮርጊስን ጦር ድል ለመንሳት መረጃ በመሰብሰብና የጦር ዝግጅት በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫወቱ።
በመጨረሻም 60 ጦር ያህል ያላቸው አፄ  ተክለጊዮርጊስ፣ ከእንግሊዙ ጄኔራል ሮበርት ናፒየር ባገኙት መሳሪያ በሚገባ የታጠቁት የካሣ 12 ሺህ የሚገመት  ጦር ሰራዊት በዐድዋ  በተደረገው  ፍልሚያ፣ ንጉሡ፣ በተክለጊዮርጊስ ጦር ተሸንፈው እጅ ሰጡ።
እናም በጦር ግንባሩ ላይ ትልቅ- የጀግንነት ስራ ለሠራው አሉላ-እንግዳ እንዲህ ተገጠመለት፡፡
የንጉስ ሠራዊት ዓድዋ ድረስ ቢመጣ
…አሉላ ቢገጥመው ብትንትኑ ወጣ
አሉላ ጦር ሜዳ ቢገባ እያገሳ
ንጉስ ተማረከ ተንበርክኮ እጅ ነሳ፡፡
ዓድዋም በዚሁ የዓለም ወንዝ ላይኛው ክፍል በተደረገው ጦርነት ንጉስዎ ተክለጊዮርጊስ ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀው ካሳ ምርጫ አባ በዝብዝ ጋር  እስከ መጨረሻው እየተፋለሙ ጦራቸውን “በርታ!...ግፋ! እያሉ አሉላ ወዳለበት አቅጣጫ ሲጋልቡ፤አሉላ አነጣጥሮ ፈረሳቸውን ሲመታው ንጉስን ይዟቸው ወደቀ፡፡ ይሄኔ ንጉሱ  የወደቁበት እጃቸው ተጎዳ፡፡ በኋላማ በአሉላ እጅ ተማረኩ፡፡ አሉላ ማራኪ ቢሆኑም ምርኮኛውን ንጉስ የያዙት በጨዋነትና በሰለጠነ መንገድ ነበር፡፡
በዚህ ጦርነት ባስገኙዋቸው ድል ምክንያት አሉላ- የሻለቅነት ማዕረግ ከማግኘታቸው በላይ ካሳ ምርጫ (አበ በዛብህ) እቅፍ አድርገው  እንደሳሟቸው ይነገራል፡፡ ሞላ ተድላ የተባሉት የታሪክ መምሀርና ፀሀፊ ስለነበረው ሁነት ሲያሰፍሩ።
….ደጃች ካሳ ምርጫ፣ አባ በዛብህ ከልባቸው እጅግ ተሰደቱ እቅፍ አድርገው ሳሟቸው፡፡ ይህንን ታሪካዊ ክስተት ተከትሎ ነበር ደጃዝማች ካሳ  አባ በዛብህ ለአጋፋሪ አሉላ የሻለቃነት ማዕረግ የሰጧቸው በመቀጠልም ስናድር ጠመንጃቸውን ሸለሟቸው፡፡ በዚህ ሳያበቃ ደግሞ “አባነጋ” ብለው የሰየሙትን ፈረሳቸውን ሸለሟቸው።”
አሉላ እንግዳም ባብዛኛው በፈረሳቸው ስም “አባ ነጋ” መጠራት የጀመሩት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ ስለዚህም ብዙዎቻችን ከአባታቸው ስም ይልቅ የምናውቃቸው በፈረሳቸው ስም ነው፡፡ ፈረሳቸው የመጣው ደግሞ በጀግንነታቸው ነው፡፡
በኋላም በጉንዳትና ጉንዳጉንዲ-በተደረገው ጦርነት የማረኩትን መሳሪያ ለንጉስ ነገስቱ ካሳ ምርጫ (አጼ ዩሀንስ) ሲያስረክቡ የሊጋባነት  ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
አሉላ በትውልድ ስፍራቸውና በሌሎችም የሠርግ ቦታዎች ሳይቀር የሚገጠምላቸውና የሚዘፈንላቸው ልጃገረዶች ሁሉ የኔ በሆነ!” በሚል ምኞት ብቻ ሳይሆን በግጥም ማቀንቀን ጀመሩ፡፡ ዐፄ ዩሀንስም፡፡ አሉላን የመሰለ ጀግና ከእጃቸው እንዳይወጣ በትዳር  ለማስከን ውሃ አጣጫቸውን ፈልገው ለመዳር ወሰኑ፡፡ እናም አልቀረም፤ በመቐለ እንደርታ ከሚገኘው የንጉስ ቤት ጎን ብትወጣ ገብረመስቀልን አግብተው መኖር ጀመሩ፡፡ በጋብቻ ለሰባት ዓመታት አብረው ቆይተው ሶስት ሴት ልጆችን ወለዱ፡፡
ሻለቃ አሉላ እንግዳ  በጉንዳ ጉንዲት 5 የጉራጌ ጦር አዛዥ ሆነው የአፄ ዩሐንስን ጦር በዋና አዛዥነት መርተው የግብፅን ሰራዊት ሲገጥሙ ትዳር ይዘው በጎጆ ተሰብስበው ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን የሀገር ጦርነት ሲዋጉ ሁለት ወንድሞቻቸውን በሺ ተሰማ እንግዳና ባሻ ገብረማርያም የሚባሉ ወንድሞቻቸውን አብረው አሰልፈው ነበር፡፡
ሕዳር 7 ቀን 1868 ዓ.ም በግብፅ ጋር የተደረገው ጦርነትና የተገኘው ድል እስከዛሬ የግብጻዊያንን ቁስል እንዲሆን ያደረጉት አሉላ አባነጋ ጦሩን በዋና አዛዥነት መርተው ነበር፡፡
“ለጌቶች የጠላት ድግስ ማቆየት አይገባም!” የሚሉት አሉላ፣ጦርነቱን ያጠናቀቁት አፄ ዮሐንስ ወደ ግንባር ከመድረሳቸው በፊት ነበር፡፡ በጦርነቱም የግብፅን ሠራዊት ይመራ የነበረው የዴንማርክ ዜግነት ያለው ኮሎኔል አረንድረሮፕ ቆስሎ ከተማረከ በኋላ ለወራተር ቆይቶ ሕይወቱ አለፏል፡፡ አሉላም በወታደራዊ ስልት አዋቂነታቸውና የአመራር ብቃታቸው የሊጋባት ማዕረጉ የሠጧቸው ይሄኔ ነበር፡፡
አሉላ፣ዳግመኛ በእልህና ቁጣ በመሐመድ ራጢብ ፐሻና በልጁ ልዑል ሐሰን ኮዲብ እስማኤል የሚመራ ዘመናዊ ጦር ይዞ መጥቶ ጉራጌ አካባቢ በመሸሸግ ሲመጣ፣አሁንም ጦሩም  የመሩት የድል አባት የሆኑት አሉላ አባነጋ ነበሩ፡፡ እናም ምሉን ሰጥተው ከምድር ደባልቀው በታሪክ ውስጥ ግብጻውያን “ደግሞ አይለምደንም!” እስኪሉ ቀጥተው አባርረዋቸዋል፡፡
አሉላ ሰው ናቸው፡፡ አሉን ጀግናና ርኅሩኅም ናቸው፡፡ ካከበሯቸው ያከብራሉ፤ ለናቋቸው ዋጋውን ይሰጣሉ። ቤተሰባቸውም ጀግና ነው፡፡ ሀገራቸውም የጀግና ሀገር ናት!..
እርሳቸውም የታሪክ መምህሩ ሞላ ተድላ እንደፃፉት እንዲህ ብለዋል፡፡ አያቶቼ ወታደሮች ናቸው፡፡ አባቶቼም እንዲሁ ወታደሮች ናቸው። እኔም ወታደር ነኝ። ያገርን ዳር ድንበር ሉዓላዊት ከወራሪ የምመክት ወታደር ነኝ፡፡ እኔ በሕይወት እያለሁ አገሬ በውጭ ወራሪ  ኋይሎች አትደፈርም፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ራሱ ቀይ ባሕር ነው፡፡ ፈረሴን ከቀይ ባህር ውሃ ሳላጠጣው አልመለስም፡፡
ቀጣዩን ሳምንት ልመለስበት፡Read 558 times