Sunday, 06 March 2022 00:00

የካራማራ ድል!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ኩባዊው ወታደር ካርሎስ ኦርላንዶ - በወቅቱ ዕድሜው 20 ነበር። ካርሎስ ኦርላንዶ ጥር 1970 ዓ.ም. የሶማሊያ ወታደሮች እጅ ላይ ወደቀ።
የዓለም መገናኛ ብዙሃን በተሰበሰቡበት የኢትዮጵያንና ኩባን ወታደራዊ ምስጢር እንዲያወጣ ተደረገ።
የኦጋዴን ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል የተደረገው ጦርነት የዛሬ 44ዓመት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. ነበር የተጠናቀቀው።
በ1966 ዓ.ም ሶማሊያ የአረብ ሊግን ተቀላቀለች። በወቅቱ የሶማሊያ መሪ የነበረው ሜጀር ጄኔራል ሲያድ ባሬ ኢትዮጵያን ወረረ። ጦርነቱ የተጀመረ ሰሞን የሲያድ ባሬ [ዚያድ ባሬ] ጦር በሶቪየት ኅብረት ይደገፍ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ወዳጅነት አለው። በወቅቱ በቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ የነበሩት ሶቪየት ኅብረትና አሜሪካ ምሥራቅ አፍሪካ ገቡ።
ፕሬዚዳንት አብዲራሺድ አሊ ሸርማርኬን በመንፈቅለ-መንግሥት ፈንግሎ ሥልጣን የጨበጠው የዚያድ ባሬ መንግሥት፤ ድንበር ማስፋፋት ዋነኛ ዓላማው አደረገ። ወሳኟ ቦታ ደግሞ - ኦጋዴን።
ኦጋዴን ሠፍሮ የሽምቅ ውጊያ ያካሂድ የነበረው የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጭ ግንባር የኢትዮጵያ ጦር ላይ ጥቃት ሠነዘረ። የጦርነቱ መባቻ ተደርጎ የሚቆጠረውም ይህ ጥቃት ነበር። በመቀጠል የዚያድ ባሬ ጦር በሶቪየት ኅብረት የጦር መሣሪያ ታግዞ ወደ ኦጋዴን ገሰገሰ።
በወቅቱ ከንጉሡ አገዛዝ ወደ ወታደራዊው ደርግ የተሻጋገረችው ኢትዮጵያ፣ በይፋ ራሷን ማርክሲስት ስትል አወጀች፤ ወዳጅነቷም ከሶቪየት ኅብረት ጋር ሆነ። አሜሪካ ደግሞ ድጋፏን ለሶማሊያ አደረገች።
ሁለቱ አገራት ወደ ቀለጠ ጦርነት ገቡ። በወቅቱ የሲያድ ባሬ መንግሥት፣ ኩባውያን የኢትዮጵያን ጦር ደግፈው እየተዋጉ ነው ሲል ወቀሰ። ይህንንም ለማሳመን ሲሉ የኩባ ወታደሮች መያዝ ጀመሩ። የዚያኔ ነው ኩባዊው ወታደር ካርሎስ ኦርላንዶ ተይዞ ለጋዜጠኞች መግለጫ እንዲሰጥ የተገደደው።
የዚያድ ባሬ መንግሥት ወራራውን አጠናክሮ በጅግጅጋ በኩል ድንበር አልፎ ገብቶ ብዙ ጥፋት አደረሰ። የንፁሃን ዜጎች ሕይወትን ተቀጠፈ። አልፎም ወደ ሐረር ገሰገሰ። ይሄኔ ነው የኢትዮጵያ ክተት የታወጀው። ሐረር ላይ 40 ሺህ ገደማ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጠበቀው። ተጨማሪ 10 ሺህ የኩባ ጦረኞች ከኢትዮጵያ ጎን ነበሩ።
የኢትዮጵያ ጦር የዚያድ ባሬን ጦር አሳዶ ከመሬቱ አስወጣ። የመጨረሻው ውጊያ የነበረው ካራማራ ላይ ነበር። በወቅቱ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታገዘው የኢትዮጵያ ጦር በሰማይ በምድር ጥቃቱን በማጠናከር የሶማሊያ ጦርን ድባቅ መታ።
ጦርነቱ ሲጀመር ኢትዮጵያ 10 በመቶ ብቻ የኦጋዴን መሬት በእጇ ነበር። ጦርነቱ ካራማራ ተራራ ላይ ሲያበቃ ኦጋዴን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ተያዘች።
በካራማራ ጦርነት በርካቶች ተሰውተዋል። በቀጣናው ያለውን ድርሻ ለማስፋት ኢትዮጵያን የወረረው ሜጀር ጄነራል ሲያድ ባሬ፤ ከሽንፈቱ በኋላ ተቀባይነቱ እየሟሸሸ መጣ።
ታላቋ የሚል ቅጥያ የነበራት ሶማሊያም ከኦጋዴን ጦርነት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት መታመስ ጀመረች። ሲያድ ባሬ በ1983 ዓ.ም ከሥልጣን ተወግዶ ወደ ናይጄሪያ ሸሸ። ሕልፈተ ሕይወቱም ለአራት ዓመታት በስደት በቆየባት ናይጄሪያ ሆነ።
በጦርነቱ ኩባ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ የመንና ምሥራቅ ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች አገራት አጋርነታቸውን ለኢትዮጵያ አሳይተዋል። ከ16ሺህ በላይ የኩባ ወታደሮች በውጊያው እንደተሳተፉ መዛግብት ያሳያሉ።
የኢትዮ-ሶማሊያ የኦጋዴን ጦርነት የብዙሃን ሰላማዊ ዜጎችን ቢቀጥፍም፤ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ጅግንነታቸውን ያሳዩበት እንደሆነ በታሪክ ይወሳል።
ክብርና ሞገስ ለሰማዕታቱ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!


Read 3527 times