Print this page
Monday, 07 March 2022 00:00

“መንግስት ለብሎኮቹ መሟላት ያለበትን መሰረተ ልማት ሊያሟላልን አልቻለም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 - ሳይቱ ለዘረፋና ለአካባቢ ብክለት ተጋልጧል
           - አሳንሰር፣ ውሃና መብራት ሳይኖረን በጨለማ እየኖርን ነው

       የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ኮርፖሬሽን 40/60 ፕሮጀክት 01 ከሚያስተዳድራቸው ቡልቡላ፣ ሳይት ገርጂ (ህንጻ አቅራቢያ) ሳይት፣ ቱሪስት ሳይትና አስኮ ሳይት ጋር አብሮ የሚተዳደረው በተለምዶ መገናኛ ሃያ አራት እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ያለውና 6 ብሎኮችን የያዘው “የእህል ንግድ ሳይት” አንዱ ነው። ይህ ሳይት ከሰንጋ ተራ 40/60 ሳይት ጋር አቻ እድሜ ሲኖረው፤ የቤቶቹ ቁልፎች ለእድለኞች ተሰጥተው፣ የተወሰኑት ሰዎች ያለምንም መሰረተ ልማት ከቤት ኪራይ ችግር ለመውጣት በተለይም ከመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ገብተው መኖር መጀመራቸውን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በሳይቱ ላይ ከጸጥታ ስጋት ጀምሮ በርካታ ችግሮች የተጋረጡባቸው መሆኑን በምሬት ይናገራሉ። ለመሆኑ የነዋሪዎቹ ችግሮች ምንድን ናቸው ስትል የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በስፍራው ተገኝታ ሳይቱን ከጎበኘች በኋላ ከእህል ንግድ ሳይት  የነዋሪዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ከሆኑት አዲስዓለም ገንታ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች።


               እስኪ ሳይቱ ስለሚገኝበት ሁኔታ ማብራሪያ ይስጡኝ?
የእህል ንግድ ሳይት 6 ብሎኮች ያሉት ሲሆን ከስድስቱ ብሎኮች አንዱ የሆነው ብሎክ ሶስት ቀደም ሲል በኪራይ ቤቶች ተገዝቶ ለተለያዩ ሰዎች ተሰጥቷል። እነዚህ ሰዎች አስፈላጊው መሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው ኑሯቸውን እየኖሩ ነው። ሌሎቹ አምስቱ ብሎኮች እድለኛ የሆንን ሰዎች በአሰራር ሂደት መሰረት ቁልፍ የተረከብነው በተለያየ ጊዜ ቢሆንም፣ በተለይ ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በየወር ልዩነት ለእድለኞች ተላልፈዋል። ከዚያ በኋላ ያደረግነው ቤቶቻችንን የውስጥ ማስዋብና የአጨራረስ ስራ መስራት ነው። ከሞላ ጎደል በየብሎኩ ከ70 በመቶ በላይ ቤቶችን አስውቦና አስተካክሎ ለመኖሪያነት ምቹ የማድረጉ ሥራ ተጠናቅቋል። እርግጥ ነው በየብሎኩ ገና ያልተጀመሩ የአጨራረስ ስራ እየተሰራላቸው የሚገኙ የተወሰኑ ቤቶች አሉ።
አንዱ ብሎክ ስንት አባወራ የመያዝ አቅም አለው?
እንግዲህ በየብሎኩ ለመኖሪያነት የሚውሉት ቤቶች ከሶስተኛ ወለል ጀምሮ ወደ ላይ እስከ 12ኛ ወለል ያሉት ናቸው። እያንዳንዱ ብሎክ 100 አባወራዎች ይዘዋል። ከሶስተኛ በታች ያሉት ማለትም መሬቱ፣ አንደኛና ሁለተኛ ወለል ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሱቆች ናቸው። ሁሉም በጨረታ ተሸጠዋል። ይሁንና እነዚህ በጨረታ ያሸነፉት አካላት ቤቱን ተረክበው ወደ ስራ አልገቡም።
ለምን እንዳልገቡ ይታወቃል?
ቤቶች ኮርፖሬሽን ቁልፍ አላስረከባቸውም ነው የተባለው። እነዚህ ባለሱቆች ቤቱን ተረክበው ወደ ስራ አለመግባታቸው ነው ለነዋሪው ትልቅ ፈተና የሆነው።
እስኪ በደንብ ያብራሩልኝ… ከ3ኛ ወለል በታች ያሉት ቤቶች ክፍት መሆናቸው እንዴት ችግር እንደፈጠረ?
ምን መሰለሽ ግራውንዱ፣ እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ላይ ሰው ባለመግባቱና ባለቤቶቹ ባለመኖራቸው ለሌላው ነዋሪ እጅግ ስጋት የሆነ የጸጥታ ችግርና ለአካባቢ ብክለት መንስኤ ሆነዋል። ተመልከቺው መሀል ከተማ ላይ  የሚገኝ ሳይት፣ ይህን በመሰለ ህንጻ ስር እያንዳንዱ የመሬቱ ወለል በሰዎች አይነምድር ተሞልቷል። የጸጥታ ችግርም ኑሮአችንን እረበሸብን ነው።
የቤት እድለኞች ቁልፍ ከተረከባችሁ በኋላ ማህበር አቋቁማችኋል። ይሄ ሁሉ የንጽህና ችግር ሲፈጠርና የፀጥታ ስጋት ሲኖር ማህበሩ ለሳይቱ እንዴት ጥበቃ አልቀጠረም?
ጥሩ!! ገና እድለኞች መሆናችንን ስናውቅ ጀምሮ ማህበሩን አቋቁመን ወዲያው ነው ወደ ስራ የገባነው። መጀመሪያ ያደረግነው ነገር፣ መንግስት በፍጥነት ቁልፍ እንዲያስረክበን የማድረግ ስራ ነበር። ከዚያ ቀጥሎ ወደ ቤት ማስዋብና አጨራረስ መግባት ነው። ያንን ስናደርግ ደግሞ ንብረት ማምጣት የግድ ይሆናል። ያንን ንብረት አውላላ ሜዳ ላይ ጥለን ለመሄድ የማይሆን ስለሆነ ጥበቃ መቅጠር አለብን ብለን ተስማማንና አወዳደርን። “ብርሃን የጥበቃ ኤጀንሲ” የሚባል ቀጠርን። ከዚያም በየብሎኩ በቀን አራት ጥበቃ አሰማራን። ይህ ማለት በየብሎኩ ቀን ሁለት ማታ ሁለት ጥበቃ መደብን። ነገር ግን ከግራውንድ ጀምሮ አይደለም የሚጠብቁት፤ ከ3ኛ ወለል ጀምሮ ነው። እኛም እንደ ማህበር ሃላፊነት የወሰድነው ከሶስተኛ ወለል በላይ ያለውን የነዋሪውን ቤት እንዲጠብቁ ነው። ምክንያቱም ከሶስተኛ ወለል በታች ያለው ገና በተቋራጮች ስራ እየተሰራባቸው ያሉና ያላለቁ ናቸው። ከሶስተኛ በታች ያለውን የሚጠብቁት፣ ተቋራጮቹ የሚቀጥሯቸው ጥበቃዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በጥበቃ ስም እኛ የማናውቃቸው በርካታ ሰዎች ናቸው የሚያድሩት። ያንን ክፍል ተመልከቺው፣ በአይነ ምድር የተሞላ ነው። እዚህ የሚያድሩት ናቸው የሚጸዳዱበት። በአምስቱም ብሎኮች ይህ ችግር አለ። ይሄ ለነዋሪዎቹ በጣም ችግር ሆኖብናል።
ከሦስተኛ በላይ ያሉ ባለእድሎች ገብተው መኖር ጀምረዋል እንዴ?
አዎ ገብተው የሚኖሩ አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ እኔ ነኝ።
እንደማየው ከሆነ መብራትም ውሃም የለውም። እንዴት ነው መሰረተ ልማት ሳይሟላ ለመኖር የገባችሁት?
ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው። አብዛኛው የዚህ ሳይት የቤት እድለኛ ቤት ተከራይቶ፣ ከሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ ላይ ቆጥቦ ያገኘው ቤት ነው። እናም የቤት ኪራይ ይከፍላል። ለዚህ ቤቱ ደግሞ የባንክ እዳም ይከፍላል። በዚህ ሁሉ ጭንቅ ነው የሚኖረው። አንድ ሰው አንድ ቤት ውስጥ ለመኖር እንዳልሽው ውሃ ያስፈልገዋል፣ መብራት ሊኖረው ይገባል፣ እንደገናም የመጸዳጃ መስመሩ መሰራት አለበት። ነገር ግን እስካሁን ውሃ መብራት አልገባልንም። ዝርጋታው (ኢንስታሌሽኑ) ተሰርቷል። ነገር ግን ከመብራት ሀይል መብራት አልተገናኘልንም። ከቤቶች ኮርፖሬሽን ማለቅ የነበረባቸው ነገር ግን ያላለቁ ነገሮች አሉ።
ውሃን በተመለከተ ከአምስቱ ሁለቱ ብሎኮች ብቻ ናቸው የውሃ ፓምፕ ያላቸው። ሌሎቹ ሶስቱ ብሎኮች የውሃ ፓምፕም ሮቶም ምንም የላቸውም። ነገር ግን ሰው በቤት ኪራይ ተማሯል። እንደገና የባንክ እዳ ይከፍላል። ይህን ጫና መቋቋም ስላቃተው ምንም በሌለበት ገብቶ ለመኖር ተገድዷል። ውሃ በጀሪካን ከግራውንድ እየቀዳ፣ እስከ 12ኛ እስከ 10ኛ ብቻ በየፎቁ እየተሸከምን ነው የምንወስደው።
በዚህ ላይ አሳንሰር (ሊፍት) የለውም። እዚህ ሳይት ላይ አቅመ ደካሞች፣ የጤና እክል ያለባቸው፣ ይህን ያህል ፎቅ መውጣትና መውረድ የማይችሉ በርካቶች ናቸው። ግን አማራጭ በማጣት ገብተው በስቃይ እየኖሩ ነው። እውነት ለመናገር ኢትዮጵያዊ ጨዋ ህዝብ ነው። ያ ጨዋነትና ባህል ይዞት ዝም ብሎ ስቃዩን ችሎ እየኖረ እንጂ ለመኖር ምቹ ሁኔታ ኖሮ አይደለም። ለምሳሌ ከአምስቱ ብሎኮች በአንዱ አምስተኛ ፎቅ ላይ ቤት የደረሳቸው እናት አሉ። ሲገቡ በሸክም ነው የገቡት። በየጊዜው ለጤና ምርመራ ሃኪም ቤት ሲሄዱ፣ በሰው ሸክም ነው የሚወርዱት የሚወጡት። ቤተሰቦቻቸው ቢቸግራቸው ለምርመራ ባለሙያዎችን ወደ ቤት እስከማምጣት ደርሰዋል። የሚገርምሽ የቧንቧ መስመር በየብሎኩ ተዘርግቷል። ከዚያ በየቤታችን ገብቶ አገልግሎት የሚሰጠው መስመር የለም። ኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን ተሰርቷል፤ መብራት አልገባም። በጣም በጣም የተቸገርነው ደግሞ ከቤቶች ከርፖሬሽን ይህን ሳይት የሚከታተል አካል አለመኖሩ ነው። ሳይቱ ምን ቀረው? ምን ላይ ደረሰ? ነዋሪው ምን እያለ ነው? ምን መደረግ አለበት የሚል አንድም አካል የለም።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዲፈቱ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በማናገርና ቅሬታ በማቅረብ በኩል እንደ ማህበር ምን ያህል ተግታችኋል?
ሰሚ አጣን እንጂ ያልወረድንበት ያልወጣንበት የለም፤ ያላንኳኳነው የመንግስት በር የለም። በተለይ ይህንን ሳይት የሚያስተባብረው ወይም የሚመራው በቤቶች ኮርፖሬሽን የ40/60 ፕሮጀክት 01 የሚባለው ነው። ቡልቡላ 40/60 ፕሮጀክት ላይ ነው ጽ/ቤታቸው። ከእነሱ ጋር ከ2013 ዓ.ም መስከረም ወር ጀምሮ ብዙ ጊዜ ስለምንገናኝ ተቀራርበን እንሰራ ነበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እኛም እየገፋን መሰረተ ልማት ይሟላልን፣ ደህንነታችን ይጠበቅ ስንል እየተነሳብን ያለው ክስ ምንድን ነው መሰለሽ? በፊኒሽንግ ስራ ላይ ከየቤቱ የምናወጣው ቆሻሻና ተረፈ ምርት አለ። እዛ ሜዳው ላይ ተጠራቅሟል፤ እንደምትመለከቺው። “ይህንን ቆሻሻ ካላነሳችሁ ምንም አይነት መሰረተ ልማት አናስገባም” የሚል ነው።
ታዲያ ለምን አታስነሱትም?
ጉዳዩ ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር የሚገናኝ አይደለም። ከቤቶች ኮርፖሬሽን በላይ የቆሻሻው እዚህ መጠራቀም የሚጎዳውም የሚያሳስበውም እኛን ነው። “ይህንን እንዲህ ስላላደረግህ እንዲህ አላደርግም” የሚል ብሽሽቅ አያስፈልግም። የመሰረተ ልማት መዘርጊያ ቦታ ላይም አይደለም የተጠራቀመው። እንደዛም ሆኖ ዝም አላልንም። በአንድ ጊዜ አንስተን እርፍ የምንለው አይደለም። ዛሬ ብናነሳ ነገ ሌላው ቤቱን አድሶ የሚያወጣው ቆሻሻ ይኖራል። በየጊዜው ለማስነሳትም አቅም ይጠይቃል። አስበን የነበረው ሁሉም ባያልቅ እንኳን እድሳቱ ሲገባደድ አንድ ጊዜ አንስተን ቀሪውን ደግሞ ሲጠራቀም ለማንሳት ነበር። በኋላ ላይ ግን ይሄን ነገር ምክንያት አድርገው ከሚያንጓትቱብን ብለን አስነስተነዋል። ከሦስት አራተኛው በላይ ተነስቷል። አሁን የምታይው የቀረው አንድ አራተኛው ነው። ይህ የቀረው በአንድ ቀን መነሳት የሚችል ነው። ለዚህም ዛሬ (ረቡዕ ዕለት) እንደምታይው የየብሎኩ ኮሚቴዎች ተሰብስበን መኪና ያላቸውም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ተነጋግረን የሚነሳበትን መንገድ እንፈጥራለን። ነገር ግን ይህ ቆሻሻ ውሃ ለዜጎች ለማስገባት የሚከለክል አይደለም። ቆሻሻው እውነት የሚያሳስባቸው ከሆነ፣ በየብሎኩ ስር በሰው አይነ ምድር የተሞላ ክፍል አለ፤ እጅግ አስፀያፊ ነው። ይህን ለምን አያስነሱም። ኮንትራክተሩ የቀጠራቸው ጥበቃዎች ናቸው የሚጸዳዱበት። ይህንን ነውር ለምን አያስቆሙም። ይሄ በጣም ነው የሚያሳዝነን። ህብረተሰቡ ቤት ሲታደስ የወጣና ምንም የማያስቸግር ቦታ ላይ  የተቀመጠ ተረፈ ምርት ውሃ መብራት ከማስገባት ጋር  የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ በአስቸኳይ መሰረተ ልማቱ ተሟልቶ በየቤታችን ገብተን እፎይ እንበል ነው እያለ ያለው። ይህንን የሚለው አምስት ወይም አስር ሰው አይደለም። 500 ሰው ነው። አምስት መቶ አባወራ በስሩ የሚያስተዳድረውንም ማሰብ ያስፈልጋል። አሁን ሁሉ ተሟልቶ ሁሉም ሰው እዚህ ቢገባ፣ ገንዘብ በአንድ ጊዜ አዋጥቶ የሚነሳ ቀላል ነገር ነው። አሁን እኮ ሰው እዚህ የለም፤ በየቦታው ነው ያለው። እኛ በማህበራዊ ሚዲያ ኔትዎርኮቻችን ሁሉ ጥሪ እያደረግን ነው፤ ይህን ቆሻሻ ቶሎ ለማንሳት። አሁንም የምለው ይህ ግን ሰበብ ሊሆን አይችልም።
ዋናው በስጋትነት ያነሳችሁት የጸጥታና የደህንነት ጉዳይ ነው። በችግር ምክንያት ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ እርስዎን ጨምሮ በየብሎኩ ቤታቸው ገብተው እየኖሩ ያሉ ሰዎች አሉ። ከሶስተኛ ፎቅ በታች ያሉት ቤቶች በጥበቃ ስም እየገቡ የሚኖሩና ችግር እየፈጠሩ እንዳሉ ነግረውኛል። እዚህ ከገባችሁ ተዘርፎ ወይም ተደብድቦ የሚያውቅ ሰው አጋጥሟችኋል? አጋጥሟችሁ ከሆነ  ምን እርምጃ ወሰዳችሁ?
እውነት ነው፤ ከገባን ጀምሮ ይሄ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ስንሰጋ ነበር የቆየነው። እኛ ስጋታችን የነበረው ደግሞ እዚህ በምንኖረው ሳይሆን በአላፊ አግዳሚውና በዚህ አካባቢ በሚንቀሳቀስ ሰው ላይ ይደርሳል ብለን ነበር። ከመንገደኛ  እየዘረፉና እየቀሙ እዚህ ስር እየመጡ ይደበቃሉ ብለን ነበር የምንሰጋው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አደጋው እኛው ላይ እያነጣጠረ መጣ። ለምሳሌ ባለፈው አርብ የካቲት 18 ቀን ከአስፓልት ተሸግሬ አሁን የቆምንበት ግራውንድ ላይ ስደርስ ከኋላዬ መጥቶ ሰው አነቀኝ። የጋብቻ ቀለበቴን ስልኬን ገንዘብና ብዙ ነገር ዘርፈውኝ ነው የሄዱት። እኔም እራሴ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ነው የነቃሁት። ምን እደተደረግኩም አላውቅም። አንቺ ስራ ውለሽ ደክሞሽ ቤትሽ ገብተሽ ማረፍ አምሮሽ ስትመጪ፣ እንዲህ አይነት አደጋ ያጋጥምሻል። ይህ መሃል ከተማ ነው። አስፓልት ዳር ነው።
ስንት ሰዓት ላይ ነው ዘረፋው የተፈጸመብዎት?
ምሽት 2፡20 አካባቢ ነው። ከዛ አይበልጥም። ሌላው ደግሞ እዚሁ እኛው ህንፃ ላይ የሚኖር ወጣት ልጅ ከት/ቤት ሲመጣ፣ በቀን እዚሁ ህንጻ ስር ስልኩን ተቀምቷል። እኔ ከመዘረፌ አንድ ቀን በፊት ነዋሪዎች መኪና አቁመው ወደ ቤታቸው ሊገቡ ሲሉ ክትትል አድርገው የዘረፋ ሙከራ አድርገው ነበር፤ ባይሳካላቸውም። ይሄ በፍጥትና በተከታታይ የሚፈጸም ዘረፋ ከፍተኛ ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ከትቶናል። ፈጣሪ ስላተረፈን እንጂ ዛሬ እዚህ ቆመን ላናወራ እንችል ነበር።
ስለዚህ መንግስት መሰረተ ልማቶቹን አሟልቶልን፣ ሁሉም ሰው ቤቱ ገብቶ ከዚያ በኋላ እንተባበራለን። አሁን እዚህ ብሎክ ላይ ችግሩ ብሶብን የገባነው 25 አባወራዎች ነን። ሌላው ፊኒሽንጉን ጨርሶ መሰረተ ልማት እስኪሟላ እየጠበቀ ነው፣ ህመምተኞች አሉ፤ ያለ አሳንሰር 12 ፎቅ እንዴት ይወጣሉ። ያለ መጸዳጃ እንዴት ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ያለውሃና መብራት መኖር እንዴት ይቻላል። ሌላውን ልንገርሽ መንግስት ቤቱን ሲያስረክበን የእጅ መታጠቢያ ሲንክ እና የሽንስ ቤት መቀመጫ አብሮ የመስጠት ውል አለው።
አንዱ ፓኬጅ ነው። እስካሁን አልተሰጠንም። አሁን ገበያ ላይ የእጅ መታጠቢያና ሽንት ቤት መቀመጫ እስከ 20ሺህ ብር ነው የሚሸጠው። ደሞዝተኛ እንዴት አድርጎ ይገዛል። ፊትለፊት ያለው ክፍል ውስጥ በካርቶን ታሽጎ የተከመረው የእጅ መታጠቢያ ነው። ነገር ግን አልሰጡንም።
በሌላ በኩል፤ ፕሮጀክት 01 የሚባለው ጽ/ቤት ከሚያስተዳድራቸው ሳይቶች ከእኛ ፊት ለፊት አስፋልቱን  ተሻግሮ ያለው “ቱሪስት ሳይት” ይባላል። ባለ 18 ወለል ሳይት ነው። የእኛ ሰንጋ ተራ ሳይት ካለው ጋር በእድሜ የሚስተካከል ሆኖ ሳለ፣ የእኛ ምንም እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ፊት ለፊት ያለው “ቱሪስት ሳይት” በደንብ ተሰርቶ እያለቀ ነው። እውነት ለመናገር ስለተሰራላቸው እኛ በጣም ደስ ይለናል። እስሁን  ቁልፍ እንኳን አልተረከቡም። ለማነጻጸሪያ ያነሳሁበት ምክንያት እዛ ሳይት ላይ ቆሞ እየተከታተለ የሚያሰራው የመንግስት አካል፣ የእኛን ሳይት ለምን ዘነጋው ለማለት ነው። የእኛንም ያንንም ሳይት የሚያሰራው አንድ አመራር ነው። እዚህ ሰው ተቸግሮ ገብቶ እየኖረ ነው።
ቱሪስት ሳይት ላይ ሰው አልገባም ቁልፍም አልተወሰደም። ያኛው ቅድሚያ አግኝቶ እንዲህ ሲቀላጠፍ የእኛ በምን ምክንያት ችላ ተባለ። ዜጎች እኩል አይደሉም ወይ እያልን፣ ይሄው በችግርና በብስጭት ላይ ነው ያለነው።
ምናልባት “የቱሪስት ሳይት” የነዋሪዎች ማህበር አመራሮች ጥንካሬ ምን  ይመስላል፤ የእኛስ ማህበር አመራር የጎደለው ነገር ምንድን ነው ብላችሁ ራሳችሁን ለመፈተሸ ሞክራችኋል?
በመሰረቱ የእኛ ማህበር በጣም ጠንካራ ማህበር ነው። አመራሮቹም የራሳቸውን ስራ እየተው ሁሉ ነው ለዚህ ሳይት መጠናቀቅና ለሰው እፎይታ እየሰራን ያለነው። በሳይታችን በየብሎኩ የቀሩ ስራዎችን ለይተን “እባካችሁ እነዚህ ስራዎች ቀርተዋል ተከታተሉልን” እያልን በየጊዜው እናመለክታለን፤ ሰሚ የለም። እንደ አንድ ምክንያት እየሰማነው ያለው “እዚህ ያለ መሀንዲስ ስራ በዝቶበታል ያንንም ይሄንንም መስራት አልቻለም” የሚል ነው። ይህ ደግሞ አሳማኝ አይደለም ለእኛ። እሺ መብራት ለምን አትዘረጉልንም ስንል፣ “እሺ በቅርቡ ይገባል፣ እረስተነው ነው እንጂ ልክ ነው መዘርጋት አለበት” የሚል አስቂኝ የሆነ መልስ ነው የሚተጡት። ይሄው በስልክ በአካልም እንሄዳለን፣ እንጠይቃለን፣ መልስ የለም። እንደ ማህበር ጠንካራ ነን። ነገር ግን በፕሮጀክት ጽ/ቤት ደረጃ ያለው ጉዳይ ችግር ሆኖብናል።
ጩኸታችን ሰሚ አላገኘም። የቀረው እኮ ትንሽ ነገር ነው። የቀረውን ህብረተሰቡም የሚያግዘው ካለ ያግዛል። ዋና ዋና ስራው አልቆ መብራት መቀጠል፣ አሳንሰር መግጠም፣ የውሃ ፓምፕ ማስገባት እንዴት ይህን ያህል ደጅ ያስጠናል። ህዝቡ አያሳዝናቸውም እንዴ? እኛ እኮ እንደ ማህበር ሳይታችንን በከተማችን የሚጠራ ምቹ ለማድረግ ብዙ እቅድ አለን። ምሳሌ መሆን እንችል ነበር። ግን በራሳችን ፈቃድና ፍላጎት የማናከውናቸው ከእኛ አቅም በላይ የሆኑት ችግሮች እንቅፋት ሆነውብናል። ለምሳሌ የውሃ ፓምፕ እኛ መግዛት አንችልም፣ መብራት መቀጠል አንችልም። ይሄ በመንግስት በኩል ያለው ነገር ነው ችግራችን።
እዚህ ቆመን የምንነጋገርበት ግራውንድ ፍሎር 003 የሚባል ክፍል ወለል ላይ ይህ ሁሉ አይነምድር ሞልቶ ስታዩ የመንግስት አካል ጠርታችሁ “ኑ ጉዳችንን እዩ” ብላችሁ አሳይታችኋል? አጸያፊ ነገር ነው እያየሁ ያለሁት…
እኛም እራስ ምታት ሆኖብናል። እኛ ከ3ኛ በላይ ያለው ነው ሃላፊነታችን። ሆኖም መውጫ መግቢያችን ነው እንደዚህ ነውር የተሰራበት። ግራ ገባን።
አንደኛ በጨረታ አሸንፈው እነዚህን ሱቆች  የገዙት ሰዎች ገና ቁልፍ አልተረከቡም። እነሱ ቢመጡና ቁልፍ ቢረከቡ ከእነሱ ጋር ተባብረን ከታች ጀምሮ እናስጠብቅ ነበር። አልቻልንም። ተይው ይህንን፣ እታች ሁለት ቤዝመንቶች አሉ፤ ለመኪና ማቆሚያ የተሰሩ። እዛ ሄደሽ ብታይ ኮንትራክተሮቹ የቀጠሯቸው ጥበቃዎች እየገቡ መጸዳጃ አድርገውታል። በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነገር ነው ያለው።
ኮንትራክተሩ ለቀጠራቸው ጥበቃዎች ጊዜያዊ የመጸዳጃ ጉድጓድ መቆፈር እንዲችል አላመለከታችሁም?
ይሄንን ኮንትራክተሩም ያውቃል። እኛም ጮኸናል ሰሚ፤ የለንም ብሎክ አምስትንና ስድስትን የሚያሰራውና የሚያስጠብቀው አንድ ተቋራጭ ነው ብሎኮቹ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ነው ያሉት። እኛም ሰሚ ስለሌለን አቃተን።
በሌሎቹም ብሎኮች ይኸው ችግር አለባቸው። በየሱቆቹ የማናውቃቸው ብዙ ሰዎች ያድራሉ። ችግሩ ከቆሻሻ አልፎ ለህይወታችን  አስጊ ስለሆነ የሚመለከተው የመንግስት አካል አንደኛ እነዚህን ሱቆች ለባለቤቶቹ ያስረክብንልና ከደህንነት ስጋትና ከአጸያፊ ቆሻሻ ይገላግለን።
 ሁለተኛ አሳንሰር፣ ውሃና መብራት ይገጠምልንና ሁላችንም ተጠቃለን ገብተን ወደ ሌላ ልማት እንሰማራ። ሶስተኛ ይሄ ነገር እስኪስተካከል የአካባቢው የጸጥታ ሀይል በዚህ አካባቢ ያለውን የጸጥታ ስጋት በአንክሮ እየተከታተለ፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቅርብልን ስንል እንጠይቃለን። እዚህ ድረስ መጥታችሁ በደላችንን ስለሰማችሁ ችግራችንን ስላያችሁልን እናመሰግናለን።


Read 2277 times
Administrator

Latest from Administrator